የጋዜጦች አስተያየት | የጋዜጦች አምድ | DW | 16.03.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የጋዜጦች አስተያየት

የጀርመናውያኑ ዕለታዊ ዚውድዶይቸ ሳይቱንግ የዚምባብዌ መንግሥት በተቃውሞው ወገን አንፃር ስለወሰደው የኃይል ርምጃ፡ ሌላው ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ክርስትያን ሳይንስ ሞኒተር ዩኤስኤ ሊቢያ ሥራ ፈላጊ አፍሪቃውያን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚያደርጉትን ሙከራ ለማስቆም ስለጀመረችው ጥረት የፃፉዋቸው አስተያየት፡

ዚውድዶይቸ ሳይቱንግ ዚምባብዌ ውስጥ ባለፈው እሁድ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ የፀጥታ ኃይላት ብርቱ የመደብደብ ጥቃት የደረሰባቸው የዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንቅስቃሴ የሚባለው የዋነኛው የተቃውሞ ቡድን መሪ ሞርገን ስቫንጊራይ፡ እንደተፈራው ክፉኛ አለመጎዳታቸው፡ በአሁኑ ጊዜ ከሀገሪቱ የተሰማው ብቸኛው ደህና ዜና መሆኑን የጀርመናውያኑ ዕለታዊ ዚውድዶይቸ ሳይቱንግ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባው አስተያየቱን ሰጥቶዋል። ስቫንጊራይ ፕሬዚደንት ሙጋቤ በሚመሩት ኢፍትሓዊ መንግሥት አንፃር አሁንም ትግላቸውን መቀጠላቸው፡ ባለፈው እሁድ በመዲናይቱ ሀራሬ በተካሄደውዓይነት የተቃውሞ ሠልፍ መሳተፋቸው ራሱ አድናቆትን ሊያተርፍላቸው ይገባል። ምክንያቱም የቀድሞው የሙያ ማኅበር ኃላፊና ቀንደኛው የፕሬዚደንት ሙጋቤ ተቃዋሚው ስቫንጊራይ የዴሞክራሲያው የለውጥ እንቅስቃሴ እአአ በ 1999 ዓም ከተቋቋመ ወዲህ በየዕለቱ ለሕይወታቸው እንደሠጉ ይገኛሉና። ብዙ ጊዜ ተደብድበዋል። የቅርብ ረዳቶቻቸው ተገድለዋል። እርሳቸውም በሀገር ክህደት ክስ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። አፍሪቃ ውስጥ እንደ ስቫንጊራይ ይህን ዓይነት ፈተና ታቁመው፡ ግዞት ሳይገቡ የተቃውሞ ፖለቲካ ለማካሄድ ብለው ሀገራቸው የሚቆዩ ተቃዋሚዎች የሉም። ስቫንጊራይ በ2000 ዓም በሀገሪቱ በተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ወቅት ፓርቲያቸው የግማሹን ያህል የመራጭ ድምፅ ባገኘበት ጊዜ ነበር ትልቅ ትውቂያ ያተረፉት። ፕሬዚደንት ሙጋቤ የያኔውን ምርጫ ውጤት ለራሳቸው እንደሚመች አድርገው ባይለዋውጡትና ተደባዳቢዎቹ የፀጥታ ኃይሉ አባላትም የሀገሪቱን ሕዝብ ባያስፈራሩ ኖሮ፡ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንቅስቃሴ ጠንካራው ፓርቲ በሆነ ነበር። ይሁን እንጂ፡ ሙጋቤ የጭቆና አገዛዛቸውን በቀጠሉበት በዚሁ ጊዜ ከተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍል የተውጣጣው የተቃዋሚው ፓርቲ የሙጋቤን ሥልጣን በማብቃቱ ዘዴ ጥያቄ የተነሳ ብርቱ ክፍፍል ገጥሞታል። ስቫንጊራይ ለሰላማዊው ለውጥ ነው የቆሙት፤ ይሁንና፡ ይኸው አቋማቸው እንደ ድክመትና ቆራጥነት እንደተጓደላቸው ነው የተቆጠረባቸው። የሙጋቤ አገዛዝ እንደሚያበቃ አዘውትሮ ይተነበያል። ወቅታዊው የዚምባብዌ ሁኔታ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛል። የሥራ አጡ ቁጥርም በጣም ከፍ ብሎዋል። ይህም በተቃዋሚው ወገን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በራሱ በገዢው ፓርቲ አባላትም ዘንድ ቁጣ ቀስቅሶዋል። የተቃውሞው ወገንና ቅር የተሰኙት የገዢው ፓርቲ አባላት ቢተባበሩ፡ ይላል ዚውድዶይቸ ሳይቱንግ እንደሚለው፡ የሙጋቤ መንግሥት ፍፃሜ ገሀድ ሊሆን ይችል ይሆናል። ይህ በዚህም የተነሳ ሁኔታው ያሰጋቸው ፕሬዚደንት ሙጋቤ በስቫንጊራይና በረዳቶቻቸው አንፃር ጠንካራ የኃይል ርምጃ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል በሚል ዚውድዶይቸ ሳይቱንግ አስተያየቱን ደምድሞዋል። ዘ ክርስትያን ሳይንስ ሞኒተር ዩኤስኤ ዘ ክርስትያን ሳይንስ ሞኒተር ዩኤስኤ የተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ እንደዘገበው፡ ያረፈባት ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሀገር ሊቢያ ከአውሮጳ ኅብረት ባረፈባት ግፊት የተነሳ በሕገ ወጡ መንገድ ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ አፍሪቃውያንን ሙከራ ማከላከል ጀመረች። ሊብያ ምንም እንኳን ብዙ አፍሪቃውያን ድንበርዋን እየተሻገሩ በሜድትሬንየን ባህር በኩል እያደረጉ ወደ አውሮጳ የሚገቡበትን ድርጊት ለብዙ አሠርተ ዓመታት እንዳላየ ስታልፍ መቆየትዋን ጋዜጣው አስታውቋል። ይሁን እንጂ ለብዙ ዓመታት ዓለም አቀፍ የመገለል ዕጣ ደርሶባትና ማዕቀብ ተጥሎባት የነበረችው አሁን ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ የተመለሰችው በኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ አገዛዝ ሥር የምትገኘዋ ሊብያ አውሮጳውያኑ ላቀረቡላት ጥያቄ አዎንታዊ መልስ መስጠት ጀምራለች። ሊብያ ውስጥ ከአንድ ነጥብ አምስት እስከ ሁለት ሚልዮን የሚገመቱ ባዕዳን ሠራተኞች ይኖራሉ። ከነዚህም መካከል ግማሾቹ በሕገ ወጥ መንገድ ነው በዚያ የሚኖሩት። ከግብፅ፡ ከቱኒዝያ፡ ከኤርትራ፡ ከሱዳንና ከጋና ሊብያ የገቡት ባዕዳን ሠራተኞች ቁጥር ከፍ እያለ የሄደበትን ሁኔታ ለመቆጣጠር ስትል ከትቂት ጊዜ በፊት አንድ ሕግ አውጥታለች። ይኸው ሕግ መውጣቱን አውሮጳውያኑ በደስታ ቢቀበሉትም፡ ሊብያ ከሰሀራ በስተደቡብ በሚገኙት አፍሪቃውያት ሀገሮች ዜጎች አኳያ የምትከተለው አሠራርዋ አንፃር ካሁን ቀደም ይሰማ የነበረውን ወቀሳ እንደገና ሊቀሰቅሰው እንደሚችል ዘ ክርስትያን ሳይንስ ሞኒተር ዩኤስኤ በማመልከት ሀተታውን አብቅቶዋል።

ተዛማጅ ዘገባዎች