የግሪኩ ሲሪዛ ድልና አንድምታው | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 27.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የግሪኩ ሲሪዛ ድልና አንድምታው

በዕሁዱ የግሪክ አጠቃላይ ምርጫ ያሸነፈው ግራ ዘመሙ ሲሪዛ የግሪክ ፓርቲ ፣ነፃ የግሪኮች ፓርቲ ከተባለው የቀኝ ክንፍ ብሔረተኛ ፓርቲ ጋር ጥምር መንግሥት መስርቷል ።በግሪክ ላይ የተጫኑትን የቁጠባ እርምጃዎች የሚቃወሙት እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ሥልጣን መያዛቸው ትኩረት ስቧል ።

። በደቡብ አውሮፓዊቷ ሃገር በግሪክ ባለፈው እሁድ የተካሄደው ምርጫ ውጤት ያልተጠበቀም ባይሆን በሃገሪቱም ሆነ በአውሮፓ ታሪክ ልዩ ስፍራ የሚይዝ ሆኗል። ምርጫው ከዛሬ 40 ዓመት ወዲህ በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ላቅ ያለ ሚና የነበራቸውን አንጋፋ ፓርቲዎች ከሥልጣን በማሰናበቱ ብቻ ሳይሆን በዩሮ ቀውስ ምክንያት በሃገሪቱ ላይ የተጫኑትን የቁጠባ እርምጃዎች የሚቃወሙ ፓርቲዎችን ለሥልጣን በማብቃቱ የዓለምን በተለይም የአውሮፓውያንን ትኩረት ስቧል ። ግራ ዘመሙ ሲሪዛ ከ300 የግሪክ ፓርላማ መቀመጫ 149ኙን አሸንፎ ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱ አነጋግሮ ሳያበቃ እንደ ሲሪዛ ሁሉ የቁጠባ እርምጃዎችን ከሚቃወመው አነስተኛ ብሔረተኛ ፓርቲ ጋር ትናንት ተጣማሪ መንግሥት መመሥረቱ ማስደመሙ አልቀረም ። ብቻውን መንግሥት ለማቋቋም 2 መቀመጫ የጎደለው ሲሪዛ ጥምር መንግሥት የመሠረተው ቀኝ ፅንፈኛ ከሚባለው የነፃ ግሪኮች ብሔረተኛ ፓርቲ በምህፃሩ ANEL ጋር ነው ። በአሁኑ ምርጫ 4 በመቶ ድምፅ ያገኘውANEL ከፓርላማው መቀመጫ 13 ቱን አሸንፏል ። የአውሮፓ ህብረትና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለግሪክ የገንዘብ ቀውስ መፍትሄ ያሉትን የኤኮኖሚ ተሃድሶና የቁጠባ እርምጃዎችን ከመቃወም ውጭ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ተቃራኒ አቋም ያላቸው የእነዚህ ፓርቲዎች መጣመር ያልተለመደ ጥምረት ሆኖ ነው የታየው ።

በግሪክ የ150 ዓመት ታሪክ ውስጥ ለዚህ ሥልጣን የበቁ የመጀመሪያው ወጣት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፕራስ ከፓርቲያቸው ድል በኋላ ባሰሙት ንግግር ሃገራቸውና ህዝቧ ከትልቅ ጫና እፎይ የሚሉበት ጊዜ ላይ መድረሳቸውን ነበር የተናገሩት ።

« የሉዓላዊt ሃገር የግሪክ ህዝብ ዛሬ ግልፅ ጠንካራና የማያከራክር ስልጣኑን ሰጥቷል።ግሪክ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተች ነው ። ግሪክ ከተመሰቃቀለው አሰጨናቂ የቁጠባ እርምጃ ፣ከፍርሃትና ከተመረጡ ሃብታሞች አስተዳደር እንዲሁም ካለፉት 5 ዓመታት መሸማቀቅና ህመም እየተገላገለች ነው ።»

ሲፕራስ ግሪካውያንን ማህበራዊ ኑሮአቸውን በእጅጉ ካናጋበቸው የቁጠባ እርምጃ በቀላሉ መገላገላቸውን ለጊዜው ማወቅ ያዳግታል ። አሁን በትክክል የሚታወቀው ከቁጠባ እርምጃው በኋላ በሃገሪቱ የሥራ አጡ ቁጥር መጨመርና የዜጎች ገቢ መቀነስ ህብረተሰቡን በእጅጉ ያማረረ መሆኑ ነው ። በአሁኑ ጊዜ ከ25 በመቶ በላይ ግሪካውያን ሥራ አጥ ናቸው ። ከዜጎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ቤተሰቦች ወደ ድህነት ወለል የሚጠጋ ህይወት ነው የሚገፉት ።አንዳንዶች እስከ መቼ እንዲህ ያለ ህይወት እንደሚመሩ ግራ ተጋብተዋል ።በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት ግሪካውያን ሲሪዛን ቢመርጡ አይገርምም ትላለች አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ።

«በቂ ምግብ የለህም ። ወይ ደግሞ ኤሌክትሪክ የለህም እስከ መቼ መታገስ ይቻላል አንድ ወር አንድ ዓመት ሁለት ዓመት ትዕግስታቸው አልቋል ።»

ሌላዋ ግሪካዊ ደግሞ ያለፉት 4 ዓመታትን ያሳለፈችው ስለ ወደፊት እጣዋ በማሰብና በማሰላሰል እንደነበር ትናገራለች ።

« ሁሌም አንድ ነገር ይሆናል በሚል ስጋት ውስጥ ነው የምኖረው።ሥራዬን አጣለሁ እናም ምናልባት ግሪክን ትቼ መውጣት ሊኖርብኝ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ ። ዋናው ነገር ፍርሃት ነው ። ሁሌም ስለ አንድ ነገር ይገጥመኛል ብዬ እሰጋለሁ እፈራለሁ ። »

ፍርሃት የነገሰባት ይህች ግሪካዊ ድምፅዋን የሰጠችው ለሲሪዛ ነው ። ሲሪዛን የመረጠችበት ምክንያትም ፓርቲው ባንኮችን ሳይሆን ህዝቡን መልሶ ለማቋቋም ቃል በመግባቱ ነው ትላለች።በርስዋ አስተያየት ከዛሬ አራት ዓመት ወዲህ ግሪክ ሉዓላዊነቷን ለአበዳሪዎች አሳልፋ ሰጥታለች ።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላይ የመንግሥት ለውጥ መደረጉ አሁን ያልተጨበጠም ቢሆን ለህዝቡ የተስፋ ጭላንጭል ተደርጎ ተወስዷል ።

«ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለሁ ። ተቃዋሚ በነበሩበት ጊዜ ቃል የገቡትን ተግባራዊ ያደርጋሉ ።»

«ተስፋ አለ ። ምክንያቱም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለኔ በግሌ ና በአጠቃላይ ለግሪካውያን አሰቸጋሪ ነበርና»

በግሪክኛ ምህፃር ሲሪዛ በመባል የሚታወቀው የእሁዱ ምርጫ አሸናፊ ፓርቲ ግራ ዘመሞችና ጽንፈኛ የግራ ፓርቲዎች የመሠረቱት የ13 ፓርቲዎች ጥምረት ነው ። ከተመሠረት ዘንድሮ 11ኛ ዓመቱን የደፈነው ሲሪዛ ነፃ ፖለቲከኞች ፣ሶሻል ዲሞክራቶች የግራ ክንፍ ታዋቂ ሰዎችና ኮምኒስት አባላትም አቅፏል ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ እያገኘ የመጣው ሲሪዛ በተለይ በ2012 ቱ ምርጫ በግሪክ ፓርላማ ባገኘው መቀመጫ ሁለተኛውን ቦታ ይዞ ነበር ። 36.3 በመቶ ድምፅ ያሸነፈው ሲሪዛ ለአሁኑ ድል የበቃው ግሪክና ግሪካውያንን የብዙ ዓመታት እዳ ውስጥ የዘፈቀውን የኤኮኖሚ ተሃድሶና የቁጠባ እርምጃ ላይ እንደገና ለመደራደር እንዲሁም ከዚሁ ጋር የተያያዙትን አስጨናቂ የቁጠባ ህጎች ለማንሳት ቃል በመግባቱ ነው ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሲፕራስ ቃላቸውን ለመፈፀም በአበዳሪዎች ላይ ግትር አቋም ይይዙ ይሆናል የሚል ስጋት አሳድሯል ።በግሪክ የቁጠባ እርምጃዎችን አስቀራለሁ የሚለው ሲሪዛ ወደፊት የአውሮፓ ህብረት ትልቅ ፈተና ሆኖ መቀጠሉ እንደማይቀር ይታመናል ። አዲሱ የግሪክ መንግሥት አራምዳለሁ የሚለው አቋም ግሪክን ጨምሮ 19 አባላት ባሉት የዩሮ ተጠቃሚ ሃገራት ማህበር ላይ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ የሚያሰጋው መዘዝም ከወዲሁ ማሳሰቡ አልቀረም ። ከሲፕራስ በኩል ለሚሰነዘረው የድርድር ጥያቄና የህጎች ስረዛ ዛቻ ከአበዳሪዎች በኩል የማስጠንቀቂያ መልሶች እየተሰጡ ነው ። የዓለም ባንክ ግሪክ የዩሮ ቀጣና ህጎችን ማክበር እንዳለባት ጉዳይዋም ከሌሎች የተለየ ትኩረት ሊሰጠው የሚችል አለመሆኑን አስጠንቅቋል።ለግሪክ ብዙ ገንዘብ ካበደሩት አንዷ የሆነችው ጀርመን በበኩሏ ሃገሪቱ ከዚህ ቀደም የገባቻቸውን ግዴታዎች ተግባራዊ እንድታደርግ አሳስባለች ። አንዳንድ የጀርመን ፖለቲከኞች ከዚያም አልፈው ግሪካውያን የፈለጉትን የመምርጥ መብታቸው የተጠበቀ ነው ።የግሪኮችን እዳ ለመሸፈን ለግሪክ የሚሰጡትን ገንዘብ የማቆም መብትም አላቸው ሲሉ ለማስፈራራት እየሞከሩ ነው ።የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ግሪክ ከአንድ ወር በኋላ ለሚጠብቃት ድርድር ራሷን እንድታዘጋጅ ጠይቋል። የህብረቱ የኤኮኖሚ ጉዳዮች ባለሥልጣን ግዩንተር ኦቴንገር በግሪክ አዲስ መንግሥት በመቋቋሙ ምክንያት ህብረቱ አቋሙን አይለውጥም ብለዋል ።

«ከግሪካውያን ጋር ከሚመጣው መጋቢት ጀምሮ እርዳታና የእዳ ክፍያን በተመለከተ አዲስ ውል ማድረግ ስለሚቻልበት ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጅት ተደርጓል ። ለአዲሱ መንግሥት ካለፈው የተለየ እድል አይሰጠውም ።ይህም ማለት የመራጩን የግሪክን ህዝብ ውሳኔ እንቀበላለን ከነርሱም ደግሞ ቅድመ ግዴታውን ያዘጋጀነውን አማራጭ እንዲቀበሉ እንጠብቃለን ።ይህ የነርሱ ውሳኔ ነው የሚሆነው ።ይህ አንዳች ጉዳት የለውም ። ይሄ ጉዳት የለውም የተሻለ ጠቀሜታም ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም ።ከምርጫ በፊትም ሆነ አሁን ከምርጫ በኋላ ያለውን የግሪክን መንግሥት በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የምንቀርበው ።»

አንዳንድ የሲሪዛ ፓርቲ የፓርላማ አባላት የግሪክን የብድርና የእዳ ማስተካከያን የሚከታተሉት የአውሮፓ ህብረት የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ተቀብለን አናነጋግርም ሲሉም ተሰምተዋል ። የፓርላማ አባላቱ አበዳሪዎቹን ማየት አንፈልግም ማለታቸው ግን ትርጉም የሚሰጥ አለመሆኑን ነው መቀመጫቸውን አቴንስ ግሪክ ያደረጉ ጀርመናዊ የኤኮኖሚ ባለሞያ ያስረዱት ።

«ከሶስቱ አበዳሪዎች ጋር አልደራደርም የምትል ከሆነ ከማን ጋር ነው የምትደራደረው ? ከሌላኛው ወገን ለንግግር የሚቀመጠው ማነው ? ማንስ ነው መፍትሄ ወደ ሚያስገኝ ድርድር የመግባት ሥልጣን ያለው »

የጀርመን ፖለቲከኞች በግሪክ አሁን ጊዜ ለመግዛት የተጀመረ የሚመስለው አካሄድ የሚያዛልቅ አለመሆኑን ነው የሚናገሩት ። ከጀርመን የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ባለሥልጣናት አንዷ ዚሞነ ፔተር በተለይ ግሪክ ስለ ተሰጣት ብድር አመላለስ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል ።

«ስለ እዳው መጠንና አከፋፈል መነጋገር ያሻል ።ግሪክ እንዲሁ ዝም ብላ የተቆለለባትን እዳ ሳትከፈል ሁኔታውን እያጓተተች ልትቀጥል አትችልም በዚህ ጉዳይ ላይ በሚቀጥሉት ቀናትና ሳምንታት ንግግር መከፈቱ የማይቀር ነው ።»

በግሪክ የተገኘው የሲሪዛ ድል በአውሮፓ ላሉ ሌሎች የቁጠባ እርምጃዎችን ለሚቃወሙ ኃይሎች አበረታች እንደሚሆን ይገመታል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሲፕራስም የእሁድ ድል የግሪኮች ብቻ አይድለም ነው ያሉት

«የኛ ድል የጋራ አውሮፓዊ መፃኤ እድላችንን በማጥፋት ላይ የነበረውን የቁጠባ እርምጃ ለሚዋጉ የአውሮፓ ህዝቦችም ድል ነው ።»

ሲፕራስ በምርጫ ዘመቻ ወቅት የሥራ አጡ ቁጥር ከ25 በመቶ በላይ እንዲሆን ያደረግውን ና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለድህነት የዳረገውን ሰፊውን የበጀት ቅነሳና ከፍተኛ የገቢ ቀረጥ ለማንሳት ቃል ገብተዋል ። ያም ሆኖ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱ የተሸከመችውን እዳ መክፈል ይቻላት ዘንድ 7 ቢሊዮን ዩሮ የምታገኝበትን ሰፊ ርዳታ በሚመለከት የሆነ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይኖርባቸው አይቀርም ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic