የጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የሽብር ክስ ተቀየረ | ኢትዮጵያ | DW | 22.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የሽብር ክስ ተቀየረ

ከታሰረ አንድ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ቀናት የቀረው የቀድሞው የ“ነገረ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ሽፈራው የተከሰሰበት የሽብር ወንጀል ተቀይሮ በመደበኛ የወንጀል ህግ ራሱን እንዲከላከል ብይን ተሰጠ፡፡ ብይኑን የሰጠው የጌታቸውን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ታህሳስ 13 በዋለው ችሎት ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:08
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:08 ደቂቃ

ጌታቸው ተከላከል ተብሏል

የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ትናንት እና ዛሬ በጋዜጠኞች የሽብር ክስ ጉዳይ ባተሌ ሆኖ ነበር፡፡ትናንት ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ እና ካሊድ መሀመድን በተያዘባቸዉ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ የመሳተፍ ወንጀል ጥፋተኛ ሲላቸው ዛሬ ደግሞ በተመሳሳይ አንቀጽ ክስ የቀረበበት ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን ክሱ ወደ መደበኛ የወንጀል ጉዳይ እንዲቀየር በይኗል፡፡ 

ጋዜጠኛ ጌታቸው የተከሰሰው “በ2001 ዓ.ም የወጣውን የጸረ-ሽብር አዋጅ በመተላለፍ መግንስት አሸባሪ በሚለዉ በግንቦት ሰባት ድርጅት ውስጥ ተሳትፎ አድርግሃል፤ እንደዚሁም ከድርጅቱ አመራሮች እና አባላት ጋር ግንኙነት አድርግሃል” ተብሎ ነበር፡፡ በማስረጃነትም የማህበራዊ መገናኛ በሆነው የፌስ ቡክ አድራሻው ተለዋውጧቸዋል የተባሉ መረጃዎች ከክሱ ጋር ተያይዘዋል፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ያደርግ የነበረውን የስልክ ግንኙነት የሚያመለክት መረጃም በአቃቤ ህግ በኩል ቀርቧል፡፡  

ዛሬ ያስቻለው አራተኛ የወንጀል ችሎት ግን በተከሳሹ ላይ የቀረበበት ማስረጃ ከሽብር ወንጀል ይልቅ በወንጀል ህጉ የተጠቀሰውን “የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር መፈጸምን” ያመለክታል በማለት ክሱ ወደዚያ ተቀይሮ ይከላከል ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡ የዛሬውን የችሎት የተከታተለዉ እና ስሙ እንዲጠቀስ የማይፈልግ አንድ ግለሰብ ሒደቱን እንዲሕ ይገልፀዋል።

“በአቃቤ ህግ [በኩል] ማስረጃ ቀርቦ ጨርሷል፡፡ ስለዚህ ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ ይከላከል ወይስ መከላከል ሳያስፈልገው በነጻ ይሰናበት የሚለውን ብይን ነበረ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው፡፡ እናም የተመረመረው የአቃቤ ህግ ማስረጃ በሰነድ ማስረጃነት ብቻ የቀረበ ነው፡፡ ተከሳሹ ምስክር አልቀረበበትም፡፡ ሌላም የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች የሉም፡፡ እርሱን መርምሮ በተከሰሰበት የሽብር ወንጀል ሳይሆን በመደበኛ የወንጀል ህጉ አንቀጽ ተቀይሮ መከላከያ ማስረጃዎቹን እንዲያቀርብ ነው ፍርድ ቤቱ የወሰነው” ሲል ጉዳዩን ከስር መሰረቱ ሲከታተል የነበረው ግለሰብ ያስረዳል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ተከላከል የተባለበት የወንጀል አንቀጽ የዋስትና ህግ የሚከለክል እንዳልሆነ የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ተከሳሹ ጠበቃው በህመም ምክንያት በችሎት ባለመገኘታቸው የዋስትና ጥያቄውን ማቅረብ እንደሚፈልግ ራሱ ለችሎት ተናግሯል፡፡ በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን በጽሁፍ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ መስጠቱን ችሎቱን የተከታተለው ግለሰብ ገልጿል፡፡ ችሎቱ የዋስትና መብቱን ጉዳይ ለመመልከት እና የመከላከያ ማስረጃዎች ዝርዝር ለመቀበል ለታህሳስ 19 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

የ“ነገረ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጌታቸው ቀደም ሲል “መሰናዘሪያ” ጋዜጣ እና “ላይፍ” መጽሔት ላይ ይሰራ እንደነበር እንደዚሁም በሌሎች የግል ፕሬሶች ላይ ጽሁፎችን ያሳትም እንደበር በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ ጌታቸው በኢትዮጵያ መታሰራቸው በይፋ ከሚታወቁ 17 ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው፡፡ መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት ሲፒጄ ባለፈው ሳምንት ባወጣው አመታዊ የታሰሩ ጋዜጠኞች ዘገባ ላይ እርሱን፣ ዳርሰማ ሶሪን እና ካሊድ መሀመድን አካትቶ ነበር፡፡ 

የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሞሬቲ ሙቲጋን የከፍተኛው ፍርድ ቤት በጋዜጠኞቹ ላይ ስላስተላለፋቸው ውሳኔዎች አስተያየት ጠየቅናቸው ነበር፡፡

“ጌታቸው በሽብር አለመወንጀሉ በእርግጥም በደስታ የምንቀበለው ነው፡፡ ነገር ግን መጀመሪያውኑ እስር ቤት መግባት አልነበረበትም፡፡ የታሰረበት በቂ ምክንያት አልነበረም፡፡ አርሱም ሆነ ሌሎች ጦማሪያን በሽብርተኝነትም ይሁን በሌላ ይከሰሱ ሁሉም የህሊና እስረኞች ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ እስር ቤት ቦታቸው አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡   

በጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቱ መሰረት ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ግብጽን እና ኤርትራን ተከትላ ከአፍሪካ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ  

Audios and videos on the topic