የጋዜጦች አስተያየት | የጋዜጦች አምድ | DW | 06.01.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የጋዜጦች አስተያየት

የኬንያ ምርጫ ሰሞኑን በዓለም ጋዜጦች ዘንድ ዓቢይ ትኩረት ተሰጥቶት የሰነበተው አፍሪቃ-ነክ ጉዳይ ነበር።

የጀርመኑ ዕለታዊ ጋዜጣ “Süddeutsche Zeitung” “የድሆች ዓመጽ” በሚል ርዕስ በዓምዱ ላይ ባሰፈረው ሃተታ የኬንያ ምርጫ የቀሰቀሰው ዓመጽ መንስዔ ከሌሎች አፍሪቃ አገሮች ያልተለየ መሆኑን አመልክቷል። ጋዜጣው ሲያትት “ሌላው ቀርቶ ኬንያ ውስጥ ለብዙ አሠርተ-ዓመታት የኖሩ ሰዎች እንኳ ይህን መሰሉን ዓመጽ አይተው አያውቁም። በናይሮቢ ግዙፍ የድሆች መኖሪያ ቀበሌዎች፣ በከተማይቱ ማዕከልና ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ቀውስና ሥርዓተ-ዓልባነት ሰፍኗል። ሕጻናትና ነፍሰጡሮች ሳይቀሩ ቁጣው በገነፈለ መንጋ እየተሳደዱ በማጭድ ተመትተውና በቆመጥ ተደብድበው ተገድለዋል። ዓመጹን በመፍራት የሸሹ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገን ያደረጉት ቤተ-ክርስቲያን በእሣት እንዲጋይ ተደርጎ በሕይወት እንዳሉ መቃጠላችውም ሌላው ዘግናኝ ሃቅ ነው”

Süddeutsche ጋዜጣ ዓመጹ በዚህ መጠን ለመቀጣጠሉም ዋነኛ መንስዔውን ለማመላከት ሞክሯል። “የኬንያ ሁኔታ በተደለዘው የምርጫ ውጤት ሳቢያ በዚህ መጠን መጋየቱ የሚያሣየው እስካሁን አንጻራዊ ዕርጋታ ሰፍኖባት የቆየችው ምሥራቅ አፍሪቃዊቱም አገር ሌሎች የአፍሪቃ አገሮችን ለጥፋት በዳረገው ተመሳሳይ ችግር የተወጠረች መሆኗን ነው። ኬንያም ከ 1963 ነጻነት ወዲህ ሥልጣን ለማጋራት ፈቃደኛ ባልሆነና የብዙሃኑን የሕብረተሰብ ክፍል አብሮ የመወሰንና የአገሪቱ ሃብት ተካፋይ የመሆን መብትን በነፈገ ቡድን ስትገዛ ነው የኖረችው። ይህ ደግሞ ለሩዋንዳ፣ ለሶማሊያ፣ ለኮንጎ፣ ለናይጄሪያ፣ ለሱዳንና ለዚምባብዌ መቅሰፍትን ነው ያስከተለው። ስለዚህም ኬንያ ውስጥ በኪኩዩና በሉዎ ጎሣዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት የዚሁ ነጸብራቅ እንጂ ሌላ አይደለም።

ኪኩዩዎች በኬንያ ታላቁ ጎሣ ብቻ ሣይሆኑ የአገሪቱ መሥራች ጆሞ ኬንያታ ሣይቀር የመነጩባቸው በመሆኑ ሃያሉም ናችው። አገሪቱን ነጻነቷን ከተጎናጸፈችበት ጊዜ አንስቶ እነዚሁ መላውን ቁልፍ ሥልጣን ይቆጣጠራሉ። የረጅም ጊዜው ገዢ ዳኒዬል-አራፕ-ሞይ ምንም እንኳ የውሁድ ጎሣ ባልደረባ ቢሆኑም በሥልጣን ለመቆየት የወቅቱ ፕሬዚደንት ኪባኪ የመነጩበትን የኪኩዩ ጎሣ ድጋፍ ያለማቋረጥ መሻት ነበረባቸው። በራኢላ ኦዲንጋ የሚመሩት ሉዎዎች በአንጻሩ ከሥልጣን ተገለው ነው የኖሩት” ጋዜጣው ሃተታውን የደመደመው አንዴ የፕሬዚደንት ኬንያታ ተተኪ ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁት የሉዎ ጎሣ ባልደረባ ቶም እምቦያ በ 1969 ዓ.ም. በኪኩዩዎች መገደላቸውን መለስ ብሎ በማስታወስ ነው።

ሌላው የጀርመን ዕለታዊ ጋዜጣ “Frankfurter Allgemeine” ደግሞ “የጎሣ ልዩነት በኬንያ ከጥንት አንስቶ የፖለቲካ አለመረጋጋት ምንጭ ነበር ሲል እንደሚከተለው አትቷል። “የኬንያ ሕዝብ ከአርባ የጎሣ ቡድኖች የመነጨ ነው። ኪኩዩዎች 22 በመቶውን ድርሻ በመያዝ ታላቁ የጎሣ ቡድን ናችው። የኪባኪ የምርጫ ተቀናቃኝ የራኢላ ኦዲንጋ ሉዎ ጎሣ 13 በመቶ የሚጠጋ ሲሆን ሶሥተኛው የሕብረተሰብ ቡድን ነው። በሌላ በኩል 14 በመቶውን ድርሻ የሚይዘው የሉሂያ ጎሣ በታላቅነቱ ሁለተኛው ቢሆንም በውስጡ በቡድን የተሰነጣጠረ በመሆኑ የረባ የፖለቲካ ክብደት የለውም” “Frankfurter Allgemeine” ዘገባውን ያጠቃለለው እስካሁን የእርስበርስ ጦርነት አደጋ ለዘብ ብሎ መቆየቱ በርካቶቹ የአገሪቱ የጎሣ ቡድኖች በመካከላቸው የሚነሣ ውዝግብን ለራሳቸው በሚበጅ መንገድ ለመፍታት ጥንካሬው የሚጎላቸው መሆኑን በማመልከት ነው።

ይሄው ጋዜጣ ወደ ሱዳን ሻገር በማለት የስዕሎች መረጃ ስለጎደለውና የመገናኛ አውታሮች አጀብ ስለተለየው አስከፊ የዳርፉር ዓመጽም የሚከተለውን ትችት በዓምዱ ላይ አስፍሮ ነበር። “የጦርነት ስዕሎች አስደንጋጭ ድርጊቶችን መዝግበው ይይዛሉ። በዓለም ላይ ብቅ የሚል ማንኛውም ፎቶ የመከራና የችግሩን መጠን የሚገባውን ያህል የሚያስተላልፍ ባይሆን እንኳ! ሆኖም ሰዎች በነዚህ ስዕሎች አማካይነት ያዩትን ያስታውሣሉ። በቀጥታ ባይመለከታቸውም ከዓይናችው አይሰወርም። እያንዳንዱ ጦርነት የራሱ አስታዋሽ ስዕል አለው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነጻ በወጡ የማጎሪያ ካምፖች፣ የቪየትናም ጦርነት በናፓልም ቦምብ ተቃጥላ እየጮኸች በአደባባይ ትሮጥ በነበረችው ልጃገረድ በኪም ፑክ ምስል፣ በሩዋንዳው ዕልቂትና በባሕረ-ሰላጤው ጦርነት ፎቶዎች በሰዎች አዕምሮ ተቀርጸዋል። ነገር ግን እንደ ዳርፉር ባለው ቦታ ጦርነቱ እያለ ስዕሉ ሲጎልስ? Frankfurter Allgemeine ለሃተታው መነሻ ያደረገው ይህን ጥያቄ ነው።

ጋዜጣው በሀተታው በመቀጠል የዳርፉርን መከራ እንዲህ ሲል ያስታውሣል። “በሱዳኗ ምዕራባዊት ክፍለ-ሐገር ከአራት ዓመታት ወዲህ ግድያ ይፈጸማል፤ ሴቶች ክብራቸውን ይደፈራሉ። በዓመጹ ሁለት መቶ ሺህ ያህል ሰዎች እንደሞቱ ሲገመት አብዛኞቹ የተገደሉት ውዝግቡ በ 2003 እንደፈነዳ ነበር። ግድያው የተካሄደውና መካሄዱን የቀጠለው ደግሞ ከሕዝብ ዓይን ተከልሎ ነው። አስከፊውን ግፍ የሚያሣዩ ስዕሎች የሉም፤ ወደፊትም አይኖርም። ምክንያቱም ከመላ-ጎደል መላው ዳርፉሪዎች ከመንደሮቻችው ሸሽተው በስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ ነው የሚኖሩት። ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ደግሞ ውዝግቡ ያስከተለውን ስብርባሪ በመጠራረጉ ድርጊት ተወስኗል። በዚህ ወር የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪቃ ሕብረት ቅይጥ የሆነ የዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ሰላም አስከባሪ ሃይል በዳርፉር እንዲሰፍር ይደረጋል። ግን ምዕራቡ ዓለም ስለ ዳርፉር ሕዝብ ስቃይ የሚያውቀውን፤ ወደፊትም ሊያውቅ የሚችለውን ሁሉ ከስደተኞች አወራር እናውቀዋለን” ፍራንክፉርተር አልገማይነ ጋዜጣ!

ወደ ኬንያው ሁኔታ መለስ እንበልና፤ Financial Times ጋዜጣ “የእኩልነት እጦት የወለደው ቁጣ” በሚል ርዕስ በዓምዱ ባሰፈረው ትችት የኬንያውን የሥልጣን ውዝግብ በሩዋንዳው የጎሣ ፍጅት ደረጃ መመልከቱ ተገቢ እንዳልሆነ አመልክቷል። “ቤተ-ክርስቲያንን ተገን ያደረጉት ሴቶችና ሕጻናት በአስከፊ ሁኔታ መገደላቸው ድርጊቱን ከሩዋንዳው የ 1994 ዕልቂት ጋር የማነጻጸርን ሁኔታ አስከትሏል። አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዳሉት! ሚኒስትሩ ተቃዋሚውን ብርቱካናማ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ በጎሣ ፍጅት ነው የወነጀሉት። እርግጥ ኪኩዩዎች ከነጻነት ወዲህ አንስቶ የአገሪቱን ኤኮኖሚና ፖለቲካ የሚቆጣጠሩ በመሆናችው ጥቂትም ቢሆን የበቀል ስሜት የለም አይባልም። ታዲያ የፕሬዚደንት ምዋኢ ኪባኪን ድል ለማረጋገጥ የምርጫው ውጤት መጭበርበሩ አሁን ቁጣው አናት ላይ እንዲወጣ ነው ያደረገው። ግን በሩዋንዳ ብዙሃኑ ሁቱዎች ውሁዳኑን ቲትሢዎች እንደፈጁበት ዕልቂት አንዱ ጎሣ በሌላው ላይ ለበቀል የተነሣበት ሁኔታ አልነበረም” ጋዜጣው የኪኩዩዎችን ሁኔታ ከቀድሞው የቀሪይቱ ዩጎዝላቪያ መሪ ከስሎቦዳን ሚሎሼቪች ሰርቢያ ጋር ማነጻጸሩን ነው የመረጠው።

“ውስብስብ በሆነው በባልካን ሰርቦች ሌሎችን በማግለል የበላይነታቸውን ለማስረገጥ መሞከራቸው አብዛኛውን ሥልጣናቸውንና ግዛታቸውን እንዲያጡ ነው ያደረገው። ኪኩዩዎችም ኬንያ ውስጥ ተመሳሳይ አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። እርግጥ በ 22 ከመቶ ድርሻ ታላቁ ጎሣ ናቸው። ግን ከሌሎች ቡድኖች ሳይተባበሩ አገሪቱን ለመቆጣጠር ብቃቱ የላቸውም። አሁን እንዲያውም ውሁዳኑ ጎሣዎች ሊቋቋሟቸው ሃይላቸውን ሲያስተሳስሩ ይበልጥ እየተገለሉ ነው” ከአሜሪካ ቀደምት ጋዜጦች አንዱ ዋሺንግተን-ፖስት ደግሞ ከኬንያ ባሻገር አንዴ የአገሪቱ ብርቱ ጠላት በነበረችው በሊቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዋሺንግተን ጉብኝት ላይም አተኩሯል። “ጉብኝቱ ለአሠርተ-ዓመታት ጸንቶ የቆየውን የአሜሪካን ፖሊሲ የሚቀለብስ ነው። አሜሪካ በ 1986 ሊቢያ በምዕራብ በርሊን ላ-ቤል ዲስኮ ላይ ላደረሰችው ጥቃት አገሪቱን በቦምብ ከደበደበች በኋላ ፕሬዚደንት ሮናልድ ሬገን ሞአማር ጋዳፊን ወንጀላቸው የታወቀና የተመዘገበ ነው ሲሉ የዩናይትድ ስቴስት ጠላት ናቸው ነበር ያሏቸው።

ሬገን ብዙሃኑ ሊቢያውያን ጋዳፊ ለአገራቸው ባተረፉት መጥፎ ዝና እንደሚያፍሩ እርግጠኛ ነኝ ብለውም ነበር። ትናንት ግን ዋሺንግተን አሁንም በጋዳፊ የሚመራውን መንግሥት አወድሳለች። የአሜሪካ ብሄራዊ ጸጥታ ሸንጎ አፈ-ቀላጤ ጎርደን ጆንድሮይ ሊቢያ የጅምላ ጥፋት መሣሪያ መሥራቷን በማቆም ታሪካዊ ውሣኔ አድርጋለች፤ እና ግንኙነታችንን ለማሻሻል ተባብረን መሥራት እንፈልጋለን ብለዋል” እርግጥ በሰብዓዊ መብቶችና በሌሎች ጉዳዮች ቅሬታ መኖሩንም ሳይጠቅሱ አላለፉም። ችግሩ ጋዜጣው በሌላ እትሙ እንዳመለከተው ዋሺንግተን ለሊቢያው መንግሥት ባለሥልጣን የእንኳን መጡ ምንጣፍ ስትዘረጋ በጋዳፊ ተቃዋሚዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ በሯን መዝጋቷ ነው። ሰለቦቹ ተቀናቃኞች ሆነዋል”

ተዛማጅ ዘገባዎች