የግብፅ ምርጫና የሕዝባዊዉ አብዮት እንቅፋት | አፍሪቃ | DW | 18.06.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የግብፅ ምርጫና የሕዝባዊዉ አብዮት እንቅፋት

የካይሮ ነዋሪ መሐመድ ካኑን «አንድ ሠይጣን አስወግደን፥ አስራ-ዘጠኝ ሰይጣኖች አፈራን» አለ።አንዱ ሰይጣን ሙባረክ።አስራ-ዘጠኙ ሙባረክን የተኩት የጦር ሐይሎች ምክር ቤት አባላት መሆናቸዉ ነዉ።የአስራ-ዘጠኙ መሪ ደግሞ ማርሻል መሐመድ ሁሴይን ተንታዊ ናቸዉ።

default

ድምፅ አሰጣጡ


19 06 12

የግብፅ ሕዝብ የሆስኒ ሙባረክን አምባገነናዊ ሥርዓት ባስወገደ በወሩ፣ የሙባረክ አገዛዝ የጭቆና መሳሪያ የነበረዉን ሕገ-መንግሥት በድምፁ ሽሯል።ግብፅ ግን ቋሚ ሕገ-መንግሥት የላትም።ሕዝቡ የምክር ቤት እንደራሴዎቹን መርጧል።ግብፅ ግን ምክር ቤት የላትም።ያ ሕዝብ ከሠላሳ ዘመን በላይ የፀናዉን አገዛዝ የመቃወም ድፍረት፣ ፅናት ጅግንነት ድሉ ዓለምን ጉድ ባሰኘ ድል ባተጠናቀቀ በአስራ-ስድተኛ ወሩ በቀደም-መሪዉን መረጠ።ምርጫዉ እንደ ሕገ-መንግሥቱ ላለመጠለፉ፣ እንደ ምክር ቤቱ ላለመሰረዙ፣አብዮቱ ወደፊት በተራመደበት ፍጥነት፥ እጥፍ ፍጥነት የኋሊት ላለመሾሩ ዋስትና አለመኖሩ ነዉ ሥጋቱ።ምርጫዉ መነሻ፣ሥጋት ምክንያቱ መድረሻችን ነዉ፣ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።


መሐመድ ሁሴይን ታንታዊ በሆስኒ ሙባረክ ተመርጠዉ የሆስኒ ሙባረክን ወንበር ሲረከቡ የጦሩን ዓለም ከቀዳሚዎቻቸዉ ወታደራዊ ገዢዎች ሁሉ በላይ ኖረዉ-ሠርተዉበት በፊልድ ማርሻል ማዕረግ ተንቆጥቁጠዉበታል።አዛዥ፣ ሿሚ፣ ሸላሚያቸዉ በሕዝብ ተጠልተዉ፣ ተወግዘዉ፣ ተዋርደዉ ሠላሳ ዘመን ረግጠዉ የገዙበትን፥ ተንደላቀዉ የኖሩበትን ሥልጣን ሲያስረክቧቸዉም ጥሩ ወታደርነታቸዉን እንጂ እንደ ነጉብ፣ ናስር፣ ሳዳት ወይም እንደ ሥልጣን አዉራሻቸዉ ሙባረክ የመሆን ምኞት ፍላጎታቸዉን ለማሳየት አልተጃጃሉም።

ተሕሪር አደባባይ ድረስ ሔደዉ ጦራቸዉ የሕዝቡን ፍቃድ እንደሚፈፅም ቃል የገቡለት ሕዝብም የማርሻሉን አላማ የሚያስተትንበት አቅም፣ የሩቅ ምኞት ፍላጎታቸዉን የሚጠረጥርበት ምክንያት ማግኘት ሲበዛ ይከብደዉ ነበር።

በሆስኒ ሙባረክ ይሁንታና ምርጫ «የጦር ሐይሎች ጠቅላይ ምክር ቤት የተሰኘዉ ስብስብ ሊቀመንበር ሆነዉ የሙባረክን መንበር ከሙባረክ በተረከቡ በወሩ ሙባረክ ይገዙበት የነበረዉ ሕገ-መንግሥት በሕዝብ ድምፅ ተሽሮ ጊዚያዊ ሕገ-መንግሥት ሲፀድቅም የማርሻል ታንታዊንና የተከታዮቻቸዉን ስዉር ሴራ ብዙም ያጤነዉ አልነበረም።

Mohammed Morsi Ägypten Wahl 2012 Präsidentschaftswahl

መሐመድ ሙርሲበአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴ ፍራንሲስካ ብራንትነር እንደሚሉት ግን ወታደራዊዉ ምክር ቤት የግብፅን ሕዝባዊ አብዮት እንደ ጭቃ ዉስጥ እሾሕ መጠቅጠቅ የጀመረዉ የሕገ-መንግሥቱ ማተሻሻ በሕዝበ-ዉሳኔ እንደ ፀደቀ ነበር።አምና መጋቢት።

«ወታደራዊዉ ምክር ቤት ገና ካለፈዉ አመት መጋቢት ጀምሮ አብዮታዊዉን ንቅናቄ ለመቆጣጠር በረቀቀ መንገድ ሲያሴር ነበር።አሁን ደግሞ ብዙዎች እንደሚሰጉት በሳምንቱ ማብቂያ ፕሬዝዳንት ቢመረጥ እንኳን ከወታደራዊዉ ምክር ቤት ትልቅ ተቃዉሞ ይገጥመዋል።»

በርግጥም አምና መጋቢት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ድፍን ግብፅ በሕዝባዊ አብዮቱ ድል፣ በዴሞክራሲያዊዉ ሥርዓት ጅምር፥ ሲፈነጥዝ ማርሻል ታንታዊና ተከታዮቻቸዉ ሙባረክንና ቤተሰቦቻቸዉን አስረዉ፣ የሙባረክን ሕገ-መንግሥት አሽረዉ፣ ሙባረክ የሾሟቸዉን የሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች በነበሩበት ነበር የተዉአቸዉ።

የግብፅ ሕዝብ ባልፈዉ ግንቦት ማብቂያ ለመጀመሪያዉ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲዘጋጅ ደግሞ ማርሻል ተንታዊ ምናልባት ስዉር-አለማ ምኞታቸዉን አፈጉት።«የወታደሮቻችንና ሰዎቻችንን ስም በሐሰት የሚያጠፉን» አሉ ማርሻል፥ ዕጩ የጦር መኮንኖችን ሲመርቁ «መላሳቸዉን እንቆርጣለን።»

Präsidentenwahl in Ägypten Ahmed Schafik gibt Stimme ab

አሕመድ ሻፊቅ

ተንታዊ የቆረጡ፥ ወይም ያስቆረጡት መላስ እስካሁን የለም።ያስገደሉት ተቃዋሚያቸዉ ግን በመቶ ይቆጠራል።አረጌዉ ሕገ-መንግሥት ሲሻር ያልተቀየሩት የአረጌዉ ሥርዓት የሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ደግሞ ባለፈዉ ሐሙስ በሕዝብ የተመረጠዉን ምክር ቤት በተኑት።

እና ዳኞቹ የተንታዊን ተቀናቃኞች፣የሙባረክን ተቃዋሚዎች መላስ ባይቆርጡ ልሳናቸዉን ዘጉት።የሙባረክ ተቃዋሚ የግብፅ ሕዝብ ነዉ።ምክር ቤቱም አነሰም በዛ በሕዝብ የተመረጠ የሕዝብ ወኪል ነዉ።ነበር።ሙባረክ የሾሟቸዉ የሕገ-መንግሥታዊዉ ፍርድ ቤት ዳኞች የምክር ቤቱ ምርጫ ተጭበርብሯል በማለት ምክር ቤቱን ያገዱት የቀድሞዉ የሙባረክ ወንድ ልጅ እንዳይከሰስ ከወሰኑ በኋላ፣የግብፅ ሕዝብ ለመጨረሻዉ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድምፁን ለመስጠት ሲዘጋጅ ነዉ።

በበርሊኑ ፍራየን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር ሐማዲ ኤል አኦዉኒ የፍርድ ቤቱን ዉሳኔ የታሪክን ሒደት የኋሊት ለመዘወር ያለመ ይሉታል።

«ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ያሳለፈዉ ዉሳኔ አለ።የዉሳኔዉ ምክንያት አልገባኝም።ሁኔታዎች የተያያዙ መሆናቸዉን መገንዘብ አለብን።ምክር ቤቱን ለመበተን የተላለፈዉ ዉሳኔና የሙባረክን ወንድ ልጅና ተቃዉሞ ሠልፈኞችን የገደሉ ሰዎችን በነፃ የማሰናበቱ ብይን፥ እኔ እንደሚመስለኝ ቀጥታ ግንኙነት አላቸዉ። ምናልባት ጦር ሐይሉ በሙሉ ላይሆን ይችላል፥ (በጦሩ መሐል) ግን የቀድሞዉ ሥርዓት ቅሪቶች የታሪክን መዘዉር ወደ ኋላ ለማሽከርከር የሚሞክሩ ንቁ (ሐይላት) አሉ።»

መሐመድ ነጉብ በ1953 የንጉስ ፋርቁን ዙፋን ሲቆጣጠሩ ጄኔራል ነበሩ።ገማል አብድናስር በ1954 ነጉብን ፈንግለዉ ከዙፋኑ በቀጥታ ሲቆናጠጡ ኮሎኔል ነበሩ።አንዋር አ-ሳዳት ዙፋኑን በ1970 ከሞቱት አለቃቸዉ ከናስር ሲወርሱ ከሌትናንት ኮሎኔልነት ማዕረግ አልዘለሉም ነበር።ሆስኒ ሙባረክ፥ በ1981 የተገደሉላቸዉን የሳዳትን ሥልጣን ሲወርሱ የአየር ሐይል ጄኔራል ነበሩ።

ትናንት ድምፁን የሰጠዉ የካይሮ ነዋሪ መሐመድ ካኑን «አንድ ሠይጣን አስወግደን፥ አስራ-ዘጠኝ ሰይጣኖች አፈራን» አለ።በቁጭት።አንዱ ሰይጣን ሙባረክ።አስራ-ዘጠኙ ደግሞ ሙባረክን የተኩት የጦር ሐይሎች ምክር ቤት አባላት መሆናቸዉ ነዉ።

የአስራ-ዘጠኙ መሪ ደግሞ ማርሻል መሐመድ ሁሴይን ተንታዊ ናቸዉ። በወታደርነቱ ሙያ የግብፅን የመሪነት ሥልጣን ለሐምሳ-ስምንት አመታት ከተፈራረቁበት ቀዳሚዎቻቸዉ በላይ ያገለገሉት፥ በጦር መኮንነቱ ማዕረግ ከሁሉም ልቀዉ የፊልድ ማርሻልነት ማዕረግ ያጠለቁት ተንታዊ «በአደራ» የወረሱትን ሥልጣን ሲሆን በዘዴ፥ ካልሆኑ በሐይል እንደያዙ ለመቀጠል «ምን ያንሰኛል» የሚሉበት ሰበብ፥ «ምንያንስወታል» የሚላቸዉ አማካሪ ያጣሉ ማለት ሞኝነት ነዉ።

Ägypten Wahl Wahlen 2011 Feldmarschall Hussein Tantawi

ማርሻል ተንታዊአንዳድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ደግሞ ማርሻል ተንታዊ ሥልጣኑን በቀጥታ መቆጣጠሩ ቢያስፈራቸዉ እንኳ ናስር በነጉብ ጥላ ሥር ላንድ ዓመት እንደገዙት ሁሉ ተንታዊም አሕመድ ሻፊቅን በምርጫ ስም እንደ መጋረጃ ከፊት ወጥረዉ ግብፅን ለመዘወር እያሴሩ ነዉ።

«የፕሬዝዳንቱን ሥልጣንና ሐላፊነት የሚደነግግ አዲስ ሕገ-መንግሥት የለም።በሕዝብ የተመረጠ ምክር ቤትም የለም።እና ሚስተር ሻፊቅ ከተመረጡ ጦሩ መቶ በመቶ ሥልጣኑን ተቆጣጠረዉ ማለት ነዉ።»

የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት እንደራሴ ፍራንሲስካ ብራንትነር።

ትናንት በተጠናቀቀዉ የመለያ ፕሬዝዳታዊ ምርጫ ከሙስሊም ወንድማማቾቹ እጩ ከዶክተር መሐመድ ሙርሲ ጋር የተወዳደሩት አሕመድ ሻፊቅ እንደ ሙባረክ ሁሉ የአየር ሐይል ጄኔራል፥ የሙባረክ የመጨረሻ ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።

የሙስሊም ወንድማማቾች አባላት የሚበዙት ምክር ቤት ከመበተኑ በፊት በፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ ዘመን ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች በወደፊቷ ግብፅ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን እንዳይዙ የሚያግድ የሕግ አንቀፅ አፅድቆ ነበር።በምክር ቤቱ ዉሳኔ መሠረት የሙባረክ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ሻፊቅ ለፕሬዝዳትነት ለመወዳደር ሕገ-ወጥ ናቸዉ።

ምክር ቤቱ የሻፊቅን መወዳደር በሕገ-ወጥነት ሲበይን የመሐመድ ሙርሲን እጩነት አፅድቆ ነበር።ሙርሲን ሕጋዊ፥ሻፊቅን ሕገ-ወጥ ያለዉን ምክር ቤት ራሱን ሕገ-ወጥ ብሎ የበተነዉ የሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የሻፊቅን እጩነት መብት አፅድቆላቸዋል።

በሕገ-መንግሥታዊዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ መሠረት ምክር ቤቱ ሕገ-ወጥ ከሆነ ሕገ-ወጡ ምክር ቤት ሕጋዊ እጩነታቸዉን ያፀደቀላቸዉ ሙርሲም ሕገ-ወጥ እጩ ናቸዉ።ምክር ቤቱ ሕጋዊ፥ ሕገ-መንግሥታዊ ምክር ቤት ሕገ-ወጥ ከነበሩ ደግሞ ሻፊቅ ሕገ-ወጥ፥ ሙርሲ ሕጋዊ እጩ ናቸዉ ማለት ነዉ።የግብፅ ምሥቅል ቅል ፍትሕ።«ፍትሐዊነቱ ምኑጋ ነዉ?» ጠየቀ ተቃዉሞ ሠልፈኛዉ።

«የዚሕ ዉሳኔ ፍትሐዊነት የቱጋ ነዉ።ያካሔድ ነዉ አብዮት ነበር።አብዮት ደግሞ አምባገነኖችን ዳግም ሥልጣን ላይ አያወጣም።ወታደራዊዉ ምክር ቤት አረጌዉን ሥርዓት መመለስ ነዉ የሚፈልገዉ።እኛ ሁላችንም ለነሱ እንድንገዛ ነዉ የሚሹት።ይሕን ግን አናደርገዉም።አሕመድ ሻፊቅን ጭምር ዳግም እንታገላለን።ኢንሻ አላሕ።»

የሌላ ትግል ጥሪ።የጦር ሐይሎች ጠቅላይ ምክር ቤት የዳግም ትግሉን ማስጠንቀቂያ አልተቀበለዉም። እንዲያዉም ትናንት በተጠናቀቀዉ ምርጫ የሙስሊም ወንድማማቾቹ እጩ መሐመድ ሙርሲ አሸንፈዋል መባሉ እንደተሰማ የጦር መኮንኖቹ የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ መቀጠል የሚያስችላቸዉ አዲስ ደንብ አዉጀዋል።

ባለፈዉ መጋቢት በተሻሻለዉ ሕገ-መንግሥት መሠረት በሕዝብ የሚመረጠዉ ምክር ቤት ሕገ-መንግሥት የማስረቀቅና የማፅደቅ ሥልጣንና ሐላፊነት ነበረዉ።በጊዚያዊነት ሥልጣን የያዙት የጦር መኮንኖች ትናንት ያወጁት ደንብ ግን አዲስ ሕገ-መንግሥት ተረቅቆ ካልፀደቀ በስተቀር የምክር ቤት ምርጫ እንደማይደረግ ይደነግጋል።

በዚሕ ሕግ መሠረት ትናንት በተጠናቀቀዉ ምርጫ ሙስሊም ወንድማማቾች እንደተመኙት መሐመድ ሙርሲ ቢያሸንፉ፥ እንደ ፕሬዝዳት ሐገር የሚመሩበት ሕገ-መንግሥት፥ ሕገ-መንግሥት እንዲያረቅ የሚያዙት ምክር ቤት አይኖርም ማለት ነዉ።በሌላ አባባል ጦሩ የርዕሠ-ብሔርነቱን ሥልጣን እንደተቆጣጠረ ይቀጥላል።

እርግጥ ነዉ ትናንት በተጠናቀቀዉ ምርጫ የተፎካከሩት ሁለቱም ፖለቲከኞች የሆስኒ ሙባረክን አገዛዝ በመቃወም አደባባይ የወጣዉን፥ ወጣት ፍላጎት የሚያሟሉ፥የሚወክሉም አይደሉም።የጦር ሐይሉ እርምጃ ግን የያኔዎቹ ወጣት አብዮተኞች እንደሚሉት በሙርሲ፥ ወይም በሙስሊም ወንድማማቾች ላይ ብቻ የተቃጣ አይደለም።በመላዉ ግብፃዊ ላይ ጭምር እንጂ።

ሙባረክን ከሥልጣን ለማዉረድ አደባባይ ይወጣ የነበረዉን ወጣት ያስተባብሩ ከነበሩት አንዷ ኒሐል ሳዓድ እንደምትለዉ ደግሞ የጦር ሐይሉ እርምጃ ግልፅ መፈንቅለ መንግሥት ነዉ።

«በተወሰደዉ እርምጃ በጣም አዝኛለሁ።ሠግቻለሁም።ያደረጉት ጥሩ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ነዉ።ይሕ ሊሆን እንደሚችል ጠብቀን ነበር።እዉነቱን ለመናገር በዚሕ መንገድ ይፈፀማል ብዬ ግን አስቤ አላዉቅም።»

የሙባረክን አገዛዝ ለማስወገድ ለአስራ-ስምንት ተከታታይ ቀናት አደባባይ የወጣዉን ሕዝብ ለመበተን ፀጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት እርምጃ ስምንት መቶ አርባ ስድስት ሰላማዊ ሰዎች፥ ሃያ-ስድስት ፖሊሶች ተገድለዋል።ወደ ሰባት ሺሕ የሚጠጉ ቆስለዋል።

ሙባረክን የተካዉ የጦር ምክር ቤት የሚወስዳቸዉን እርምጃዎች በመቃወም በተለያየ ጊዜ አደባባይ በወጣዉ ሕዝብ ላይ ፀጥታ አስከባሪዎች በከፈቱት ተኩስ ከሰወስት መቶ በላይ ሰዉ ተገድሏል።ሺዎች የሞቱለት ብዙ ሺዎች የቆሰሉለት ሕዝባዊ አብዮት በካይሮዉ ወጣት ቋንቋ አንድ ሰይጣን አስወግዶ አስራ-ዘጠኝ በመተካት ማሳረጉ ኒሐል እንዳለችዉ በርግጥ አሳዛኝ አስጊም ነዉ።

ያም ሆኖ ወጣትዋ እንደምትለዉ «የፈርዖኖቹ ወጣት» እጅ አይሰጥም።አብዮቱም እንደተቀለበሰ አይቀርም።

«ሌላ አብዮት ይካሔዳል።እንዴት የትና መቼ እንደሚደረግ አላዉቅም።አሁን የሚፈፀመዉን ለማስወገድ ግን ሁሉንም ዳግም ከመጀመሪያዉ መጀመር፥ ሁሉም አደባባይ መዉጣት አለበት።»

Ägypten - Protest in Kairo

የዳግማዊዉ አብዮት ጅምር

በአብዮቱ ሰበብ ወደ ግብፅ መጓዝ ያቆመዉ የዉጪ ሐገር ጎብኚ አሁንም ወደ ግብፅ ለመመለስ ፈራ ተባ እንዳለ ነዉ።የግብፅ የሥራ አጥ-ቁጥር በሐገሪቱ የአስር አመት ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተንቻሯል።አስራ-አምስት ከመቶ።ሊቢያ ዉስጥ ይሠሩ የነበሩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ግብፃዉያን ወደ ሐገራቸዉ በመመለሳቸዉ እነሱም፥ የሚደጉሙት ቤተ-ሠበብም ወደ ተመፅዋችነት እያሽቆለቆለ ነዉ።

ግብፅ በተለይ ወደ ሊቢያና የመን በብዛት የምትልከዉ የኢንዱስትሪ ዉጤት በራሷም በሁለቱ ሐገራት ምስቅልቅልም ሰበብ ቆሟል።በሁለት ሺሕ አስር ማብቂያ የግብፅ ቅምጥ የዉጪ ምንዛሪ ሰላሳ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ነበር።ዘንድሮ አስራ ስድስት ቢሊዮን ብቻ ነዉ።የሐገሪቱ አመታዊ የአጠቃላይ ምርት እድገት ከአምስት ወደ ኔጌቲቭ አራት አሽቆልቁሏል።

አብዮቱም አልሰመረም።ዳግም አብዮት።ግብፃዊዉ ታሪክ ምሑር ኻሊድ ፋሕሚ እንዳሉት መጪዉ አብዮት እንደ እስካሁኑ አያሳዝንም።አያሰጋምም።በእጥፍ ይዘገንን-ያስፈራል እንደሁ እንጂ።


በብዛቱ ከመላዉ አረብ አቻ የማይገኝለት የግብፅ ሕዝብ፥ በጣሙን ወጣቱ ለዳግም አብዮት ከአፍሪቃም ከአረብም ተወዳዳሪ ከሌለዉ ጦር ጋር ተፋጧል።ግብፅ የፍፃሜዉ ጦርነት እንዲሉ ይሆንባት ይሆን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic