የግል ንፅህና እና የዓይን ሕመም | ጤና እና አካባቢ | DW | 25.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የግል ንፅህና እና የዓይን ሕመም

የዓይን ማዝ በሽታን በቀላሉ መከላከል ሲቻል ዛሬም ለብዙዎ የዐይን ብርሃን ማጣት ምክንያት እየሆነ ነዉ። የድህነት በሽታ በመባል የሚገለፀዉ ይህ የዐይን ህመም በዓለም 21 ሚሊዮን ሰዎችን እንደጎዳ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ዉስጥም ይህ የዓይን ሕመም በተለያዩ ክልሎች ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ እየተገለጸ ነዉ።

Gentherapie am Auge Moorfield UCL London Großbrittanien

በሞቃትና ርጥበት ያዘለ የአየር ሁኔታ ባለበት አካባቢ የሚገኙ የተዘነጉ በሽታዎችን ለማጥፋት የሚንቀሳቀሰዉ ሳይትሴቨርስ፤ ዋና ዳይሬክተር ሲሞን ቡሽ ዓይነ ማዝን የድህነት በሽታ ይሉታል። ለዚህም መነሻ የሆናቸዉ በሽታዉ በተለይ የንፅህና ጉድለት ባለበትና የዉሃ አቅርቦት በተጓደለበት ቦታ ሁሉ ተንሰራፍቶ መገኘቱ ነዉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዓይን ህክምና ትምህርት ክፍል የሚያገለግሉት በብሩህ ቪቭን የዓይን ህክምና ማዕከል የሚሠሩት ዶክተር ትልቅሰዉ ተሾመም ስለበሽታዉ የሰጡት ማብራሪያ ከዚሁ ጋ ይመሳሰላል።

የዓለም የጤና ድርጅት በዓለም ዙሪያ 21 ሚሊዮን ሰዎች በዓይነማዝ እንደተጎዱ ያመለክታል። በመረጃዉ መሠረት በዚሁ ምክንያት 1,2 ሚሊዮን ሕዝብ ለዓይነስዉርነት ሲዳረግ፤ 2,2 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ የዓይናቸዉ የማየት አቅም እክል ገጥሞታል።

An Flussblindheit erkrankter Afrikaner

በሽታዉ በዓይን በማይታዩ ጥቃቅን ሕዋሳት እንደሚመጣ ያመለከቱት የሕክምና ባለሙያ በዝንብ አማካኝነት እና በቀጥታ ንክኪ በሽታዉ ከሰዉ ወደሰዉ እንደሚተላለፍ ጠቁመዋል። የግል እና የአካባቢ ንፅህና መጓደል ለበሽታዉ መስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች መሆናቸዉን በማመልከትም በተለይ እናቶች በሕፃናት ልጆቻቸዉ አማካኝነት ለበሽታዉ የተጋለጡ እንደሆኑ ነዉ የሚገልፁት። ያም ሆኖ ግን ልጆች ባሉበት ደረጃ የዓይን ብርሃን እስከማጣት ላያደርሳቸዉ ይችላል። ፈጥነዉ ሕክምና ካላገኙ ለአዋቂዎች ግን አደገኛ ነዉ።

የዓይነማዝ ማለትም ትራኮማ በንፅህና ጉድለት የሚመጣና የሚስፋፋ እንደመሆኑ በቀላሉ የግልና የአካቢን ንፅህና በመጠበቅ መከላከልም ይቻላል ነዉ የሚሉት ዶክተር ትልቅሰዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ በየአካባቢዉ በሽታዉ የሚገኝበትን የመስፋፋት ደረጃ የሚያሳይ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል። ያ ሲጠናቀቅም በየቦታዉ ያለዉ የተጎጂዎች ብዛት ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል። በዓለም ዓቀፍ ደረጃም እንዲሁ የችግሩን ስፋት ለማወቅ በ30 ሃገራት እስከጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም ድረስ ወደአራት ሚሊዮን ሰዎችን የመመርመር ተግባር ይከናወናል። እግረ መንገዱን በየቤቱ በሚሰጠዉ ቀላል የሕክምና ርዳታም በጣይ ሰባት ዓመታት ዉስጥ በሽታዉን ለማጥፋት እቅድ አለ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic