የግብይት አድማዉ እና አንድምታዉ | ኢትዮጵያ | DW | 14.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የግብይት አድማዉ እና አንድምታዉ

በኦሮሚያ ክልል ከሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት መጠራቱ ይታወሳል። የአድማዉ አላማ የፖለቲካ እስረኞች ያለቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና መከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቆ ይዉጣ የሚል እንደነበር ከተሳታፊዎቹ ተሰምቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:26

የግብይት አድማ

 

አቶ በቀለ ጋርባን ጨምሮ ሌሎች እስረኞች መፈታታቸዉን ተከትሎ አድማዉ ዛሬ እንዲቆም ቢነገርም ዛሬም በአንዳንድ ቦታዎች አድማ እና ተቃዉሞው ቀጥሏል።  አድማዉ ከኦሮሚያ ክልል አልፎም ወደ ሌሎች ክልሎችም መሻገሩን የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ለሦስት ቀናት የተጠራው የግብይት አድማ ሰኞ እና ማክሰኞ ዕለት ተጠናክሮ መካሄዱ ታይቷል። የአድማዉ አላማ የፖለቲካ እስረኞች ያለቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና መከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቆ ይዉጣ የሚል እንደነበር ተሳታፊዎቹ ይናገራሉ። ሆኖም ትናንት እነ አቶ በቀለ ጋርባን ጨምሮ ሌሎች እስረኞች መፈታታቸዉን ተከትሎ አድማዉ እንዲቋረጥ «ቄሮ» በመባል የሚታወቁት ወጣቶች በማሕበራዊ መገናኛው ዘዴ አዉጡ የተባለዉ መግለጫ ያመለክታል።

ይሁን እንጂ ዛሬም በአንዳንድ ቦታዎች አድማዉና ተቃዉሞው መቀጠሉን የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ላለፉት ሁለት ቀናት አድማ እና ተቃዉሞው በደንብ ተካሂዷል የሚለዉ አንድ የባቱ ነዋሪ«ቄሮ» ዛሬ ከተማዋ የዋለችበትን እንዲህ ይገልፃል፣

አድማዉ በዋናነት አንግቦ የተነሳዉ አላማ የፖለቲካ እስረኞች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና መከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቆ ይዉጣ የሚል መሆኑን ወጣቶቹ ይገልፃሉ። ለመሆኑ አድማው አላማዉን አሳክቷል? የባቱ ከተማ «ቄሮ» መልስ አለዉ፣

መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን ክስ ዉድቅ ማድረጉ የአድማዉ ዉጤት መሆኑን የሚናገሩት ወገኖች፤ ወጣቶቹ ዛሬም ከእስር ለተፈቱት የእንኳን በደህና ለቤታችሁ አበቃችሁ የሚል መልካም ምኞታቸውን በየቦታው እያሰሙ እንደሚገኙም ለመረዳት ተችሏዋል። ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር ከእስር ከተፈቱት ዉስጥ የአቶ ጉርሜሳ አያኖን አቀባበል በቦታዉ የተገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጥሩነህ ገምታ እንዲህ ያሰሙናል፤

የጥያቄዉ ይዘት ይለይ እንጂ የግብይት አድማዉ በኦሮሚያ ክልል ብቻ እንዳልተገደበም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለምሳሌ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ የሁለት ቀን የግብይት አድማ መጠራቱን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የዉጭ ግንኙነት መምህር አቶ ዳንኤል መኮንን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በአድማዉ ምክንያት በዉጥረት ዉስጥ እንደሚገኙ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መረጃዎች ይጠቁማሉ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic