የግብፅ ሕዝብ አመፅና የሐያሉ ዓለም አቋም | ዓለም | DW | 07.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የግብፅ ሕዝብ አመፅና የሐያሉ ዓለም አቋም

የሕዝቡ ፅናት፥ቁርጠኝነት-ግን የገዢዎቹን ሥልጣን እየገዘገዘ፣ የአፍሪቃና የአረብ ብጤዎቻቸዉን በነግ በኔ እያሸማቀቀ፣ የአለም-ሐያል ፖለቲከኞችን አቋም ግራ ቀኝ እያላጋ እንደ ሼክ-ቀሳዉስት ያፀልያቸዉ ይዟል

default

ሠልፈኛዉ

07 02 11

የግብፅና የሱዳንን ንጉስ የቀዳማዊ ፋርቁን ዘዉዳዊ ሥርዓት በ1952 አስወግደዉ የካይሮን ቤተ-መንግሥት መጀመሪያ በተዘዋዋሪ-ኋላ በቀጥታ የተቆጣጠሩት ሌትናንት ኮሎኔል ገማል አብድናስር የአረብ-አፍሪቃን የእስከዚያ ዘመን ፖለቲካዊ ሥርዓት ለበጎ ይሁን ለመጥፎ ቀይረዉታል።ናስርና ተከታዮቻቸዉ ሥልጣን የያዙበት ሐምሳ ዘጠነኛ አመት ሊዘከር ወራት ሲቀሩት ዘንድሮ በገዢዎቹ ላይ ያመፀዉ የግብፅ ሕዝብ የግብፅ-አፍሪቃን የአረብ-ዓለምን የሐምሳ ዘጠኝ ዘመን ፖለቲካዊ ጉዞ መቀየር አለመቀየሩ በርግጥ አለየም።የሕዝቡ ፅናት፥ቁርጠኝነት-ግን የገዢዎቹን ሥልጣን እየገዘገዘ፣ የአፍሪቃና የአረብ ብጤዎቻቸዉን በነግ በኔ እያሸማቀቀ፣ የአለም-ሐያል ፖለቲከኞችን አቋም ግራ ቀኝ እያላጋ እንደ ሼክ-ቀሳዉስት ያፀልያቸዉ ይዟል።የአመፁ ግመት መነሻ፣ አስተጋብኦቱ መጣቃሻ፣ የሐያሉ አለም አቋም መረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

የቱኒዝያዉን እዉነት፥ የግብፅ ሕዝብን ብሶት ምሬት በቅጡ የሚያዉቁት ሕዝባዊዉ አመፅ አሁን ከደረሰበት እንደሚደርስ ለመገመት ብዙ ማሰብ-ማሰላሰል አላስፈለጋቸዉም ነበር።የዚያኑ ያክል ያቺን ጥንታዊ፥ ታሪካዊ፥ ታላቅ፥ ሥልጡን አረብ-አፍሪቃዊት ሐገርን እንደ ምክትል ፕሬዝዳት ሥድስት አመት እንደ ፕሬዝዳት ሠላሳ አመት የገዙትን የፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክን የአገዛዝ ሥልት-ይትብሐል፥ ከምዕራቦች በጣሙን ከዩናይትድ ስቴትስ የሚደረግላቸዉን ዙሪያ መለስ-ድጋፍ የሚያዉቁት ሕዝባዊ አመፁን መድረሻ መጠራጠራቸዉ አልቀረም።

ያምሆኖ በሙንስተር-ጀርመን ዩኒቨርስቲ የአረብና የእስልምና ጥናት ተቋም ሐላፊ ቶማስ ባወር ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ እንዳሉት የአካባቢዉን ማሕበረ-ምጣኔ ሐብታዊ ይዞታ የሚያዉቁ ወገኖች የሕዝቡን ጥያቄ ተገቢነት፥ ለተገቢዉ ጥያቄዉ ተገቢ መልስ ለማግኘት የነበረና ያለዉን ፅናት ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባቸዉም።

NO FLASH Ägypten Mubarak Kairo Proteste Panzer Demonstration 01.02.2011


«ከትናንት ወዲያ ትንሽ ተጠራጥሬ ነበር።ዛሬ ግን ከእንግዲሕ ለየትኛዉም ተቋም፥ ለተቃዋሚዉ ይሁን፥ ለጦር ሐይሉ ወደ ኋላ ማፈግፈግ የሚቻል አይመስለኝም።አሁን ሙባረክ በርግጥ መሰናበት አለባቸዉ።»

ለሙባረክ፥ ለደጋፊ፥ ታማኞቻቸዉ፥ ለአገዛዛቸዉ ተጠቃሚዎችም የሕዝቡ ብሶት፥ ምሬት
ፍላጎት፥ ፍላጉትን ገቢር ለማድረግ የነበረዉ ቁርጠኝነት፥ የአዋቂዎች ምክር-አስተያየትም ልክ እንደ ከዚሕ ቀደሙ ሁሉ ሰሞናዊ ጫጫታ አይነት ነበር።የካይሮ ገዢዎች የማፈኛ መዋቅሮቻቸዉን አቅም፥ የፖሊስ ጦር ሐይላቸዉን ዝንባሌ በትክክል አዉቀዉት ነበር ማለትም ያሳስታል።

ለሙባረክ አገዛዝ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከማንቆርቆር እስከ ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ ድጋፍ የሚሰጡት የምዕራባዉያን ሐገራት በጣሙን የዋሽንግተን መሪዎች የሙባረክን ሥርዓት ከሙባረክ እኩል፥የግብፅን ሕዝብ በጣሙን የወጣቱን ማሕበረ፥ፖለቲካ-ምጣኔ ሐብታዊ ችግር፥ምናልባትም ፍላጎት-መፍትሔዉን ከየትኛዉም አዋቂ በላይ አያዉቁቱም ማለት በርግጥ ጅልነት ነዉ።

የአገዛዙ አፈና፥ መረን የለቀቀዉ ሙስና፥ የኑሮ ዉድነት፥ ሥራ አጥነት ያስመረረዉ የግብፅ ወጣት የካይሮ፥ የአሌክሳንደሪያ፥ የስዌዝን አደባባዮች ማጥለቅለቅ በጀመረበት ሰሞን ግን ልክ እንደ ሙባረክ ሁሉ የዋሽንግተን ሹማምንትም የሕዝቡን ጥያቄ በትክክል ያወቁት አልመስሉም ነበር።ወይም በትክክል የሚያዉቁትን ማሳወቅ አልፈለጉም።

ከሳምንታት በፊት የቱኒዝያ ወጣቶች የቤን አሊ አገዛዝ የሚፈፅምባቸዉን ግፍ-በደል በመቃወም እራሳቸዉን ባደባባይ እያቃጣሉ ብሶት ምሬታቸዉን ሲገልፁ፥ ነፍጥ ከታጠቀዉ የአገዛዙ ጦር ጋር ሲጋፈጡ የቅድሞዋ የቱኒዚያ ቅኝ ገዢ የፈረንሳይ መሪዎች ቤን ዓሊ የሕዝቡን አመፅ የሚደፈልቁበትን

Barack Obama und Husni Mubarak - Thema USA drängen auf Wende

ትናንት ዛሬ አይደልም

መሳሪያ ለማቀበል ቃል ይገቡ ነበር።

የፈረንሳይዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሚሼለ አሊዮት-ማሪ የቤን ዓሊ አገዛዝ ቀጣይነትን ለማረጋገጥ ድጋፍ ለመስጠት ቃል እንደገቡት ሁሉ የግብፅ ወጣቶች አመፅ ሕዝባዊ መልክና ባሕሪ መያዝ በመጀመረበት ባለፈዉ ጥር ሃያ-አምስት የዩናይትድ ስቴትስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን «የሙባረክ መንግሥት የተረጋጋ እና አስተማማኝ ነዉ-»አሉ።በሳምንታት ልዩነት ዉስጥ የፓሪሶችን ሥሕተት ዋሽንግተኞች ደገሙት።ክሊንተን ከዋሽግተን ሥለ ሙባረክ መንግሥት የተረጋጋነት ሲናገሩ የሙባረክ ታጣቂዎች በተለይ የስዌዝና የአሌክሳንደሪያ ሠልፈኞችን ይገድሉ ነበር።የስልክ፥ ኢንተርኔት አገልግሎቶችን ዘግተዉ ነበር።

ጥር-ሃያ ሰባት ክሊንተን ሌላ መግለጫ ሰጡ።
«የግብፅ ፖሊስና ፀጥታ አስከባሪዎች በተቃዉሞ ሠልፈኞች ላይ የወሰዱት ሐይል እርምጃ በጣም አሳስቦናል።የግብፅ መንግሥት የፀጥታ ሐይሎቹን ለመቆጣጠር አቅሙ የፈቀደዉን እንዲያደርግ እንጠይቃለን።የዚያኑ ያክል ተቃዉሞ ሠልፈኞቹም ከግጭት መታቀብ እና እራሳቸዉን በሰላማዊ መንገድ መግለፅ አለባቸዉ።»

ክሊንተን ያሉትን ባሉ ማግስት የአደባባዉን ሰልፍ ከመሩት ወጣቶች አንዱ መሐመድ አብዱል ኤል ሔታ እንዳለዉ የዋሽግተኖች አቋም ወይም የክሊንተን መግለጫ ለግብፅ ሕዝብ በጣሙን ለወጣቶች አለማወቅ፥ ሥሕተት ወይም ቸልተኝነት ብቻ አልነበረም።ዋሽንግተኖች ባለቀ-ሠአትም ከሙባረክ ጎን የመቆማቸዉ ምልክት፥የግብፅ ሕዝብ ጨካኝ ገዢዎቹን ለማስወገድ በአመፁ ከመፅናት ባለፍ ከማንም ምንም ድጋፍ ያለማግኘቱ ፍንጭ ጭምር እንጂ።
«የዩናይትድ ስቴትስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሙባረክ ሥርዓት የተረጋጋ ነዉ ብለዋል።የተቃዉሞ ሠልፈኛዉ ግን ከግጭት እንዲታቀብ ተናግረዋል።ሥለዚሕ እስከምናሸንፍ ድረስ በሠላማዊ የተቃዉሞ ሠልፋችን እንቀጥላለን።አደባባዮቹ የኛ ናቸዉ።»

በርግጥ ፀኑ።የታሕሪር አደባባይ፥ የካይሮ፥ አሌክሳንደሪያ፥ የሲዌዝ አደባባይ-አዉራ ጎዳኖች ድፍን ግብፅም የግብፆች ሆኑ።የሙባረክ አጋዛዝ በርግጥ አልተገረሰሰም።ሙባረክ በሰላሳ አመት ታሪካቸዉ አድርገዉት የማያዉቁትን ግን ለማድረግ ተገደዱ።ምክትል ፕሬዝዳት ሾሙ።ካቢኔያቸዉን ሽረዉ ሌላ ሾሙ። የፓርቲያቸዉን መሪነት ለቀቁ።ከስምንት ወራት በሕዋላ ቢሆንም ሥልጣን እንደሚለቁ አስታወቁ።

ፕሬዝዳት ሩዘቬልት የጀርመን ናትሲ ፋሽስቶችን የተዋጉ፥ ያሸነፉት፥ አይዘናወር ኮሪያ ልሳነ ምድር የፒዮንግ-ዮንግ፥ የሞስኮ ቤጂንግ ኮሚንስቶችን የተዋጉት፥ጆን ኤፍ ኬኔዲ-ኩባ ላይ ለመዋጋት የዛቱት፥ ኒክስነን ቬትናም የተዋጉት-ዲሞክራሲን የሚረግጡ አምባገነናዊ ሥርዓቶችን ለማስወገድ በሚል ነበር።ፕሬዝዳት ሮናልድ ሬጋን እንደዘመናቸዉ ፈሊጥ በርሊን ድረስ መጥተዉ የሶቬት ሕብረቱ አቻቸዉ የበርሊን ግንብን እንዲያፈርሱ የተማፀኑት የምሥራቅ አዉሮጳ ሕዝብ ፍላጎት በኮሚንስቶች ሥርዓት እንደታፈነ መቀጠል የለበትም በሚል ምክንያት ነበር።

«አቶ ጎርቫቾቭ እባክዎ ይሕን ግንብ ይናዱት»

ሬጋን የተወለዱበት መቶኛ አመት ሊከበር ሰወስት ቀን ሲቀረዉ ባለፈዉ ሐሙስ የዩንይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ለግብፅ ሕዝብ የአደባባይ ጩኸት-ጥያቄ እንደ ልዕለ ሐያል የዲሞክራሲ ቀንዲል ሐገር ትልቅ ፖለቲከኛ እቅጩን መልስ ከመስጠት ይልቅ እንደ አል-አዛሐር መሻኢኮች፥ ዶዓ-ሶላት፥ እንደ አሌክሳንደሪያ ቀሳዉስት ፆም-ፀሎት ይሉ ገቡ።

«የግብፁ አመፅ-ግጭት እንዲቆም፥ የግብፅ ሕዝብ መብትና ፍላጎት እንዲሳካ፥ በግብፅም በመላዉ አለምም አዲስ ዘመን እንዲበርቅ እንፀልያለን።»

የሕዝቡ አመፅ ሲግም፥ የአገዛዛቸዉ ጠንካራ መሠረት ሲፍረከረክ ግን የዋሽንግተን ብራስልሶች አቋምም የግድ መቀየር ነበረበት።ተቀየረ ወይም የተቀየረ መሰለ።አርብ ብራስልስ።

«እዉነቱን ለመናገር እስካሁን የተወሰዱት እርምጃዎች የግብፅ ሕዝብ ፍላጎትን አላሟሉም።ዛሬ እኛ የአዉሮጳ መሪዎች ሥርዓት የጠበቀ ሽግግር እንዲኖር ለመርዳትና ለማገዝ ዝግጁነታችንን ማሳየት፥ በጋራ መቆም እና ማድረግ አለብን።እንደሚመስለኝ ከሁሉም ይበልጥ ዛሬ በካይሮ አደባባዮች የሚፈፀመዉን በመንግሥት የተደገፈ ግጭትና የሐይል እርምጃ ወይም ገንዘብ የሚከፈላቸዉ ጋጠ ወጦች ተቃዉሞ ሰልፈኞችን መደብደባቸዉን ስናስተዉል ግብፅ እና ገዢ ሥርዓቷ የቀራቸዉን ታማኝነት ወይም ብሪታንያን ጨምሮ ከምዕራብ የሚገኙትን ድጋፍ እንደሚያጡ ግልፅ መልዕክት መተላለፍ አለበት።»

የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካምሩን።የግብፅ አደባባዮች በሕዝብ እንደ ተጨናነቁ ነዉ።ሰልፈኛዉ «የስንብት ቀን ባለዉ» በአርቡ የተቃዉሞ ሠልፉ ያነሳዉ ጥያቄም ከጥር ሃያ አምስት ጀምሮ ካነሳዉ የተለየ አልነበረም።አንድ ነዉ።ሁሲኒ ሙባረክ ከስልጣን ይዉረዱ።

አርብ ካይሮ እና ብራስልስ ሲመሽ ዋሽንግተን ነጋ።ፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ።የሐሙሱ አልነበሩም።ግብፅ መለወጥ አለባት አሉ።አሁን።

«የግብፅ የወደፊት እጣ ፈንታ በሕዝቧ ይወሰናል።የሽግግር ሒደቱ አሁኑኑ መጀመር እንዳለበትም ግልፅ ሊሆን ይገባዋል።ሽግግሩ ለግብፅ ሕዝብ ሁለንተናዊ መብቶችን የሚያስከብር፥ ከነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሚያደርስ መሆን አለበት።የዚሕ ሽግግር ዝርዝር አፈፃፀም በግብፃዉያን መረቀቅ አለበት። እንደተረዳሁት አንዳድ ዉይይቶች ተጀምረዋል።»

München Sicherheitskonferenz Merkel Cameron

ካምሮን እና ሜርክል

አሁን ይባል እንጂ ሽግግሩ መቼና እንዴት እንደሚሆን በርግጥ አይታወቅም።ምዕራቡ አለም ሠልፉን ከግብፅ ሕዝብ ጎን ለማስተካከል መጣሩን መግለፁ ግን እየተደጋጋመ ነዉ።ቅዳሜ።የጀርመንዋ መራሔተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል።

«እኛ የአዉሮጳ ሕብረት አባላት ትናንት በጋራ እንዳልነዉ ሕዝባዊዉን ጥያቄ ለመርዳት አዲስ ወዳጅነት መመሥረት አለብን።እኛ የሰሜን አፍሪቃ ጎረቤቶች ነን።»

ፕሬዝዳት ገማል አብድናስር በ1960ዎቹ ፥-ሕዝባችን ሐገር ወዳድ ነዉ።በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከምትሰጡት አንድ የድጋፍ ቃል ብትነግሩት ይመርጣል አይነት ብለዉ ነበር።ናስር በከፈቱት ቀዳዳ ገብተዉ፥ ሳዳት ካደላደሉት መንበር ሰላሳ አመታት የተቀማጠሉበት ሙባራክ በሕዝባቸዉ ግፊት መሰናበታቸዉ የርግጥ ያሕል እዉነት እየመሰለ ነዉ።ቤን ዓሊ አንድ፥ ሙባራክ ሁለት፥ የሚባልበት፥ አሰላሹ የሚጠየቅበት ጊዜም ሩቅ አይመስልም።ሕዝባዊዉ አመፅ የምዕራቡ መርሕ፥ የአረብ-አፍሪቃ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ መቀየር አለመቀሩን ግን ያዉ ጊዜ ነዉ ነጋሪዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ