የግሪክ የበጀት ቀውስና መፍትሄ ፍለጋው | ኤኮኖሚ | DW | 17.02.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የግሪክ የበጀት ቀውስና መፍትሄ ፍለጋው

የኤውሮ ተገልጋይ አገሮች ስብስብ በበጀት ኪሣራ ተወጥራ በክስረት አፋፍ ላይ በምትገኘው በግሪክ የዕዳ ቀውስ የተነሣ በ 11 ዓመት ሕልውናው ለመጀመሪያ ጊዜ ፈታኝ ሁኔታ ላይ ወድቋል።

default

መንግሥታቱ ባለፈው ሣምንት ብራስልስ ላይ ባካሄዱት ልዩ የመሪዎች ስብሰባ ምንዛሪውን ለማረጋጋት ሲሉ ግሪክን ለማገዝ መስማማታቸው አይዘነጋም። ሆኖም የገንዘብ ዕርዳታን በተመለከተ ይህን ያህል ተብሎ በጭብጥ የተገባ ቃል የለም። በሌላ በኩል ግሪክ ጥብቅ የቁጠባ መርህ በማራመድ ቀውሱን እንድትቋቋም ሲጠየቅ አቴን ችግሯን ለመወጣት የዓለምአቀፉን ምንዛሪ ተቋም የ IMF ን ዕርዳታ ብትሻ ይሻላል የሚለው አስተሳሰብም ጎልቶ መሰማቱ አልቀረም። ለመሆኑ ኤውሮ-ዞን ግሪክን ከተፈራው መንግሥታዊ ክስረት ለማዳን ይችላል ወይ? ከሆነስ እንዴት?

ኤውሮ የጋራ ምንዛሪ ሆኖ ከሰፈነ እ.ጎ.አ. ከጥር ወር. 1999 ዓ.ም. ወዲህ በተገልጋዩ አካባቢ ላይ እንደዛሬ እርጋታውን ሊያዛባ ያሰጋ ሁኔታ የተደቀነበት ጊዜ አልነበረም። ዛሬ ከባድ የበጀት ቀውስ ላይ የወደቀችው ግሪክ በ 2001 መጀመሪያ ቅድመ-ግዴታዎችን አሟልታለች በመባል ስብስቡን ለመቀላቀል ስትበቃ በዓመቱም ኤውሮ በ 12 አገሮች ይፋ የሕዝብ መገልገያ መሆን መጀመሩ ይታወሣል። የተነሣውም በማስትሪሽት ውል መሠረት የአውሮፓ ሕብረት ዓባል ሃገራት የዕዳ ኪሣራ ከሶሥት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት በሚደነግግ ቅድመ-ግዴታ ነበር። ዛሬ የኤውሮ-ዞን ዓባል ሃገራት ቁጥር 16 ሲደርስ በአጠቃላይ ብሄራዊ ምርት መስፈርት ሲታይ ክልሉ በዓለም ላይ ሁለተኛው ታላቅ የኤኮኖሚ አካባቢም ነው።

ይሁንና የግሪክ የበጀት ኪሣራ መናር በወቅቱ ማለቂያው በውል ከማይታወቅ ፈታች ሁኔታ ላይ ጥሎታል። ለጋራ ምንዛሪው ተረጋግቶ መቀጠል ግሪክን ማዳኑ የማይታለፍ ግዴታ ነው የሆነው። ለጊዜው አቴን ጠንካራ የቁጠባ ዕርምጃ በመውሰድ የበጀት ኪሣራዋን እንድትቀንስ ጥሪ ከማድረግ በላይ ይህ ነው የሚባል ጭብጥ ዕርዳታ አልተጠቀሰም። እንዲያውም የበጀት ኪሣራዋን በመሸፋፈን ችግሩ እንዲባባስ ባደረገችው አገር ላይ ግፊቱ እየተጠናከረ ሲሄድ ነው የሚታየው። የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ የምጣኔ-ሐብት ባለሥልጣን ኦሊ ሬህን ግሪክ የበጀት ኪሣራዋን ለማድበስበስ የወሰደቻቸውን ውስብስብ የፊናንስ ዕርምጃዎች እስከያዝነው ሣምንት መጨረሻ በዝርዝር እንድታስረዳ አሳስበዋል።
የቀድሞው የጀርመን የፊናንስ ሚኒስትር ሃንስ አይሽል እንደገለጹት ደግሞ ግሪክን በ 2001 ዓ.ም. በኤውሮ-ዞን ዓባልነት መቀበሉ ራሱ ትክክል አልነበረም። አገሪቱ በጊዜው ያቀረበቻቸው የፊናንስ ዳታዎች ሃቀኛ እንዳልነበሩ መለስ ብለው ሲያስቡት መቀበሉ ስህተት እንደነበር ግድ መሆኑን ነው ያስረዱት። በነገራችን ላይ ግሪክ ከዚያው አሠርተ-ዓመት ቀደም ሲል የአውሮፓ ሕብረት ዓባል ለመሆን የበቃችው እንኳ በቀላሉ አልነበረም። ከዚህ አንጻር የኤውሮን-ዞን ስትቀላቀል ጠንከር ያለ ቁጥጥር አለመደረጉ በመጠኑም ቢሆን የሚያስገርም ነው።

ያም ሆነ ይህ አሁን ከተደረሰበት ሁኔታ ለኤውሮ-ዞን አገሮች ግሪክን ከለየለት ውድቀት ከማዳን የተሻለ አማራጭ አይታይም። በሌላ በኩል ግሪክ ችግሯን ለመወጣት የዓለምአቀፉን የምንዛሪ ተቋም የ IMF ን ዕርዳታ ብትጠይቅ የተሻለ ነው የሚሉት እየተበራከቱ ነው። የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ኢንስቲቲዩት ተመራማሪዎች በግሪክ ላይ መንግሥታዊ ክስረት የመድረሱን አደጋ አስመልክተው ባካሄዱት ጥናት መሠረት ሁኔታው ለጊዜው ከዘጠናኛዎቹ አመታት ሲነጻጸር ለዘብ ያለ ነው። ይሁንና መቶ ገጽ ገደማ የሚጠቀልለውን ጥናት አብረው ያጠናቀሩት ዩርገን ማቲስ እንደሚሉት ይዞታው አደገኛ ሊሆን የሚችልበትም ሁኔታ አለ።

“አደጋው በፊናንሱ ገበዮች ላይ መደናገጥ ሊፈጠርና ወለድ እንዲንር ሊያደርግ መቻሉ ላይ ነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ግሪክ በአንድ በተወሰነ ጊዜ በካፒታል ገበዮች ላይ ገንዘብ መልሶ ማዋሉ ሊከብዳት ይችላል። ዕዳ ይጫንባታል ማለት ነው። ይህንኑ ዕዳ ለመወጣት ደግሞ አዲስ ብድር ግድ ነው የሚሆነው። እናም ግሪክ አዲስ ብድር ማግኘት ከማትችልበት ደረጃ ከደረሰች፤ ወይም ወለዱ ከበዛ አገሪቱን ለመንግሥታዊ ኪሣራ ከሚዳርግ ችግር ላይ ተደረሰ ማለት ነው”

አንድን የዕዳ ክምር እርግጥ ጥብቅ የቁጠባ ዲሢፕሊንን በማስፈን መቋቋም ይቻላል። ግን ይህ አካሄድ የማቆልቆል አደጋን የሚያስከትልም ነው። መንግሥት ወጪውን መቆጠቡ፣ የስራ አጦች ቁጥር መጨመር፣ የፍጆት መቀነስና የመንግሥት ግብርም ማነስ ተዋህደው የሚያስከትሉት ችግር ለወደፊቱ የሚበጅ አይሆንም።

“ግሪክ ኪሣራ ላይ ብትወድቅ ይህ ለአገሪቱ የኤኮኖሚ ፖሊሲና የሚከተለውን ሁኔታ ለማስተካከልም አስችጋሪ ሁኔታን ነው የሚፈጠረው። ከዚሁ ባሻገር ሌሎች የኤውሮ-ዞን አገሮችም አብረው መጎተታቸው የማይቀር ነው”

ይሄው ተራ በተራ የመፈረካከስ ሁኔታ ከዛሬው መልክ የያዘ መምሰሉም አልቀረም። የተፈራው ከደረሰ ለምሳሌ ስፓኝ፣ ኢጣሊያ፣ አየርላንድና ፖርቱጋል ተራ በተራ ሊወድቁ ይችላሉ። የኤኮኖሚው ኖቤል ተሸላሚ ፓውል ክሩግማን ለኒውዮርክ-ታይምስ ጋዜጣ በጻፉት ሃተታ እንዳስረዱት ለነገሩ ዛሬም ቢሆን ለኤውሮው-ዞን ዋነኛዋ አደጋ በተቀዳሚ ስፓኝ እንጂ ግሪክ አይደለችም። ምክንያቱም ስፓኝ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ አንጻር ባላት 11,4 በመቶ የኪሣራ ድርሻ ምንም እንኳ 12,7 ከመቶ ከተሸከመችው ከግሪክ ብትሻልም ኤኮኖሚዋ ግን ከአራት ዕጅ በላይ ሰፊ መሆኑ ነው። ይሄው ሁኔታ አደጋነቷንም ከፍተኛ ያደርገዋል። የጀርመን የኤኮኖሚ ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ዩርገን ማቲስ እንደሚሉት ይሄው አደጋ ደግሞ እንደሰደድ እሣት ሊስፋፋ የሚችል ነው።

“ከዚህም ባሻገር የግሪከ መንግሥትና የሌሎቹ አደጋው የተደቀነባቸው አገሮች ብድር በባንኮች፣ በመድህንና መዋዕለ-ነዋይ ድርጅቶች ውስጥ ተቀምጦ እንደሚገኝ እናውቃለን። እነዚህ መንግሥታት ክስረት ላይ ቢወድቁ ይህ ለፊናንኑ ዘርፍ አዲስ ችግር የሚፈጥርና ምናልባትም የፊናንሱን ቀውስ ሊያባብስ የሚችል ነው። አዲስ የፊንናስ ቀውስ! ይህ እርግጥ በጣም የጨለመ ሁኔታ በሆነ ነበር”

ሌላው ችግር ግሪክን ኤኮኖሚያቸው ጤናማ በሆነው የኤውሮ-ዞን ዓባል ሃገራት ማዳኑ በአውሮፓ ጽናት ያለውን የአሠራር ደምብ የሚጻረር መሆኑ ነው። የማስትሪሽት ውል አንቀጽ 103 ይህን መሰሉን ድጎማ የሚያግድ ሲሆን ማንኛውም የኤውሮ-ዞን አገር የሌላውን ዕዳ መሸፈን አይፈቀድለትም። ግሪክን በውስጣዊ ዕርምጃ ለማዳን ቢሞከር እንግዲህ የሄው የአውሮፓን ሕግ ከመጣሱም በላይ የሌሎቹን በመንገዳገድ ላይ ያሉትንም ፍላጎት የሚቀሰቅስ ነው የሚሆነው። በመሆኑም የጀርመን ኤኮኖሚ ኢንስቲቲዩት ተመራማሪዎች የሚመክሩት ግሪክ በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ዕርዳታ ላይ እንድታተኩር ነው።

“ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ለማገዝ ልምድና ብቃቱ ያለው ነው። ብድር ይሰጣል። ይህም ራሱ በመጀመሪያ መንግሥታዊ ክስረትን የሚገታ ነው። እርግጥ ብድሩን የሚሰጠው ያለ ቅድመ-ግዴታ አይደለም። አሠራሩ ደግሞ እዚህ በአውሮፓ ካለው ይልቅ አስተማማኝም ነው። በአውሮፓ ግን ግሪክን መርዳት የማይቻልበት የሕግ አንቀጽ አለ። ይሁንና አንድ መንግሥታዊ ክስረት ቢከተል በአውሮፓ በኩል ጣልቃ መገባቱ ግን አይቀርም። እንግዲህ አንቀጹ ያን ያህል ጽናት አይኖረውም። በሌላ በኩል ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ከመተዳደሪያ ደምቡ አንጻር ቅድመ-ግዴታዎችን ማስቀመጥ ስላለበት ሂደቱ አስተማማኝ ነው”

እንግዲህ የአውሮፓ የምንዛሪ ሕብረት ተቋም የበጀት ይዞታ ስነ-ስርዓትን ለማስከበር የሚያስፈልገው የማስፈጸምና የማቀብ አቅም ይጎለዋል ማለት ነው። ባለሚያዎቹ እንደሚሉት አውሮፓ በጥቅሉ የምንዛሪውን ተቋም የምትፈልግ ነው የሚመስለው። እርግጥ ይህ መሆኑ እያደር የሚታይ ይሆናል።

መስፍን መኮንን/DW/AFP/apn/dpa

አርያም ተክሌ