የግብፅ አዉሮፕላን ባህር ላይ ወደቀ | አፍሪቃ | DW | 19.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የግብፅ አዉሮፕላን ባህር ላይ ወደቀ

የግብፅ የአዉሮፕላን አደጋን ከቴክኒክ ብልሽት ይልቅ በይበልጥ የአሸባሪ ጥቃት ሳይሆን እንደማይቀር የሩስያ የደህንነት ሚኒስቴርና የግብፅ አቪየሽን ሚኒስትር መግለፃቸዉ ተዘግቦአል። ይህን ተከትሎ ግብፅ አደጋዉን ለማጣራት ፈረንሳይን ያካተተ አንድ የምርመራ ኮሚቴ ማቋቋማ ተመልኮአል። የአዉሮፕላኑ ስብርባሪም ግብፅ ባህር ዳርቻ ሳይገኝ አልቀረም።

የግብፅ መንግሥት ራድዮ ጣብያ ሃሙስ አመሻሹ ላይ እንደዘገበዉ የወደቀዉ አዉሮፕላን ስብርባሪ በግሪክዋ ካርፓቶስ ደሴት ባሕር ዳርቻ ተገኝቶአል። ከፓሪስ ፈረንሳይ ወደ ግብፅ በማምራት ላይ የነበረ አንድ የግብፅ አየር መንገድ ሜዲተራንያን ባሕር ላይ መዉደቁ ግልፅ መሆኑን የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፋራንስዋ ሆላንድ ዛሬ በኤሌዜ ቤተ-መንግሥት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ሆላንድ አዉሮፕላኑ በባህር ዉስጥ ሳይሰምጥ አልቀረም ጠፍቶአል፤ አዉሮፕላኑ የተከሰከሰበት ምክንያት ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም ሲሉ ገፀዉ ነበር። ቢሆንም አሁን አዉሮፕላኑ የተከሰከሰበትን ምክንያት መፈለግና በአዉሮፕላኑ ከነበሩ ተሳፋሪ ቤተሰቦች ጎን መቆም እንደሚያስፈልግ ነዉ የገለፁት። ከዚህ ቀደም ሲል የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑኤል ቫልስ በሰጡት መግለጫ ሀገራቸዉ ሜዲተራንያን ባህር ላይ ወደቀ የተባለዉን የግብፅ አየር መንገድ ለመፈለግ ዝግጁ መሆንዋን ተናግረዉ ነበር።


« ከግብፅ ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናት ጋር የቅርብ ግንኙነት እያደረግን ነዉ። የግብፅ ባለሥልጣናት አዉሮፕላኑ ጠፍቶአል በሚባልበት አካባቢ ከአየር የሚቃኝ ቡድን ልከዋል። ፈረንሳይም የግብፅ ባለስልጣን ጥያቄ ካቀረቡ ለመተባበር ዝግጁ ናት። እንደማስበዉ አሁን ባለበት ደረጃ አዉሮፕላኑ የጠፋበትን ምክንያቶች መግለፅ አንችልም፤ አዲስ መረጃ እስኪደርስን እንጠብቃለን።»


56 ተሳፋሪዎችን፤ ሰባት የአዉሮፕላኑን ሠራተኞችና ሦስት የደሕንነት ባለሥልጣናትን ይዞ ከፓሪስ ወደ ካይሮ ግብፅ ይጓዝ የነበረዉ EgyptAir A 320 የግብፅ አዉሮፕላን ከግሪክዋ ካርፓቶስ ደሴት 240 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሳለ ከራዳር መሰወሩ ተገልፆ ነበር። በአዉሮፕላኑ ዉስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ተጓዦች ግብፃዉያንና ፈረንሳዉያን መሆናቸዉም ተዘግቦአል።


ዘግየት ብሎ ወጣ ዜና የግብፅ የአዉሮፕላን አደጋን ከቴክኒክ ብልሽት ይልቅ በይበልጥ የአሸባሪ ጥቃት ሳይሆን እንደማይቀር የሩስያ የደህንነት ሚኒስቴርና የግብፅ አቪየሽን ሚኒስትር ገልፀዋል። ይህን ተከትሎ ግብፅ አደጋዉን ለማጣራት ፈረንሳይን ያካተተ አንድ የምርመራ ኮሚቴ ማቋቋማ ነዉ የተዘገበዉ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ