የግሪክ ቀውስና የቁጠባው ግፊት | ኤኮኖሚ | DW | 29.06.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የግሪክ ቀውስና የቁጠባው ግፊት

የግሪክ ፓርላማ ዛሬ በአቴኑ መንግሥት የአምሥት ዓመት የቁጠባ ዕቅድ ላይ ተሰብስቦ ድምጽ ሰጥቷል።

default

መማክርቱ ዓለምአቀፍ አበዳሪዎች በጠየቁት መሠረት ሰፊውን የቁጠባ ፓኬት በመደገፍ ድምጽ የሰጡት ከፓርላማው ውጭ በፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት ባየለበት ሁኔታ ነው። በድምጽ አሰጣጡ ውጤት መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትር ፓፓንድሬዉ መንግሥት የቁጠባ ዕርምጃውን ገቢር ,ለማድረግ የሚያስፈልገውን 155 ድምጽ ለማረጋገጥ በቅቷል።
የቁጠባው ፓኬት ተቀባይነት ማግኘት አገሪቱ ከአውሮፓ ሕብረትና ከዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ከአይ.ኤም.ኤፍ. ተጨማሪ ብድር ማግኘት እንድትችል ወሣኝ ቅድመ-ግዴታ ነው። አገሪቱ አሁን ባለችበት የበጀት ሁኔታ ተጨማሪ ብድር ባታገኝ በጥቂት ቀናት ውስጥ ክስረት ላይ እንደምትወድቅ ነበር የተነገረው። ዕለቱ በግሪኮች አዕምሮ ውስጥ ምናልባት ለረጅም ጊዜ ተቀርጾ የሚቆይ ነው የሚመስለው። ጠቅላይ ሚኒስትር ፓፓንድሬዉ በቁጠባና ለውጥ ፓኬቱ ክርክር መክፈቻ ላይ ዕቅዱን ከመደገፍ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ ነበር በተማጽኖ መንፈስ ለመማክርቱ ያስገነዘቡት።

“መንፈሳችሁና አገር ወዳድ ሕሊናችሁ የሚላችሁን አድምጡ! ዕቅዱን ደግፋችሁ ድምጽ መስጠታችሁ አገሪቱ መልሳ በሁለት እግሯ ለመቆም ትችል ዘንድ ያለው የመጨረሻ ዕድል ነው”

የቁጠባው ዕቅድ የም/ቤቱን ድጋፍ ማግኘት ግሪክ በአስቸኳይ 12 ሚሊያርድ ኤውሮ፤ በሚቀጥሉት ዓመታትም በተጨማሪ እስከ 120 ሚሊያርድ የሚደርስ ብድር እንዲቀርብላት ጥርጊያን የሚከፍት ነው። ሆኖም ከወደቀችበት አዘቅት በቀላሉ መውጣቷ ቢቀር በወቅቱ ያጠያይቃል። ለዚህም ነው ሕዝቡ ተጨማሪ ሸክም አልችልም ሲል ሰሞኑን የአደባባይ ተቃውሞውን ያጠናከረው። እርግጥ ነው አዲሱ የቁጠባ ዕርምጃ በዝርዝሩ ነገም በም/ቤት ድጋፍ ካገኘ ተጽዕኖው ከሞላ ጎደል መላውን የግሪክ ሕዝብ የሚነካ ነው የሚሆነው። የመንግሥት ግብር እንዲጨምር ይደረጋል። ከዚሁ ሌላ ወደፊት አንድ ሺህ ኤውሮና ከዚያ በላይ የወር ገቢ ያላቸው ዜጎችም የቀውስ ጊዜ አስተዋጽኦ እንዲከፍሉ ሊጠየቁ ነው። እነዚህ እንዲሁም ሌሎች የግብር ጭማሪዎችና የቁጠባ ዕርምጃዎች በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት 28 ሚሊያርድ ኤውሮ ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሎ ነው የታመነው።
የግሪክ መንግሥት በይዞታው የሚገኝ ንብረትን፤ እንበል ርስት፣ መሬትንና የኩባንያ ድርሻን የመሳሰሉትን በመሸጥ ተጨማሪ 50 ሚሊያርድ ኤውሮ ለማስገባትም ያስባል። ይህ ከምድር ባቡር፣ ውሃ ልማትና የኤነርጂ ማመንጫ አንስቶ እስከ አቴን ዓለምአቀፍ አየር ጣቢያ ድርሻ ድረስ ብዙ የመንግሥት ተቋማትን የሚያዳርስ ነው። እርግጥ ይህ ሁሉ የሚሆነው ጉዳዩን በሚከታተል ነጻ ተቋም ክትትል ነው። ነገር ግን በተባለው መልክ ገቢር መሆን መቻሉ እያደር የሚታይ ጉዳይ ይሆናል። በወቅቱ መሪሩ የግሪክ ሃቅ የኤኮኖሚው መመንመንና ከሁሉም በላይ ደግሞ የወጣቶች ሥራ አጥነት በፍጥነት እያደገ መሄድ ነው። የአደባባይ ተቃውሞ የያዙት ዜጎች እንደሚሉት ከሆነ ሂደቱ ጨርሶ ተሥፋ ሰጭ አይደለም።

“ከአንድ ዓመት ተኩል ወዲህ የምንኖረው ከቁጠባ ዕርምጃዎች ጋር ብቻ ነው። ለነገሩ ሁኔታው ይሻሻላል ተብለናል። ግን የምንታዘበው ተቃራኒውን ነው። ዕዳው እየጨመረና ቀዉሱም እየከፋ ይገኛል። ይህን ደግሞ ልንቀበል አንችልም”

የግሪክ መማክርት በአንድ በኩል ይህ የሕዝብ ቁጣ ተደቅኖባቸው በሌላ በኩልም የቁጠባ ፓኬቱን እንዲደግፉ በአውሮፓ ሕብረት የሚደረግባቸው ግፊት እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ነው በፓርላማ ድምጽ የሰጡት። የግሪክ መንግሥት ከአበዳሪዎቹ ከአውሮፓ ሕብረት፣ ከአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክና ከዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በመጪዎቹ ዓመታት 78 ሚሊያርድ ኤውሮ መቆጠብ ይጠበቅበታል። ይህ ደግሞ 11 ሚሊዮን ገደማ ከሚጠጋው የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር አንጻር በነፍስ ወከፍ ሰባት ሺህ ኤውሮ መቆጠብ ማለት ነው። ግሪኮች እንግዲህ የገንዘብ ቦርሳቸው ይብስ መራቆቱን የሚያዩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

የውጭ የምጣኔ-ሐብት ታዛቢዎችም በተለይም የግሪክ መንግሥት በይዞታው የሚገኙ ኩባንያዎችን በመሽጥ ወደ ግል ዕጅ ለማሻገር የያዘውን ውጥን መሳካት በጥርጣሬ አይን ነው የሚመለከቱት። ከነዚሁ አንዱም በጀርመን የሃምቡርግ የዓለም ኤኮኖሚ ጥናት ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ቶማስ ሽታውብሃር ናቸው።

“ለዚህ አስፈላጊ የሆነው ተቋምና ቅንጅታዊ መዋቅር ይጎላል። እናም ኩባንያዎቹን ወደ ግል ዕጅ ማዛወሩ እጅግ ግዙፍ ተግባር በመሆኑ በሚሊያርዶች መጠን ከታሰበው ገቢ ላይ መድረሱ አጠያያቂ ነው”

ቀደም ሲል የጠቀስነው የቀውስ ጊዜ አስተዋጽኦ ግብር ወደፊት ከሺህ ኤውሮ በላይ ገቢ ካለው ዜጋ ሁሉ እንደየአቅሙ ከአንድ በመቶ እስከ አራት በመቶ ከደሞዙ ወይም ከገቢው ሊቆረጥ ነው። የተሽከርካሪ ግብር አሥር ከመቶ ይጨምራል። የማሞቂያ ዘይት ዋጋ በሊትር በአምሥት ሣንቲም የሚያድግ ሲሆን በግል ተዳዳሪዎች፣ ለምሳሌ በጠበቆችና በዕጅ ሥራ ባለሙያዎች ላይ ተጨማሪ 300 ኤውሮ ግብር እንደሚጣል ነው የሚጠበቀው። እንግዲህ የሕዝቡ ተቃውሞ ማየሉ ብዙም አያሰደንቅም። የግሪክ የፊናንስ ሚኒስትር ኤቫንጌሎስ ቪኒዜሎስ ሳይቀሩ የመንግሥታቸው የቁጠባ ዕቅድ ከባድና ፍትህ የጎደለው መሆኑን አልካዱም። ሆኖም የአገሪቱን የፊናንስ ስርዓት ከውድቀት ለማዳን ሌላ ምርጫ የለም ባይ ናቸው።

“ይሄ ስር የሌለው ቀዳዳ በርሚል መልሶ መሠረት ማግኘት ይኖርበታል። እንግዲህ ይህ ከሆነ በኋላ ነው ዕድገት ልናይና የሥራ አጡን ቁጥርም ልንቀንስ የምንችለው። ከዚያ በፊት ዕዳችንን መልሰን መክፈላችንን ማረጋገጥ አለብን”

ይህ ሁሉም ለግሪክ የሚመኘው ሲሆን በሌላ በኩል የቁጠባውን ዕቅድ ትተን አገሪቱ ክስረት ላይ ብትወድቅ በአውሮፓ ሕብረትና በጋራ ምንዛሪው በኤውሮ ላይ ምንድነው የሚከተለው? በሕብረቱ ውስጥ ይህን በግልጽ ማንሳት ባይፈለግና ፕላን-ቢ ሁለተኛ መፍትሄ አልተሰላም ተብሎ በብራስልሱ ኮሚሢዮን በተደጋጋሚ ቢነገርም ውስጥ ውስጡን መላ መፈለጉ እንዳልቀረ ነው የሚታመነው። ብራስልስ ውስጥ የሚታሰበው የሕብረቱ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል ባሮሶ ቀደም ሲል ሰሞኑን እንዳሉት ግሪክ የገንዘብ ዕርዳታ በማግኘት ራሷን ከክስረት ለማዳን ጥረት በማድረግ ፋንታ ምንም አማራጭ አልነበራትም።

“አገሪቱ ለዓመታት ከአቅሟ በላይ ሆኗ ልትኖር አትችልም። ግሪክ ያለማቋረጥ የፊናንስ ማረጋጊያውን ደምብ ስትጥስና በዚሁም በሌሎች ዓባል ሃገራት ፊት ያለባትን ግዴታ ለመወጣት ሳትችል ነው የቆየችው። ሃቁ እንግዲህ ይህ ነው። እናም አገሪቱ በዚህ የሃቅ ሰዓት ከቀውሱ ለመውጣት ትክክለኛውን መንገድ እንደምትመርጥ ተሥፋ አደርጋለሁ”

የባሮሶ የቃላት አመራረጥ የሁኔታውን ከባድነት ያመለከተ ነበር። የቁጠባው ፓኬት በም/ቤት ተቀባይነት ባያገኝ የአውሮፓ ሕብረት ምናልባት ፈጣንና ትልቅ ክብደት ያለው ውሣኔ ማስተላለፍ በተገደደ ነበር። ከዚህ አንዱ የግሪክ መንግሥት ተቃዋሚዎች ዕቅዱን እንዲደግፉ በአስታራቂ ሃሣብ ማግባባት ነው። በሌላ አነጋገር የአውሮፓ ሕብረትና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም የቁጠባው ዕቅድ ዕድል እንዲኖረው ይዘቱን ማለዘብ ሊገደዱ ይችላሉ። ሌላም ግሪክ ቢቀር ለጥቂት ቀናት እንኳ ከከስረት እንድትድን እያንዳንዱ የኤውሮ አገር በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ የድንገተኛ ጊዜ ብድር ማቅረቡ ሊታሰብ የሚችል ነው። እነዚህ ሁሉ ታዲያ በወቅቱ ማንም ሊያነሳቸው የማይፈልጋቸው ቢሆንም ጊዜ ሳይፈጅ መጣራት ያለባቸው ነጥቦች ግን ናቸው። የሆነው ሆኖ ለጊዜው ከዚህ መሰሉ ሁኔታ አልተደረሰም።

ለማንኛውም የቁጠባው ፓኬት የም/ቤቱን ድጋፍ አግኝቷል። ሆኖም ግን የተዳከመው የአገሪቱ ሶሻሊስት መንግሥት ለውጡን ገቢር ማድረጉ ገና ብዙ የሚያጠራጥር ነው። ብዙ የኤኮኖሚ ጠበብትና የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች አሁንም ግሪክ በአማካይ ጊዜ ክስረት ላይ መውደቋ እንደማይቀር ነው የሚናገሩት። ከሆነ ለኤውሮ ምንዛሪ አደገኛ ነገር ነው የሚሆነው። እስካሁን አየርላንድንና ፖርቱጋልን የመሳሰሉትን ዓባል ሃገራት ከቀውስ ለማላቀቅ ዕርዳታ ተደርጓል። ግሪክም ቢሆን ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ከአውሮፓ ሕብረትና ከዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም 110 ሚሊያርድ ኤውሮ ብድር ማግኘቷ አይዘነጋም። ግን ይህ አለመብቃቱ ነበር ችግሩ።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic