የግብጽ ክርስቲያኖች ስደት  | ዓለም | DW | 31.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የግብጽ ክርስቲያኖች ስደት 

በግብጽ በሲና ልሳነ ምድር የሚኖሩ ክርስቲያኖች ፣ አካባቢያቸውን ለቀው እየሸሹ ነው ። ሰዎቹ ቀያቸውን ለቀው የሚሰደዱት ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድን በአካባቢው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመው ግድያ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ነው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:53

Nordsinai Christen* - MP3-Stereo

 ቡድኑ በአካባቢው በክርስቲያኖች ላይ የሚያካሂደውን  ግድያ አጠናክሮ የቀጠለው በተለይ በጎርጎሮሳዊው 2013 ወታደሩ የግብጹን ፕሬዝዳንት መሀመድ ሞርሲን ከሥልጣን ካወረደ በኋላ ነው ።የዶቼቬለው ዩርገን ስትሪያክ የላከውን ዘገባ ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ። 
በሲና ልሳነ ምድር ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድን በክርስቲያኖች ላይ ከሚፈጽመው ግድያ ለማምለጥ አካባቢያቸውን ለቀው የሚሸሹ ክርስቲያኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ

እየጨመረ ነው ። ባለፈው ወር እንኳን ቢያንስ 118 ቤተሰቦች ከሰሜን ሲናይ ፣ ከካይሮ በስተሰሜን ምሥራቅ ወደ ምትገኘው ኢስማኤልያ ወደተባለችው ክፍለ ግዛት ተሰደዋል ። በየካቲት ተጠርጣሪ ሙስሊም ሚሊሽያዎች በሲናዋ በአል-አሪሽ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ቢያንስ 6 ክርስቲያኖችን ገድለዋል ። ማግዳ ቡትሩስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አልአሪሽ ሲኖሩ 40 ዓመት ይጠጋል ። ወደ እስማኤልያ ከተሰደዱት ክርስቲያኖች አንዷ ናቸው ። አል አሪሽ መቼም አልመለስም ይላሉ ። 
«ማን ጋ ልመለስ ? እዚያ እያለሁ የሚንከባከበኝ ወንድ ልጅ ነበረኝ ። ስታመም መድሐኒት የሚያመጣልኝ ።የሚደግፈኝ ልጅ ነበረኝ ። አሁን ግን የለም ። መቼም ቢሆን ልጄን ወደነጠቀችኝ ከተማ  አልመለስም ። »
የቡትሩስ ልጅ ነጋዴው ዋኤል ዘንድሮ በጎርጎሮሳውያኑ ጥር 30 በንግድ መደብሩ ውስጥ ነበር በታጣቂዎች የተገደለው ። ነፍሰ ገዳዮቹ በሰሜናዊ ሲና ልሳነ ምድር ለጋዛ ሰርጥ ቅርብ በሆነው በአል አሪሽ እና አካባቢዋ የሚንቀሳቀስ የአንድ አሸባሪ ቡድን አባላት ናቸው ። ይህ ቡድንም በጎርጎሮሳዊው 2014 ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ተቀላቅሏል ።

ከልጃቸው ከዋኤል ግድያ በኋላ ማግዳ ቡትሩስ እና ቤተሰባቸው ከተማዋን ለቀው ሸሹ ። በጥር እና በየካቲት ወር አሸባሪዎቹ በአካባቢው ቢያንስ 7 ክርስቲያኖችን ገድለዋል ።ክርስቲያን ስደተኞች በሙሉ እንደሚናገሩት ከሙስሊም ጎረቤቶቻቸው ጋር ከዚህ ቀደም ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው ።በአል አሪሽም ይሄ ግንኙነት በፖለቲካ እና በጽንፈኛ ርዕዮተ ዓለም እና በጽንፈኞች ሳይበረዝ ነበር የቆየው እንደ ቡትሩስ ።
«መገመት ከሚቻለው በላይ ግንኙነታችን ጥሩ ነበር ። በበዓላት ስጋም ሆነ ጣፋጭ ምግቦች ያመጡልናል ። የልጅ ልጄ አደጋ በደረሰበት ጊዜ ሙስሊሞች ሆስፒታል ድረስ መጥተው ጠይቀውታል እርዳታም አድርገውልናል ።»  
ይሁን ግን አሁን ያለፈ ታሪክ ነው ። ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከመጋቢት መጀመሪያ አንስቶ ወደ 250 የሚደርሱ ክርስቲያን ቤተሰቦች ከአል-አልሪሽ ወጥተዋል ። ምናልባት ከተማዋን ለቀው የሄዱት ክርስቲያኖች ቁጥር 2500 ይጠጋል ። ከተማይቱን መጀመሪያ ለቀው ለወጡት 195 ቤተሰቦች ኢስማኤሊያ ያለ አንድ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ነበር እርዳታ ያደረገላቸው ። ሰዎቹን ለመርዳት ሌላው የተከተማ ነዋሪም ተረባርቧል ። የኢስማኤልያ ክፍለ ሀገር የወጣቶች ሆስቴል ከአልሪሽ የተሰደዱ በርካታ ቤተሰቦችን አስጠልሏል ። እዚያ ከተጠጉት መካከል የራሚ

ማካራም ቤተሰብ ይገኝበታል ። የ37 ዓመቱ ታክሲ ነጂ ማካራም በአሁኑ ጊዜ ጦሩም ሆነ ፖሊስ በአል- አሽሪ በጽንፈኞቹ ላይ እርምጃ መውሰድ የሚችሉበት እድል አላቸው ብሎ አያምንም ። 
«ውጊያ የሚካሄደው ከማይታወቁ ሰዎች ጋር ነው ። እኛው መካከል ነው የሚኖሩት እኛ እንደምንለብሰው ነው የሚለብሱት ማንነታቸው ሳይታወቅ የፍተሻ ኬላዎችን ያልፋሉ ። በመካከሉ ሰዎችን ይገድላሉ ። ከዚያ በኋላ ይደበቃሉ ።ዋኤልን የገደሉት አሸባሪዎች ፖሊስንም ቢሆን ማንንም አንፈራም በሚሊ ስሜት ተረጋግተው ለስላሳ ጠጥተው የተጠበሰ ድንች በልተው ነው የሄዱት ።»
ዋኤል የቅርብ ጓደኛው እንደሆነ የሚናገረው ማካራም ዋኤል ከሁለት ዓመት በፊት ዛቻ ደርሶበት ነበር ይላል ። ያኔ አካባቢውን ለቆ እንዲሄድ ተመክሮ ነበር ። ግን ፈቃደኛ አልሆነም ። ምናልባት ያኔ የተባለውን ሰምቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በህይወት ሊኖር ይችል ነበር ያላሉ ወዳጆቹ እና ቤተሰቦቹ ።  

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ 
 

Audios and videos on the topic