የግብፅ የግድቡ ድርድር ይፋጠን ጥያቄ  | ኢትዮጵያ | DW | 30.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የግብፅ የግድቡ ድርድር ይፋጠን ጥያቄ 

በህዳሴዉ ግድብ ላይ የሚካሄዱ ዉይይቶችና  ስምምነቶች እንዲፋጠኑ መፈለጓን ግብፅ አስታወቀች።የሀገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር በትናንትናዉ ዕለት እንዳስታወቁት የጋራ ጥቅሞችን በማስጠበቅ ላይ የተመሰረተ ዉይይት እንዲፋጠን ሀገሪቱ ትፈልጋለች።  ርምጃዉ በኢትዮጵያ በኩል አወንታዊ ተደርጎ ቢወሰድም፤

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:24

«ገዢ የሆኑ የዉሃ አጠቃቀም የህግ ማዕቀፎችና ተቋማት ያስፈልጋሉ።» ወ/ሮ ፍሬህይወት፤ የአ/አ/ዩ መምህርት


በአንዳንድ ባለሙያወች ዘንድ ግን  ከዚህ ቀደም ከሚታወቀዉ ተለዋዋጭ የግብፅ አቋም የተነሳ  ድርርድሩን ከማፋጠን ባለፈ  ወደ ስምምነት መምጣት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል። 
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረች ካለፉት ሰባት አመታት ወዲህ ከተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ገግብፅና ከሱዳን ጋር በርካታ ዉይይቶችን አካሂዳለች።ይሁን እንጅ በግድቡ ላይ የተካሄዱት ዉይይቶች እስካሁን ድረስ መቋጫ አላገኙም። ለዚህም ፤ግብፅ ከሶስቱ ሀገራት ዉይይት ይልቅ ሌላ ገለልተኛ አካል በዉይይቱ እንዲሳተፍ መፈለጓ፤ እንዲያም ሲል ከድርድሩ አቋርጦ መዉጣቷ ፤  ለዉይይቶቹ ዉጤት ማጣትና መጓተት በምክንያትነት ሲጠቀስ ቆይቷል።ይሁን እንጅ  ከዚህ አቋም በተለዬ ሁኔታ ግብፅ ድርድሩ እንዲፋጠን  መፈለጓን በትናንትናዉ ዕለት ሮይተርስ የዜና ወኪል የሀገሪቱን የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሽኩሪን ጠቅሶ ዘግቧል።ይህ የግብፅ ጥያቄ በኢትዮጵያ በኩል በአወንታዊ መልኩ የሚታይና የሀገሪቱ የምትፈልገዉ መሆኑን በኢትዮጵያ የዉሃ ሀብት ሚንስትር የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አማካሪ የሆኑት አቶ ተፈራ በየነ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። 
«እንደተባለዉ የተሰማዉ እንዲፋጠን እንፈልጋለን የሚል ነዉ።በኛ በኩልም ይሄዉ ሀሳብ አለ።ዉይይቱ እንደተባለዉ አንዳንድ ጊዜ ፈጠን ብሎ ይሄዳል  ሌላጊዜ በተለያዬ ምክንያት ወደ ኋላ ይጎተታል።እኛም በዚህ መሰረት ስብሰባዉ ተፋጥኖ እንዲካሄድ ተግባብተናል።»ካሉ በኋላ ምክንያቱ «ያ ነዉ ይሄ ነዉ»ማለት ግን እንደሚያስቸግር ነዉ የተናገሩት።በሁሉም በኩል ግን ጉዳዩ ቶሎ ቢያልቅና መቋጫ ቢያገኝ ፍላጎቱና ምኞቱ አለ ብላዋል።


እንደ አቶ ተፈራ የሶስቱ ሀገራት የዉሃ ሀብት  ሚንስትሮች በተገኑበት በመጭዉ ግንቦት አጋማሽም ዉይይት ይካሄዳል። ከዚህ ቀደም ብሎም  የሶስትዮሽ ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።በዉይይቶቹ በህዳሴዉ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረዉ ጥናት ለየሀገሮቹ ቀርቦ አስተያየት የሚሰጥበት ሲሆን በግድቡ የዉሃ ሙሌት፤ አለቃቀና ሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ተነስተዉ ስምምነት ላይ ይደረስበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።  በአሁኑ ወቅት ግብፅ የምታነሳዉ «የዉይይቱ ይፋጠንልኝ» ጥያቄ አንፃር በሶስቱ የተፋሰሱ ሀገራት ከአሁን ቀደም ከተደረጉ ዉይይቶች የተለዬ ዉጤት ያመጣ ይችል ይሆን? አቶ ተፈራ በየነ።
«እንግዲህ በተወሰነ ደረጃ በምንነጋገርባቸዉ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ መቋጫ ያለዉ ዉጤት ላይ ለመድረስ ነዉ በኛ በኩል ጥረት የሚደረገዉ።እንግዲህ ከሌላም ወገን ተመሳሳይ ሁኔታ ኖሮ የተጠበቀዉ ዉጤት እንዲመጣ እንፈልጋለን በማለት ነዉ የገለፁት።»ያም ሆኖ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ በሀገሮቹ መካከል ዉይይቱ መቀጠሉ ዋናዉ ቁም ነገር መሆኑን ነዉ ያብራሩት።
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ወይዘሮ ፍሬ ህይወት ስንታየሁ በአባይ ተፋሰስ ሀገራት የጋራ የዉሃ አጠቃቀምና ግንኙነት ላይ ለዶክትሬት ዲግሪያቸዉ ማሟያ ጥናት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።እሳቸዉ እንደሚሉት ሶስቱ የተፈሰሱ ሀገራት ወደ ስምምነት መምጣት ያልቻሉት ግብፅ ዉሃዉን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ያላት ፍላጎትና የሌሎቹ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ፍላጎት የሚያቀራርብ ባለመሆኑ ነዉ። 

አንዳንዴ ንግግሮቹ ዲፕሎማቲክ የሆኑት ነገሮች ወደፊት የሄዱና የተራመዱ ይመስላል ያሉት ወይዘሮ ፍሬህይወት ነገር ግን «ናይል ብቻ ነዉ የዉሃ ምንጨ እና ይሄ ዉሃ ሊነካብኝ አይገባም» የሚለዉ የግብፅ አቋም ለችግሩ መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ነዉ ያመለከቱት።

የ1959 ዓም የዉሃ አጠቃቀም ስምምትም በግድቡ ላይ ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ ወደ ስምምነት እንዳይመጡ ያደረገ ሌላዉ ምክንያት መሆኑን ወይዘሮ ፍሬህይወት ገልፀዉ ፤ በሀገራቱ መካከል የቱንም ያህል ፈጣን ዉይይቶች ቢደረጉ የሀገራቱን የጋራ ተጠቃሚነትና እስካላረጋገጡ ድረስ ዉጤት  ሊኖራቸዉ  አይችልም ሲሉ ነዉ ያመለከቱት።

«የመፍጠን የመዘግየት ነገር ሳይሆን አቋማቸዉን ምን ያህል ለመቀየርና፤ ለመዉሰድ ብቻ  ሳይሆን  ለመስጠት ምን ያህል ዝግጁ ናቸዉ የሚለዉ ነገር ነዉ የሚወስነዉ።ስምምነቱን በተመለከተ ዉጤታማ ከማድረግ አንፃር።» ሲሉ ነዉ የገለፁት። 

ስለስምምነት ሲነሳ የተፋሰሱ ሀገራት ከግድቡ በላይ ማሰብ እንዳለባቸዉ የገለፁት  ወይዘሮ ፍሬህይወት ይህንን ለማድረግም አዳዲስ ፕሮጀክቶች በመጡ ቁጥር ከመነጋገር ባለፈ የወንዙን የጋራ ተጠቃሚነት በተመለከተ ገዢ የሆኑ የህግ ማዕቀፎችና ተቋማት መኖር ለዘላቂ ጥቅምና ስምምነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል። 
ጉዳዩን በተመለከተ የግብፅ የዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያቤትን ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም። 

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ

 

Audios and videos on the topic