የግብፅ የዉጪ መርሕ-አፍሪቃና አረብ | ዓለም | DW | 16.05.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የግብፅ የዉጪ መርሕ-አፍሪቃና አረብ

ሳዳት በእናታቸዉ ከሱዳን መወለዳቸዉን፥ የሐገራቸዉ ሕዝብ የእስትንፋስ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗን በርግጥ አያላጡትም።አልካዱትምም።መንግሥታቸዉ ከኢትዮጵያ፥ ከሱዳን ይሁን ከተቀሩት የአፍሪቃ ሐገራት ጋር ለጋራ ጥቅም አብሮ ከመስራት ይልቅ ወገኖቻቸዉ እንዳፌዙት አፍራሹን ነበር የሚፈፅመዉ።

default

ከግብፅ መሪዎች አንዱ

በ1970 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የግብፅን የፕሬዝዳትነት ሥልጣን የያዙት አንዋር አል-ሳዳት ሥልጣን አዉራሻቸዉ ናስርን ያደንቁ፥ ያከብሩ ነበር እንጂ መርሐቸዉን አልተከተሉም።ሳዳትን የተኩት ሆስኒ ሙባረክ በሳዳት በጀመሩት ቀጠሉ እንጂ ወደ ናስር አልተመለሱም፥አዲስ መርሕም አልቀየሱም።ሙባረክን ያስወገደዉ ሕዝባዊ አብዮት ለስልጣን ያበቃቸዉ ሐይላት መርሕ እንዴትነት በርግጥ ለግምገማ ገና ለጋ ነዉ።ከዋሽንግተን፥ ብራስልስ ይልቅ ሪያድ-ዶሐ፥ጁባ-ካርቱም፥ አዲስ አበባ-ካምፓላ፥ ምናልባትም ጋዛ-ቴሕራን የማለታቸዉ ጅምር ግን በርግጥ ያነጋግራል።አብራችሁን ቆዩ።
የአዲስ አበባዉ የቀድሞዉ አብዮት አደባባይ «አለም አቀፍ ኢፔሪያሊዝምን» ለማዉደም በሚፈክሩ፥ በሚያቅራሩ አብዮተኞች ሠልፍ-ዉግዘት በሚጤስበት ዘመን ሽሙጥ-የሚወዱት ግብፆች ይቀልዱ ነበር አሉ።እንዲሕ እያሉ «ግብፃዊዉ ጋዜጠኛ ፕሬዝዳንት አንዋር አሳዳትን ኢትዮጵያ ግብፅን ትወራላች ወይም ትተናኮላለች ብለዉ አይሰጉም» አይነት ብሎ ጠየቃቸዉ።
ሳዳት ፈገግ አሉ-አሉ።መለሱም።«ኢትዮጵያ ግብፅን በቀጥታ ትወጋለች ብለን አንሰጋም፥ የኢትዮጵያ መሪዎችም አሜሪካንን እንጂ ግብፅን እንወጋለን አላሉም---የሚያሰጋን እንዲያዉ ምናልባት የኢትዮጵያ ጦር አሜሪካን ለመዉጋት በሜድትራንያን በኩል የሚያልፍ ከሆነ እኛን እንዳይረመርመን ነዉ።»ብለዉ አፌዙ።
ዛሬ ግን ቀልድ-ፌዙ ያቀርቶ ሌላ ዘመን መጥኖ አይነት ነዉ።የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት የሙባረክን ሥርዓት ሲጠራርግ የአብዮቱ ዘዋሪዎችና አብዮቱ ለስልጣን ያበቃቸዉ ወገኖች አባይ ቁል ቁል የሚወርደዉን አቀበት በሱዳን በኩል ኢትዮጵያ፥ በኢትዮጵያ አሳብረዉ ዩጋንዳ እያሉ ሽቅብ እየወጡት ነዉ።የአፍሪቃ ጉዳይ የፖለቲካ አዋቂ አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ያሁኖቹም ሆኑ የወደፊቶቹ የግብፅ መሪዎች የቀዳሚዎቻቸዉን ሥሕተት አይደግሙትም።
የግብፅና የሱዳን ይባል የነበረዉን የግብፅን ዘዉዳዊ አገዛዝ በ1952 በፈንቅለ መንግሥት ያስወገደዉ የጦር መኮንኖች ቡድን መሪ ገማል አብድናስር፥ «መጀመሪያ የአረቦች፥ቀጥሎ የሙስሊ ዓለም አሰልሶ አፍሪቃ» የሚል ጠንካራ የዉጪ መርሕ ነበራቸዉ።ናስር ሲሞቱ አብዛኛ መርሐቸዉም በርግጥ አብሮ ሞተ።ሳዳት እንደ ምክትል ፕሬዝዳት ናስርን በታማኝነት ቢያገለግሉም የናስርን ምጣኔ ሐብታዊ፥ ፖለቲካዊ፥ በጣሙን የዉጪ መርሕ ቀይረዉት ነበር።

NO FLASH Ägypten Kairo Demonstration

ሕዝባዊዉ አብዮት

ሳዳት በእናታቸዉ ከሱዳን መወለዳቸዉን፥ የሐገራቸዉ ሕዝብ የእስትንፋስ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗን በርግጥ አያላጡትም።አልካዱትምም።መንግሥታቸዉ ከኢትዮጵያ፥ ከሱዳን ይሁን ከተቀሩት የአፍሪቃ ሐገራት ጋር ለጋራ ጥቅም አብሮ ከመስራት ይልቅ ወገኖቻቸዉ እንዳፌዙት አፍራሹን ነበር የሚፈፅመዉ።

ሳዳት አፍሪቃን አግልለዉ በናስር መርሕ መጀመሪያ ላይ የተቀመጠዉን አረቦችን ችላ ብለዉ የካምዴቪዱን ስምምነት መፈረማቸዉ ለመንግሥታቸዉ አይደለም ለሕይወታቸዉም አልጠቀመም። ሥልጣን በያዙ በአስራ-አንደኛ አመታቸዉ ተገደሉ።ሳዳትን የተኩት ሆስኒ ሙባረክ ከአፍሪቃ-አረብ ይልቅ የዋሽንግተን-ለንደን ታማኝነታቸዉን ለማስከበር እንደባተሉ-በሰላሳኛ አመት ዘመነ-ሥልጣናቸዉ በሕዝብ ተጠልተዉ፥ ተወግዘዉ ተዋርደዉ ወረዱ።

ሙባረክን ከሥልጣን ያስወገደዉ ሕዝባዊ አብዮትን ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የመሩት ወይም በአብዮተኛዉ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸዉ ወገኖች የመሠረቱት ስብስብ «ሕዝባዊ ዲፕሎማት» ብለዉታል እነሱ መጀመሪያ ወደ ሱዳን ነበር የተጓዘዉ።ቀጥሎ ኢትዮጵያ።አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ኢሳም ሻረፍ ተከተሉት።

አዲሱቹ የግብፅ መሪዎች ወይም ሕዝባዊ ዲፕሎማቶች አረብ-አፍሪቃ ማለታቸዉ የናስር ዘመኑን አይነት መርሕ የመከተላቸዉ ፍንጭ ይሁን አይሁን በርግጥ አለየም።አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ግን ሙባረክን ከሥልጣን ያስወገደዉ ሕዝብ ካነሳቸዉ ትላልቅ ጥያቄዎች ቢያንስ አንዱን ለመመለስ እሞከሩ ነዉ።

የግብፆች በተለይ ኢትዮጵያና ዩጋንዳን የጎበኙት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግዙፍ ግድብ መገንባት መጀመሯ በተለይ ደግሞ የወንዙ የላይኛዉ ተፋሰስ የሚባሉት ሐገራት ሥለ አባይ ዉሐ አጠቃቀም በቅኝ ገዢዎች ዘመን የነበረዉን ደንብ የሚተካ አዲስ ደንብ ማዘጋጀት-ማፅደቃቸዉ ካይሮዎችን ሥላሰጋቸዉ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ።

አርባ-ስምንት አባላት ያሉት የሕዝባዊ ዲፕሎማሲ መልዕክተኞች አዲስ አበባን በጎበኙበት ወቅት ያነሳዉ ጥያቄ፥ ከኢትዮጵያ ሹማምንት የተገባላት ቃል፥ ከጠቅላይ ሚንስትር ኢሳም ሻረፍ ጋር የተደረገዉ ስምምነትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነዉ።ሻረፍ ያስከተሏችዉ የግብፅ ነጋዴዎች፥ ባለኩባንዮችና የነጋዴዎች ፌደሬሽን ምክር ቤት ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያዉያን አቻቸዉ ጋር ያደረጉት ሥምምነት ግን ጉብኝት ዉሉ ከዉሐም ያለፈ መሆኑን ጠቋሚ ነዉ።የነጋዴዎቹን ልዑካን የመሩት የግብፅ ነጋዴዎች ፌደሬሽን ምክር ቤት ፕሬዝዳት ሰዒድ አሕመድ አል-ወኪል እንዳሉት ደግሞ ኢትዮጵያና የግብፅ ነጋዴዎች ትብብር መላዉ አፍሪቃን ከሚያቀራርብበት ደረጃ መድረስ አለበት።

ናስር አንደኛ ይሉት ለነበረዉ ለአረቡ ዓለምም አዲሱ የግብፅ መሪዎችም የአንደኝነቱን ደረጃ አልነፈጉትም።ጠቅላይ ሚንስትር ኢሳም ሻረፍ ከየትኛዉም ሐገር በፊት የጎበኙት ሪያድ-ስዑዲ አረቢያን ነዉ።ሻረፍ ባለፈዉ ሚዚያ ከስዑዲ አረቢያዉ ንጉስ አብደላሕ ጋር ባደረጉት ዉይይት ላይ የተካፈሉ አንድ የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣን «የሁለቱ መሪዎች ዉይይት በመግባባት ላይ የተመሠረተ ነበር።መግባባቱ በሙባረክ ጊዜ እንደነበረዉ አይነት ነበር ማለት ግን አልችልም» ነበር ያሉት።

ሻረፍ በዚያዉ እግራቸዉ ኩዌትና ቀጠርን ጥቂት አረፍ ብለዉ የተባበሩት አረብ ኤምሬትንና ባሕሬንን ጎብኝተዋል።ጉብኝት ዲፕሎማሲዉ ግብፅ እንደ ባለቤት የምትጠበቀዉን የአረብ ሊግን የመሪነት ሥፍራ እንዳታጣ ረድቷታል።ያም ሆኖ አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የግብፅ ፖለቲከኞች የሕዝባቸዉን ጥያቄ፥ የሐገራቸዉንም ክብር ለመመለስ የሚያደረጉት ጥረት ፈተናም አላጣዉም።

በዚሕም ብሎ በዚያ የግብፅ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የሚመሩት ጊዚያዊ መንግሥት የሙባረክን የዉጪ መርሕ እየመነቃቀረዉ መሆኑ ግልፅ ነዉ።ሕዝባዊ ዲፕሎማት የተባሉትም ሆኑ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከተለያዩ ሐገራት መሪዎች ጋር የሚያደርጉት ዉይይትና ስምምነት የግብፅ ቋሚ መርሕ ነዉ ማለት ግን አይቻልም።

በግብፅን ሕዝባዊ አብዮት ለሥልጣን ያበቃቸዉ ፖለቲከኞችም ሆኑ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸዉ ወገኖች የጀመሩት ዲፕሎማሲ የረጅምም ይባል ያጭር ጊዜ መርሕ እሳካሁን የተደረገዉ ግንኙነት ባብዛኛዉ የየሐገሩን ሕዝብ «ሠብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች» የሚደፈልቁ ከሚባሉት መሪዎች ጋር ነዉ።የአንዳዱ ሐገር ሕዝብ ደግሞ ምናልባት እንደሙባረክ የሚያምፅባቸዉ መሪዎች ናቸዉ።
ግብፆች የሕዝባቸዉን ጥያቄ የመመለሱን አስፈላጊነትና ሕዝባዊ አብዮት ከሚያሰጋቸዉ መሪዎች ጋር ግንኙነት የመፍጠሩን ተቃርኖ የሚያጣጥሙበትን ብልሐት-ማወቅ የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ለታዛቢዎች አስቸጋሪ ነዉ።የግብፅ መሪዎች ከእስራኤልም ከዩናይትድ ስቴትስም ፍላጎት ወጣ ብለዉ የፍልስጤም ተቀናቃኝ አንጃዎች ሐማስና ፈታሕ መታረቃቸዉን ደግፈዋል።የፖለቲካዉን ስልጣን የያዙት ወገኖች ባይኖሩበትም የግብፅ ነጋዴዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ቴሕራንን ለመጎብኘት ተዘጋጅተዋል።

Arabische Liga Ägypten Nabil al-Arabi

አዲሱ የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ የቀድሞዉ የገብፅ ዉጉሚ ነቢል አል-አረቢ

የቴሕራኑ ጉብኝት እንደተባለዉ ከተፈፀመ ግብፅ አንዋር አሰዳት ከተገደሉ ጀምሮ እንደ ጠላት ታያት ከነበረችዉ ኢራን ጋር ጠብ-ግጭቱ ከሙባረክ አገዛዝ ጋር አለፈ ከማለት እኩል የሚቆጠር ነዉ። ካይሮዎች በእቅዳቸዉ ከገፉ የዋሽንግተንን ትዕዛዝ፥ የእስራኤልን ግፊት፥ የባሕረ-ሠላጤዉ አካባቢ ሐገሮችን ፍላጎት ከመጣስ ሊቀጠርባቸዉም ይችላል።

የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት የቱኒዚያዉን ተከትሎ ለድል እንደበቃ፥ አል-ጄሪያ፥ ዮርዳኖስ፥ ባሕሬን፥ የመን እና ሊቢያ ዉስጥ ተመሳሳይ አብዮት መቀጣጠሉ ግብፅ የሚሆነዉ በነናስር ዘመን እንደነበረዉ ዳግም የአረቡን ዓለም ፖለቲካዊ ስርዓት ሊቀይረዉ ነዉ አሰኝቶ ነበር።እስካሁን ግን ሊቢያ በቦምብ-ሚሳዬል፥ ጥይት አረር ማረሯ፥ የባሕሬኑ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መዳፈኑ፥ የመንና ሶሪያ በሰልፍ፥ ግድያ እስራት መሰቃቀላቸዉን ከማየት-መስማት ባለፍ የሕዝባዊዉ አብዮት ድል-ዉድቀት አልተረጋገጠም ። የነገዉን ነገ ለማየት ያብቃን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰAudios and videos on the topic