የግብፅ የቱሪዝም ኤንዱስትሪ እና ስጋቱ | ዓለም | DW | 20.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የግብፅ የቱሪዝም ኤንዱስትሪ እና ስጋቱ

ከፓሪስ ወደ ካይሮ ሲጓዝ የነበረዉ የግብፅ መንገደኞች አውሮፕላን ስብርባሪዎችና የመንገደኛ ንብረቶች ከወደብ ከተማዋ ከአሌክሳንድሪያ በስተሰሜን 290 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኘታቸዉ ተገልፆአል።ሥጋት የጋረደዉ የግብፅ የቱሪዝም ኤንዱስትሪ በግብፅ አውሮጵላን ላይ በደረሰዉ በዚህ አደጋ ዳግም ጥላ ያጠላበት ሳይሆን እንዳልቀረ ነዉ የሚነገረዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:28
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:28 ደቂቃ

የግብፅ የቱሪዝም ኤንዱስትሪ

«ሞት በአባይ ወንዝ ላይ» ይሰኛል ፤ የታዋቂዋ ብሪታንያዊት የወንጀል ታሪኮች ደራሲ የአጋታ ክርስቲ ልብ ወለድ መጽሐፍ። በልብ ወለዱ ላይ ከ 80 ዓመት ግድም በኋላ በግል የወንጀል መርማሪ የሆኑት ሄርኩለ ፒሮት በዓለም በርዝመቱ በሚታወቀዉ አባይ ወንዝ ላይ የሚቀዝፉ ቱሪስቶችን የጫኑ መርከቦች ፍሪያማ ዓመታትን ማሳለፋቸዉን ይተርካሉ። በእነዚህ ጊዜያት ሀገር ጎብኚዎች በሉክሶርና አስዋን ከተማ የሚገኙትን ታዋቂ ጥንታዊ ቤተ- እምነቶችን ሲጎበኙ ቆይተዋል። የያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2016 የግብፅ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከምንጊዜዉም በላይ የተዳከመበት እንደሆነ በዘርፉ የሚገኙ ዉስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ባለፈዉ መጋቢት ወር ግብፅን የጎበኙት ቱሪስቶች ቁጥር ካለፈዉ ዓመት በግማሽ ቀንሷል።

ጀርመናዊትዋ ካትሪና ቪንስ ኮነራድ በአባይ ወንዝ ላይ በሚቀዝፈዉ « MS Zeina» በተባለዉ መርከብ መጓዝ ከፈለጉ፤ ወደ መርከቡ ለመግባት በመጀመርያ በአካባቢዉ በቆመ አንድ መርከብ በኩል ማለፍ ይኖርባቸዋል። በሀገር ጎብኝዎች እጥረት በቆመዉ በዚህ መርከብ ሰፊ ክፍል ዉስጥ የሚገኙትን መቀመጫና ሶፋዎች ከአቧራ ለመከላከል ሰፊ ጨርቅ ሸፍኗቸዋል። ጀርመናዊትዋ በአባይ ወንዝ ላይ በመርከብ ሲጓዙ ይህ ሁለተኛቸዉ ሲሆን ለመጀመርያ ጊዜም በጎርጎሪዮሳዊዉ 2010 ዓ,ም በግብፅ ከታዩት ሁለት ብሔራዊ የሕዝብ ንቅናቄዎች ቀደም ሲል ግብፅን ጎብኝተዉ ነበር።

«በአካባቢዉ ለጥላ የሚሆን ጃንጥላ መያዝ አልያም መከናነብ የግድ ይላል። አሁን በጣም ጥቂት ሰዎች እንዲሁም መርከቦች ናቸዉ ቦታዉ ላይ ያሉት። በርግጥ አሁን ለኛ ሁኔታዉ ጥሩ ነዉ። አካባቢዉ ላይ የትም ቦታ መቆም አይቻልም፤ መሄድ ብቻ ነዉ። »

ግብፅ ዉስጥ ወደ 250 መርከቦች በአባይ ወንዝ ላይ ለመቅዘፍ የሚያስችል ፈቃድ ቢኖራቸዉም አብዛኞቹ ግን ከአገልግሎት ዉጭ ናቸዉ። በደቡባዊ ሉክሶር ወደ 12 የሚሆኑ አነስተኛ ጀልባዎች በረድፍ በረድፍ ተሰልፈዉ ቱሪስቶችን ለሟጓጓዝ ቆመዉ ይጠባበቃሉ። በአሁኑ ወቅት ካሉት አንድ አምስተኛ የሚሆኑት መርከቦች ብቻ ናቸዉ ሰዎችን የሚያጓጉዙት። እነዚህም ቢሆኑ በቂ ተሳፋሪዎን ማለት ቱሪስቶችን አልጫኑም። በመርከቡ ሰፊ የምግብ አዳራሽ ጥቂት ሰዎች ብቻ መታየታቸዉ፤ ሥራዉ መቀዛቀዙን አመላካች ነዉ ይላሉ የመርከቡ ዘዋሪ ፋራዲ ሩሺዲ። ሩሺዲ የሚመሯቸዉ የሀገር

ጎብኝዎች 40 እንኳ አይሞሉም።

ለሀገር አስጎብኝዉ ፋራዲ ሩሺዲ ይህን የጎብኝዎች ቡድን ይዘዉ ሲመሩ ለዚህ ዓመት የመጀመርያቸዉ ነዉ፤ ምናልባትም ይህ የጎብኝዎች ቡድን የመጨረሻዉ ሊሆንም እንደሚችል ነዉ ራሽድ የገለፁት። ግብፃዊዉ ሀገር አስጎብኚ ይህን ያሉት ሌላ የቱሪስቶች ቡድን እስካሁን ባለመመዝገቡና ይመዘገባልም የሚል ግምት ስለሌላቸዉ ነዉ። ፋራዲ ሩሺዲ የቱሪስቶች መስሕብ የሆኑት በሉክሶርና አስዋን ከተሞች የሚገኙትን ጥንታዊ ቤተ-እምነቶች ፤ በግድግዳ ላይ የተሳሉ ጥንታዊ ቅቦችን ሁሉ ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። ፋራዲ ሩሺዲ ሱዳን አዋሳኝ ላይ የሚገኙዉን የቱቱታን ቻማን ጥንታዊ መካነ መቃብር አልያም ጥንታዊዉን የአቡ ሲምቤል ቤተ- እምነት ለጎብኝዎች ማሳየት ከጀመሩ 40 ዓመታትን አስቆጥረዋል። በዚህም ፋራዲ ሩሺዲ በግብፅ የቱሪዝም ከፍተኛ ገቢ የነበረበትን ጊዜ እንዲሁም በዚሁ ዘርፍ የነበረዉን አንዳንድ ቀዉሶች ጠንቅቀዉ ያዉቃሉል። እንደ ፋራዲ ሩሺዲ በግብፅ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንደ ዘንድሮ ያለ ቀዉስ ደርሶበት እንደማያዉቅ ነዉ የሚናገሩት፤

« በፊት መርከቦቻችን ሙሉ ነበሩ። መርከቡ ላይ 120 ተጓዦች ካሉ ለአራት ቡድን ተከፍሎ አራት የመርከብ ሠራተኞች ያስተናግዱ ነበሩ። ይህ ማለት በእንዳንዱ ቡድን 30 ተሳፋሪዎች ይደለደላሉ። አሁን አሁን ግን በመርከቡ ላይ በጠቅላላ 30 ወይም 35 ሰዉ ብቻ ነዉ የሚኖረዉ፤ ልክ አንደዛሬዉ,,,አልያም መርከቡ ጨርሶ ባዶ ሆኖ ነዉ የሚዉለዉ።»

በአባይ ወንዝ ላይ በሚቀዝፈዉ ግዙፍ መርከብ ዉስጥ የሚያገለግሉት ተቀጣሪ ግብፃዉያን ቁጥር ከ 80 እስከ 100 ይደርሳል። እነዚህ ሠራተኞች ኑሯቸዉን የሚገፉትና ቤተሰቦቻቸዉን የሚያስተዳድሩት በሚያገኙት ደመወዝና ሀገር ጎብኚዉ ከሚሰጣቸዉ አነስተኛ ጉርሻ ነበር። በግብጽ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ የደረሰዉ ቀዉስ የጎዱትዉ የመርከብ ላይ ሠራተኞቹ ብቻ ሳይሆኑ፤ የከተማ አዉቶቡስና የታክሲ አሽከርካሪዎች እንዲሁም ለሀገር ጎብኝዎች ባህላዊ ቁሳቁስ የሚሸጡት ነጋዴዎችም ጭምር ናቸዉ። በዚህ ሁሉ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩት ግብፃዉያን ሁሉ የሀገር ጉብኚዎች ግብፅን ገሸሽ እያደረጉ ናቸዉ የሚል እምነት አድሮባቸዋል። ካንዴም ሁለቴ ግብፅን የጎበኙት ጀርመናዊት ካትሪን ቪንስ ኮነራድ ግን ግብፅን በቀጣይ ከመጎብኘት ወደኋላ እንደማይሉ ነዉ የሚናገሩት።

«ወደ ግብፅ ለመሄድ መነሳቴን ስናገር በርግጥ አትፈሪም እንዴ? የሚል ጥያቄ ይቀርብልኛል። እኔ ግን በፍፁም አልፈራም ! የጉዞ እቅድሽን አትሰርዥም ? የሚል ጥያቄም ሳይቀር እጠየቃለሁ። የተለያየ ሁኔታ በግብፅ ብቻ ሳይሆን በሌላም ቦታ ሊያጋጥም ይችላል። እኔ ግን በግብፅ ደህንነቴ የተጠበቀ እንደሆነ ይሰማኛል፤ አልፈራም።»

ካትሪና ቪንስ ኮነራድ ከግብፅ ጉብኝት በኋላ ወደ ጀርመን ሲመለሱ በግብፅ ያለዉን እዉነታ ለሌሎች ማካፈል ይችላሉ። የሀገር አስጎብኝዉ ፋሪድ ሩሺዲ ዋንኛ ሃሳብም ወኔን አለማጣት የሚል ነዉ።

«አንድ ቀን ይሻሻላል ብሎ ማሰቡ ጥንካሬን ከሁሉ በላይ ደግሞ ተስፋን የሚሰጥ ነዉ። ሀገሪቱን እንደሚወዱና ምንም ቢሆን እንመጣለን የሚሉን ሰዎችን መስማትም በራሱ ክብር ነዉ።»

ያን ዴቪድ ቫልተር / አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic