የጋና የምርጫ ሂደት፣ | ዓለም | DW | 09.12.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የጋና የምርጫ ሂደት፣

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ጋና፣ በአፍሪቃው ክፍለ-ዓለም በአመዛኙ እንደተለመደው ሁከት ሳይታይባት፣ የፓርላማና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዋን፣ ባለፈው እሁድ፣ በሰላም ያከናወነች ስትሆን፣ ከፊሉ የምርጫ ውጤት በመገለጥ ላይ ነው።

default

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በጋና፣

በያዝነው ታኅሳስ ወር 3ኛ ሳምንት ገደማ ላይ ከስልጣን የሚሰናበቱትን ፕሬዚዳንት ጆን ኩፉርን ለመተካት ገዥውን ፓርቲ New Patriotic Party ን ወክለው የተወዳደሩት Nana Akufo-Addo ሲሆኑ፣ ከአክራ፣ የዶቸ ቨለ፣ የሃውሳው ቋንቋ አግልግሎት ባልደረባ እንደዘገበልን የተቃውሞው National Democratic Congress እጩ ተወዳዳሪ John Atta Mills እስካሁን በ 2 ከመቶ የድምፅ ብልጫ ማሰባሰብ በመምራት ላይ ናቸው ።

አምና 50ኛ ዓመት የነጻነት በዓሏን ያከበረችው ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ጋና፣ ባለፈው እሁድ የፓርላማና የፕሬዚዳንት ምርጫ ያካሄደች ስትሆን፣ በዚያው በሥፍራው በመገኘት የተከታተለውን ባልደረባችንን ቲጃኒ ላዋልን በስልክ አነጋግረነው ነበር።

«ምርጫ በሰላም ነው የተካሄደው። በጣሙን በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ነው የተደረገው። ካለፈው እሁድ ማታ አንስቶም የድምፅ ቆጠራ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ህዝቡ፣

አሁን ውጤቱን ለማወቅ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነው የሚገኘው። ሰዎችን ስታነጋግር፣ የተለያዩ የራዲዮ ጣቢያዎችን ዘገባዎች ስታዳምጥ፣ በተከታታይ በአገሪቱ በመላ ጊዜያዊ የድምፅ ውጤቶችን እንደሚያስተዋውቁ መገንዘብ ይቻላል። የምርጫው ተሳትፎም 90---90 ከምናምን--ያህል ከፍ ያለ ነበር ። የተመዘገቡ መራጮችን ተሳትፎ ማለቴ ነው።»

በገዥው ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪናና አኩፎ-አዶ እና በተቃውሞው ወገን እጩ ተወዳዳሪ፣ ጆን አታ ሚልስ መካከል በተካሄደው የምርጫ ዘመቻውድድር ፣ ነጥረው የወጡ አከራካሪ ዐበይት ጉዳዮች የትኞቹ ነበሩ?

«በምርጫ ው ዘመቻ፣ ዋናው የመከራከሪያ ነጥብ ኤኮኖሚ ሆኖ ተገኝቷል። ምንም እንኳጋና፣ ኤኮኖሚዋ እያበበ ነው ቢባልም ብዙሃኑ የአገሪቱ ተወላጆች በጉስቁልና ፣ በድህነት ነው፤ የሚኖሩት ። በህብረተሰቡ ውስጥ ድህነት እየተንንሠራፋ ነው የሚገኘው። ሰዎች፣ ጧት፣ ተነስተው፣ ወደ ሥራ ቦታ ሲጓዙ ታያለህ። ይሁንና በወር ማለቂያ ላይ ደመወዝ ሲከፈላቸው ኑሮን ለመግፋት በቂ እንዳልሆነ ነው ተጨባጩ ሁኔታ የሚያሳየው። መጓጓዣው፣ ራሱ፣ ከቤት ወደ ሥራ ቦታ ፣ ግማሹን የሠራተኛውን ደመወዝ እምሽክ ያደርገዋል። ትምህርት ቤት ደግሞ አለ። በጋና፣ ትምህርት ነጻ ቢሆንም፣ (እስከ 2ኛ ደረጃ ማለት ነው)፣ ወላጆች፣ ለመጻህፍትና ተማሪዎች ለሚያስፈልጓቸው፣ የትምህርት መሣሪያዎች መክፈል አለባቸው። መሣሪያዎቹ ደግሞ፣ በጣም ውድ ናቸው። እናም፣ በምርጫው ዘመቻ ቀልብ የሳበው ጉዳይ ኤኮኖሚ ነው። በአገሪቱ ድህነትን እንዴት መቅረፍ ይቻላል? በሚለው ነጥብ ላይ ላቅ ያለ ትኩረት ተደርጓል። የሥራ አጦች ዜጎች ቁጥር ብዙ ነው። በዛ ያሉ ወጣቶች ሥራ በማጣት ሲንገላወዱ ነው የሚታዩት ። ይህ ሁሉ ነበር የምርጫ ዘመቻውን አጧጡፎት የቆየው። »

ኤኮኖሚ፣ ድህነት፣ ትምህርት፣ ከአነዚህም ጋር የጤና ጥበቃ ችግር ፣ የሀኪሞች እጥረት ፣ ሌላው ዐቢይ የመነጋገሪያ ርእስ እንደነበረ ቲጃኒ ጠቁሞአል።

«የጤና መደኅን እንዲሠራበት ቢደረግም፣ (የመንግሥት የጤና መድኅን ማለት ነው-- እርግጥ፣ ሠራተኛው ከደመወዙ እየተቆረጠ የሚከፍለው ማለት ነው፣ ) ያም ሆኖ፣ ,ፍተኛ የሃኪሞች እጥረት አለ። ለየ 10,000 ው ጋናዊ አንድ ዶክተር ነው የሚደርሰው፤ የህክምና ዶክተር!በአገሪቱ በመላ፣ ለየአሥር ሺው ጋናዊ አንድ ዶክተር ይደርሰዋል ቢባልም፣ አብዛኞቹ ዶክተሮች የተከማቹት በደቡብ ነው፣ በተለይ በአክራና በኩማሲ! ይህም፣ በምርጫው ዘመቻ የተተኮረበት ጉዳይ ነበረ።»

ነጻ እንደወጣች፣ ለመላ አፍሪቃ፣ የአንድነት ዓርማ ጥባቅና በመቆም ትታወቅ የነበረችው ፣ ከዚያም በመሃሉ በወታደራዊ አምባገነኖች መፈራረቅ፣ ተረስታ የነበረችውና እ ጎ አ ከ 1981 ዓ ም ወዲህ ወደ ማለፊያ አስተዳደርና ዴሞክራሲ ያመራችው ጋና፣ አሁን በዴሞክራሲ ሥርዓት መደርጀቷን ታሥመሰክራለች ወይስ እንከን ያጋጥማል የሚል ሥጋት አለ?

«እንደሚመሰለኝ፣ ጋና ፣ ለቀሪው አፍሪቃ አርአያነትን ተክላለች። ምክንያቱም ፣ ይህ ዴሞካራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ 5ኛ ጊዜዋ ነው። የርእሳነ-ብሔር ልውውጥ ሲደረግም ፣ ያሁኑ፣ 3ኛ ጊዜ ይሆናል ማለት ነው። ከአየር ኃይል መቶ አለቃ ጀሪ ሮውሊንግስ ወደ አቶ ጆን ኩፉር፣ አሁን ደግሞ፣ ናና አኩፎ አዶ ወይም ጆን አታ ሚልስ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ማለት ነው። ጋናውያን ለሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ተምሳሌት የሆኑ ይመስለኛል። የመጨረሻው ውጤት ከተገለጠ በኋላ፣ መጥፎ ነገር፣ ሁከት ወይም ይህን የመሰለ እንከን የሚያጋጥም አይመስልኝም።»