የግብፅ የዐባይ ወንዝ ውሀ ፖለቲካ | ኢትዮጵያ | DW | 05.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የግብፅ የዐባይ ወንዝ ውሀ ፖለቲካ

የግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በካርቱም፣ ሱዳን በዐባይ ወንዝ ውሃ ክፍፍል እና ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ለሶስት ቀናት ያደረጉትን ዉይይት ዛሬ አጠናቀዋል። የውይይቱ ውጤት ገና በይፋ አልወጣም።

በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል በዐባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም የተነሳ የተፈጠረው ልዩነት ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ረገብ እያለ የመጣ መጥቷል። በበርሊን የሚገኘው የሳይንስና ፖለቲካ ጥናት ተቋም ባለደረባ ቶቢያስ ፎን ላሶቭ እንደሚሉት፣ የግብፅ አመራር ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ አመራር ጋ በፍጥጫ ፈንታ ትብብርን ማስቀደሙን መርጧል።
ግብፅ ለብዙ አሠርተ ዓመታት ስትከተለው የቆየችውን የዐባይ ወንዝ ውሀ አጠቃቀም ፣ ብሎም፣ የውሀውን ክፍፍል ፖሊሲ አሁን ማለዘብ በመጀመር 80% የወንዙን ውሀ ከምታቀርበው ከኢትዮጵያ ጋ ለመቀራረቡ ዘዴ ቅድሚያ ሰጥታለች። ይሁንና፣ ግብፅ በዚሁ ርምጃዋ በውሃ ክፍፍሉ ጥያቄ አኳያ አቋሟን ቀይራለች ማለት ሳይሆን ገሀዱን ሁኔታ የማስለወጥ አቅም እንደሌላት በመገንዘብ ሳይሆን እንዳልቀረ መሆኑን የበርሊኑ የሳይንስና ፖለቲካ ተቋም ባለደረባ ቶቢያስ ፎን ላሶቭ ይገምታሉ።
«ግብፅ አቋሟን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋ አጣጥማለች ማለት ይቻላል። ለብዙ ዓመታት ግብፅ የሕዳሴን ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል ወይም የግድቡ መጠን ገደብ እንዲያርፍበት ለማስደረግ ሞክራለች። ግን ካይሮ በወቅቱ ይህ ገሀድ ሊሆን የማይችል ነገር መሆኑን ሳትረዳው አልቀረችም። ይህ አመለካከቷ እና ግብፅ እንደገና ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ የተመለሰችበት ድርጊት ካይሮ የዚህኑ ግድብ ኅልውና፣ የዚህኑ ግድብ ግንባታ በተዘዋዋሪ መንገድ መቀበሏን የሚጠቁም ነው። »


ይህ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለፉት አሠርተ ዓመታት፣ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በታየው ውጥረት ባላጣው ግንኙነት ላይ ወሳኝ እና አዎንታዊ ርምጃ መሆኑን ተንታኙ ላሶቭ ቢያመለክቱም፣ ግብፅ ስለ ዐባይ ውሃ በምትከተለዉ መርሕ ላይ ያለው ችግር ሁሉ የመጨረሻ መፍትሔ አገኘ ማለት አለመሆኑን ገልጸዋል። የሕዳሴው ግድብ ግዝፈትን እና የውሀውን ሙሌት በተመለከተ በግብፅ ህብረተሰብ ውስጥ ስጋት ያላቸው ወገኖች ግንባታው እንደታቀደው ሊቀጥል በመቻል አለመቻሉ ጉዳይ ላይ እንደገና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊመከርበት ይገባል በሚል ባለፉት ቀናት ያወጡዋቸው መግለጫዎች በዐባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ላይ በግብፅ ተቃውሞው ጨርሶ አለመጥፋቱን የሚያሳይ ነው። ያም ቢሆን ግን፣ የአል ሲሲ መንግሥት በተለይ ባካባቢው ተፅዕኖዋ ከፍ እያለ ከሄደው የኢትዮጵያ አመራር ጋር መተባበሩ የሚያዋጣ ሆኖ በማግኘቱ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ከፍጥጫ ይልቅ ትብብር መፍጠሩን አስፈላጊ አድርጎ ተመልክቶታል፣ እንደ ጀርመናዊው የሳይንስና ፖለቲካ ተቋም ባለደረባ ቶቢያስ ፎን ላሶቭ አስተያየት።
« እዚህ ላይ ሁለት ጉዳዮችን መመልከት ይኖርብናል። አዲሱን የኢትዮጵያ ሚና ስንመለከተው ያካባቢ ኃያል መንግሥትነቷን፣ እንዲሁም ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲው ተፅዕኖዋ ከፍ እያለ መምጣቱን እናያለን። ለዚህም ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችው ኤኮኖሚያዊ ዕድገትም ድርሻ አበርክቶዋል። አለመረጋጋት የሚታይበትን የአፍሪቃ ቀንድን በማረጋጋቱ ረገድ እና በዓለም አቀፉ ፀረ ሽብር ዘመቻ ላይ ኢትዮጵያ ዋነኛ የምዕራቡ ዓለም ተባባሪ ናት። በሌላ በኩል፣ የግብፅ ሚና ባካባቢው ቀንሶዋል። ከዚህ በተጨማሪም የግብፅ አቋም ደካማ በመሆኑ የቀድሞ ወዳጆችዋ ገሸሽ እያሉባት ነው። ግብፅ ከምዕራብ አጎራባችዋ ሊቢያ ጋር ችግር አላት፣ የየመን ትርምስ መባባሱም ለግብፅ ችግር ነው። ለረጅም ጊዜ ወንድማዊ ግንኙነት አላት ከምትባለው ዐረባዊት ሀገር ሱዳንም ጋር እስከቅርብ ጊዜ የነበራት የቅርብ ግንኙነት እየተሸረሸረ ነው። ስለዚህ፣ ባካባቢው እንደ ብቸኛዋ አጋር ከምትመለከታት ኢትዮጵያ ጋር በመራራቅ ፈንታ፣ ከዚችው ሀገር ጋር መቀራረቡ እና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አጋርነት መፍጠሩ ስልታዊ ጥቅሟን በተሻለ መንገድ ለማስጠበቅ እንደሚያገለግላት ዘዴ አይታዋለች። »

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic