የግንቦት 10 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 18.05.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የግንቦት 10 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ዳግም በጀመረው የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ የባየር ሙይንሽኑ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ዳግም ወደ ግብ አዳኝነቱ ተመልሷል። ምናልባትም የፕሬሚየር ሊጉ የሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ሊጀምር ይችል ይኾናል ብለዋል። ማይክ ታይሰን እና ሆሊፊልድ ወደ ውድድር ልንመለስ ነው ብለዋል። 53 እና 57 ነው ዕድሜያቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:48

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ከኹለት ወራት በፊት ቡንደስሊጋው ለጊዜው ከመቋረጡ ጥቂት ቀደም ብሎ ጉዳት ደርሶበት ነበር።  የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ወደ ስታዲየሞች እና ኳስ መመልከቻ ቤቶች እንዳይጎርፉ በሚል ምናልባት ቴሌቪዥን የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በነጻ የሚያሳዩበት ኹኔታ እየታሰበበት ነው። ምናልባትም የፕሬሚየር ሊጉ የሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ሊጀምር ይችል ይኾናል ብለዋል። ማይክ ታይሰን እና ሆሊፊልድ ወደ ውድድር ልንመለስ ነው ብለዋል። 53 እና 57 ነው ዕድሜያቸው።

ተወዳጆቹ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ዳግም የሚጀምሩበትን ቀን ከመወሰናቸው በፊት ጀርመን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በርካታ ግጥሚያዎችን አከናውናለች። እግር ኳስ በጀርመን የተቋረጠው መጋቢት 4 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ነበር።  ከ2 ወር በኋላ ቅዳሜ ዕለት በዝግ ስታዲየም ጨዋታዎች ተጀምረዋል። በጥቅሉ አጀማመሩ ጥሩ የሚባል ነው፤ ግን ደግሞ የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ስጋት ሙሉ ለሙሉ አልተወገደም። አንዳንድ ተጨዋቾች እና የቡድን አባላት በጥብቅ እንዲከተሉት የተሰጣቸውን መመሪያ በአግባቡ ሲጠቀሙ አልተስተዋሉም።

ለአብነት ያኽል፦ የሔርታ ቤርሊን ተጨዋቾች በጀርመን እግር ኳስ ሊግ የተላለፈውን ጥብቅ የጤና መመሪያ ጥሰዋል። ግብ ከተቆጠረ በኋላ መነካካት አይቻልም ቢባልም፤ ደስታቸውን በመተቃቀፍ ገልጠዋል። የቡንደስሊጋ ዓለም አቀፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሮቤርት ክላይን፦ «መመሪያዎቹ ግልጽ ናቸው። ኹሉም ያን እንዲያከብር እንሻለን» ሲሉ አስጠንቅቀዋል። መሰል ድርጊቶች ተሻሽለው ኹሉም ነገር እንደታሰበው ከቀጠለ የዘንድሮ ቡንደስሊጋ ሰኔ 23 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ጀርመን ውስጥ እግር ኳስ ዳግም ከተጀመረ በኋላ የተከናወኑ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች ሙሉ ለሙሉ ተሳኩ የሚባለው ዛሬ ማታ የሚደረገው ጨዋታ ከተፈጸመ በኋላ ነው። ምሽት ላይ ቬርደር ብሬመን ከባየር ሌቨርኩሰን  ጋር ይጋጠማል።

የምሽቱ ጨዋታ 18 ነጥብ ይዞ 17ኛ ደረጃ ላይ በወራጅ ቃጣናው ግርጌ ለተዘረጋው ቬርደር ብሬመን ከወራጅ ቃጣናው ለመውጣት ወሳኝ ፍልሚያው ነው። ብሬመን በዛሬው ተስተካካይ ጨዋታ ካሸነፈ 21 ነጥብ ይዞ ዱይስልዶርፍን በኹለት ነጥብ ብቻ ይከተላል ማለት ነው። 

ለባየር ሌቨርኩሰንም ቢኾን አራተኛ ደረጃ ይዞ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ የሚያደርገው የሞት ሽረት ግጥሚያ ነው። ባየር ሌቨርኩሰን የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ 50 ነጥብ ይዞ በላይፕሲሽ በአንድ ነጥብ ብቻ ይበለጣል። በነገራችን ላይ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ52 ነጥብ 3ኛ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ54 ነጥብ 2ኛ፤ እንዲሁም ባየር ሙይንሽን በ58 ነጥብ መሪነት በቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ በቅደም ተከተል ተደርድረዋል።

የኮሮና ስጋት ባልጠፋበት ኹኔታ ጨዋታው እንዲጀመር የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት የኢኮኖሚ ወይንም የገንዘብ ጉዳይ ነው። የጀርመን እግር ኳስ ሊግ Deutsche Fußball Liga (DFL) ነው ኳሱ እንዲጀመር በጥብቅ የወተወተው። አለበለዚያ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ፣ የስፖንሰር እና ሌሎች ገቢዎች ቀርተው ኪሳራው እጅግ ብርቱ ስለሚኾን። ለዚያም ነው እግር ኳሱ እንዲጀምር ውይይት ከተደረገ ከዐሥር ቀናት በኋላ ብቻ በኹለቱም ሊጋዎች ጨዋታው የተጀመረው።

ኹለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ የሚገኙት ያን ሬገንስቡርግ እና ሆልሽታይን ኪይል የተሰኙ ቡድኖች  ባደረጉት ግጥሚያ ነው የጀመረው። እግር ኳስ ግጥሚያ በአጠቃላይ ለኹለት ወራት እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ ዳግም በጀመረው ግጥሚያ የመጀመሪያውን ታሪካዊ ግብ በ3ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው የሆልሽታይን ኪይሉ አማካይ ደቡብ ኮሪያዊው ሊ ጃይ ሱንግ ነው። ጨዋታው በኋላ ላይ ኹለት እኩል ተጠናቋል።

ተጨዋቾች ግብ ሲያስቆጥሩ ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ ቢነገራቸውም አንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ያን መተግባር ሲሳናቸው ተስተውሏል። የሚፈቀደው ቡጢን ወይንም ክርንን ማነካካት ነው። ጨዋታው ውስጥ የማይሳተፉ ተጨዋቾች እና ኹሉም የቡድኑ አባላት ተመልካች የሚቀመጥበት ወንበር ላይ ተራርቀው እንዲቀመጡ ነው የሚፈቀደው፤ ጭምብል እንዲያደርጉም ይጠበቃል። ተመልካች ግን ወደ ስታዲየም እንዲገባ አልተፈቀደም።  ዋናው የቡንደስሊጋ ግጥሚያም የተከናወነው ወይንም ወደፊት የሚከናወነው ያለ ታዳሚ ነው።

በበርካቶች ዘንድ በጉጉት የተጠበቀው እና ዶርትሙንድ በሜዳው ዚግናል ኢዱና ፓርክ ከሻልከ ባደረገው የቅዳሜ ዕለት ግጥሚያ 4 ለ 0 በኾነ ሰፊ ውጤት ነው ለድል የበቃው። ቅዳሜ እና እሁድ ያለአንዳች ተመልካች በተከናወኑት የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች በሜዳው ማሸነፍ የቻለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ብቻ ነበር።

በዓለም ዙሪያ የአንድ አካባቢ ቡድኖች ከሚያደርጓቸው ግጥሚያዎች (ደርቢ)መካከል እጅግ በጉጉት ከሚጠበቊት ጥቂቶቹ ውስጥ የቦሩስያ ዶርትሙንድ እና የሻልከ ቡድኖች ናቸው። ቡድኖቹ እጅግ ባላንጣ በኾኑ ደጋፊዎቻቸው ይታወቃሉ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ የሚገኝበት ዶርትሙንድ ከተማ እና የሻልከ ቡድን በሚገኝበት የጌልዘንኪርሸን ከተሞች መካከል ያለው ርቀት 32 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ኹለቱም ቡድኖች ሩር በሚባለው አካባቢ ነው የሚገኙት።

ይኼ ሩር ጌቢት ማለትም የሩር አካባቢ ለዘመናት በጀርመን የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ሥፍራነቱ ይታወቃል። የሠራተኛ መደብ እና የኳስ ፍቅር ያነኾለለው ማኅበረሰብ የሚኖርበት አካባቢ ነው። ምናልባትም ይኽ ኹኔታ የኹለቱን ከተሞች የአንድ አካባቢ ቡድኖች ባቀራረበ ነበር።

ሌሎች ሃገራት ውስጥ የሚገኙ የአንድ አካባቢ ቡድኖች እምነት፣ ምጣኔ ሐብት እና ፖለቲካ ባላንጣ ሲያደርጋቸው ይታያል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ሻልከን የሚለያቸው ግን አንድ ነገር ብቻ ነው። ያም የቦሩስያ ዶርትሙንድ ጥቊር እና ቢጫ መለያ፤ እንዲኹም የሻልከ ሠማያዊ መለያ ልብስ ብቻ ነው። እንዲያም ኾኑ የቡድኖቹ ደጋፊዎች በነውጠኝነታቸው ይታወቃሉ። የጀርመን ና የባየር ሙይንሽን ታሪካዊ ተጨዋች ፍራንትስ ቤከንባወር በአንድ ወቅት ስለ ኹለቱ ቡድኖች እና ደጋፊዎች የተናገረው አይረሳም። «የጀርመን እግር ኳስ ልብ ትርታው በሩር አካባቢ ውስጥ ነው» ብሏል። ሩር አካባቢ ኹለቱ ባላንጣ ቡድኖች ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ሻልከ የሚገኙበት አካባቢ ነው።

ዶርትሙንዶች እስካኹን በጀርመን ሊግ ስምንት ዋንጫዎችን በእጃቸው አስገብተዋል። ከሻልከ በአንድ ይበልጣሉ። ሻልከን የበለጡት ግን በአኹኑ የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬይርገን ክሎፕ እገዛ ነው። ክሎፕ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 እና በ2012 በተከታታይ የቡንደስሊጋውን ዋንጫ በመውሰዳቸው ነው ዶርትሙንድ ሻልከን በዋንጫ ብዛት የበለጠው።

ሻልከ ለመጨረሻ ጊዜ የቡንደስሊጋ ዋንጫ የወሰደው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1958 ነው።  ሽቱትጋርት ዋንጫውን በወሰደበት የ2007 የእግር ኳስ ግጥሚያ ሻልከ ዋንጫውን እንዳይወስድ በስተመጨረሻ መሰናከል የኾነበት ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነበር። በወቅቱ ሻልከ፤ ሽቱትጋርት እና ቬርደር ብሬመን የመጨረሻዎቹ ኹለት ግጥሚያዎች ላይ የደረሱት እያንዳንዳቸው በኹለት ነጥቦች ተለያይተው ነበር። በስተመጨረሻ ግን የዋንጫ ዕድል ያልነበረው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሻልከን አሸንፎ ደጋፊዎቹን አስለቅሷል።

በቅዳሜ ዕለቱ የቦሩስያ ዶርትሙንድ እና የሻልከ ግጥሚያ ብርቱ ሽንፈት የገጠመው ሻልከ በ37 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ካለፈው ኹለት ደረጃ ነውያሽቆለቆለው። ባለፈው ስድስተኛ ኾኖ ለአውሮጳ ሊግ ማጣሪያ የማለፍ ዕድል ነበረው። ወትሮ ኹለቱ ቡድኖች ሲገናኙ የሚደምቊ ከተሞች ቀዝቅዘው ነው የታዩት። መንገዶች ላይ ብዙም ሰው ዐይታይም ነበር።

ዳቪድ ቫግነር «ያሳዝናል ያለተመልካች ይኽን ትልቅ ጨዋታ ማድረግ» ብለዋል፤ የአንድ ከተማ ቡድኖች ደርቢ ግጥሚያ ነበር። የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አሰልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬም፦ «ያለ ደጋፊ፤ ያለ ቢጫው ባንዲራ ትንሽ ግራ የኾነ ኹኔታ ነበር» ብለዋል።

ሃላንድ ጨዋታው እንደተጀመረ አየር ላይ ዘሎ የመታት ኳስ በሻልከው ኬኒ በእጅ ተነክታ ነበር። ፍጹም ቅጣት ምት ሊሰጥ በተገባም ነበር። በቅዳሜው ግጥሚያ ሻልከ ለዶርትሙንድ እጅግ ቀሎ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ 29 ደቂቃ ላይ ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው ኧርሊንግ ሀላንድ ነው። ሀላንድ ግብ ከማስቆጠሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ግን ከሻልከ ተከላካይ በኩል አላስፈላጊ ነገር ደርሶበት ነበር። በስታየሙ ደጋፊዎች ባለመኖራቸው የተጨዋቾቹ ንግግር በቴሌቪዥን በደንብ ነው የተሰማው።

23ኛው ደቂቃ ላይ በሻልከ የግብ ክልል የተከሰተው ከሩቅ ሲታይ ሰላማዊ ይመስል የነበረው የኹለቱ ቡድኖች ግጥሚያ ቊርቊዝ እንደነበረበት አመላካች ነው። ኧርሊንግ ሀላንድ እና የሻልከው ተከላካይ ጆን ክሌ ቶዲቦ ትንሽ ከተጎነታተሉ በኋላ የሻልከው ተከላካይ ድንገት ኖርዌጂያዊውን አጥቂ በብልግና አያትህ እንዲህ ትሁን ብሎ በፈረንሳይኛ ይሰድበዋል። ስድቡ በደንብ ነው የተሰማው። ኧርሊንግ ሃላንድ ፈረንሳይኛ ስድቡን ይረዳ አይረዳ ዐይታወቅም። ግን የቶዲቦ የቡድን አጋር ሴኔጋላዊው ሳሊፍ ሳኔ በፍጥነት መሀላቸው ገብቶ ነገሩን ለማብረድ ሞክሯል። ሳሊፍ ፈረንሳይና በደንብ ነው የሚናገረው። ኧርሊንግ ሃላንድ አፍታም ሳይቆይ ግን የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ለቶዲቦ በተግባር መልስ ሰጥቷል።

ቅዳሜ በተደረጉ ግጥሚያዎች፦ ቤርሊን ሆፈንሀይምን 3 ለ 0 አሰናብቷል። አውስቡርግ በቮልፍስቡርግ 2 ለ1 ተሸንፏል። የአውስቡርግ አሰልጣኝ ሀይኮ ሔርሊሽ ከለይቶ መቆያ ሆቴል ወጥተው የገላ ክሬም እና የጥርስ ብሩሽ ለመግዛት መደብር መሄዳቸው በብርቱ ተነቅፏል። አሰልጣኙ በተሸነፉበት ግጥሚያ ስታዲየም እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም። አውስቡርግ 4ኛ የቡንደስሊጋ ጨዋታውን በተርታ ነው የተሸነፈው።

ግላድባኅ ፍራንክፉርትን 3 ለ1 አሸንፏል። ላይፕሲሽ ከፍራይቡርግ ጋር አንድ እኩል እንዲሁም ፓዴርቦን ከዱይስልዶርፍ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። በትናንትናው ዕለት ማይንትስ ከኮሎኝ ጋር 2 እኩል ሲወጣ፤ ባየር ሙይንሽን ዑኒዮን ቤርሊንን 2 ለ0 ድል አድርጓል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀው 45ኛው ደቂቃ ላይ ራፋኤል ጉዌሬሮ ከግቡ በስተግራ በቀጥታ መሬት ለመሬት አክርሮ በመታት ግብ 2 ለ 0 ነው። ግቡ የተቆጠረው በሻልከው ግብ ጠባቂ ማርኩስ ሹበርት ጥፋት ነው። ሃላንድ አጠገቡ ሲመጣበት በተፈጠረው ጫና ኳሱን በቀጥታ የሰጠው ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋች ነው። አሰልጣኝ ዳቪድ ቫግነርም ለኹለተኛው ግብ ተጠያቂው ግብ ጠባቂው ነው «ያን ማንም ማየት ይችላል» ብለዋል።  የቀድሞው ዋናው ግብ ጠባቂ የ23 ዓመቱ አሌክሳንደር ኑይቤል ግን ከበጋ ወራት ረፍት በኋላ ወደ ባየር ሙይንሽን መኼዱ ይፋ ስለኾነ ማርኩስ ሹበርት የዋና ግብ ጠባቂነት ቦታው አያሰጋውም።  በአንጻሩ ግን ተደጋጋሚ ስኅተት ታይቶበታል። በባየር ሙይንሽን 5 ለ0 ሲሸነፉ ለኹለት ግቦች ተጠያቂው ግብ ጠባቂው  ነበር። ከቮልፍስቡርግ ጋር አንድ እኩል ሲለያዩ የ21 ዓመቱ ግብ ጠባቂ አቋሙ ጥሩ አልነበረም። በሰባት ጨዋታዎች እስካኹን 13 ግቦች ተቆጥረውበታል። አሰልጣን ዳቪድ ቫግነር፦ «ያ ከመሻሻል ሒደት ውስጥ የሚካተት ነው። ከእሱ ጋር መሥራታችንን እንቀጥላለን» ብለዋል። ይክ አባባል ግብ ጠባቂውን ለጊዜው እፎይ ሊያስብለው ይችላል። ሰላማዊ እንቅልፍ የሚነሳው መኾኑ ግን አያጠራጥርም።

የሻልከ ቡድን ኃላፊ የ63 ዓመቱ ክሌሞ ቶይኒየስ፦ «መናፈጥ ይገባናል። አኹን አሰልጣኙ እና ቡድናቸው ተጠይቀዋል። አበቃ» ሲሉ ቆጣ ብለው ነው አስተያየት የሰጡት።  ዳቪድ ቫግነር ግን አጠቃላይ ቡድናቸውን በተመለከተ፦ በዚህ አንድ ጨዋታ ሽንፈት ብቻ ጥያቄ ውስጥ መክተት እንደማይገባ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ዐስታውቀዋል።

ከረፍት መልስ 48ኛው ደቂቃ ላይ  ቶርጋን ሃዛርድ ሲያገባ፤ ሀዛርድ ላይ ጥፋት ተሠርቶ ስለ ነበር ሳኔ ቢጫ ዐይቷል። 63ኛው ደቂቃ ላይ ራፋኤል ጉዌሬሮ በግራ እግሩ በድንቅ ኹኔታ ነው በማስቆጠር ሻልከ ድባቅ ተመትቷል። ኧርሊንግ ሃላንድን የሰደበው ጆን ክሌ ቶዲቦ ከረፍት መልስ አልተሰለፈም።  ከባርሴሎና በውሰት የመጣው ፈረንሳዊው ቶዲቦ የተቀየረው ግን ስለተሳደበ ሳይኾን ታፋውን ደጋግሞ እየያዘ ስለነበረ ነው።

ፕሬሚየር ሊግ

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ በሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት መጨረሻ ላይ ሊጀምር እንደሚችል እየተነገረ ነው። ይኽን ያሉት የእንግሊዝ የዲጂታል፤ ባሕል፤ መገናኛ ብዙኃን እና ስፖርት ክፍል ኃላፊው ሚንስትር ኦሊቨር ዶውደን ናቸው። እንግሊዝ የጀርመን ቡንደስሊጋን ካየች በኋላ ልምምድ የሚጀምርበት ቅድመ ኹኔታዎች ላይ ለመነጋገር እና ለመስማማት ለዛሬ ቀጠሮ ይዛ ነበር። ጨዋታዎቹን ለማስጀመር ከ20ዎቹ የፕሬሚየር ሊግ ቡድኖች ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ላይ የኮሮና ተሐዋሲ መለያ ምርመራ ተጀምሯል።

በስፔን ላሊጋውም ገና አልተጀመረም። ኾኖም ኃያሉ ሪያል ማድሪድ የፓሪስ ሳንጄርሜኑ ኮከብ ተጨዋች ኪሊያን ምባፔ እና የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አጥቂ ኧርሊንግ ሀላንድ ላይ ዐይኑን መጣሉ ዛሬ ተዘግቧል። አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ሁለቱን ድንቅ ተጨዋቾች በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ወደ ስፔን መዲና አስመጥቶ ከኤደን ሐዛርድ ጋር ማቀናጀት ምኞቱ ነው።

ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎች ተሳታፊ የነበሩበት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቨርቿል ሩጫ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተከናውኗል። ቨርቹዋል ሩጫ ውድድሩ በኢንተርኔት እገዛ ነው የተከናወነው። እቤት ውስጥ አለያም ግቢ ውስጥ ወይንም ሰዎች ባልተሰበሰቡበት ቦታ ኾኖ በኢንተርኔት ታዋቂ አትሌቶችን እየተከታተሉ እራስንም እየቀረጹ በውድድሩ ተሳታፊ መኾን ይቻል ነበር። የሩጫው አስተባባሪ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የታላቁ የአፍሪቃ ሩጫ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ነው። ውድድሩ የተከናወነው ዙም በተሰኘው የኢንተርኔት ማስተናበሪያ ነው። ከዝግጅቱ የሚገኘው ገቢ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለሚሠሩ ኹለት መንግሥታዊ ያልኾኑት አነስተኛ ድርጅቶች የሚበረከት መኾኑም ተጠቅሷል።

ከዘመናችን ድንቅ የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ማይክ ታይሰን ስለብቃቱ ሙገሳ የደረሰው  ኮኖር ማክ ግሬጎር ከፍሎይድ ማይዌዘር ጋር ዳግም መጋጠሙ የማይቀር እንደኾነ በይፋዊ የትዊተር ገጹ ዐስታውቋል። ማይዌዘርንም ለማሸነፍ እንደማይጠራጠር ገልጧል። ማይዌዘር እና ማክ ግሬጎር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2017 ያደረጉት ፍልሚያ በዓለም የቡጢ አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት የተጠበቀ ነበር። በውድድሩ ዐሥረኛ ዙር ላይ  የላስቬጋስ ዳኞች ጨዋታው እንዲቋረጥ አድርገዋል።

Mike Tyson

በቡጢ ታሪክም እጅግ ከፍተኛው ክፍያ የተፈጸመበት ነበር። ፍሎይድ ማይዌዘር በዚያ ፍልሚያ 300ሚሊዮን ዶላር እንዳፈሰ ነው የተናገረው። በዚያ ግጥሚያም ፕሮፌሽናል የቡጢ ውድድሩ እንዳበቃ እና ጓንቱን እንደሰቀለ ዐስታውቆ ነበር። በወቅቱ ታዲያ ከማክ ግሬጎር ጋር አስፈላጊ ከኾነ ዳግም ለመጋጠም ዝግጁ መኾኑንን ይፋ አድርጎ ነበር። ከማክ ግሬጎር ጋር የሚያደርገውን ውድድሩንም ከቡጢ ፍልሚያ ይልቅ «የመዝናናት እና የገንዘብ» ውድድር ይኾናል ብሏል። ኹለቱ ቡጢኞች ዳግም ከተገናኙ ፍሎይድ ማይዌዘር ዳግም ሊረታ እንደሚችል ብዙዎች ይገምታሉ።

በነገራችን ላይ የ53 ዓመቱ ማይክ ታይሰን እና የ57 ዓመቱ ኢቫንደር ሆሊፊልድም ወደ ውድድር ብቅ ሊሉ እንደኾነ ይፋ አድርገዋል። ማይክ ታይሰን ከ23 ዓመት በፊት የሆሊፊልድን የጆሮ ጫፍ በመንከሱ ከውድድሩ መባረሩ ይታወሳል። ኹለቱም ታዲያ ብቃታቸውን ቡጢ ሲለማመዱ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች አሳይተዋል። በእርግጥም እድሜያቸው ቢገፋም ጥሩ ብቃት ላይ እንዳሉ ግን መመስከር ይቻላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች