የጋዛ ዉድመትና ዲፕሎማሲ | ዓለም | DW | 21.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የጋዛ ዉድመትና ዲፕሎማሲ

የእሥራኤል ጦር ትንሽቱን ሠርጥ ለቅቆ ቢወጣም ዙሪያ ገባዋን እንደከበባት ነዉ።ጋዛ ነዋሪዎችዋ እንደሚሉት ጣራ-የሌላት ትልቅ «እስር ቤት» ናት።በጀርመን የፍልስጤም አምባሳደር ኾሉድ ዳይቤስ ደግሞ የሕዝብ ጉረኖ-ይሏታል።

የእስራኤል፤ የዩናትድ ስቴትስ እና አንዳድ የአዉሮጳ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንዳሉት እስራኤል ጋዛን፤ ካየር፤ ከምድር ከባሕር መክበብ፤ መድብድቧ፤ ራስዋን ከጥቃት የመከላከል እርምጃ ነዉ።ባለፉት ሁለት ሳምንታት የከፈችዉ ጥቃት ሠላማዊ ፍልስጤማዉያንን መመግደል ፤ ማቁሰል ማሰደዱም ከእግረ-መንግድ (collateral damage) ብዙም ያለፈ አልነበረም። የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች የትናንት አፀፋ ከየሩሳሌም፤ ቴል አቪቭ አልፎ ዋሽግተኖችን ሲቆጠቁጥ ግን የሠላም ጥሪ ጥረቱ-ከየአካባቢዉ ይጎርፍ ያዘ።ጆን ኬሪ ካይሮ ናቸዉ።ፓን ጊሙን ካይሮ ናቸዉ።ፌድሪካ ሞግሐሪ እዚያ ደርሰዉ ተመልሰዋል።ሁሉም ተኩስ ይቁም ይላሉ።ከዚያስ? አይታወቅም።የሚታወቀዉን እየጠቃቀስን የማይታወቀዉን እንጠይቃለን ።

ከወደ ጭንቅላቷ ሠፋ፤ ከግርጌዋ ጠበብ ያለች ቀጭን ሠርጥ ናት።ጋዛ።አጠቃላይ ቁመቷ ከአዲስ አበባ-ቢሸፍቱ ወይም ደብረዝይት ካለዉ ርቀት አይበልጥም። 38 ኪሎ ሜትር።ሥፋትዋ-ሠፊ ቦታዋጋ አሥራ-ሠወስት ጠበብ የሚለዉ ጋ ስድስት ኪሎ ሜትር ነዉ።1.8 ሚሊዮን ሕዝብ ተፋፍጎ ይኖርባታል።

እስራኤል በ1967 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከግብፅ ከማረከቻት ወዲሕ ለረጅም ጊዜ በቀጥታ ሥትቆጣጠራት ነበር።የቀድሞዉ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚንስር አርየል ሻሮን በ1967 እንደ ጦር መኮንን የማረኳትን ያቺን ጥንታዊ፤ ትንሽ፤ የብዙዎች መኖሪያን ሠርጥን በ2005 እንደ ጠቅላይ ሚንስትር የተናጥል ባሉት እርምጃ የአይሁድ ሠፈራ መንደሮችን አፈራርሰዉ ጦራቸዉን ሲያስወጡ ጋዛ ከዉጪ ሐይላት ቀጥታ ቁጥጥር የመላቀቂያዋ ጅምር መስሎ ነበር።

በዚያ ምድር የሚመስለዉ አይሆንበትም።የእሥራኤል ጦር ትንሽቱን ሠርጥ ለቅቆ ቢወጣም ዙሪያ ገባዋን እንደከበባት ነዉ።ጋዛ ነዋሪዎችዋ እንደሚሉት ጣራ-የሌላት ትልቅ «እስር ቤት» ናት።በጀርመን የፍልስጤም አምባሳደር ኾሉድ ዳይቤስ ደግሞ የሕዝብ ጉረኖ-ይሏታል።

«ነዋሪዎቹ አሳማጥመድ አይፈቀድላቸዉም።ማረስ አይፈቀድላቸዉም።ሥራ የላቸዉም።ከግዛቲቱ መዉጣት አይችሉም።ትንሽ ጉሮኖ ዉስጥ እንዳለ (እንሰሳ) ነዉ-የሚኖሩት።»

የእስራኤል ጦር ያየር፤ የባሕር፤ የምድር መገናኛዎችን ዘግቷል።ከግብፁ የሲናይ በረሐ ጋር የሚያገናኘዉን ትንሽ መስመርን ደግሞ አብዛኛዉን ጊዜ ግብፅ እንደዘጋችዉ ነዉ።

«(ጋዛዎች) ተስፋ ሊኖራቸዉ ይገባል።» ይላሉ የፍልጤሟ ተወካይ።ሙሉ ተስፋ ቀርቶ እንጥፍጣፊዉም የለም።ዓለምም ጋዛን የሚያስታዉሳት እያሰልሰ በሚያጠፋት እልቂት-ዉድመቷ ነዉ። የእስራኤል ጦር ግዛቲቱን ለቅቆ በወጣ ባመቱከፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ጋር ይቆራቆስባት ያዘ።በ2008 ለመጠነ-ሠፊ ጥቃት ዘመተባት።በ2012 የመከላከል ምሰሶ ያለዉን ሌላ ዘመቻ ከፈተባት።በየዘመቻዉ በሺ የሚቆጠሩ ሠላማዊ ፍልስጤማዉያን አልቀዋል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።ከተሞች፤ መንደሮች፤ የንግድና የልማት ተቋማት፤ የእርሻ ማሳዎች ወድመዋል።

ዘንድሮም ያዉ ነዉ። እልቂት፤ ጥፋት፤ ዉድመት።«ለምን?» ይጠይቃሉ ፍልስጤማዊዉ አዛዉንት።«እዚሕ የሚሆነዉን ተመልከቱ።ኑሯችን ምን ያሕል ከባድ እንደሆነ እዩ። መከራ ይፈራረቅብናል።የሁዲዎቹ ለምንድን ነዉ በቦም የሚደበድቡን።እንዴት እንደሚሆን አናዉቅም።---ምን አደረግናቸዉ።»

አሷ ትንሽ ልጅ ናት።ዓለም አልገባትም።ግን ልክ እንደ ሽማግሌዉ ትጠይቃለች። «እናንት የሁዲዎች ለምን ይሕን ታደርጋላችሁ።ለምን ሰዎችን ከቤታቸዉ ታባርራላችሁ።ባዶ እግራችንን ነዉ የሸሸ ነዉ።ይሕን በታናሽ እህቴ ላይ መፈፅም አልነበረባቸሁም።ልቤን ነዉ የተሰበረዉ፤ታናሽ እሕቴ።የሁዲዎች እንዲሕ አይነት ነገር የሚፈፅሙብን ለምንድ ነዉ?ለምን?ለምን

የእስራኤል የሥልታዊ ጉዳይ ሚንስትር አክራሪዉ የሊኩድ ፖለቲከኛ ዩቫል ስታይኒትስ መልስ አላቸዉ።አክራሪዉን የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ሐማስን መሠባበር የሚል።

«የአጭር ጊዜዉ ዓላማ ፀጥታ ነዉ።የረጅም ጊዜዉ ደግሞ ትጥቅ ማስፈታት።ከእንግዲሕ በአጫጭር ጊዜ መፍትሔዎች ልንደሰት አይገባም።(ችግሩን) ከሥር-መሠረቱን መንቀል አለብን።አሸባሪዎቹን እኛዉ ራሳችን ሠባብረን ለመጣል እግረኛ ጦር ከማዝመት ሌላ ሌላ-ምርጫ የለንም ብየ አምናለሁ።የተወሳሰበ ነዉ ግን ሌላ ምርጫ ያለን አይመስለኝም።»

እስራኤል ባለፈዉ ወር የተገደሉ ሰወስት ወጣቶችዋን ደም ለመበቀል አዲስ ጥቃት ከከፈተች ወዲሕ አብዛኞቹን የሐማስ መሪዎች አንድም-ገድላለች ወይም አስራለች።ሚንስር ስታይኒትስ የተመኙት ግን አልቀረም።ጋዛን ካየር-በቦምብ ሚሳዬል ሲቀጠቅጥ የሰነበተዉ የእሥራኤል ጦር ካለፈዉ ሐሙስ ጀምሮ-ከየብሥ በታንክ መድፍ ያንቀረቅባት ያዘ።

በአብዛኛዉ በየጓዳዉ የተሠሩ ሮኬቶችን የሚያወነጭፈዉን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ለመምታት የዘመኑን ምርጥ ጦር መሳሪያ የታጠቀዉ የዓለም ምርጥ፤ ጠንካራ ጦር ተጠባባቂ ሕይሉን ሳይቀር የማዝመቱ፤ ዓላማ -የጦር አዋቂዎችን ማነጋገሩ አልቀሩም።

አንዳዶች የእስራኤል ጋዛ ሠርጥን መልሳ ለመቆጣጠር ሳትፈልግ አትቀርም ይላሉ።ሚንስትር ስታይኒትስን የመሳሰሉ የእሥራኤል ባለሥልጣናትም ይሕን ፍላጎታቸዉን አልሸሸጉም።የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ጄኔራል ብሬንት ስኮቭክሮፍት ግን ከዚያስ ይላሉ?

«እስራኤሎች ጋዛ ሠርጥን መረምረማቸዉ አይቀርም።ይሕ ምንም ጥያቄ የለዉም።ከዚያስ? የእሥራኤል ጦር የጋዛ ሠርጥን (ዳግም) በሐይል የሚቆጣጠር ከሆነ ይሕ ትልቅ ችግር የሚያስከትልባቸዉ ይመስለኛል።

መዉጪያ መግቢያዉ ተዝግቶበት፤ ከሰማይ የቦምብ-ሚሳይል፤ ከምድር የታንክ መድፍ አረር-የሚወርድበት ፍልስጤማዉያ ግን የእስራኤል ርምጃ ጋዛን ከመቆጣጠርም ያለፈ ነዉ ባይ ነዉ።የእስራኤል ጦር በሁለት ቀን ዉስጥ ሰባ-ሠላማዊ ሰዎችን የገደለባት የሸርጂያ መንደር ነዋሪ እንደሚሉት የእስራኤል ዓላማ የፍልስጤሞችን መሬት መቀማት ነዉ።

«ሸርጂያ ወድማለች።ጠፍታለች።የሁዲዎቹ በሁሉም አቅጣጫ እየተኮሱ ነዉ።ሰዉ እንዲሸሽ ሁሉንም ነገር እያጋዩት ነዉ።መሬታችንን ሊወስዱ ነዉ።»

ዓላማዉ ምንም ሆነ ምን-የእስራኤል ጦር እስከ ትናንት ድረስ ከአምስት መቶ በላይ ፍልስጤማዉያንን ገድሏል።የተባበሩት መንግሥትት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ሰማንያ በመቶ ያሕሉ ሰላማዊ ሰዎች፤ አብዛኞቹ ሴቶችና ልጆች ናቸዉ።ከሁለት ሺሕ በላይ ቆስለዋል።

አምስት ሺሕ የሚሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጠለያ ጣቢያ ተሸሽገዋል።እስራኤልን በሥም ለመጥራት የፈሩት በፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጠሪ ሮበርት ተርነር «ያልተመጣጠነ» እርምጃ እንዲቆም ተማፅነዋል።

«ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፉን የሠብአዊ ጥበቃ ሕግ እንዲያከብሩ እንጠይቃለን።ሠላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ ጥፋትን ማስቀረት፤ ተመጣጣኝነትን እና ጥንቃቄን ከግምት እንዲያስገቡ እንጠይቃለን።»

የእሥራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ማርክ ሬጌቭ መልዕክቱ ለመንግሥታቸዉ እንደሆነ አልተጠራጠሩም። ሠላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀናል ይላሉ።

«በዚሕ ግጭት ሠላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ አካባቢያቸዉን ለቅቀዉ እንዲወጡ በተደጋጋሚ ሥናስጠነቅቅ ነበር።አለመታደል ሆኖ ሐማስ ቀጥታ ተቃራኒዉን ነዉ-ያደረገዉ።ሐማስ ሰላማዊ ሰዎችን እንደ ሠብአዊ ጋሻ ሊጠቀምባቸዉ ሥለፈለገ በያሉበት እንዲቆዩ ነግሯቸዋል።የጦር መሳሪያዎቹን ሠላማዊ ሕዝብ ባለበት ሥፍራ ሸሽጘል።»

ለእሥራኤል ሁለንተናዊ ድጋፍ የምትሰጠዉ ዩናይትድ ስቴትስም ለቅርብ ወዳጅዋ የምትሰጠዉን የማይናወጥ ድጋፍ ባሁኑ ግጭትም በድጋሚ አረጋግጣለች። ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባለፈዉ ሮብ እንዳሉት እሥራኤል የከፈተችዉ ጥቃት ማንኛዉም መንግሥት የሚያደርገዉ «እራስን የመከላከል» እርምጃ ነዉ።

«በተደጋጋሚ እንዳልኩት እሥራኤል ሕዝቧን ከሚያሸብረዉ የሮኬት ጥቃት እራሷን የመከላከል መብት አላት።በየቀኑ ሮኬት እየወረደበት ዝም ብሎ የሚቀመጥ ሐገር የለም።በአሜሪካኖች ርዳታና ድጋፍ እስራኤል የሠራችዉ ፀረ-ሮኬት ሚሳዬል የብዙ እስራኤሎችን ሕይወት በማዳኑም ኮርቻለሁ።»

የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ትናንት ባንድ ጊዜ አሥራ-ሰወስት የእስራኤል ወታደሮችን ሲገድሉ ግን ነገሮች ተለዋወጡ።ከሥራ-ሰወስቱ የእሥራኤል ወታደሮች ሁለቱ የአሜሪካ ዜጎች መሆናቸዉ ደግሞ በግጭቱ አሜሪካኖች ለእስራኤል ገንዘብ፤ዕዉቀት፤ ጉልበታቸዉን ብቻ ሳይሆን ሕይወት-ደማቸዉን ጭምር እየገበሩ መሆኑ በይፋ ፈጋ።

ግጭቱ ከተጀመረ ጀምሮ ሁለቱን አሜሪካዉያንን ጨምሮ የተገደሉት እሥራኤላዉን ቁጥር ሃያ ደረሰ።ሁለቱ ሠላማዊ ሰዎች ናቸዉ።እርግጥ ነዉ እስከ ትናንት ድረስ ተኩስ እንዲቆም የተለያዩ ሐገራት መሪዎች መጠየቃቸዉ፤ የወቅቱ የአዉሮጳ ሕብረት ሊቀመንበር የኢጣሊያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍሬድሪካ ሞግሪኒን ጨምሮ የብዙ ሐገራት ዲፕሎማቶች እየሩሳሌም እየደረሱ መመለሳቸዉ አልቀረም።

የዓለምን ሠላም የማስከበር ሐላፊነት ያለበት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የጉዳዩን አሳሳቢነት በግልፅ ያስታወቀዉ ግን ትናንት ነዉ።ምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ወደ ካይሮ እንዲሔዱ የደገፈዉም ትናንት።ፕሬዝዳንት ኦባማ «እራስን መከላከል» ማለታቸዉን አቁመዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉን ወደ ካይሮ ለመላክ የወሰኑትም ትናንት ነዉ።ዛሬና ነገ ካይሮ ላይ የሚቀለጣጠፈዉ ዲፕሎማሲ እሥራኤልና ሐማስን ተኩስ አቁም ያፈራርም ይሆናል።ከዚያስ? ምናልባት የሚቀጥለዉ ተኩስ እስኪከፈት?

ነጋሽ መሐመድ

ሂሩት መለሠ

 

 

 

Audios and videos on the topic