የግሪክ ብድርና የጀርመን ድርሻ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 28.02.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የግሪክ ብድርና የጀርመን ድርሻ

የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግሪክ ሊሰጥ በታቀደው ሁለተኛው ተኛ ዙር ብድር ና እርዳታ ላይ ትናንት ተስማምቷል። ምክር ቤቱ ከስምምነት የደረሰዉ በቀላል አልነበረም። ትናንት የፀደቀው ይህ ብድር እዚህ ጀርመን ብዙ ሲያነጋግር ከርሟል።

default

ግሪክን ከበጀት ጉድለት ና ከዕዳ ቀውስ ለመታደግ በአውሮፓ ህብረት እባል ሃገራት ና በዓለም ዓቀፍ አበዳሪ ተቋማት ስምምነት ላይ የተደረሰበት 2 ተኛ ዙር ብድር እንደ መጀመሪያው ዙር ሁሉ ጀርመናውያንን ሲያከራከር ነበረ የሰነበተው ። ብድሩ ያሰፈልጋታል አያስፈልጋትም ከሚሉት አንስቶ የለም እይገባትም ፣ እስከነአካቴውም እዳውን መክፈል አትችልምና ከዩሮ ማህበሩ ትወጣ እስከሚሉት አስተያየቶች ድረስ ከፖለቲከኞች ጭምር ተደምጠዋል ። በዚሁ ክርክር መካከል ትናንት የጀርመን ፓርላማ ድምፁን እንዲሰጥበት የቀረበው ይኽው ብድር በብዙ ድምፅ ተቀባይነትን አግኝቶ ለማለፍ በቅቷል ።

« 496 በመደገፍ ድምፃቸውን ሰጥተዋል ፣ 90 ተቃውመዋል ፣ 5 ድምፀ ተዓቅቦ አድርገዋል ። ማመልከቻው ተቀባይነትን አግኝቷል ። »

የጀርመን ፓርላማ ትናንት ከሰዓት በኋላ የግሪከ ሁለተኛ ዙር ብድር በምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዘዳንት Wolfgang Thierse እንደተገለፀው በብዙ ድምፅ ቢያልፍም የተቃዋሚዎቹ ቁጥር ከቀድሞው መጨመሩ ግን ለመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከባድ ምት መሆኑ አልቀረም ። ብድሩ በፓርላማው መፅደቁ ፣ ጉዳዩ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሲባዝኑ ለከረሙት ለሜርክል እፎይታን አስገኝቷል ። የውጤቱ አንድ ጎን ግን በሃገር ውስጥ ያላቸው ድጋፍ እየቀነሰ የመምጣቱ ማሳያ ሆኖ ነው የቀረበው ። ለዚህም በማስረጃነት የተጠቀሰው ከራሳቸው ፓርቲ ከክርስቲያን ዲሞክራቶች ህብረት ፓርቲ ማለትም ከ CDU እና ከመንግሥታቸው ተጣማሪ ከነፃ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ በምህፃሩ ከ FDP ብድሩን በመቃወም ድምፅ የሰጡት የህዝብ እንደራሴዎች ቁጥር ከከዚህ ቀደሙ ከፍ ማለቱ ነው ። ከ CDU 13 ከተጣማሪው ከ FDP ደግሞ 4 የህዝብ እንደራሴዎች በአጠቃላይ 17 የህዝብ እንደራሴዎች ብድሩን ተቃውመዋል ። ከጥምሩ መንግስት ፓርቲዎች 3 የምክር ቤት ተወካዮችም ድምፀ ተዓቅቦ አድርገዋል ። ባለፈው መስከረም ዩሮን ከውድቀት ለማዳን በአውሮፓ ህብረት ደረጃ የሚመደበው የመጠባበቂያ ገንዘብ ከፍ እንዲል ጥያቄው ለጀርመን ፓርላማ በቀረበበት ወቅት 13 የህዝብ እንደራሴዎች ነበሩ የተቃወሙት ። የትናንቱ ድምፅ አሰጣጥ ውጤት ሜርክል በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ያጋጠማቸው ብርቱ ዱላ መሆኑ ነው የተነገረው ። ከአንድ ሳምንት በፊት በጀርመን ዕጩ ፕሬዝዳንት ምርጫ ወቅት ተጣማሪያቸው የነፃ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ የርሳቸውን ምርጫ ወደ ጎን በመተው ተቃዋሚዎች በጠቆሙት ዕጩ በመስማማቱ ሜርክል የነርሱን ዕጩ ለመቀበል መገደዳቸው ይታወሳል ። ለግሪክ በሚሰጠው ብድርም ከየአቅጣጫው ተቃውሞና ትችት ሲወርድባቸው ነው የከረመው ። ሜርክል ትችቱንና ወቀሳውን ለማርገብና የጀርመን ፓርላማም በብድሩ እንዲስማማ ትናንት ከድምፅ አሰጣጡ በፊት የህዝብ እንደራሴዎችን በተለይ ግሪክ በዩሮ ተጠቃሚነት መቀጠል የለባትም የሚሉትን ወገኖች ማግባባት ነበረባቸው ። ትናንት ፓርላማው ስምምነቱን ከመግለፁ በፊት ባሰሙት ንግግር ለዚሁ ጉዳይ አፅንኦት ሰጥተው ነበር ።


« ግሪክን ወለል ላይ መቀመጫ እንደሌለው በርሜል በመቁጠር በተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ የሚናገሩ እንዳሉ አውቃለሁ ። ግሪክ ምናልባት እንደገና የቀድሞ ገንዘቧን ድርሃምን መልሳ በመጠቀም በኢኮኖሚ የመወዳደር አቅም መገንባት ትችል ይሆን ? የዩሮ ተጠቃሚ ሃገራትስ ግሪክ አባል ሆና በማትቆይበት ሁኔታ የተሻለ እደል ሊያጋጥማቸው ይችል ይሆን ወይ እነዚሀ ጥያቄዎች ቢሰነዘሩም ተገቢነት ያላቸው ናቸው ። ደጋፊና ተፃራሪ ሃሶቦቸነ ከመረመርኩ በህዋላ በአዲሱ መርሃ ግብር ያለው እድል ፣ ከሚገጥሙት ፈተናዎች የላቀ ይሆናል ነው የምለው ። »

ትናንት ፓርላማው ያፀደቀው ለግሪክ እንዲሰጥ የተጠየቀው የ 130 ቢሊዮን ዩሮ ወይም የ174.4 ቢሊዮን ዶላር ብድርና የገንዘብ እርዳታ ነው ። ግሪክ ይህን ገንዘብ ለማግኘት እጅግ ጥብቅ የቁጠባ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተስማምታለች ። ለዚህ ብድር ጀርመን 34 ቢሊዮን ዩሮ የሚደርስ የብድር ዋስትናዎች መስጠት ይጠበቅባታል ። ይሁንና ብዙ ጀርመናውያን ይህ ሁሉ ገንዘብ የሚሰጣት ግሪክ የገባቻቸውን ቅድመ ግዴታዎች መፈፀም መቻልዋን ይጠራጠራሉ ። ቢልድ የተባለው ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ የዳሰሳ ጥናት ያካሄደ አንድ ድርጅትን ጠቅሶ እንደዘገበው በዚህ የተነሳም ከጀርመን መራጭ ህዝብ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ፣ የህዝብ እንደራሴዎች ብድሩን መደገፋቸውን ይቃወማል ። በብድሩ የሚስማማው 33 ከመቶው ብቻ ነው ። ህዝቡ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ፖለቲከኞችም የሚሰጡዋቸው አስተያየቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች በግሪክ ተስፋ መቁረጣቸውን የሚያመለክቱ ናቸው ። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሃንስ ፔተር ፍሪድሪሽ የሰጡት አስተያየት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው ። ሚኒስትሩ Spigel ለተባለው ታዋቂ የጀርመን መፅሄት በሰጡት ቃለ ምልልስ ግሪክ መልሳ ለማንሰራራትና ተወዳዳሪም ለመሆን በዩሮ ቀጣና አባልነት ከመቀጠል ይልቅ ከገንዘቡ ህብረት ብትወጣ ሳይሻል አይቀርም ሲሉ ነበር የናገሩት ። ይህን መሰሉ አስተያየት ከአንዳንድ ምሁራንም ሆነ ከህዝቡ ሲደመጥ የቆየ ቢሆንም በተለይ ከአንድ የጀርመን መንግሥት ባለሥልጣን በኩል ሲነገር የፍሬድሪሽ የመጀመሪያው መሆኑ ነው ። ሜርክል ትናንት ለፓርላማቸው እንዳስረዱት ግን የህብረቱ የገንዘብ ሚኒስትሮች የተስማሙበት መርሃ ግብር የግሪክ እዳ እስከ ዛሬ 6 ዓመት ድረስ በአርባ በመቶ ዝቅ እንዲል ያደርጋል ። ይህንንም ለማሳካት የዩሮ መጠናከርና ህብረት ወሳኝ ናቸው ።

« ዩሮ ከተሰናከለ የአውሮፓ ሀበረትም ስንኩለ እድል ይገጥመዋል ። ዩሮ ከተደላደለ አውሮፓ ይሰምርለታል ። ዩሮ የሚቃናው ጠንካራ መሠረት የጣልን ፣ እድገት ያስገኘን ፣ ትብብርን መርህ ያደረግን ወገኖች የተረጋጋ ህብረትን መፍጠር ስንችል ነው ። ጥንካሬ እድገትና ትብብር እነዚህም ቢሆኑ ግሪክን ከውድቀት ለማዳን ለተቀየሰው መርሃ ግብር መሠረቶች ናቸው ። ባለፈው ጥቅምት ርዕሳነ ብሔርና መራህያነ መንግሥት በተስማሙት መሠረት የግሪክ የዕዳ መጠን ከአንድ መቶ ስልሳ ከመቶ እ.ጎ.አ በ ሁለት ሺህ ሃያ ወደ አንድ መቶ ሃያ ነጥብ አምስት ከመቶ ዝቅ ማለት አለበት። »

ሜርክል ይህን ቢሉም አንዳንድ የጀርመን ፖለቲከኞች ግን ግሪክ ምንም ያህል ገንዘብ ቢሰጣት መሠረታዊ ችግሮቿ አልተፈቱምና የታቀደው አይሳካም ባዮች ናቸው ። ይህን ከሚሉት ውስጥ የሜርክል ፓርቲ የ CDU ው ቮልፍ ጋንግ ቦስባህ ይገኙበታል ።
« ግሪክ ባለፉት ወራት የወሰደችው ብርቱ ቁጥጥር ና የቁጠባ እርምጃ ኤኮኖሚውን እንደሚጠበቀው እላንቀሳቀሰውም ። ቃል የሚገባላት አልተጣሰም ። የፖለቲካ በጎ ፈቃደኝነቱም አለ ። ይሄ አይደለም ችግሩ ። የኤኮኖሚ ጥንካሬ መጥፋት ፣ የኩባንያዎቹ የመወዳደር አቅም እጦትና የተቀላጠፈ አስተዳደር ችግር ናቸው ። እኔ እንደማየው ግሪክ ፍጹም ከዚህ ማጥ ውስጥ የምትወጣበት መፍትሄ ልናገንኝ አንቸለም ብዮ እሰጋለሁ ። »
ብዙዎች ለግሪክ የሚያስፈልገው ገንዘብ በዚህ ብቻ የሚይበቃ አይሆንም ብለው ይሰጋሉ ። ለግሪክ 3ተኛ ዙር የብድር መርሃ ግብር ማስፈለጉ እንደማይቀር የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትር ቮልፍ ጋንግ ሾይብለም ከተጨባጩ ሁኔታ በመነሳት በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ለግሪክ በትክክል የሚያስፈልጋትን ብድር መጠን መወሰኑ አዳጋች መሆኑን ነበር በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተናገሩት ። ቦስባህም ተጨማሪ እርዳታ የማስፈለጉ ስጋት እንዳላቸው መጠቆማቸው አልቀረም ።

« ቀጥለን ማለት የምንችለው ነገር ቢኖር ግሪክ የምታሰበው ግብ ላይ አልደረሰችም ። ይሁንና በመልካም ጎዳና ላይ ነው ያለነው ። አሁንም ቢሆን የኔ ስጋት እንደገና ሌላ የእርዳታ መርሃ ግብር ማቅረብ ሳይኖርብን አይቀርም »

ለግሪክ ሌላ የእርዳታ መርሃ ግብር ማለት ግን ሌላ ራስ ምታት መሆኑ አይቀርም ። ለግሪክ ከተሰጠው የመጀመሪያው ዙር ብድር ከ 27 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሸፈነው የዓለም የገንዘብ ድርጅት በሁለተኛው ዙር ብድር ወደ 10 በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሚሰጥ ነው ያሳወቀው ። ያም ማለት 13 ቢሊዮን ዩሮ ነው ። ይህን ያህል ብድር መገኘቱም እስካሁን በርግጠኝነት አልታወቀም ። ገንዘቡ የሚከፈለውም በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የድርጅቱ ቦርድ ሰራ አስፈፃሚ አባላት ከተስማሙ ብቻ ነው ፣ ለግሪክ ተጨማሪ ገንዘብ መሰጠቱን ከቦርዱ ውስጥ በተለይም ኤኮኖሚያቸው በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘው አንዳንድ አባላት ይቃወማሉና ። በሌላ በኩል የግሪክ በጀት አመዳደብና አተገባበር ፣ የግሪክን ጉዳይ በሚከታተለው ቡድን ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታል ። የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ጉዶዮች ኮሚሽነር ኦሊ ሬን ስምምነት የተደረሰባቸውን ፖሲሲዎች በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያገኙ ሃገሮች ይጠበቃል ።


« ባለው ሁኔታ በመግባቢያ ሰነዱ ላይ ስምምነት በተደረሰበት መሠረት የተወሰዱትን የፖሊሲ እርምጃዎች የመዋቅር ለውጥን ጨምሮ ሙሉ በሙሉና በወቅቱ ተግባራዊ ለማድረግ የገዘብ ድጋፉ መርሃ ግብር ተጠቃሚዎች ስምምነት ላይ ለተደረሰባቸው ግቦች ተገዥ መሆን ይገባቸዋል ። »

ጠንካራ የቁጠባ እርምጃዎችን ከመውሰድ በተጨማሪ ጥብቅ የበጀት አስተዳደር ቁጥጥር እንዲደረግባት የተስማማችው ግሪክ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን አንድ ባልደረባ ተመድቦላት የበጀት አደላደሏን ይከታተላል ። ሬን ቁጥጥርና ክትትሉ በምን መልኩ እንደሚከናወን አስረድተዋል ።

« ድርብ ሚና ነው ያለን ። ቁጥጥር ማድረግን በሚመለከት የኛ ድርሻ ልክ እንደ እግር ኳሱ ጨዋታ መሃል ዳኛነት ነው ። የቴክኒክ እገዛን በሚመለከት ደግሞ ሚናችን አሠልጣኝነት ነው ። ሁለቱን በአንድ ላይ ማካሄዱ ከችግር የፀዳ አይደለም ። ግን ሊሆን ይችላል ። ይህን በማከናወን ላይ ነው የምንገኘው ። »

የአውሮፓ ህብረት ለግሪክ ያሰበው ቁጥጥር አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ሉዓላዊነቷን የሚጋፋ ነው ። የግሪክ ሁለተኛ ዙር ብድርን በሌሎቹም የዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገራት ምክር ቤቶች መፅደቅ ይኖርበታል ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic