የግል መዋዕለ-ነዋይ በአፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 28.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የግል መዋዕለ-ነዋይ በአፍሪቃ

የአፍሪቃን ልማት ወደፊት ለማራመድ ወደ ክፍል-ዓለሚቱ የግል መዋዕለ-ነዋይን መሳብ መቻሉ አንዱ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ በየጊዜው ሲነገር ቆይቷል።

default

የአፍሪቃን ልማት ወደፊት ለማራመድ ወደ ክፍል-ዓለሚቱ የግል መዋዕለ-ነዋይን መሳብ መቻሉ አንዱ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ በየጊዜው ሲነገር ቆይቷል። እርግጥ አፍሪቃ በተለይ በጦርነትና በአስተዳደር ጉድለት መጠመድ የተነሣ ለረጅም ጊዜ የግል ባለሃብቶችን ብዙም የምትስብ አልነበረችም። አሁን ግን ምንም እንኳ በርከት ባሉት ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት በጎ አስተዳደር ባይሰፍንም የግል ባለሃብቶች ዓይን ይበልጥ በአፍሪቃ ላይ እያረፈ ሲሄድ ነው የሚታየው።

የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች በአፍሪቃ ላይ ያላቸው ዕይታ በጣሙን እየተቀየረ በመሄድ ላይ ነው። ዛሬ ከሣሃራ በስተደቡብ መዋዕለ-ነዋይ የሚያደርጉት የግል ባለሃብቶች ቁጥር በሰፊው መጨመሩ ጎልቶ የሚታይ ነገር ሆኗል። ለመሆኑ ምንድነው ለዚህ ምክንያቱ? ፍላጎቱን ምን አመጣው? Africa Assets በመባል የሚታወቀው ሂደቱን በቅርብ የሚከታተል የፊናንስ ምርምር ቡድን ሃላፊ ራሄል ኪለር እንዲህ ይላሉ።

«ፍላጎቱ ከክፍል-ዓለሚቱ የፖለቲካ መረጋጋትና ከብዙዎቹ ሃገራት የኤኮኖሚ ዕድገት መጨመር የመነጨ ይመስለኛል። ቀድሞ ምናልባት በደቡብ አፍሪቃ ማዕድኖች ላይ ነበር የሚተኮረው። ከዚሁ ሌላ የግል ባለሃብቶች አሁን ይበልጥ ወደ አፍሪቃ ለማዘንበላቸው የምዕራቡ ዓለም ገበዮች መቀዝቀዝም አንዱ ምክንያት ነው። ለግል መዋዕለ-ነዋይ ብዙ ዕድል ተከፍቷል። እናም ባለሃብቶቹ በአፍሪቃ ይህንኑ ዕድል ለመጠቀም እየሞከሩ ነው። ገንዘባቸውን በስራ ላይ ለማዋል በቂ ዕርጋታ መኖሩ ይሰማቸዋል»

በቅርቡ በጉዳዩ የወጣ መግለጫ እንደሚያመለክተው የግል መዋዕለ ነዋይ ፍሰት ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ 2011 ዓመተ-ምሕረት በአፍሪቃ በስፊው ሲጨምር በተለይም በምሥራቅ አፍሪቃ ዕርምጃው ከሁሉም የበለጠ ነበር። የምዕራቡ ዓለም ገበዮች ዕድገት በኤኮኖሚ ችግር የተነሣ ጋብ ሲል ይሄው ደግሞ አማራጭ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ክፍለ-ዓለሚቱን ማራኪ ማድረጉ አልቀረም። ምሥራቃዊው አፍሪቃ ባለፈው ዓመት ከተፈረሙት 3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ 66 የግል መዋዕለ-ነዋይ ኮንትራት ወይም ውሎች 30 በመቶውን ድርሻ ለመያዝ ችሎ ነበር።

Armut in Simbabwe

ይህ ከደቡባዊው አፍሪቃ 33 በመቶ ድርሻ የተጠጋና ከምዕራባዊው አፍሪቃ እንዲያውም ጥቂት መብለጥ የቻለው ድርሻ ለምሥራቁ ክፍል ትልቅ ዕርምጃ ሆኖ የሚታይ ነው። ምናልባትም ለብዙዎች አስደናቂም ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል እርግጥ ራሄል ኪለር እንደሚያመለክቱት ዕድገቱ መላውን ክፍል-ዓለም የሚጠቀልል ነው።

«ይሄ ዕድገት መላውን ክፍለ-ዓለም የሚመለከት ነው። የምሥራቅ አፍሪቃ ብቻ አይደለም»

ሆኖም ከሌሎች የክፍል-ዓለሚቱ አካባቢዎች ሲነጻጸር የምሥራቅ አፍሪቃው ዕርምጃ በጣም ፈጣን ሆኖ መገኘቱ አካባቢው በፖለቲካ ብዙም ያልተረጋጋ መሆኑ ሲታሰብ እንዴት ማሰኘቱ አይቀርም። ግን ለመሆኑ እነዚህ መዋዕለ-ነዋይ አድራጊዎች የቶቹ ናቸው።

«የምናወራው ስለ ትልቅ ገንዘብ ብቻ አይደለም። እናም በምሥራቅ አፍሪቃ የተለያዩ የግል ባለሃብቶችን ነው የምናገኘው። ከአውሮፓና ከአሜሪካም ጭምር። እሢያን መሠረቱ ያደረገ ያለ አይመመስለኝም። መካከለኛ ምሥራቅን ካየን ከገብጽ የሚመነጭ መዋዕለ-ነዋይ አለ። ከእሢያ ወደፊት ብዙ የግል መዋይለ-ነዋይ እንጠብቃለን። ለጊዜው ግን በአፍሪቃ ላይ ያተኮረው መዋዕለ-ነዋይ አሁንም ከአውሮፓና ከአሜሪካ ነው የሚመነጨው»

ለማንኛውም በምሥራቃዊው አፍሪቃ ባለፈው ዓመት ትልቁ የግል መዋዕለ-ነዋይ የቀረበው ከግብጽ ነበር። ይሄው ሲታዴል- ካፒታል የተሰኘ ድርጅት የኬንያን ወደብ ሞምባሣን ከኡጋንዳ ዋና ከተማ ከካምፓላ ሊያገናኝ ለታቀደው ለኬንያ ሪፍት-ቫሊይ የምድር ባቡር ሃዲድ ስራ 287 ሚሊዮን ዶላር አቅርቧል። አንድ የኬንያ የኢንተርኔት ኩባንያና የታንዛኒያ የፍጆት ዕቃ አምራችም እንዲሁ ከመዋዕለ-ነዋይ አድራጊዎቹ መካከል ይገኛሉ።

በሌላ በኩልም መዋዕለ-ነዋይ አድራጊዎች በኢትዮጳያ፣ በደቡብ ሱዳንና በዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ አዳዲስ ገበየችን በመክፈት ላይ ናቸው። አፍሪቃ-አሴትስ የተሰኘው የፊናንስ ምርምር ቡድን ሃላፊ ራሄል ኪለር እንደሚጠቁሙት እነዚህ ገበዮች ከፍተኛ ትኩረት ነው የተሰጣቸው።

«እነዚህ ዛሬ ግንባር-ቀደም ገበዮች ናቸው። እስካሁን ብዙ መዋዕለ-ነዋይ የታየባቸው አልነበሩም። የፖለቲካው ዕርጋታ ጉዳይ በደቡብ ሱዳን፣ በዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎና በኢትዮጵያም በሆን አጠያያቂ ነው። እርግጥ ኢትዮጵያ በተወሰነ ደረጃ የፖለቲካ መረጋጋት አለባት ለማለት ይቻላል። ለውጭ መዋይለ-ነዋይ ክፍት እየሆነችም ነው። ባለፉት ጊዜያት ኤኮኖሚው በመንግሥት ቁጥጥር ስር ሲራመድ ቆይቷል። ስለዚህም ለመዋዕለ-ነዋይ ቀላል ሁኔታ አልነበረም»

Flash-Galerie Äthiopien Land Grab

በኢትዮጵያ የውጭ ባለሃብቶች በተለይም በአገሪቱ ለም የእርሻ መሬቶች ላይ ዓይናቸውን ካሳረፉ ሰንበት ብለዋል። የተለያዩ መንግሥታዊና የግል ባለሃብቶች በረጅም ጊዜ ወሎች እጅግ ሰፊ የሆነ መሬት ሲኮናተሩ ጉዳዩ አከራካሪ መሆኑም አልቀረም። ለምሳሌ ብዙዎች ገበሬዎች ከአካባቢያቸው ሲፈናቀሉ ድርጊቱ ቁጣን እየቀሰቀሰ መሆኑም የሚሰማ ጉዳይ ነው። ከዚህ አንጻር ለባለሃብቶቹ ከረጅም ጊዜ አንጻር ችግር መፈጠሩ ምናልባት የማይቀር ይሆናል።

«የግል ባለሃብቶቹ አደጋውን በሚገባ ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ። የአገሩ ሁኔታ ለመዋዕለ-ነዋይ ይበጅ-አይበጅ ያጤኑ ይመስለኛል። በአፍሪቃ ለምሳሌ በንግድ እርሻ ላይ በሚጠቅም ሁኔታ መዋዕለ-ነዋይ ለማድረግ መንገድ አለ ብዬ ነው የማምነው። እርግጥ የመዋዕለ-ነዋይ አደራረጉን ሁኔታና በምርቱም ተጠቃሚ መሆኑን ማረጋገጥን ይጠይቃል። መዋዕለ-ነዋይ ማድረግ የሚፈልጉ አሉ። እነዚህም አሁን አፍሪቃ ውስጥ ውጤት እያዩ ነው»

ውጤቱ እያደር በውል የሚታይ ሲሆን በሌላ በኩል አፍሪቃ የግል መዋዕለ-ነዋይን በመሳብ እንደምትቀጥል በጉዳዩ ላይ ያተኮሩ ተመራማሪዎች ያምናሉ።

«የግል መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት እየጠነከረ የሚሄድ ይመስለኛል። ብዙዎቹ የአካባቢው አዳጊ ገበዮች ምሥራቅ አፍሪቃንም ጨምሮ በተለይ በጋና፣ በናይጄሪያ፤ እነዚህ ሁሉ አዳጊ ገበዮች ወደፊት መራመዳቸውን የሚቀጥሉ ናቸው። በተለያዩ ዘርፎች ከዓለም ዙሪያ የሚመነጨው መዋዕለ-ነዋይ እየጨመረ መሄዱ ነው የሚጠበቀው። ይህ በብዙዎቹ አዳጊ ገበዮች የሚታይ ነገር ነው»

ያም ሆነ ይህ የግል መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች ገንዘባቸውን በስራ ላይ ለማዋል ዛሬ አፍሪቃ ተስማሚዋ ገበያ አይደለችም ከሚል ከቀድሞ አመለካከታቸው ስንብት ማድረጋቸው ግልጽ ነው።

የምዕራቡ ዓለም ገበዮች መዳከም ከተነሣ የጀርመን መለስተኛ ኩባንያዎችም ሁኔታው ቀለል ወዳለባት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ብቻ ሣይሆን ከሣሃራ በስተደቡብ ጋናን፣ ቦትሱዋናን ወይም ታንዛኒያን ወደመሳሰሉት ሃገራትም መሻገር ይዘዋል። የአውሮፓ ዕድገት በትንሽ ዕርምጃ ወደፊት ሲነፏቀቅ የአፍሪቃ ሃገራት በተፋጠነ ዕድገት ላይ መሆናቸው ነው የሚነገረው። በዓለም ባንክ ግምት መሠረት በአፍሪቃ ክፍል-ዓለም በዚህ በያዝነው ዓመት ከ 5 በመቶ በላይ አማካይ ዕድገት ነው የሚጠበቀው። ታዲያ ለጀርመን ኩባንያዎችም ክፍለ-ዓለሚቱ አንድ ቀን ሰፊ ሸቀጥ ማራገፊያ ጠቃሚ ገበያ መሆኗ ሳይታያቸው አልቀረም።

እርግጥ እስከዚያው መንገዱ ውጣ-ውረድ የበዛው ነው። ሙስና፣ አስተማማኝ ያልሆነ የፍርድ ስርዓትና ወንጀል ብዙዎቹ የኢንዱስትሪው ዓለም ኩባንያዎች በአፍሪቃ በተግባር እንዳይሰማሩ ስጋት ላይ ይጥሏቸዋል። ይሁን እንጂ የክፍለ-ዓለሚቱ የተፈጥሮ ጸጋ ደግሞ የሚማርካቸው ነው። ብዙዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት በርካታ ጥሬ ሃብት ሲኖረቸው ይህም በረጅም ጊዜ ለውጩ ኩባንያዎች ብዙ ጠቀሜታ አለው።

ለምሳሌ ያህል የአፍሪቃን መዋቅራዊ ይዞታ ብንመለከት 80 በመቶው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን ለማግኘት አልታደለም። ከአርባ በመቶ የሚበልጠው ንጹህ የመጠጥ ውሃ አያገኝም፤ መገናኛ መንገዶች በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት፤ ወይም ጨርሰው የሉም። ይህን ጉድለት ለማስወገድ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ገንዘብ ነው የሚጎለው። እርግጥ ለአውሮፓውያኑ ኩባንያዎች በመንግሥት ከሚደጎሙት ከቻይና ኩባንያዎች መፎካከሩ ቀላል ነገር አይሆንም። ግን ወደፊት በአፍሪቃ ገበያ ተጠቃሚ ለመሆን ከተፈለገ ምርጫው በጥራት ለማሸነፍ መጣር ይሆናል።

አፍሪቃ እስካሁን ትልቅ የፍጆት ገበያ ለመሆን አለበቃችም። ይሁንና መካከለኛው የሕብረተሰብ መደብ በጣሙን እያደገ መሆኑን ነው Trade and Invest የተሰኘው የጀርመን መንግሥታዊ የውጭ ኤኮኖሚ ተግባር አራማጅ ድርጅት የሚያመለክተው። በድርጅቱ አባባል በዓመት ከሶሥት ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ያለው ቤተሰብ በወቅቱ 60 ሚሊዮን ገደማ ሲጠጋ አሃዙ በሶሥት ዓመት ጊዜ ውስጥ አንድ መቶ ሚሊዮን እንደሚደርስም ይጠበቃል።

ታዲያ አውሮፓውያን ይህን ሂደት እንዲደግፉም ነው የሚመከረው። ምክንያቱም የአንድ የጀርመን ኢንጂነር ቢሮ ባልደረባ የሆኑት የሤኔጋል ተወላጅ አባባካር ሤክ እንደሚሉት የአፍሪቃውያን የመግዛት አቅም ካደገ በአውሮፓ ቀጥተኛ ተጎራባች ክፍል-ዓለም ግዙፍና አዳጊ ገበያ ተፈጠረ ማለት ነው።

«አውሮፓውያን የአፍሪቃ መካከለኛ የሕብረተሰብ መደብ ዕድገት ወደፊት እንዲራመድ ማድረግ አለባቸው። አፍሪቃውያኑ ውድ የአውሮፓ፤ በተለይም የጀርመን ምርቶችን መግዛት እንዲችሉ!ምክንያቱም ጀርመን የመግዛት አቅም የሰመረበት ገበያ ነው የሚያስፈልጋት»

እንግዲህ ከሣሃራ በስተደቡብ አፍሪቃ በተግባር ለመሰማራት የተነሳሱት የጀርመን መለስተኛ ኩባንያዎችም ይህን በሚገባ ያጤኑት ነው የሚመስለው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 28.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14T54
 • ቀን 28.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14T54