የግሪክ ፖሊስ ኢዶሚኒን ማስለቀቅ ጀመረ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የግሪክ ፖሊስ ኢዶሚኒን ማስለቀቅ ጀመረ

የግሪክ ፖሊስ ሐገሪቱን ከመቂዶንያ ጋር በሚያዋስነዉ ኢዶሚኒ በተባለዉ አካባቢ ሰፍረዉ የሚገኙ ሥደተኞችን ማስለቀቅ ጀመረ። ኢዶሚኒ ላይ ሰፍረዉ የሚገኙት ስደተኞች ወደ መሃል አዉሮጳ የሚገቡበት የባልካን መንገድ ዳግም ተከፍቶ በቀጣይ መጓዝ እንችላለን በሚል ተስፋ ትናንሽ ድንኳን ተክለዉ ይኖሩ ነበር።

የነዚህ ስደተኞች ቁጥር ወደ 9000 እንደሆነም ተዘግቦአል። ሊስ ቦታዉ ላይ በድንኳን ሰፍረዉ የነበሩትን ስደተኞች ለማስለቀቅ በደረሰ ጊዜ ተሰብስበዉ የነበሩ ጥቂት ሰዎች ለማስተጓጎል ሞክረዉ ነበር። በኢዶሚኒ የሚታየዉን የስደተኞች ቀዉስን በተመለከተ ግሪካዊዉ ጊዮርጎስ ኬርቲሲስ ለጀርመን መገናኛ ብዙኃን እንደገለፁት ስደተኞች ስፍረዉበት የሚገኘዉን ኢዶሚኒን ለማስለቀቀ በርከት ያሉ ቀናቶች ይወስዳል። የማስለቀቁ ሥራም ጉልበት ያልቀላቀለዉ እንዲሆን ይሞከራል። በኢዶሚኒ ድንኳን ዉስጥ ሰፍረዉ የሚገኙት ሰዎች ወደ ተስተካከለ መኖርያ ቦታ እንደሚወሰዱም ተመልክቶአል። ቦታዉ ላይ የሚገኝ የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ ሶሊቨር ሳሊት፤ ቦታዉ ለጋዜጠኞችም ዝግ መሆኑን ገልጾአል።

«ወደ ኢዶሚኒ የሚወስድ የፈጣን ተሽከርካሪ መሄጃ ጎዳና ይታየኛል። ስደተኞቹ እኔ ካለሁበት ቦታ እጅግ ርቀት ላይ ነዉ የሚገኙት፤ ጋዜጠኞች ከሁለት እስከ ሦስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ማለፍ አይችሉም ፤ ተዘግቶአል። ብዙ ባዶ አዉቶቡሶች ወደዝያ ሲያልፉ ይታየኛል፤ ከዝያም ሰዎችን የጫኑ አዉቶቡሶች ሲመለሱ ብቻ ነዉ የሚታየዉ። እንደሚመስለኝ አዉቶቡሶቹ ወደ 9000 ሺህ የሚሆኑትን ስደተኞች ነዉ እያመጡ ያሉት። »

የግሪክ መገናኛ ብዙኃን ይፋ እንዳደረጉት ኢዶሚኒን ከስደተኞች ለማስለቀቅ ወደ 1400 ፖሊሶች ተሰማርተዉ ይገኛሉ። እንደ ዓይን እማኞች ጥቂት ስደተኞች አካባቢዉን በመልቀቅ አቅራብያዉ ወደ ሚገኘዉ ጫካ ተደብቀዋል። ሌሎች ያለምንም ኃይልና ትዕዛዝ በገዛ ፈቃዳቸዉ ወደ ሚወሰዱበት ቦታ ተነስተዉ ሄደዋል። አብዛኞች በገዛ ፈቃድ የተነሱት ሰዎች ሕፃናትና ልጆችን የያዙ መሆናቸዉ ተዘግቦአል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ