የግጭቱ መንስኤ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ነው | ኢትዮጵያ | DW | 23.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የግጭቱ መንስኤ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ነው

በደቡብ ክልል በሚገኘው ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ ሚዛን አማን ከተማ ተዛምቶ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ። የሚዛን አማን ከተማ ዛሬ ወደ መረጋጋት መመለሷን የሚናገሩት አሁንም ቢሆን ግን ነዋሪዎች በፍርሃት ተሸብበው ነው ያሉት ብለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:15

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ተቃውሞ ለግጭቱ መንስኤ ነው ተብሏል

በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ እና ሚዛን አማን ከተማ ትናንት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ሁከት ዛሬ ጋብ ማለቱን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የአማን ክፍለ ከተማ ነዋሪ በከተማይቱ የሥራም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ቆሟል ብለዋል። ስለዛሬው የከተማይቱ ውሎ እንዲህ ይላሉ። 

“ዛሬ ምንም አይልም። ተረጋግቷል። ትናንት ግን ቤቶች ተዘርፈዋል። አሁን መከላከያም ገብቷል። ፌደራልም አለ፤ ልዩ ኃይሎችም አሉ። ምንም የለም። ለጊዜው አሁን አረጋግተው ሁሉም ሰው ወደ የቤቱ ገብቷል። ብዙ ቢሮዎች ዝጎች ናቸው። ምናልባት ከተረጋጋ ነገ ሊጀመር ይችላል እንጂ አሁን ሁሉም አልሄደም። ተማሪም አልተላከም፤ ትምህርት ቤትም፣ ሱቅም ዝግ ነው። ምንም በቃ እንቅስቃሴ የለም። ትራንስፖርት አልፎ አልፎ ነው እንጂ አብዛኛው [ቆሟል]። እነዚህ ረጅም ርቀት የሚሄዱ ናቸው እንጂ ወደ ዲማ አንዳንድ ይሄዳሉ እንጂ ሌላ የለም” ይላሉ ነዋሪው። 

በትናንትናው ዕለት የአካባቢው ተወላጅ ወጣቶች ከሌላ ቦታ መጥተው በከተማይቱ በንግድ ሥራ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ንብረት ላይ ዘረፋ እና ውድመት መፈጸማቸውን እኚሁ ነዋሪ ይናገራሉ። በወቅቱ በነበረው ሁከት በሚዛን ከተማ አንድ ሰው እንደተገደለ ሰምቼያለሁ ብለዋል። የሁከቱ መንስኤ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የነበረ ተቃውሞ መሆኑን በወሬ ደረጃ ከመስማት ውጭ ከወጣቶቹ እርምጃ ጀርባ ያለውን ትክክለኛውን ምክንያት እንደማያውቁ ነዋሪው ይገልጻሉ። ትናንት በሚዛን አማን ከተማ የነበረውን ደግሞ እንዲህ ያስረዳሉ።

“ጥሉ መጀመሪያ ዩኒቨርስቲ ጋር ነበር መሰለኝ። ግቢ ማለት ነው። ከዚያ የአካባቢው ወጣት ወደ ማኅብረሰቡ ሆ እያሉ ነው የመጡብን። እንግዲህ እነዚህ ወጣቶች፣ ሕጻናት ናቸው፤ መብታችን ይከበር እያሉ ነው የመጡት። በኅብረተሰቡ በየሱቁ እየገቡ፣ እየሰበሩ ሱቁን፣ ከልብስ ቤት፣ ከቡቲክም፣ ሸቀጦች፣ ብርም፣ ምንም ያገኙትን ነው ይዘው የሄዱት። ባለሀብቱን ነው። በቃ የተጠና ነው የሚመስልህ። እነዚህ ትልልቅ ሱቆች ያላቸውን የሌላ አካባቢ ተወላጆችን ነው እንደዚያ እያደረጉ ያሉት” ሲሉ የታዘቡትን አካፍለዋል።

በከተማይቱ ሱቆች ላይ የተፈጸመው ዘረፋ በሁለት ዙር ጠዋት እና ከሰዓት መደረጉን የሚናገሩት ነዋሪው ከቴፒ እና ጅማ የጸጥታ ኃይሎች ከመጡ በኋላ ነገሩ መብረዱን ይገልጻሉ። የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጣልቃ ባይገቡ ኖሮ ነገሮች የከፉ ሊሆኑ ይችልሉ ነበርም ይላሉ። ከሚዛን አማን ከተማ 45 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ቴፒ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ መምህር በሁለት ፒካፕ የተ ጫኑ የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊሶች እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ትናንት ግጭቱ ተቀሰቀሰ ወደ ተባለት ቦታ ሲያመሩ መመልከታቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ስለግጭቱ መንስኤ የሰሙትንም አጋርተዋል።

“ዩኒቨርስቲ አካባቢ ሴት ተማሪ መደፈር አጋጥሟት ነበር። ከዚያ በዚያ የተነሳ ተማሪዎች አድማ ነገር መትተው ነበር። እዚያ ተማሪዎች ተሰብስበው እያሉ ስለ ልጅቷ መደፈር ውይይት እያደረጉ እያለ  የዚያን አካባቢ ብሔረሰብ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተናግረዋል ይባላል። ያ ነገር ወደ ከተማው ተዟዙሮ ከተማ ላይ ያሉ የአካባቢው ማህብረሰቦች በሌላው ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱት የሚባለው። ትላንትና ችግሩ እዚያ ሲፈጠር እዚህ አካባቢ የነበሩት ፌደራል ፖሊሶች ሲሄዱ ነበር በፒካፕ መኪና ከዚያ ውጭ ነገሩ እነርሱ ከሄዱ በኋላ እንደቆሙ ነው” ሲሉ የቴፒው ነዋሪ ገልጸዋል።    

የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪው የጸጥታ ኃይሎች በዝርፊያ የጠረጠሯቸውን የተወሰኑ ወጣቶችን ሲያስሩ መመልከታቸውን አስረድተዋል። ስለ ግጭቱ ከቤንች ማጂ ዞን ባለስልጣናትም ሆነ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።   

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች