የጎሳ ፖለቲካ የጎላበት የኬንያ ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 12.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጎሳ ፖለቲካ የጎላበት የኬንያ ምርጫ

በኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታና በተቃዋሚው እጩ ራይላ ኦዲንጋ መካከል የተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውዝግብ አሁንም እንዳወዛገበ ይገኛል። የተቃዋሚው ቡድን እጩ ራይላ ኦዲንጋ የመራጭ ድምፅ ከሚከማችበት ዋና ከኬንያ አስመራጭ እና ድንበር ማካለል ኮሚሽን፣ ከ«አይኢቢሲ» ኮምፒውተር ድምፅ ተሰርቋል በሚል ውጤቱን እንደማይቀበሉ መግለጻቸው ይታወቃል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:59
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:59 ደቂቃ

አወዛጋቢው የኬንያ ምርጫ

የኬንያ ተቃዋሚ ብሔራዊ ከፍተኛ ህብረት፣ በምህፃሩ የ«ናሳ» መሪ ሙሳሊያ ሙዳቫዲም ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በአስመራጩ ኮሚሽን ያሉ ታማኝ ያሏቸውን ምንጮች ጠቅሰው እንዳመለከቱት፣ ራይላ ኦዲንጋ  ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታን በ300,000 ድምፆች አሸንፈዋል።  
« ይህን መሰረት በማድረግ፣ የ«አይቢሲ» ሊቀ መንበር የተከበሩ ራይላ አሞሎ ኦዲንጋን እና ስቴፈን ካሎንዞ ሙስዮካን የኬንያ ፕሬዚደንት እና ምክትል ፕሬዚደንት ብለው እንዲያሳውቁ እንጠይቃለን። » 


አስመራጩ ኮሚሽን ኦዲንጋ ያቀረቡትን ወቀሳ  አጣርቶ፣  ኮምፒውተሩን ለመጥለፍ በርግጥ ሙከራ ተደርጎ እንደነበረ ፣ ግን ጥረቱ እንደከሸፈ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ዋፉላ ቼኩባቲ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
የተቃዋሚው ቡድን ኦዲንጋ አሸንፈዋል በሚል ያወጣውን ውጤት የተሳሰተ ነው በሚል አጣጥሎታል። የምርጫውን ውጤት መግለጽ የሚችለው አስመራጩ ኮሚሽን ብቻ መሆኑንም ኮሚሽነር ሮዝሊን አኮምቤም አስታውቀዋል።
« የኬንያ ሕገ መንግሥት ግልጽ ነው። ምርጫ የማዘጋጀት፣ የመቁጠር እና ውጤቱን የማሳወቅ ስልጣን ያለው ብቸኛው አካል ገለልተኛው የኬንያ አስመራጭ እና ድንበር ማካለል ኮሚሽን፣ በምህጻሩ «አይኢቢሲ» ነው። »


ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ወቀሳ ቢያሰሙም፣ ምርጫውን የታዘቡ ዓለም አቀፍ ቡድኖች ምርጫው ነፃ እና ትክክል ነበር በማለት አሞግሰዋል። ምርጫውን ከታዘቡት መካከል አንዱ የሆነው የካርተር ማዕከል ቡድን መሪ ኬንያዊቷ አሚናታ ቱሬ ስለምርጫው ሂደት ግልጽነት ተናግረዋል።


« በምርጫው ዕለት ሁኔታዉን ተከታትለናል፣ በዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ መብታቸው ለመጠቀም ቆርጠው የተነሱ በብዛት ተሰልፈው ሲጠባበቁ የነበሩ ሰዎችን አይተናል። በምርጫ ጣቢያያዎችም ውስጥ ነበርን፣ሁኔታው የተረጋጋ ነበር። በኋላም ለድምፅ ቆጠራው ወደምርጫ ጣቢያዎች ተመልሰናል። ቆጠራው ግልጽ ነበር። እና የእያንዳንዱ ፓርቲ ተወካይ የተቆጠረው ድምፅ የተመዘገበበት ወረቀት ቅጂ ደርሶታል፣ ይኸው ሂደትም ግልጽ ነበር። »   
የአውሮጳ ህብረት ቡድን መሪ ማሪየትየ ሻከም ተመሳሳይ አስተያየት ከሰጡ እና አስመራጩ ኮሚሽን የሚቀርቡ ወቀሳዎች በትክክል ሊያጣራ እንደሚገባ አስታውቀው፣  የምርጫ ተፎካካሪዎች ደጋፊዎቻቸውን እንዲያረጋጉ ሀሳብ አቅርበዋል።
« በምርጫው የተወዳደሩት ዋነኞቹ እጩዎች በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ትልቅ ተሰሚነት ያላቸው ይመስለኛል፣ እና ህዝቡ እንዲረጋጋ፣ ከኃይል ተግባር እንዲቆጠብ እና የምርጫውን ውጤት እንዲጠባበቅ የማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። ከዚያ በምርጫው ታይቷል የሚሉት ያልተስተካካለ አሰራር ካለ ያለውን ሕግ በመከተል እንዲጠይቁ እና የሕግ የበላይነትን እንዲያከብሩ እናሳስባለን። »    

 
ውጥረቱ በተካረረበት ባሁኑ ጊዜ  ግን ብዙዎቹ የኬንያ ወጣቶች የሀገራቸው ፖለቲከኞች በሚከተሉት የጎሳ አሰራር  እንደተሰላቹ ይናገራሉ። እንደሚታወሰው፣ በመዲናዋ ናይሮቢ እና በሌሎች አካባቢዎች ባሉት የተቃዋሚው ጠንካራ ሰፈሮች አልፎ አልፎ በኦዲንጋ ደጋፊዎች እና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት  አራት ሰዎች ተገድለዋል። ይሁንና፣ የነሀሴ ስምንት 2017 ዓም ምርጫ ውጤት የሀገሪቱን ሰላም እንደማይናጋ ተስፋቸውን ሲገልጹ ነበር የተሰሙት። 
«  እርግጥ ምርጫ ነው። ሁሉም ሰው በውጤቱ ሊደሰት አይችልም። ቅር የሚሰኙ ወገኖች ይኖራሉ። ይህንን ቅሬታቸውን  በሚገልጹበት ሁኔታ ላይ  ግን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። »
«  የወቅቱ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ወይም የተቃዋሚው እጩ ራይላ ኦዲንጋ የምርጫው አሸናፊ ሆኑ አልሆኑ፣ የኬንያ ህዝብ ሰላሙን እንዲጠብቅ እፈልጋለሁ። »

በምሥራቅ አፍሪቃዊት ሀገር መራጩ ህዝብ፣ በተለይ፣ በዕድሜ ጠና ያሉት ድምፃቸውን የሚሰጡት በፖለቲካ ሳይሆን በጎሳ መስመር መሆኑን እና ፖለቲከኞቹም ይህን ለራሳቸው ጥቅም ማዋላቸውን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። እስከዛሬ እንደታየው ኬንያ ውስጥ በምርጫ ወቅት ትልቅ ሚና የሚጫወቱት ትልቆቹ አምስት ጎሳዎች ናቸው፣ በኬንያ ስታትስቲክስ መስሪያ ቤት መዘርዝር መሰረት፣  ከ48 ሚልዮን የሀገሪቱ ህዝብ መካከል የኪኩዩ ጎሳ  6,6ሚልዮኑን፣  የሉህያ ጎሳ 5,3 ሚልዮኑን  የካሌንዢን ጎሳ 5ሚልዮኑ ን፣ የሉዎ ጎሳ አራት ሚልዮኑ ን እና የካምባ ጎሳ 3,8 ሚልዮኑን ይሸፍናሉ።  በዚህ ዓመቱ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ በናይሮቢ ከኪኩዩ ጎሳ የሚወለዱት ኡሁሩ ኬንያታ እና በምዕራብ ኬንያ ካሉት የሉዎ ጎሳ የመጡት ራይላ ኦዲንጋ የተፎካከሩ ሲሆን፣ ያቋቋሟቸው የፓርቲዎች ህብረትም በጎሳው መስመር ነው የተቀናጁት።  የፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ምክትላቸው ዊልያም ሩቶ የጁብሊ ጥምረት የኪኩዩ እና የካሌንዢን ጎሳዎች፣ የተቃዋሚው የኬንያ ብሔራዊ ከፍተኛ ህብረት፣ በምህፃሩ የ«ናሳ» ህብረት እጩ ራይላ ኦዲንጋ፣ ሞዘስ ዌታንጉላ እና ካሎንዞ ሙሶይካ  ደግሞ  የሉዎ፣ ሉህያ እና የካምባ ጎሳዎች ድጋፍ አላቸው። በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ የጎሳ ተፅዕኖ ስር የሰደደ በመሆኑ ይህን የመቀየሩ ሁኔታ አዳጋች እንደሚሆን ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው ኬንያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ማርቲን ኦሎ ጠቁመው፣ ይህ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ማብቃቱን እንደሚጠራጠሩት  ገልጸዋል።
«  ይህ ቀላል ተግባር ይሆናል ብዬ አላስብም፣ እኛ ፖለቲካችንን ከጉዳዮ ክብደት ወይም ከፖለቲከኞች ችሎታ አኳያ መመልከት እስክንጀምር ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል ባይ ነኝ። በአሁኑ ጊዜ ነገሮችን የምናደራጀው እና በምርጫ ወቅትም ድምፃችን የምንሰጠው በጎሳ መስመር ነው። ይህም እኛን ለመከፋፈል እያገለገለ ነው። በዚህም የተነሳ ከዚህ ዓይነቱ ጎጂ አሰራር ማላቀቅ የሚችሉ የተለያዩ ፖለቲከኞች ያስፈልጉናል።  »
እንደ ፖለቲካ ተንታኙ ኦሎ ፣ ብዙዎች ተስፋቸውን በወጣቱ የኬንያ ትውልድ ላይ አሳድረዋል። በነሀሴ ስምንቱ፣ 2017 ዓም  ምርጫ ላይ ድምፅን ለመስጠት ከተመዘገበው 19 ሚልዮን ኬንያዊ መካከል አምስት ሚልዮኑ አዳዲስ ወጣት መራጮች በመሆናቸው ፣ ተስፋቸው ምናልባት እውን ሊሆን እንደሚችል ኦሎ ገምተዋል።
« ከአምስት ዓመታት በኋላ ፣ ማን ያውቃል፣ ብዙዎቹ መራጮች ወጣቶች ሊሆኑ ይችላሉ፣ እና እነዚህ ወጣቶች በጎሳ ላይ የተመሰረተ  አስተሳሰባቸውን ጋር ተጣብቀው ከሚገኙት በዕድሜ የገፉት መራጮች በመጠኑ የተሻለ አመለካከት አላቸው። »
በተለይ በጎርጎሪዮሳዊው 2007 እና 2008 ዓም ከተካሄደው ምርጫ በኋላ ተጠናክሮ የታየው ጎሳ ነክ ውጥረት በዘንድሮው ምርጫ  እንዳይደገም ስጋት ቢኖርም፣ መንግሥት አስቀድሞ የወሰዳቸው ርምጃዎች ሁከት እንዳይነሳ ሊያግዙ እንደሚችሉ ማርቲን ኦሎ ጠቁመዋል።


« መንግሥት ባሁኑ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ተዘጋጅቷል። በስምጥ ሸለቆ በ2007 እና 2008 ለተፈጠረው ግጭት መነሻ የሆኑትዋነኞቹ  ምክንያቶች አሁን የሉም፣ ምክንያቱም በዚሁ አካባቢ ተቀናቃኝ የነበሩት ማህበረሰቦች አሁን አንድነት ፈጥረዋል። ስለዚህ ያ አካባቢ ሰላማዊ ነው። ይህ ቢባልም ግን በምርጫው የሚሸነፈው እጩ ማንም ሆነ ማን፣ ተሸናፊው  እጩ በይፋ ሽንፈቱን መቀበል ይኖርበታል። አሁን እንደሚታየው ተሸናፊው  የ«ናሳ»እጩ ነው። »
ይህ ኬንያን ካለፉት ምርጫዎች በኋላ ከታየው ዓይነት ግጭት ሊጠብቃት እንደሚችል ተንታኙ ማርቲን ኦሎ አስታውቀዋል።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች