የጋዜጣ ነፃነትና የሚደቀንበት አደጋ | የጋዜጦች አምድ | DW | 26.10.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የጋዜጣ ነፃነትና የሚደቀንበት አደጋ

የጋዜጣ ነፃነት ከ፪፻ ዓመታት ከሚበልጥ ጊዜ በፊት ነበር ሰብዓዊ መብት መሆኑ የተረጋገጠለት--በዩኤስ-አሜሪካና በፈረንሳይ ሕግጋተ-መንግሥት። ግን፥ “ጋዜጠኞች ያለድንበር” የተሰኘው ድርጅት ጥናት አሁን ግልጽ አድርጎ እንደሚያመለክተው፥ ይኸው መብት እስከዛሬው ጊዜ ነው በብዙዎቹ ሀገራት ውስጥ በእግር የሚረገጠው። መብቱ የሚረገጥበትን አድራጎት በጥንካሬ ለመታገል የሚያስችል ፍቱን ዘዴ የለም፣ ግን፥ የዶይቸ ቬለ ራዲዮ ባልደረባ ፔተር ፊሊፕ እንደሚለው፥ የ

ዴሞክራታውያኑ መንግሥታት የዘወትር ግፊት ብዙ የሚረዳ ይሆናል፥

“እያንዳንዱ ሰው ሐሳቡን በቃል፣ በጽሑፍ እና በስእልም በነፃ ለመግለጽና ለማሰራጨት፣ በጠቅላላው ሊገኙ በሚችሉም የመረጃ ምንጮች አማካይነት ራሱን ለማሳወቅ መብት አለው፤ የጋዜጣ ነፃነትና መረጃን በራዲዮና በፊልም የማቅረብ ነፃነት ዋስትና ይሰጠዋል፤ ሳንሱር ክልክል ነው።” ይህን የሚለው፥ እ ጎ አ በግንቦት ፳፫ ፲፱፻፵፱ የታወጀው የጀርመን ሕገመንግሥት፣ አንቀጽ ፭ ነው። ዩኤስ-አሜሪካ ውስጥ የጋዜጣ ነፃነት ገና በ፲፯፻፺፩ ዓ.ም. ነበር በሕገመንግሥት ውስጥ የፀናው፤ ልክ እንደዚሁ በፈረንሳይም ነበር መብቱ ጽናት ያገኘው--ሆኖም ፈረንሳይ ውስጥ በኋላ ወደ አንድ መቶ ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ ብቻ ታግዶ ነበር የቆየው። ዴሞክራሲ በሠፈነባቸው በመላው የምዕራብ አውሮጳ ሀገሮች ውስጥ የጋዜጣ ነፃነት በአንዱ ወይም በሌላው መንገድ በሕገመንግሥት የተዘረዘረ ዋስትናን ነው ያገኘው።

ስለዚህም ነው፥ “ጋዜጠኞች ያለድንበር” የተሰኘው ድርጅት ስለ ጋዜጣ ነፃነት አሁን ባቀረበው በሦሥተኛው ዝርዝሩ ውስጥ እነዚሁ ምዕራባውያን መንግሥታት ጥሩውን ቦታ ይዘው የሚታዩት። በመብቱ ጥበቃ ረገድ እጅግ ምሥጉን ከተባሉት ፳ ሀገራት መካከል ፲፯ቱ በአውሮጳ ነው የሚገኙት። በዝርዝሩ ዘብጥ ላይ የተመዘገበችው ሰሜን ኮርያ ስትሆን፥ ከርሷ በፊት ኩባ፣ በርማ፣ ቱርክሜኒስታን፣ ኤርትራ፣ ቻይና እና ቬትናም ናቸው ዋና የጋዜጣ ነፃነት አማቂዎች ተብለው በተለይ የተጠቀሱት። ሌሎችም አሉ፣ ዝርዝሩ ረዥም ነው።

በብዙዎቹ ሀገሮች ውስጥ የጋዜጣ ነፃነት ብዙ ትርጓሜ የለውም። እነዚያው አማቂ ሀገሮች ዴሞክራሲ ስለሌላቸው፣ ፕሬስን እንደ አራተኛ ሕዝ’ባዊ ኃይል አያዩትም--ከሐጋጊው፣ ከሕግ ተርጓሚውና ከሕግ አስፈጻሚው አካል ጎን ማለት ነው። በአምባገነን መንግሥታት ዘንድ በእነዚህ ሦሥት የሥርዓተ-መንግሥት አካላት መካከል ልዩነት አይደረግም፤ ሁሉም በአንድ ቅንጣት እጅ ነው የሚያዙት። ነፃ ጋዜጣ፣ ነፃ ሐሳብ ቦታ የለውም።

ሥልጣኑን ሁሉ በራሱ እጅ አካብቶና ሞጭጮ የሚይዘው አምባገነኑ መንግሥት የጋዜጣ ነፃነት ያይን ጉድፍ ስለሚሆንበት ሊያምቀው ነው የሚቻኮለው። በቂ የመንግሥት ሥልጣን በሌለባቸው ሥርዓትአልባ ሀገሮችም ውስጥ ነፃ ጋዜጣ ሊስፋፋና ዕድገት ሊያገኝ አይችልም። በዚህ ረገድ አፍጋኒስታን ዓይነተኛ ምሳሌ ነበረች፣ አሁንም ነች። አሁን ኢራቅም ናት ተጨማሪ ምሳሌ በመሆን ለማሸርተት የምትቃጣው።

የጋዜጣ ነፃነት የማይከበርባቸው የሦሥተኛው ምድብ ሀገሮች በጦርነት ወይም በእርስበርስ ጦርነት ላይ የሚገኙቱ ናቸው። በእነዚያው ሀገሮች ውስጥ ለጋዜጣ ነፃነት እመቃ የሚሰጠው ምክንያት፥ “በፀጥታ ምክንያት መረጃ መገደብ አለበት” የሚል ነው። ይህ ታዲያ በኢራቁ ጦርነት፣ ያኔ በፎክላንድ ፍልሚያ ዘመን፣ በእሥራኤል በተያዙት ግዛቶች ወዘተ በግልጽ ነው የታየው፣ ዝርዝሩ ረዥም ነው።

ዛሬ በብዙ ሀገሮች ውስጥ ለእውነት፣ ለመረጃ ነፃነት የሚነሳሱ ምሥጉን ዘጋቢዎች ራሳቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ነው ድርጊቶችን የሚያብራሩት። የጋዜጦች ሕትመት ክልክል እንዲሆን የሚደረግበት፣ ጋዜጠኞችም የሚታሠሩበትና የሚገደሉበትም ድርጊት ዛሬ በብዙ ሀገሮች ውስጥ ነው የሚታየው። ይህ በመላው የቅርብ ምሥራቅ እና በብዙ የእስያ ሀገሮች ውስጥ የየዕለት ድርጊት እንደሆነ ነው የሚገኘው። በሩሲያና በቀድሞይቱ ሶቭየት ኅብረት ግማዶች ዙሪያም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው።

ድርጅቱ “ጋዜጠኞች ያለድንበር” ጦርነት ወዳለባቸው ቦታዎች ለሚጓዙ ጋዜጠኞች ጥይት የማይዘልቀው ሰደርያ ያከራያል፤ ግን በጋዜጣ እመቃ አንፃር ሰደርያው ፋይዳ የለውም። ዴሞክራታውያኑ መንግሥታት በአማቂዎቹ አንጻር የዘወትር ግፊት ከማድረግ መቆጠብ የለባቸውም።