የግብፅ አብዮት ቅጭትና የቅድሞ ፕሬዝደንቷ ፍርድ | ዓለም | DW | 19.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የግብፅ አብዮት ቅጭትና የቅድሞ ፕሬዝደንቷ ፍርድ

አል-ሲሲ መለዮም ለበሱ ካራቫት፤ ፖለቲካዊ፤ ዲፕሎማሲያዊ፤ ወታደራዊ፤ ምጣኔ ሐብታዊዉ ድጋፍ ይንቆረቆርላቸዋል።ድጋፉ ሺዎችን እያስገደሉ፤ አስር ሺዎችን እያሳሰሩ፤ በጅምላ ሞት እያስፈረዱ፤ አምባገነን ወዳጆቻቸዉን እያስፈቱ አረባዊ-አፍሪቃዊቱን ሐገር ረግጠዉ ለመግዛት ጠንካራ ምርኩዝ ሆናቸዋል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:37
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
14:37 ደቂቃ

የግብፅ አብዮት ቅጭትና የቅድሞ ፕሬዝደንቷ ፍርድ

ግንቦት 2012 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ነዉ) ለፕሬዝደንትነት ተወዳደሩ።የረጅም ዘመን ታሪካዊቱ ሐገር ሕዝብ ለመጀሪያ ጊዜ በነፃነት በሰጠዉ ድምፅ ተመረጡም።ሰኔ 24 2012

ዶክተር መሐመድ መሐመድ ሙርሲ ኢሳ አል አያት። በዘመነ-ዘመናት የነፃነት ታሪኳ ነፃ ምርጫ፤ ፍትሕ፤ ዴሞክራሲ በማታዉቀዉ ታሪካዊ ሐገራቸዉ አዲስ ታሪክ ሊሠሩ እንደ ፕሬዝደንት አንድ-ሁለት ማለት ሲጀምሩ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ተወገዱ።ታሠሩም።ሐምሌ 2013።በሁለተኛ ዓመቱ ዘንድሮ-ቅዳሜ ሞት ተፈረደባቸዉ።

በጀርመኝኛ ARD-በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ የካይሮ ዘጋቢ ፎልከር ሽቬንክ «ግብፆችን ሥለ አረብ ሕዝባዊ አብዮት ድል ስጠይቃቸዉ» አለ ባለፈዉ ቅዳሜ «ከመልሳቸዉ በፊት ፈገግታ» ያስቀድማሉ።ወጣትዋ ጋዜጠኛም እንዲሁ።

«የማዳ መስራዋን ወጣት ጋዜጠኛም ተመሳሰይ ጥያቄ-ጠይቂያት ነበር።ፈገግ አለች።ቀጠለችም የአብዮቱ (ዲሞክራሲያዊ) ዉጤት የሆነ ጊዜ ይታይ ይሆናል የሚል የተስፋ እንጥፍጣፊ ይኖር ይሆናል። እዉነቱን ለመናገር ግን-ይሕ የሚሆን አይመስልም።» እያለች።»

የፕሬዝደንት ሆስኒ ሙባረክን 30 ዘመን አምባገነናዊ አገዛዝ ባደባባይ ሠላማዊ ሠልፍ ግዝግዞ የገረሰሰዉ ሕዝባዊ አብዮት እንደ አብዮተኛዉ ሕዝብ ፍቃድ፤ ፍላጎት ጥያቄ-የዴሞክራሲያዊያ ሥርዓት ጭላንጭል አሳይቶ ከነበር ግንቦት 20012 በርግጥ ደማቅ ነበር።ነፃ ምርጫ።የምርጫዉ ዉጤት ሲታወጅ ደግሞ የሒደቱ ሠላማዊ፤ነፃና ፍትሐዊነት ማረጋገጪያ።

ለአሮጌይቱ ሐገር ሕዝብ አዲስ ተስፋ።ደስታም ጭምር።የሕዝባዊ አብዮቱን የእስከዚያ ጊዜ ሂደት ዉጤት፤ የግብፆችን ተስፋ-ደስታ በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች ደጋግመዉ እንዳሉት ከፒራሚድ እስከ ፎቶ ጥበብ፤ከሕክምና እስከ ሥነ-ፈለክ፤ ከክሊዮፓትራ እስከ ነጉብ ማሕፉዝ ለዓለም ያበረከተችዉ ግብፅ በአዲሱ ዘመንም ሠላም፤ ዲሞክራሲ፤ ፍትሕ፤ ነፃነት ለማያዉቀዉ ለአረብና ለአፍሪቃ አዲሱን ሥርዓት አስተዋወቀች አስኝቶ ነበር።

የግብፅ ሕዝብ ትግል ዉጤት ለዓረብ፤ ለአፍሪቃ ሕዝብ እንደ ጥሩ አስተምሕሮት፤ ለሕዝብ ነፃነት፤ እኩልነት፤ ለዲሞክራሲ ልዕልና ለሚታገለዉ ለተቀረዉ ዓለም ሊሕቅ እንደ ታላቅ ድል የመታየቱን ያክል ለአምባ ገነን ገዢዎች፤ ለጠምንጃ ቸርቻሪዎች፤ በአምባገነን ገዢዎች ጥቅማቸዉን ለሚያስከብሩ መንግሥታት ጭምር በርግጥ አስደንጋጭ ነበር።

1952 ኮሎኔል ገማል አብድል ናስር የመሩት መፈንቅለ መንግሥት የሐገሪቱን ጦር መኮንኖች ለሥልጣን ካበቃበት ሙባረክ የሾሟቸዉ ጄኔራሎች በሕዝባዊ አመፅ ግፊት፤ በነፃ ምርጫ ሽንፈት ሥልጣን ለመልቀቅ እስከተገደዱበት እስከ 2012 ድረስ የአረብ-አፍሪቃዊቱ ታላቅ ሐገር ሁለንተናዊ ሒደት የሚወሰነዉ በጄኔራሎች ነበር።

ሥም፤ የጦር ክፍል፤ ማዕረጋቸዉ ከመቀያየሩ በስተቀር የግብፅን ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ወታደራዊ መዋቅሮች 60 ዘመናት የተቆጣጠሩት ጄኔራሎች የሕዝባዊዉን አብዮት ሒደትና ዉጤት በፀጋ ይቀበሉታል ብለዉ የገመቱ በርግጥ የዋሆች ነበሩ።

ከሪያድ እስከ ራባት ያሉ የአረብ ፈላጭ ቆራጭ ነገሥታት፤ አብዛኞቹ የአፍሪቃ አምባገነን ገዢዎችም በየሕዝባቸዉ ዘንድ እንደ ጥሩ አስተምሕሮ መታየት የጀመረዉን የሕዝባዊ አብዮት ድል፤ ተስፋ፤ ከመቅጨት እንደማያመነቱ ያልገመተ ከነበረ-እሱ በርግጥ ቢያንስ ለፖለቲካዉ ጅል ነበር።ግብፃዊዉ ስደተኛ ፖለቲከኛ አሚር ደአረግ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ «አንድም ከግብፅ ሕዝባዊ አብዮት አለያም ከቀልባሾች መወገኑን ይወስን» አሉ-ባለፈዉ ቅዳሜ።

«ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሐላፊነቱን መሸከም አለበት።የግብፅን (ሕዝባዊ) አብዮትና የግብፅን ዴሞክራሲያዊ ሒደት ለመቀልበስ የሚሸረበዉ ሴራ አካል ከመሆንና፤ ዴሞክራሲ ግብፅ እና በአካባቢዉ ዳግም እንዲያሠራራ የሚሻ ከመሆኑ አንዱን መምረጥ አለበት።»

እርግጥ ነዉ የግብፅ ፍርድ ቤት በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን በተወገዱት በመሐመድ ሙርሲ ላይ ባለፈዉ ቅዳሜ የሞት ቅጣት መበየኑን ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት «አሳሳቢ» ብለዉታል።ቅጣቱ ሲበየን ዮርዳኖስ የነበሩት የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይማየር ከዚሕም አልፈዉ ጀርመን የሞት ቅጣትን አጥብቃ እንደምትቃወም በግልፅ ተናግረዋል።

ይሁንና በሕዝብ ድምፅ ለሥልጣን ከሚበቃ፤ለሕዝብ ፍላጎት ካደረ፤ በሕግ-ሥርዓት ከሚገዛ ሥርዓት ወይም ፖለቲከኛ ይልቅ እንዳሻቸዉ በሚያዙት አምባገነን ሁለንተናዊ ጥቅማቸዉን በቀላሉ እንደሚያስከብሩ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት የዓለም ሐያላን የሕዝባዊዉን አብዮት ሒደት ዉጤት መደገፋቸዉ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።

ጥንታዊቱ ግብፅ ለዓለም ጥንታዊ ታሪክ፤ ቅርስ ሥልጣኔን አበርክታለች።የመንግሥትነት ቅርፅ ከያዘች ሰባት ሺሕ ዘመናት እስቆጥራለች።ሕዝቧ ሕግ ለፈላጭ ቆራጮች ከመገዛት ባለፍ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ዉስብስብ ሒደት፤ የሰጥቶ መቀበል አስተሳሰብን ጠቃሚነት፤ የፍትሕ ሥርፀትን አዝጋሚነት አያዉቅም።የሚያሳዉቁ አዋቂ፤ ተቋማት፤ መገናኛ ዘዴዎችም አላገኘም፤ ካገኘም ኢምንትና ደካማ ናቸዉ።

ከሁሉም በላይ -2011 ጀምሮ በሚያደርገዉ የአደባባይ ሠልፍ የተሠላቸዉ፤ በምጣኔ ሐብት ድቀት መራብ፤ መጠማት የጀመረዉ ግብፃዊ የታገለ፤የተራበ፤ የቆሰለ፤ የሞለተለትን አብዮት ለመቀልበስ የሚጣጠሩትን የዉጪም የዉስጥም ሐይላትን ሴራ ለማስተንተን አቅም፤እዉቀት፤ ትዕግሥቱም በርግጥ አልነበረዉም።

ግብፅ 1928 ጀምሮ መጀመሪያ በብሪታንያ፤ ቀጥሎ በሐገሬዉ ነገስታት፤ አሰልሶ በጦር ጄኔራሎች የተገፋ፤የተበደለ፤ የደኽየዉን ደካማ ሕዝብ ሲረዳ የኖረ አንድ ማሕበር አላት።የማሕበሩ ዓላማና ምግባር የማረካቸዉ የአብዛኞቹ የአረብ ሐገራት የድሐ ተቆርቋሪ፤ ሐይማኖት ሰባኪና ሙሕራን ተመሳሳይ ማሕበር ወይም ቅርንጫፍ መሥርተዋል።

የማሕበሩ ሥም የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበረሠብ፤ አርማዉ ሠይፍ፤ መሠረቱ እስልምና ነዉ። በግብፅ ታሪክ በነፃ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን የያዙት ፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲ የዚሕ ማሕበር አባል ናቸዉ።

ከፅኑ ሐይማኖተኝነት፤ ከጎበዝ መሐንዲስ፤ ፕሮፌሰርነት ባለፍ የዓለምን ጥልፍልፍ ፖለቲካዊ ጨዋታ የማያዉቁት ሙርሲም የማሕበራቸዉ ሥም፤ አርማም የሕዝባዊዉን አብዮት ድል፤ የበጎ እስተምሕሮቱን በጎ ተስፋ መትቶ ለመጣል የሚያሴሩትን ሐይላት ደባ በዘዴ ለማለፍ አቅሙ፤ የመተጣጠፍ ችሎታ፤ ብልጣብልጥነቱ፤ ጊዜዉም አልነበራቸዉም።

የማሕበሩ መሠረት፤ አላማ አርማም ለዚሕ ዘመኑ ፖለቲካዊ ጥቃት በቀላሉ ተጋላጭ ነበር።

ሕዝባዊዉ አብዮት ግብፅ ዉስጥ ሥር-እንዳይሰድ፤ ወይም እንዳይዛመት የሚሹት ሐይላት፤ የግብፅ ሕዝብን ብሰለት፤ መሠላቸት፤ የሙርሲን ድክመት፤ የማሕበራቸዉን ሥም-አርማን ሕዝብን ለመቀስቀሻ ለማዋል-ጊዜ አላጠፉም።ባመቱ ጄኔራል አብዱል ፈታ አል-ሲሲ በሕዝብ የተመረጡትን ፕሬዝደንት መሐመድ ሙርሲን አስወግደዉ ግብፅን ሰባት ሺሕ ዘመን ወደኖረችበት መለሷት።ሐምሌ 2013።ጀርመናዊዉ ጋዜጠኛ ሰሞኑን ያስተዋለዉ ይሕንን ነዉ።

«መንግሥትን የሚተቹ ጋዜጦች አይታተሙም።የራዲዮና የቴሌቪዥን ዝግጅቶችም እንዳይሰራጩ ይታገዳሉ።ይሕችን ሐገር ሥርዓቱን የሚደግፍ አንድ አስተሳሰብ ብቻ የሚንፀባረቅባት ሐገር ለማድረግ ጠንካራ ግፊት አለ።ይሕ ርምጃ ዝምታ ፈጥሯል።ዝምታዉ ግን የመቃብር ዓይነት ዝምታ ነዉ።መረጋጋት ግን የለም።የአሸባሪዎች ጥቃት ተባብሷል።ብዙዎቹ እንደሚሉት አጠቃላዩ ሁኔታ በሙባረክ ዘመን ከነበረዉ በጣም የከፋ ነዉ።»

የሰዉ ነብስ በማስጥፋት፤በሥልጣን በመባለግ፤ የመንግሥትና የሕዝብ ሐብት በመዝረፍ ወንጀል እድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸዉ የነበሩት ሙባረክ ብይኑ ወደ ሰወስት ዓመት ዝቅ ሲልላቸዉ፤ የጄኔራል አል-ሲሲን መፈንቅለ መንግሥት በመቃወም ሰልፍ የወጡ ሰዎች ባደባባይ ተረሸኑ።የሠብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ጄኔራል አል-ሲሲ ሥልጣን ከያዙ ከሐምሌ 2013 እስከ ሐምሌ 2014 በነበረዉ አንድ ዓመት ብቻ 3ሺሕ በላይ ሰዉ ተገድላል።

የተቃዉሞ ሠልፉ በሐይል ሲደፈለቅ እየታፈሱ ከታሰሩት ወይም ከተሰደዱት ከሁለት ሺሕ የሚበልጡ በጅምላ ሞት ተበይኖባቸዋል።ባለፈዉ ሚያዚያ ተረኛዉ ሙርሲና ባልደረቦቻቸዉ ነበሩ።ሃያ ዓመት ተበየነባቸዉ።ወንጀላቸዉ የመንግሥትን ሚስጥር ለፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ፤ ለሊባኖሱ ብጤዉ ሒዝቦላሕ እና ለቀጠር አሳልፈዉ ሰጥተዋል የሚል ነበር።የቀረበ መረጃ ግን የለም።የቅዳሜዉ ደግሞ የከፋ ነዉ የሞት ቅጣት።በወንጀልነት የተጠቀሰዉ የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት በተቀጣጠለበት 2011 የሆስኒ ሙባረክ መንግሥት አስሯቸዉ የነበሩት ሙርሲና ጓደኞቻቸዉ እስር ቤት ሰብረዉ አምልጠዋል የሚል ነዉ።

የጆርጅ ታዉኑ ዩኒቨርቲ ፕሮፌሰር አብዱላሕ አል አርያን እንደሚሉት ሙባረክ በነፃ የመለቀቅ ያክል ሰወስት ዓመት ሲፈረድባቸዉ ሙርሲ ሞት በቃ የተበየነባቸዉ ከፖለቲካዊ ፍርድ ሌላ -ሌላ ወንጀል አድርሰዉ ዓይደለም።

«እንደሚመስለኝ ታሪክን ዳግም የመፃፍ ሙከራ እየተደረገ ነዉ።የ2011ዱን ሕዝባዊ አብዮት ታሪክን።ሥለዚያን ጊዜዉ እዉነት ሥናስብ ሁስኒ ሙባረክ የከፋ ወንጀል ፈፅመዋል።እሳቸዉ ግን ፍርዱ ተሠርዞላቸዉ ተለቀዋል።ያሁኑ ፕሬዝደንት አል ሲሲ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ የተመረጡ መሪን በመፈንቅለ መንግሥት በማስወገድ ተጠያቂ ናቸዉ።ከዚሕም በላይ ለበርካታ ሰዎች መገደል ተጠያቂ ናቸዉ።የምናወራዉ ሥለ አስር ሰዎች መገደል አይደል አይደለም።ሲሲ ራባ ዉስጥ ብቻ ባንድ ቀን ከሺሕ በላይ ሰዎች ያስገደሉ ናቸዉ።ከዚያ በሕዋልም ብዙ ሰዎች አስገድለዋል።ይሕ እንግዴሕ ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት በተወሰደዉ እርምጃ በግብፅ እስር ቤቶች የሚማቅቁትን ከአርባ ሺሕ በላይ እስረኞችን ሳይጨምር ነዉ።»

በሙርሲ ላይ ሞት የተፈረደ ዕለት እዚያዉ ካይሮ ዉስጥ ከዚሕ ቀደም ሞት የተበየነባቸዉ ስድስት ሰዎች በስቅላት ተቀጥተዋል።

አል ሲሲ በመፈንቀለ መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ መሪ ከስልጣን ሲያስወግዱ ከሪያድና ከማናማ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ተንቆረቆረላቸዉ።የብራስልስና የዋሽግተን መሪዎች መፈንቅለ መንግሥቱን እንቃወማለን ማለታቸዉ አልቀረም።

የአፍሪቃ ሕብረትም ሲሲ የጄኔራል ማዕረጋቸዉን በይፋ እስኪያወልቁ ድረስ ግብፅን ከአባልነት አግዶ ነበር።ሁሉም ግን ከመገናኛ ዘዴዎች ፍጆታነት ባለፍ ከልብ አልነበረም።የአዉሮጳ ሕብረት ሲሲን ብራስልስ ለመጋበዝ የአፍሪቃ ሕብረትን ያክል እንኳን አልታገሠም። ዋሽግተን በፋንታዋ አቋርጣዉ የነበረዉን ለግብፅ የምትሰጠዉን ወታደራዊ ድጋፍ እንደምትቀጥል አስታዉቃለች።

አል-ሲሲ መለዮም ለበሱ ካራቫት፤ ፖለቲካዊ፤ ዲፕሎማሲያዊ፤ ወታደራዊ፤ ምጣኔ ሐብታዊዉ ድጋፍ ይንቆረቆርላቸዋል።ድጋፉ ሺዎችን እያስገደሉ፤ አስር ሺዎችን እያሳሰሩ፤ በጅምላ ሞት እያስፈረዱ፤ አምባገነን ወዳጆቻቸዉን እያስፈቱ አረባዊ-አፍሪቃዊቱን ሐገር ረግጠዉ ለመግዛት ጠንካራ ምርኩዝ ሆናቸዋል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic