የግብርና ዓይነቶችና የምግብ ዋስትና | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 14.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የግብርና ዓይነቶችና የምግብ ዋስትና

የወደፊቱን የሰው ቀጣይ ህልውና ለማረጋገጥ ፤ ከወዲሁ ስለፕላኔታችን አያያዝ ጠንቀቅ ማለት እንደሚገባ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ምሁራን አጥብቀው ይመክራሉ። አንዳንዱ መግለጫቸው እንዲያውም አደናባሪም፤ ተስፋ አስቆራጭም የሚመስልበት ሁኔታ አለ።

ለምሳሌ ያህል ዕውቁ የአስትሮ ፊዚክስ ሊቅ፤ ስቲፈን ሆክኪንግ ፣ ከ 3 ዓመት ከ 8 ወራት ገደማ በፊት ፤ ሰው በሚመጡት 200 ዓመታት ውስጥ ሌላ ፕላኔት ፈልጎ በዚያ መሥፈር ግድ ይለዋል ፦ አለበለዚያ ምድሪቱ በላይዋ የሚኖሩትን ቁጥራቸው ከመጠን እያለፈ የሚሄደውን ኑዋሪዎቿን ማስተናገድ ፈጽሞ ይሳናታል ብለው እንደነበረ አይዘነጋም። ከዚያ ቀደም ሲል ደግሞ፤ ሰው፣ በኅዋ በሥነ ቴክኒክ ከርሱ የላቀ የመጠቀ ሥልጣኔ ባላቸው መሰል ፍጡራን እንዳይጠቃ መጠንቀቅ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበውም ነበር።

Living Planet Report በመባል የታወቀው ትልቅ ስም ያለው ፣ በዓለማችን መሪውን ቦታ የያዘ መሆኑ የሚነገርለት የብሪታንያ የምርምርተቋም በሳይንስ በመመርኮዝ ፤ የፕላኔታችንን ጤንነትና የሰዎች አዎንታዊና አሉታዊ ተግባር ስለሚያስከትለው ተጽእኖ በየጊዜው በጥናት የተመሠረተ መረጃ ያቀርባል። በ የ 2 ዓመት አንድ ጊዜ ሰፋ ያለ ዘገባውን ይፋ የሚያደርገው፤ ከለንደኑ የዱር ዐራዊትና እንስሳት የምርምር ማሕበርና «ግሎባል ፉትፕሪንት ኔትዎርክ» ከተሰኘው ሌላ መሰል ድርጅት ጋር በመተባበር ነው። እ ጎ አ ከ 2010 ወዲህ በ 2012 የወጣው ዘገባው፤ በዱር ዐራዊትና እንስሳት ህልውና ላይ ብርቱ ጫና በማሳደር የራሳችንን የወደፊት መጻዔ ዕድል ሥጋት ላይ በመጣል ላይ እንገኛለን ብሏል። እ ጎ አ ከ 1970 ወዲህ ከ 9014 የተለያዩ እንስሳት ና ዐራዊት በተለይ ከ 2,600 በላይ በሚሆኑት 30 ከመቶ ህልውናን እጅግ የሚያሠጋና ብሎም ማክሰም የሚችል ጠንቅ ተከሥቷል ነው ያለው። ምድራችን ከምታመርተው ይልቅ ሰዎች የሚያጋብሱት ምርት 50 ከመቶ መጠን ያለፈ መሆኑንም ተቋሙ ያብራራል። የ 2012 ቱን ዘገባ ያቀረቡት የዓለም ዐራዊትና እንስሳት ጥበቃ ድርጅት የበጎ ፈቃደኛ ልዑክ ጠፈርተኛው አንድሬ ኪፐርስ ናቸው።

እናም አዝማሚያው በዚህ ከቀጠለ(ልውጥ አልታዬም) እ ጎ አ ፣ በ 2030 ለመኖሪያ 2 ፕላኔቶች ያስፈልጉናል ይላል --Living Planet Report..። ይህ እንግዲህ የዓለም ህዝብ ብዛት መጠን 8, 3 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ በሚጠበቅበት ዘመን ፤ ማለት እ ጎ አ በ 2030 ነው ሁለት ፕላኔቶች ያስፈልጉናል የተባለው። ያኔ የኢትዮጵያ ህዝብም አሁን ከደረሰበት 91,728,849 ወደ 137 , 669, 000 አኀዙ ከፍ ይላል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። እ ጎ አ በ 2050 የዓለም ህዝብ በጠቅላላ ቁጥሩ ወደ 9,7 ቢሊዮንበ 2083 ደግሞ 10 ቢሊዮን ይደፍናል ተብሎ ነው የሚሰላው። ያኔ ስንቱ የሚላስ የሚቀመስ ያገኛል? ለዚህ ይሆን ሌላ ፕላኔትም ያስፈልጋል የሚባለው? ብቸኛይቱን ፕላኔት አላግባብ ከመቦጥቦጥ ያልተቆጠበው ሰው ሌላስ ፕላኔት ቢያገኝ አያያዙን እንዴት ይችልበታል?

በዝች ምድር ከሚኖረው ሰው ሌላ ተመሳሳይ የርሱን ያህል የሚያስተውሉ ምናልባትም የበለጡ አሉ የሉም እስካሁን ከግምትና ፤ ጎድጓዳ ሳህን በመሰለ መንኮራኩር ሲከንፉ አየን መሬት ላይ አርፈው ድንገት ተሠወሩ እያሉ በዓለም ዙሪያ ከሚተርኩ ወገኖች በስተቀር በዚህ ረገድ አንዳች ተጨባጭ የሆነ ማረጋገጫ ያገኘ የለም።

ግራም ነፈሰ ቀኝ ፣ ስለምድራዊው ችግርና መፍትኄው የሚያስላስሉ ወገኖች ፣ ግብርና በየረድፉ በጥሞና ካልተያዘ ፣ ማለትም የኢንዱስትሪ ግብርናና የአነስተኛ ይዞታ ግብርና ለአፈርና ውሃ አያያዝ ተገቢው ክብካቤ ካልተደረገለት የሚከተለው ልማት ሳይሆን ጥፋት እንደሚሆን ነው በአጽንዖት የሚያስጠነቅቁት። ምድራችን ጫናው እጅግ ሳያይልባት ለኑዋሪዎቿ ምግብ ታቀርብ ዘንድ ፣ በዓለም ዙሪያ አነስተኛ ይዞታዎች ያሏቸው አንድ ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ የአዳጊ ሃገራት አርሶ አደሮችና የአይዱስትሪው ግብርና ዘርፍ ፣ ሁሉም ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረጉ ፤ ውጤቱ የሚፈራው ነው የሚሆነው። አስፈሪው ሁኔታ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ሳይሆን፤ ሰዎች ለምድራችን ተገቢውን ጥበቃ ባለማድረጋቸው፤ ለምሳሌ ያህል የፕላኔታችን ሙቀት በሰው ሰራሽ ስህተት መጨመሩ፣ የውሃና አየር ብክለትም እየተባባሰ መምጣቱ በቂ ምልክቶች ናቸው።

በአፍሪቃው ክፍለ ዓለም ብቻ፤ ከ 1,033 ቢሊዮኑ ህዝብ 226 ሚሊዮኑ ፣ የረሃብ ሰለባ ነው። ምክንያት ፤ የእርሻ መሬት በአግባቡ እንዲዳብርና በቂ ምርት እንዲያስገኝ ባለመደረጉ ነው። የአፈeር መሸርሸር፤ የደንና ቁጥቋጦ መመንጠርና፤ እንዲሁም የአፈር በመርዘኛ ቅመማት መበከል ነው የተጠቀሰውን አደጋ የሚያስከትለው። አፈር በመርዘኛ ቅመማት (ኬሚካልስ)መበከል ሳይሆን ለምርት የሚበጁ ማዕድናትና አጣምሮ እንዲገኝ ነው ጠረት መደረግ ያለበት። አፈርን ምርታማ የሚያደርጉት እንደ ማግኒዚየም ፣ ካልስየም፤ ናይትሮጂንና ፎስፎረስ የመሳሰሉት ናቸው። በኢንዱስትሪ በገሠገሡትም ሆነ በአዳጊ አገሮች 90 ከመቶው ለምግብ የሚውለው ፣ ጥራጥሬ፤ አትክልት፤ ቅጠላ-ቅጠልና ፍራፍሬ የሚገኘው በግብርና ልማት ፤ ከአፈር መሆኑ የታወቀ ነው። ጤናማ አፈር ሲባል የተጠቀሱት ጠቃሚ የተፈጥሮ ማዕድናት በንጹሕ ውሃ አማካኝነት የተዋኻዱበት ማለት ነው። በደንም ሆነ ቁጥቋጦ መመንጠር የአፈር መሸርሸር ብዙዎቹን አዳጊ ሃገራት ለአስከፊ ችግር ዳርጓል። የአፈር መሸርሸርም ሆነ መራቆት ሲባል ፤ እዚህ ላይ ፤ የጠቃሚ ማዕድናት መሟጠጥ ጭምር መሆኑ እሙን ነው። ይህ ደግሞ፣ ድርቅን እያስፋፋ መምጣቱና በተለይ በምድር ሰቅ አዋሳኝ አካባቢዎች ለአርሶ አደሮች ከባድ ፈተና ሆኖ መጋረጡ የታወቀ ነው። ያም ሆኖ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች፤ የተለያዩ አዝርእትን ማምረት ብቻ ሳይሆን፤ ድርቅን ይበልጥ መቋቋም የሚችሉ የአዝርእት ዓይነቶችን ቢመርጡ እንደሚበጅ የግብርና ጠበብት ይመክራሉ።

የኢንዱስትሪው ግብርና ዓላማ በሰፋፊ መሬት በገፍ ማምረት ሲሆን ፤ የአየር ጠባይ መዛባት እያጋጠመ ባለበት ዘመን ፣ በተለይ በአንድ ወጥ የእህል ዘር ላይ የሚያተኩር ግብርና ፣የተሟላ የአፈር ጥበቃ ይኖረዋል ብሎ መተማመን አያስችልም። እርግጥ በአነስተኛ የእርሻ መሬት እንደሚታያው ፣ያን በአኢንዱስትሪ የአርሻ ጣቢያዎች በቀላሉ ማስተዋል ያዳግታል።

በአፍሪቃው ክፍለ ዓለም በዝናምና በነፋስ የሚደርሰውን የአፈር መሸርሸር፣ በተለያዩ ሃገራት በቀጥታ ማየት እንደሚቻልየገለጹት የዓለም አቀፉ የሞቃት አገሮች ግብርና ማዕከል ባልደረባ ሮልፍ ዞመር፤ ፣ አደጋው ወይም ብክነቱ የሚጎላው ዝናም በሚያይልባቸው ቦታዎች ነው ይላሉ። በተፈጥሮ ፣ አልፎ-አልፎ ዛፎች በብዛት ግን ረዣዣም ሣር በሚበቅልበት (ሳቫና) በሚሰኘው አካባቢ ዛፉም፤ ሳሩም ቁጥቋጦውም፤ ለምግብ ማብሰያ እየተባለ የመመንጠሩ ሁኔታ፤ በግብርናው አያያዝ ያስከተለው ችግር ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል። መፍትኄው ምን ይሆን? ለሚለው በበኩላቸው ይበጃል ስላሉት እንደሚከተለው ያብራራሉ።

«በቀጥታ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ተግባራዊ ለማድግ፣ በተፈጥሮ ለአፈር ማዳበሪያ በሚውሉት በመጠቀም፣ የእርሻ ቦታን ማዘጋጀቱ ለአፍሪቃም አብነቱ አያጠራጥርምና ፤ ይህ እንዲሠራበት ነው አጥብቄ የምመኘው። በቅድሚያ የሚያሥፈልገውምን እንደሆነ ማሰላሰል ያሻል። ትልቁ ችግር ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያው በገፍ አለመገኘቱ ነው። ፍግ፤ ኩበት ፣ እበት፤ እነዚህን መሰል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚበጅ ባያጠያይቅም፣ ለአርሻ ቦታ በቂ የሚሆነውን መጠን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። »

የአፈር መሸርሸርን ለመቋቋምን የተሻለ ምርት ለማግኘት፤ ጎን ለጎን የተፈጥሮ አካባቢን መንከባከብ የሚያስችል የደን ችግኝ ተከላ መርኀ-ግብርም ሊካተት ይገባል ። ዘንድሮ 1.033ቢሊዮን መድረሱ የተነገረለት የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ሕዝብ፤ እ ጎ አ በ 2050 በአጥፍ ጨምሮ መገኘቱ እንደማይቀር ነው የሚተነበዬው።የአፍሪቃ አርሶ አደሮች ዘርተው የሚያገኙት የምርት መጠን፤ ከፍ እንዲል ቀስ በቀስ የሚያስፈልጉትን ቅድመ ግዴታዎች ማሟላትን ይጠይቃል። ሮልፍ ዞመር፣ በኢንዱስትሪ የገሠገሡ አገሮች አርሶ አደሮች፣ በተወሰነ ቦታ ዘርተው የሚያመርቱትን መጠንr በተለይም በጀርመን ሀገር ካለው ጋር ለንጽጽር በማቅረብ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«አንድ አርሶ አደር፤ በአንድ ሄክታር መሬት ግማሽ ቶን ብቻ ሲያመርት በጀርመን ሀገር ከ 6- 10 ቶን ነው የሚታፈሰው። ስለሆነም ፤ ግማሽ ቶን በማምረት ፣ ከድህነት መላቀቅና በእርሻ ቦታ አፈርን መንከባከብ ይቻል ዘንድ ተፈላጊ ወጪ ለማድረግ ያለው ዕድል የመነመነ (አነስተኛ)ነው።»

አንድ ቶን = 10 ኩንታል ወይም 1,000 ኪሎግራም ነው።
አንድ ኩንታል = 100 ኪሎግራም መሆኑ የታወቀ ነው።

ቀጣይነት ለሚኖረው ግብርና ፣ የአፈር አጠባበቅ በተጠና መልኩ አገልግሎት ላይ የሚውል የአፈር ማዳበሪያ፣ በየጊዜውr የተለያዩ አዝርእትን እያቀያየሩ ማልማት፣ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የግብርና ድርጅት፣ (FAO) ም የሚያበረታታው መርኅ መሆኑ ነው የሚነገረው። ከሞላ ጎደል 70 ከመቶውን የዓለem ምግብ የሚያመርቱ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ናቸው። ይሁን እንጂ በቂ የአርሻ ቦታ ስለሌላቸውና ለምርታቸውም ተመጣጣኝ ዋጋ ስለማይከፈላቸው፣ ኑሮአቸው ጎስቋላ ነው። ነገር ግን፣ የተጠቀሱት 2 ጉዳዮች ቢሟሉላቸው 70 ከመቶ ያህል ረሃብን ማስወገድ እንደሚቻል ነው የሚነገረው። በአመዛኙ ለትርፍ በማሰብ ግብርናን ማካሄዱ፣ ጥቂቶችን ብቻ ይበልጥ ለመጥቀም መሥራቱ፣ ለጤናማ ግብርና እንደማይበጅ፤ የማሕበራዊ ኑሮን ም እንደሚያቃውስና ድህነትን ይበልጥ እንደሚያስፋፋ የሚያጠራጥር አይሆንም። ስለሆነም ፣ የተፈጥሮ አካባቢን ለመጥቀም እንጂ ላለመጉዳት ትኩረት የሚያደርግ ግብርና ዘላቂነት ይኖረዋል። እዚህም ላይ የሥነ ሕይወትና ሥነ ቅመማ ሳይንስ ሕብረሰብን ለመታደግ በግብርናው በኩል ሰፊ፣ ጠቃሚና ገንቢ ድርሻ እንደሚያበረክት እሙን ነው።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic