የግሪኩ ቀውስና የኤውሮ ክልል ፈተና | ኤኮኖሚ | DW | 21.09.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የግሪኩ ቀውስና የኤውሮ ክልል ፈተና

የኤውሮ ምንዛሪ አገሮች በግሪክና በሌሎች ዓባል ሃገራት ዘንድ ለተፈጠረው የዕዳ ቀውስ መፍትሄ ለማግኘት መባከናቸውን ቀጥለዋል።

default

ቀውሱ በዚህ በጀርመን ያስከተለው ክርክር የጥምሩን መንግሥት ሕልውና ሲፈታተን በዓለምአቀፍ መፍትሄ ፍለጋው ረገድም በአውሮፓና በአሜሪካ መካከል ጥልቅ የሃሣብ ልዩነት መኖሩን በጉልህ እያሳየ ነው። 17ቱ የኤውሮ ምንዛሪ ክልል ሃገራት የፊናንስ ሚኒስትሮች በበኩላቸው የሕብረቱን ርዕስነት በያዘችው በፖላንድ ከተማ በቭሮስላቭ ባለፈው ሣምንት ማብቂያ ላይ ባካሄዱት ስብሰባ ቀውሱን በመቋቋሙ ጥረት በፊናንስ ገበዮች የገንዘብ ሽግግር ላይ ግብር ለመጣል ወስነው ነበር።
በወቅቱ በዚህ በአውሮፓ ግሪክን ከለየለት ክስረት ለማትረፍና የኤውሮን ሕብረትም ሕያው አድርጎ ለማቆየት ያልተቆጠበ ጥረት እየተደረገ ሲሆን በሌላ በኩል ግሪክንና ፖርቱጋልን የመሳሰሉት የዕዳው ቀውስ ክፉኛ የተጠናወታቸው አገሮች የኤውሮን ክልል ለቀው ቢወጡ ይሻላል የሚለው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሲነሣ የቆየው ሃሣብ አሁን ጠንከር ማለት እየያዘ ነው። ሃሣቡ ከኤኮኖሚ ስሌት አንጻር ጭብጥነት ቢኖረውም በፖለቲካ ግምት ግን ለአውሮፓውያን የምንዛሪው ሕብረት መሸንሸን ቢቀር በወቅቱ ተቀባይነት የለውም።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የፊናንስ ገበዮች የገንዘብ ሽግሽግ ግብር እንዲጣል አጥብቃ ግፊት የምታደርገው በተለይ ጀርመን ናት። በአንጻሩ ብሪታኒያ ጉዳዩን በጥርጣሬ ዓይን ትመለከተዋለች። ይሁንና በ 17ቱ የኤውሮ አገሮች ውስጥ የዕዳውን ቀውስ የመታገሉ ጉዞ በዚህም በዚያም መቀጠል አለበት። በመሆኑም የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ በዓለምአቀፍ ደረጃ የፊናንስ ገበዮች የገንዘብ ሽግግር ግብር ለማስፈን ተደርጎ የነበረው የመጀመሪያ ሙከራ ባለፈው ዓመት ከከሽፈ ወዲህ አሁን ከፈረንሣይ ጋር በመሆን በአውሮፓ ደረጃ ሃሣቡን ለማሣካት እንደገና ሙከራ ያደርጋሉ። አሜሪካ በበኩሏ በፊናንስ ገበዮች ላይ ግብር መጣሉን ጨርሶ አትቀበልም።

በሌላ በኩል የአውሮፓ ኮሚሢዮን በቅርቡ፤ ማለትም በመጪው ጥቅምት ወር ለዚሁ የሚሆን የሕግ ረቂቅ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። በነገራችን ላይ ጉዳዩን ከብሪታኒያ ሌላ ፖላንድና ኢጣሊያም በጥርጣሬ መመልከታቸው አልቀረም። ይሁን እንጂ የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ከከፋ ከከፋ ኤውሮን በጋራ ምንዛሪነት የሚገለገሉት 17ቱ የአውሮፓ አገሮች ግብሩን ለብቻቸው ያሰፍናሉ ባይ ናቸው።

“እርግጥ ነው የጉዳዩን ዝርዝር ሁኔታ በተመለከተ ትግል እንደሚኖር አንድና ሁለት የለውም። ይህ ግን ከትግሉ ሜዳ ወደ ኋላ እናሸገሽጋለን ማለት አይደለም። በአንጻሩ ለአውሮፓ ሕብረት የሚሆን አንድ ሕግ ለማስፈን ነው የምንፈልገው”

ግብሩ የተፈለገበት ዓላማ በአንድ በኩል መንግሥታት ቀደም ሲል ባንኮችንና መድህን ድርጅቶችን ከክስረት ለማዳን ያወጡትን ገንዘብ ለመመለስ ነው። ከዚሁ ሌላ አደገኛ የሆነ የፊናንስ ንግድ በግብሩ ሳቢያ ውድ ስለሚሆን ቢቀር በኤውሮው ክልል ውስጥ የማያዋጣ ይሆናል።

የኤውሮው ክልል የፊናንስ ሚኒስትሮች ከክስረት አፋፍ ላይ የምትገኘው ግሪክ በፊናዋ የቁጠባ ዳታዎቿን ቀደም ሲል በተታለባት ግዴታና በገባችው ቃል መሠረት አስተካክላ እንድትገኝም አስገንዝበዋል። ሶሥትዮሹ ተቆጣጣሪ አካላት የአውሮፓ ሕብረት፣ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ. በፊታችን ጥቅምት መጀመሪያ በሚያካሂዱት ምርመራቸው ጥሩ ምስክርነት ካልሰጡ የኤውሮው ቡድን ሃላፊ ዣን-ክላውድ-ዩንከር እንዳሉት ግሪክ ቀጣዩን ስምንት ሚሊያርድ ኤውሮ የዕርዳታ ብድር ከሕብረቱ ልታገኝ አትችልም።

“ሶሥትዮሹ ወገን ግሪክ ግዴታዋን አለሟሟላቷን ካረጋገጡ ብድሩ አይሰጥም። እርግጥ ስለሚከተለው ማሰቡ ፍሬ የለውም። ግሪክ የሚጠበቅባትን ካላሟላት ምን ይሆናል፤ ምላሽ ለመስጠት አሁን ጊዜው አይደለም”

ግሪክ የክፍያ አቅም አጥታ ክስረት ላይ ብትወድቅ ምን ይደረጋል ለሚለው ጥያቄ በአውሮፓውያን ዘንድ መልስ ለመስጠት ቀርቶ ለማሰብ እንኳ የሚሻ የለም። ታዲያ የምንዛሪውን ሕብረት ጠብቆ ለመቀጠል ትግል በተያዘበት በዚህ ወቅት ከአትላንቲክ ባሻገር ከአሜሪካ ደግሞ የግሪክና ምናልባትም የፖርቱጋል ከኤውሮው ሕብረት መውጣት እንደ መፍትሄ ሃሣብ ሆኖ መቅረቡ አልቀረም። ይህን ሃሣብ የሰነዘሩት በአሜሪካ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ-ሐብት ፕሮፌሰር የሆኑት ታዋቂ ምሁር ማርቲን ፌልድሽታይን ናቸው።
የኤኮኖሚው ጠቢብ ከፕሬዚደንት ሬገን አንስቶ እስከ ባራክ ኦባማ ዘመን በምጣኔ-ሐብት አማካሪነት በመንግሥት የተሰየሙ መሆናቸው ሲታወቅ ገና ኤውሮ ይፋ ከመሆኑ አምሥት ዓመታት ቀደም ብለው ነበር ምንዛሪው ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ያስጠነቀቁት። ፌልድሽታይን ዛሬ የሚናገሩት ያኔ በዘጠናኛዎቹ ዓመታት በጉዳዩ ያወጡት ጽሑፍ አሁን በተጨባጭ ሁኔታ ዕውን እንደሆነ ነው። አስተሳሰባቸውንም እንደሚከተለው ያብራራሉ።

“ከፖለቲካ ይልቅ ይበልጡን በኤኮኖሚው ሂደት ላይ ማተኮሩ ጠቃሚ ነው። እኔ የታየኝ ችግር፤ አሁን ግልጽ የሆነ ይመስለኛል፤ ይህን ያህል የተለያዩ ለሆኑት በርካታ አገሮች የጋራ ምንዛሪ እንደማይሰራ ነው። ብዙዎች ያኔ ወደ አሜሪካ በማመልከት አገሪቱ ምንም እንኳ ትልቅ ልዩነት ቢታይባትም የጋራ ምንዛሪ ለማስፈን መቻሉ እንዳልገደዳት ነበር የሚናገሩት። እኔ ግን አሜሪካ ውስጥ በጣም ተንቀሳቃሽ የሆነ የሥራ ሃይል እንዳለን፤ በአንዱ አካባቢ ሥራ ሰጠፋ በቀላሉ ወደ ሌላ የአገሪቱ ክፍል ለቆ የሚሄድ ሕዝብ እንዳለን ነበር ያስረዳሁት። ይህ እርግጥ በቋንቋ፣ በታሪክና በሙያ ማሕበራት ሁኔታ ልዩነት ባለባት በአውሮፓ ቀላል ነገር አይደለም። ከዚሁ ሌላ በሥራ ገበያ፣ በክፍያና በግብር አሰባበብ ሁኔታም ልዩነቱ ብዙ ነው። ፖለቲካውን ካነሣን የኤኮኖሚው ችግሮች በፖሊሲ ጉዳይ ላይ ትልቅ አለመግባባትን እንደሚያስከትሉ ቀድሞ የታየኝ ጉዳይ ነበር”

ይህ እርግጥ ባለፉት ጊዜያት በያጋጣሚው ሲንጸባረቅ መታየቱም አልቀረም። የኤውሮው ምንዛሪ ክልል የዕዳ ቀውስ እጅግ ከባድ ሲሆን መገታት መቻሉ በሰፊው ማጠያየቅ የያዘ ጉዳይ ነው። እና የአሜሪካው የኤኮኖሚ ባለሙያ ማርቲን ፌልድሽታይንም ግሪክን ከክስረት ማዳን ይቻላል የሚል ዕምነት የላቸውም።

“ቀውሱ ሊገታ በመቻሉ እርግጠኛ አይደለሁም። ምክንያቱም እኔ የማምነው ግሪክ የመክፈል አቅም እንደምታጣ/እንደምትከስር ነው። ይህ እርግጥ በብዙዎች እንዳስከፊ ውድቀት ሆኖ መታየቱ አይቀርም። በበኩሌ ይህ ትክክል ነው ብዬ አላስብም። ሁኔታው በዓለም ላይ በብዙ አገሮች የታየ ነው። እና ይህ ደግሞ ቀውስ ላይ የወደቁ አገሮች በጀታቸውን በመጠኑም ቢሆን እንዲያስተካክሉ መርዳቱ አይቀርም። ይሁን እንጂ ፖርቱጋልም ወደ ክስረቱ ማምራቱ የሚቀርላት አይመስለኝም። የሌሎቹ የኢጣሊያና የስፓኝ ይዞታ በትክክል ምን እንደሆነ አይታወቅም። በነዚህ ሁለት አገሮች የበጀትና የባንኮች ይዞታ ላይ ሃቀኛ መረጃ ማግኘት ከባድ ነው”

እንደ ፌልድሽታይን ከሆነ ለግሪክ መፍትሄው የኤውሮውን ክልል ለቆ መውጣቱ ብቻ ነው። አገሪቱ ከምንዛሪው ሕብረት ወጥታ በጀቷን ካስተካከለች በኋላ መልሳ ለዓባልነት ብታመለክት ይበጃታል ነው የሚሉት።

“ይህ ለግሪክ የሚጠቅም ነው ብዬ አስባለሁ። አገሪቱ የዕዳ ችግሯን ለጊዜው ብታስወግድና በሌሎች ዕርዳታ ወይም በራሷ ጥረት ከለየለት ክስረት ላይ ከመውደቅ ብታመልጥ እንኳ ምን ይከተላል የሚለው ጥያቄ ሊነሣ የሚገባው ነው። ግሪክ ለዓመታት የብሄራዊ ምርት ትርፍ ለማግኘትም ሆነ ለምሳሌ እንደ ጀርመን ምርታማነትና የኤኮኖሚ ዕድገት ለማስፈን ተስኗት ነው የኖረችው። ታዲያ የፉክክር ብቃት ከየት ሊመጣ ይችላል? ግሪከ እንግዲህ በኤውሮ ምንዛሪ ደረጃ ይህን ለማሳካት አትችልም”

ቀውሱ እየከፋ ሄዶ አንዳንድ አገሮች ወደ ቀድሞ ብሄራዊ ምንዛሪያቸው ቢመለሱ ለአውሮፓ ሕብረት በተለይም ከኤኮኖሚ ይልቅ በፖለቲካ አንድነቱ ረገድ እንደ ኋልዮሽ ሂደት ነው የሚቆጠረው። ስለዚህም የሚድነውን አድኖ የምንዛሪውን ሕብረት በመጠበቅ ወደፊት ማራመዱ ቀደምቱ ጥረት ሆኖ ይቀጥላል። ይሳካል አይሳካም ግን ጠብቆ ከመታዘብ ሌላ በወቅቱ የተሻለ ምርጫ የለም።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ


Audios and videos on the topic