የግሪክ አዲስ የብድር ጥያቄ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 19.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የግሪክ አዲስ የብድር ጥያቄ

ግሪክ ያቀረበችው ጥያቄ የዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ነገ በሚያደርጉት ስብሰባ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲሱ የግሪክ መንግሥት ለዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገራት ማህበር ሃላፊ ዛሬ አዲስ የብድር ጥያቄ የያዘ ደብዳቤ አቅርቧል። ይኽው ደብዳቤ ግሪክ ከአበዳሪዎች ጋር ከዚህ ቀደም የተስማማችበት የ240 ቢሊዮን ዩሮ የብድርና የኤኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ውል ቀርቶ ሌላ የብድ ማራዘሚያ የሚጠይቅ ነው። ደብዳቤው የግሪክ የብድር ስምምነት ለ6 ወራት እንዲራዘም ይጠይቃል ። ግሪክ ያቀረበችው ጥያቄ የዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ነገ በሚያደርጉት ስብሰባ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲሱ የግሪክ ጠ/ሚንስትር አሌክሲስ ሲፕራስ ፣ አውሮፓውያኑ ተጓዳኞቻቸው የብድሩን ውል በ 6ወር እንዲያራዝሙላቸው ቢጠይቁም ፣ ጀርመን ለመፍትኄ የሚበጅ ሐሳብ አይደለም በማለት እንደማትቀበለው ገለጠች። የጀርመን የገንዘብ ሚንስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ ቃል አቀባይ ፤ ብድርን በተመለከተ የመሸጋገሪያ ጊዜ ቢጠየቅም፤ የጠቅላላውን ሰነድ ግዴታ ወደ ጎን የሚገፋ፤ ባለፈው ሰኞ የዩውሮ ተጠቃሚ ሃገራት ማሕበር ያቀረበውን መለኪያም የማያሟላ ነው ሲሉ አስታውቀዋል። በዕዳ የተዘፈቀችው ግሪክ፤ በዚህ ወር ማለቂያ ገደማ የሚያከትመውን የብድር መርኀ ግብር አስመልክታ ፣ የብድር ክፍያው ለ6 ወር እንዲራዘምላት ፣ እንዲሁም የተጠላው የቁጠባ ርምጃ እንዲወገድመጠየቋ ነው የተነገረው። የግሪክ ጠ/ሚንስትር አሌክሲስ

ሲፓራስ---
«በድርድር ረገድ አስቸጋሪና ወሳኝ ቅጽበት ላይ ደርሰናል። እጅግ አስቸጋሪና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ሐሳብ አቅርበናል፤ እናም ይህን ጠመዝማዛ መንገድ እንደምንሻገረውና ወደፊት ለመራመድ እንደሚያስችለን ነው ተስፋ የማደርገው።»
የአውሮፓው ሕብረትና ሌሎች ገንዘብ አባዳሪ ተቋማት የግሪኩ መሪ ያቀረቡት ሐሳብ አስደንግጧቸዋል። የጀርመን የገንዘብ ሚንስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ---
«እርስ- በርስ መተማመንን ካጨናፈግን፣ በአውሮፓ ላይ ነው አሰናካይ ሁኔታ የምንፈጥረው።» የአዉሮጳ የገንዘብ ሚኒስትሮች ባለፈው ሰኞ የግሪክ መንግሥት ተጨማሪ ብድር ለማግኘት ከዚህ ቀደም በተስማማመበት የኤኮኖሚ ማሻሻያና የብድር መርሃ ግብር የሚቀጥል መሆኑን እስከ ነገ ድረስ እንዲያሳውቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። የብራስልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።
ገበያው ንጉሴ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic