የግብፅ የ ጦር አዛዥ የምርጫ ዝግጅት | ዓለም | DW | 27.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የግብፅ የ ጦር አዛዥ የምርጫ ዝግጅት

የግብፅ የጦር ኃይል አዛዥ አበደል ፈታህ አል ሲሲ የወታደራዊ የደንብ ልብሳቸዉን በይፋ የሚቀይሩበት ጊዜ ተቃርቧል። ትናንት ነዉ የጦር አዛዡ ከመከላከያ ሚኒስትርነታቸዉ በይፋ በመልቀቅ ለፕሬዝደንትነት ለመወዳደር መወሰናቸዉን ያስታወቁት።

ባለፈዉ ጥር ወር ነዉ ጊዜያዊዉ የግብፅ ፕሬዝደንት አብዲ ማንሱር የፊልድ ማርሻልነትን ማዕረግ የሰጧቸዉ። ትናንት ግን በሀገሪቱ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለዉ ለፕሬዝደንትነት ለመወዳደር ተዘጋጅቻለሁ የሚል ዉሳኔያቸዉን ካሳወቁ በኋላ አሁን ወታደራዊ የደንብ ልብስ እንደማይለብሱ አመለከቱ። በሀገሪቱ ሕገ መንግስትም ከወታደራዊ ስልጣናቸዉ በመሰናበት ነዉ ለፕሬዝደንትነት መወዳደር የሚችሉት። ለዚህም አል ሲሲ የመከላከያ ሚኒስትርነትና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸዉን መልቀቃቸዉን ይፋ አድርገዋል።

በጎርጎሪዮሳዊዉ 1954ዓ,ም ካይሮ የተወለዱት አል ሲሲ በግብፅ የጦር ኃይል ዉስጥ ስኬታማ ርምጃዎች ተራምደዋል። በጎርጎሪዮሳዊ 2011ዓ,ም የግብጽ የረዥም ዘመን መሪ ሆስኒ ሞባረክ በሕዝባዊ አመፅ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሀገሪቱን ያስተዳደረዉ የግብፅ ጦር ኃይሎች ላዕላይ ምክር ቤት ዉስጥ በእድሜ የሚያንሱት ጀነራል አል ሲሲ አንዱ ሆኑ። በዓመቱ በተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊና ምክር ቤታዊ ነፃ ምርጫ ሙስሊም ወንድማማቾች ስልጣን ያዙ። መሐመድ ሙርሲም የፕሬዝደንትነት ስልጣን ሲይዙም ጠንካራ አማኝ የሆኑትን አል ሲሲን የጦር ኃይሉ ጠቅላይ አዛዥና የመከላከያ ሚኒስትር አድርገዉ ሾሟቸዉ። ሆኖም ባለፈዉ ዓመት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግጭት ሀገሪቱ ዉስጥ ሲባባስ በምርጫ የሙርሲ ተቃራኒ ሆኑ። ሙርሲን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች በተጠናከሩበት ባለፈዉ ሐምሌ ወርም ፕሬዝደንቱን ከስልጣን አስወገዱ። ከዚያ ወዲህ በተመሠረተዉ በግብፅ የሽግግር መንግስት ዉስጥ በመከላከያ ሚኒስትርነት እና በጠቅላይ ጦር አዛዥነት ስልጣናቸዉ ቆዩ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም ናቸዉ። በዚህ ምክንያትም በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያሉ ጠንካራ ሰዉ ተደርገዉ ይታሰባሉ።

በርካታ ግብፃዉያን አል ሲሲ በምርጫዉ እንዲሳተፉ ጋብዘዋል። እሳቸዉም ቢሆኑ «ሕዝቡ ከፈለገኝ» የሚለዉን አበክረዉ በተደጋጋሚ ይገልፃሉ። በካይሮ የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ሙስጠፋ አል ሰይድ በበኩላቸዉ በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነታቸዉን ነዉ የሚገልፁት፤

«በፖለቲካዉ ረገድ ሕዝቡ ይደግፋቸዋል። ሙስሊም ወንድማማቾችን በማይደግፈዉ በተራዉ ግብፃዉ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና የተወዳጅነት አላቸዉ። የንግዱን ኅብረተሰብ ካየንም ድጋፋቸዉ አይለያቸዉም።»

ባለፉት ወራትም የአል ሲሲ ሰብዕና ከዕለት ወደዕለት ከፍ ያለ ሲሄድ ነዉ የታየዉ። ምስላቸዉ በአብዛኞቹ የግብፅ ከተሞች በየስፍራዉ ይታያል። መገናኛ ብዙሃኑም ቢሆኑ ስለእሳቸዉ ብዙ ይላሉ። የፍሬደሪሽ ኤበርት የካይሮ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሮናልድ ማይናሩዱስ፤

«ከግብፃዉያን ጋ ስትነጋገር ለኝህ ሰዉ ያላቸዉን አክብሮት በግልፅ ታያለህ። ሚዛናዊነት በጎደለዉ መልኩም በጣም ከፍተኛና ጥሩ ነገር እንደሚጠብቁ መረዳት ይቻላል። ማለትም ያሉትን ችግሮች በሙሉ በአንዴ ያስወግዳሉ የሚል ስሜት ነዉ ያላቸዉ።»

እሳቸዉ እንደሚሉት ይህ መጠን ያለፈ ተስፋ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ባልተሳካላቸዉ ፖለቲከኞች ከገጠማቸዉ የከሸፈ ግምት የተነሳ ነዉ። 80 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት ግብፅ በአሁኑ ወቅት በርካታ ችግሮች አሉባት። ሕዝቡ እርስ በርስ ተከፋፍሏል። ኤኮኖሚዉ ወድቋል። በዚያ ላይ አሸባሪ ቡድኖች ሲና በረሃና ሌሎች አካባቢዎችም የፀጥታዉ ሁኔታ አስተማማኝ እንዳይሆን አድርገዋል። ሙስሊም ወንዳማማቾችም ቢሆን ያጣዉን ስልጣን መልሶ ለመያዝ አይተኛም። አል ሲሲ በዚህ ቀዉስ ዉስጥ የተዘፈቀችዉን ሀገር አረጋጋለሁ ነዉ ዓላማቸዉ። እንዲያም ሆኖ ጦር እና የፖሊስ ኃይሉ፤ እንዲሁም የሙስሊም ወንድማማቾች እንቅስቃሴ ዋናዉ አሳሳቢ ጉዳይ ነዉ የሚሆነዉ።

አንድሪያን ጎርስቪስኪ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic