1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የጋዛ እልቂትና የተኩስ አቁም ተስፋ ቅጭት

ሰኞ፣ የካቲት 25 2016

የኃይማኖት መሪዎች ሰላም እንዲወርድ ፈጣሪያቸዉን ይማፀናሉ፣ ኃይለኞችን ያባብላሉ።የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ትናንት ለተከታዮቻቸዉ እንደነገሩት ከፀሎት-ምሕላ-ተማፅኗቸዉ ጋር ራሳቸዉ-ለራሳቸዉ ያነሱት ጥያቄም አላቸዉ። በዚሕ መንገድ የተሻለ ዓለም ዓለም መገንባት ይቻላል? የሚል መሠረታዊ ጥያቄ።

https://p.dw.com/p/4dA2e
ራፋሕ-ጋዛ ሕፃናቱ ከጥፋት-ወድመቱ ቢተርፉ እንኳን እድገት ኑሯቸዉ እንዴት ይሆን ይሆን?
የጋዛ እልቂት ማብቂያ አለዉ ይሆን? ምስል Ibraheem Abu Mustafa/REUTERS

የጋዛ እልቂትና የተኩስ አቁም ተስፋ ቅጭት


የሙስሊሞች ቅዱስ የጾም ወር ረመዳን መጣሁ፣ መጣሁ እያለ ነዉ።አይቀርም።ጋዛ ግን አምስት ወር እንደለመደችዉ ሕፃናት፣ሴቶች፣ ሽማግሌዎች መዓለት ወሌት እየተገደሉባት አስከሬን በቅጡ ሳትቀብር፣ አስከሬን እየተከመረባት፣ ቁስለኞች በወጉ ሳይታከሙ ቁስለኛ እየተጨመረባት፣ አካሚ-ተንከባካቢዎች እየተገደሉ እየቆሰሉባት ነዉ።ረሐብ ጊዜ አልሰጥ ብሎት ምፅዋት ፍለጋ የተሰባሰበ ፍልስጤም በጥይት እየረገፈ፣ሚሊዮኖች ተሰደዉ ዳግም እየተሰደዱ፣እየተራቡ መቶዎች እንደታገቱ ረመዳንን ሊቀበሉ ሳምንት ቀራቸዉ።በቅዱሱ ወር እንኳ ተኩስ እንዲቆም የሚደረገዉ ጥረትና ለመከራኛዉ ሕዝብ የተሰጠዉ ተስፋ እከዛሬ ከተስፋ አለማለፉ ነዉ የከፋዉ ሰቀቀን።የጋዛ እልቂት፣ የተኩስ አቁሙ ጥሪና የተስፋዉ ቅጭት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

ሰሚ ያጣዉ የሠላም ጥያቄ

የኃይማኖት መሪዎች ካንጀትም ሆነ ካንገት ዛሬም እንደ እስከዛሬዉ አምስት ወር ሰላም እንዲወርድ ፈጣሪያቸዉን ይማፀናሉ፣ ኃይለኞችን ያባብላሉ።የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ትናንት ለተከታዮቻቸዉ እንደነገሩት ከፀሎት-ምሕላ-ተማፅኗቸዉ ጋር ራሳቸዉ-ለራሳቸዉ ያነሱት ጥያቄም አላቸዉ።በዚሕ መንገድ የተሻለ ዓለም ዓለም መገንባት ይቻላል? የሚል መሠረታዊ ጥያቄ። 
«በሚካሔደዉ ግጭት ምክንያት በፍልስጤምና በእስራኤል ሕዝብ ላይ በሚደርሰዉ የስቃይና ሰቆቃ የሚሰማኝን ሕመም በየዕለቱ በልቤ ዉስጥ እብሰለስለዋለሁ።በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣መቁሰልና የደረሰዉ ከፍተኛ ዉድመት በርግጥ ያምማል። ይሕ (ድቀት) የወደፊቱ ተስፋቸዉን ባጨለመዉ ወጣቶችና መከላከያ በሌላቸዉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ሕመም አስከትሏል።እራሴን እጠይቃለሁ፦በዚሕ መንገድ (ለወደፊቱ) የተሻለ ዓለም መገንባት ይቻላል ብሎ ተብሎ ይታሰባል? ሰላም ማስፈን እንችላለን ብለን በርግጥ እናሰባለን? እባካችሁ አቁሙ! ሁላችንም አብረን እንበለዉ፣ እባካችሁ አቁሙ።»

የኃይማኖት መሪዎች ፀሎት፣የዲፕሎማቶች ምክር፣ የምሁራን ትንታኔም ሆነ የአደባባይ ሰልፈኞች ጥሪ ጋዛን ከጥፋት ማዳን አልቻለም
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ትናንት ለተከታዮቻቸዉ ባደረጉት ንግግር ጦርነቱ እንዲቆም በድጋሚ ጠይቀዋል።ምስል Tiziana Fabi/AFP/Getty Images

ሰማናቸዉ።ፈጣሪያቸዉ ተቀብሏቸዉ ይሆን? ጦረኞቹስ? አናዉቅም።የምናዉቀዉ እስራኤልና ምዕራባዉያን መንግስታት በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ባለፈዉ መስከረም 26፣ 2016 ደቡባዊ እስራኤልን ወርሮ 1,139 የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎችን መግደሉንና በመቶ የሚቆጠሩ ማገቱን እስራኤል ማስታወቋን ነዉ።ከሟቾቹ 764ቱ ሰላማዊ ሰዎች እንደሆኑ እስራኤል ማስታወቋን ሰምተናልም።የምናዉቀዉ የእስራኤል መሪዎች፣ ሐማስን ለማጥፋት ደጋግመዉ መዛታቸዉን ነዉ።

የዋሽግተን፣ ብራስልስ፣ ለንደን መሪዎችና ተባባሪዎቻቸዉ ለእስራኤል መሪዎች ዛቻና ዘመቻ ስኬት ከጦር መሳሪያ-እስከ ዲፕሎማሲ፣ ከምጣኔ-ሐብት ድጎማ፣እስከ ፕሮፓጋንዳ፣ከፖለቲካ፣ ጦር ኃይል እስከማዝመት የሚደርስ የማይናወጥ ድጋፍ እየሰጡ ነዉ።ከምዕራባዉያን መንግስታት ሁለንታናዊ ድጋፍ የሚሰጠዉ የእስራኤል መንግስት ጦር ካለፈዉ መስከረም ወዲሕ ጋዛ ሰርጥ ላይ በከፈተዉ ጥቃት ከ31 ሺሕ በላይ ፍልስጤማዉያንን መግደሉን የፍልስጤም ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ሎይድ አዉስቲን ባለፈዉ ሳምንት ከሐገራቸዉ ምክር ቤት እንደራሴ ለቀረበላቸዉ ጥያቄu በሰጡት መልስ የእስራኤል ጦር ጋዛን መደብደብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ25 ሺሕ በላይ ሰላማዊ ፍልስጤማዉያን መገደላቸዉን አረጋግጠዋል።
«ከ25 ሺሕ ይበልጣል።»

ራፋሕ ጋዛ፣ የእስራኤል ጦር ኃይል ባወደመዉ አካባቢ የደረሰዉን ጥፋት ለማየት የተሰበሰበ ሕዝብ
ጋዛ አስከሬን ቀብራ አስከሬን የሚከመርባት፣ ሙቷን ቀብራ ሳታባቃ ሌሎች የሚገደሉባት ግዛትምስል Ibraheem Abu Mustafa/REUTERS

ከ60 ሺሕ በላይ ሕዝብ ቆስሏል። ሕፃናት፣ሴቶች፣ አዛዉቶች ሐኪሞች፣ ጋዜጠኞች፣ የርዳታ ሰራተኞች ጭምር ያለቁበት ጥቃት ከ1.3 ሚሊዮን የሚበልጥ የጋዛ ሕዝብን ከየቤት ንብረቱ አፈናቅሏል።ሆስፒታሎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ትምሕርት ቤቶች፣የርዳታ መስጪያ ማዕከላት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።ሚሊዮኖች ለረሐብ ተጋልጠዋል።
የጋዛዉ ጦርነት እዚያዉ ጋዛ ዉስጥ ከሚያደርሰዉ ጥፋትና ዉድመት አልፎ ከሊባኖስ እስከ የመን፣ከኢራን እስከ የመን፣ ከሊባኖስ እስከ ኢራቅና ሶሪያ የሚደርሱ አጎራባቾችን እያተራመሰ ነዉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ ዛሬ «አደገኛ» ያሉት የጋዛዉ ጦርነት ካልቆመ የከፋ መዘዝ እንዳያስከትል ያሰጋል ይላሉ።

«የጋዛ ጦርነት በአጎራባች ሐገራት ላይ በጣም አደገኛ መዘዝ አስከትሏል።እና ይሕ አደገኛ ሁኔታ በጣም የሰፋ ጥፋት ያደርሳል ብዬ እሰጋለሁ።በመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐገራት ከዚያም አልፎ በሌሎች አካባቢዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያደርሳል።» 

 

የአሜሪካኖች የተኩስ አቁም ጥሪ

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዳራሾች እስከ መስክ ድንኳኖች፣ ከአብያተ መንግስታት እስከ እስከ ዩኒቨርስቲ ቢሮዎች፣ ከሰልፍ አደባባዮች እስከ  አብያተ-መፅሐፍት፣ ከአብያተ ክርስቲያናት እስከ መሳጂዶች የሰላም ጥሪ፣ ማሳሰቢያ፣ምክር፣ ተማፅዕኖዉ ይንዠቀዠቃል።ጋዛ ላይ የሚወርደዉን ቦምብ፣ ሚሳዬል ግን አንዱም ማስቆም አልቻለም።
ይሁንና ለወትሮዉ ጥያቄ፣  ትንታኔ፣ ሥጋት፣ ተማፅዕኖዉን ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ከእስራኤል መሪዎች ጎን የቆሙት የዋይት ሐዉስ መሪዎች አሁን ለእዉነቱ የቀረቡ መስለዋል።ብዙዎች እንዳሉት የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ለሐገር ዉስጥ የምርጫ ዘመቻ ፍጆታቸዉ ሲሉ የጋዛዉ ጦርነት ላጭር ጊዜ እንዲቆም የሚሹ መሆናቸዉን እያስታወቁ ነዉ።ምክትል ፕሬዝደንት ካሜላ ሐሪስ ትናንት።
«እደግመዋለሁ።ሐማስ የእስራኤል ሕዝብን ማስጋቱ መወገድ አለበት።ጋዛ ዉስጥ የሚደርሰዉን መጠነሰፊ ስቃይ ከግምት በማስገባት ቢያንስ ለ6 ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ተኩስ አቁም መደረግ አለበት።ይሕ አሁን ለድርድር የቀረበ ነዉ።(ተኩስ አቁሙ) ታጋቾችን ለማስወጣትና ከፍተኛ ርዳታ ለማስገባት ይረዳል።» 

ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም ባለፈዉ ሳምንት በሰጡት መግለጫ ከረመዳን መጀመሪያ ጀምሮ ይፀናል የተባለዉ ተኩስ አቁም ዛሬ «ይፈረማል« ብለዉ ነበር።በቀጠር፣ በዩናይትድ ስቴትስና በግብፅ ሽምግልና የሚደራደሩት እስራኤልና ሐማስ ለተኩስ አቁሙ «የመጨረሻ» የተባለዉን ልዩነታቸዉን ለማስወገድ ትናንት ካይሮ ዉስጥ ይደራደራሉ ተብሎም ነበር።ይሁንና የሸምጋዮችና የሐማስ ተወካዮች ካይሮ ሲገኙ የእስራኤል ተወካዮች አልተገኙም።

የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች አምስት ወር ሙሉ ቆይተዉ አሁን ተኩስ አቁም የሚሉት «ለምርጫ ዘመቻ አስበዉ ነዉ» ይላሉ
የዩናይትድ ስቴትስዋ ምክትል ፕሬዝደንት ካሜላ ሐሪስ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል።ምስል Johannes Simon/Getty Images

 

የተኩስ አቁሙ ተስፋና እንቅፋቱ

የእስራኤል መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት የእስራኤል ተደራዳሪዎች ወደ ካይሮ ያልሄዱት ሐማስ ያገታቸዉን ሰዎች ዝርዝር እንዲሰጥ እስራኤል ያቀረበችዉን ጥያቄ ባለመቀበሉ ነዉ።ቴል አቪቭ እስራኤል የሚኖረዉ ጋዜጠኛ ዜናነሕ መኮንን እንደሚለዉ ግን በሱ ቋንቋ «ሌላ ማርሽ» ካልተቀየረ እስራኤልና ሐማስ የተኩስ አቁም ይባል በሌላ ድርድር አይስማሙም።
«ኦክቶበር 7 ላይ ጦርነቱ ሲጀመር (ሐማስን) መደምሰስ አለባቸዉ ብሎ የተጀመረ ነዉ።ይኸ ተኩስ አቁም ስምምነት በሁለቱ መካከል ሊሆን አይችልም።ሐማስ የያዛቸዉ አቋሞች አሉት። በእስራኤል በኩልም ሠፈራዉ እንደቀጠለ ነዉ።እራሱ ኔታንያሁ እየተናገረ ያለዉ ሌላ ማርሽ መቀየር አየለበት።»

ዜናነሕ «ማርሽ» ያለዉ የመሪዎች መቀየር ወይም መጥፋት ሊሆን ይችላል።አምስተኛ ወሩን ያስቆጠረዉ ጥቃት፣ ዉጊያና እመቃ ግን ከሰላማዊ ሰዎች እልቂት ባለፍ አሸናፊና ተሸናፊ አልተለየበትም።የመከከለኛዉ ምሥራቅ ፍፁም ኃያል፣ በጠላቶችዋ የማትደፈር፣ የካይሮ፣የደማስቆ፣ የትሪፖሊ፣ የባግዳድ፣ የአማን የሌሎችም የአረብ ጠላቶችዋን ሲሻት በስድት ቀን፣ ሲያሰኛት በሁለት ሳምንት «ደመሰሰች» የምትባለዉ እስራኤል።

ታጋቾቹ እንዲለቀቁ የታጋቾች ዘመድ ወዳጆች ያደራጁት ሰልፍ በተደጋጋሚ ይደረጋል
ሐማስ ያገታቸዉ የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎች እንዲለቀቁ እስራኤል ዉስጥ ከሚጠይቁ የአደባባይ ሰልፎች አንዱምስል Maya Alleruzzo/AP Photo/picture alliance

የዓለምን ዘመናይ ጦር መሳሪያ፣ የጦርና የስለላ ቴክኖሎጂን እስካፍንጫዋ የታጠቀችዉ እስራኤል፣ የምዕራባዉያን መንግስታት ድጋፍ እንዳሻት የሚንቆረቆርላት እስራኤል በአንድ ተራ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የመጠቃትዋ ሚስጥር ዛሬም እንዳነጋገረ ነዉ።
ይበልጥ አነጋጋሪዉ ግን የእስራኤል መሪዎች እንደፎከሩት ያን በየስደተኛ መጠለያ ጣቢያ፣ በየጉድጓድ ቦዩ የሚሽሎሎክ ደፈጣ ተዋጊ ቡድንን ማጥፋት እንዴት ተሳናቸዉ የሚለዉ ነዉ።እንደገና ዜናነሕ።
«ለሐማስ የተሰጠዉ ግምት በእስራኤልም ሆነ በዩናይትድ ስቴትስና በአዉሮጳ የተሳሳተ ነዉ። ጋዛ ትንሽ ግዛት ናት።ግን አምስት መቶ ኪሎ ሜትር አለ ዉስጥ ለዉስጥ በጣም አስቸጋሪ ነዉ።ዋሻዉ።ከቬትናም ይበልጣል ነዉ የሚባለዉ።ሥለዚሕ ሐማስ እንዲሕ በቀላሉ የሚናቅ አይደለም»

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ ዛሬ እንዳሉት ዓለም 55 ግጭቶችን እያስተናገደች ነዉ።በተለይ ዩክሬንና ጋዛ ላይ ብዙ ሺዎችን የሚፈጀዉን  ግጭትና ጦርነት ማስቆም ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉት የኃያል ሐገራት መሪዎች፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራስሲስ እንዳሉት ለወደፊቱ ትዉልድ የተሻለ ዓለም የመገንባት ፍላጎት አላቸዉ ብሎ ማመን ይቻላል? 

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ