የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተከፈተ | አፍሪቃ | DW | 16.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተከፈተ

ሻምሳ አብዲ ባሬ እና ሎቬንደር ሞሴቲ የዛሬን አያድርገው እና የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነበሩ። 800 ተማሪዎች የነበሩት ዩኒቨርሲቲው ለዘጠኝ ወራት ተዘግቶ ሲከፈት ከመግቢያ በሩ ላይ ከፍተኛ ፍተሻ ተጀምሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 06:13
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
06:13 ደቂቃ

የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተከፈተ

ወደ ቅጥር ግቢው የሚያመሩ ግለሰቦች መላ ሰውነት ላይ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የታገዘ ፍተሻ ይደረጋል። መኪኖች ይበረበራሉ። የኬንያ መንግስት የዩኒቨርሲቲው ደህንነት የተረጋገጠ መሆኑን ወስኖ ሲከፈት የተመለሱት ተማሪዎች ግን 20 ብቻ ናቸው። ከእነዚህ መካከል አንዷ ሻምሳ አብዲ ባሬ ነች።
«በዚህ ግቢው ውስጥ ምንም ነገር ቢፈጠርም አስቀያሚው ትዝታ ቢኖርም ትምህርታችንን መቀጠል ይኖርብናል። አካባቢያችንን ስንመለከት የምንደሰትባቸው፤የምናነብባቸው የምንወያይባቸው እና ጓደኞቻችንን የምናገኝባቸው ቦታዎች አሉ። እነዚህን ስንመለከት አስቀያሚ ስሜት ይሰማናል።»
የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አሸባብ ከፈጸማቸው አሰቃቂ ጥቃቶች መካከል አንደኛው ለሻምሳ አብዲ ባሬ እና ጓደኞቿ መጥፎ ትዝታ ጥሎ ያለፈው አንዱ ነው። የአሸባብ ታጣቂዎች በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ሶማሊያ ድንበር ላይ በሚገኘው ጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ላይ በፈጸሙት ጥቃት 147 ተማሪዎችን ገድለው በርካቶችን አቁሰለዋል።የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ዶክተሮችም የጥቃቱ ዒላማ ሆነው ህይወታቸውን አጥተዋል።ከዚያ በኋላ ከዋና ከተማይቱ ከናይሮቢ በስተምሥራቅ 370 ኪሎሜትር ላይ የሚገኘው ጋሪሳ ተዘጋ። ከዘጠኝ ወራት በኋላ ሲከፈት ሎቬንደር ሞሴቲ ወደ ጀመረችው ትምህርት ለመመለስ የደህንነት ስጋት ተሰምቷታል።
«መንግስት የትምህርት ቤቱ ደህንነት የተጠበቀ ነው ብሏል። የፖሊስ ጣቢያም በዚያ ተቋቁሟል። ከቅጥር ግቢው ውጪስ? በአካባቢው ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ እንሰማለን። ለእኔ ይህ ምቾት አይሰጠኝም። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸውን ሰምቻለሁ። ለሁሉም መልካሙን ሁሉ እመኝላቸዋለሁ። ደህንነት ከተሰማቸው ትምህርታቸውን መቀጠላቸው ጥሩ ነው። እኔ ግን ወደ እዚያ በፍጹም ተመልሼ አልሄድም።»


ኬንያ ከሶማሊያ በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ተደጋጋሚ ግን ደግሞ አነስተኛ ጥቃቶች ይፈጽማል። በምላሹ የኬንያ ጦር እርምጃ ይወስዳል። የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ኬንያ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ በመላኳ ምክንያት ጥቃቶቹ በቀል መሆናቸውን አስታውቋል።
በትናንትናው ዕለት እንኳ ታጣቂ ቡድኑ በሶማሊያ በሚገኝ የአፍሪቃ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የጦር ሰፈር ላይ በፈጸመው ጥቃት 63 ወታደሮች መገደላቸውን የአሸባብ ቃል-አቀባይ ተናግረዋል። በደቡባዊ ሶማሊያ ከኤል-አዴ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘው የጦር ሰፈር መቆጣጠሩንም አሸባብ አስታውቋል። የአፍሪቃ ህብረት የሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ዴቪድ ኦቦንዮ ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠው የሟቾችን ቁጥር ከማናገር ግን ተቆጥበዋል።
«በአካባቢው ከኬንያ ወታደሮች ጦር ሰፈር አጠገብ በሚገኝ የሶማሊያ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። የኬንያ ወታደሮች ለጥቃቱ ምላሽ የሰጡ ሲሆን እስካሁን በውጊያ ላይ ናቸው። በሁለቱም ወገን እስካሁን የሞተ የለም። መረጃውን እንዳገኘን ግን እናሳውቃለን።»
የአሸባብ ታጣቂ ቡድን በጦር ሰፈሩ ሰንደቅ አላማውን ማውለብለቡን እና የበርካታ ወታደሮች አስከሬኖች በከተማዋ ተደርድረው መመልከታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሮይተርስ ተናግረዋል። ኬንያዊው ቃል አቀባይ በጥቃቱ የተገደሉ ወታደሮችን ዜግነት እና ብዛት ለመናገር ፈቃደኛ አይሁኑ እንጂ ታጣቂ ቡድኑ ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ኬንያውያን ናቸው ብሏል።
የአሸባብ ቃል አቀባይ አብዲ አዚዝ አቡ ሙዳን በአሸባብ የድረ-ገጽ ሬዲዮ አማካኝነት እንደተናገሩት ጥቃቱ የተፈጸመው በዕለተ አርብ ማለዳ በደቡባዊ ሶማሊያ ነው። የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በሶማሊያ ከተገደሉት ወታደሮች መካከል ኬንያውያን እንደሚገኙበት አረጋግጠዋል። የአፍሪቃ ሕብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በምህጻሩ አሚሶም በትዊተር ማህበራዊ ድረ-ገጽ ባወጣው መግለጫ የሟቾቹን ቁጥር ከመግለጽ ቢቆጠብም አሸባብ የተገደሉ ወታደሮችን በአደባባይ አስጥቶ ለሰዎች ማሳየቱን አውግዟል።
ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ያጣችው ሶማሊያን የሚያምሰው የአሸባብ ታጣቂ ቡድን በኬንያም ላይ ይበረታል። ታጣቂ ቡድኑ ናይሮቢ በሚገኘው የዌስትጌት የገበያ ማዕከል ላይ በፈጸመው ጥቃት 69 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከ75 በላይ ደግሞ ቆስለዋል፡፡ የኬንያ መንግሥት እና የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማቱ የሽብር ጥቃትን በመከላከልም ረገድ አብዝተው ይወቀሳሉ። የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማቱ የሚተቹበት ሙስና እና ብልሹ አሰራርም በዌስትጌት የገበያ ማዕከል እና የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ አይነት የሽብር ጥቃቶችን ለመከላከል እንቅፋት መፍጠራቸውን የጸጥታ ተንታኞች ይናገራሉ።


ሶማሊያውያን ለሚበዙባት የጋሪሳ ከተማ የአሸባብ ጥቃት አዲስ አይደለም። ኬንያ እና ሶማሊያ ከሚዋሰኑበት ድንበር አቅራቢያ የምትገኘው ከተማ በተሽከርካሪዎች፤የግብይት ቦታዎች እና አደባባዮች ላይ በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል። የኬንያ ፖሊስ ሰራዊት አባላት እና የጸጥታ ኃይሎችም የጥቃቱ ኢላማ ናቸው። ኬንያውያን የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተመልሶ ይከፈት አይከፈት በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያየ አቋም ነበራቸው። መሪያም ሳኪዳ ወደ ጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ከተመለሱት መካከል አንዷ ነች። መሪየም በምትኖርባት የጋሪሳ ከተማ እና የትምህርት ቤቷ ላይ አሁንም የሽብር ስጋት እንዳጠላ ይሰማታል። በእሷ እምነት ስጋቱን ለማስወገድ ሁነኛው መፍትሔ ትምህርት ብቻ ነው።
«ወደ ጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ለምዝገባ በመመለስ በጋሪሳ የሽብር እና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩም የከተማ ነዋሪዎች በመሆናችን የትም ጥለን አንሄድም የሚል መልዕክት እያስተላለፍን ነው። በዚህ ትምህርት ቤት ካለ መጥተን እንማራለን። ሰዎች ሽብርተኞችን መግደል መፍትሔ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል። በእኔ እምነት ግን ሽብርን ማቆም የሚቻለው በትምህርት ብቻ ነው።»
የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ አሁን ታድሷል። የመማሪያ ክፍሎች ግድግዳ እና የመስኮት መስታዎቶች ላይ የነበሩት የጥይት ቀዳዳዎች በቦታቸው የሉም። የአሸባብ ታጣቂዎች በርካታ የክርስትና እምነት ተማሪዎች የገደሉባቸው ክፍሎች አሰቃቂውን ትዝታ እንዳይቀሰቅሱ አገልግሎታቸው እና ስያሜያቸው ተቀይሯል።


ወደ ጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ለመመለስ የደህንነት ስጋት ያደረባት ሎቬንደር ሞሴቲ ብቻ አይደለችም። ባንሲ ዋሆሚ ቤተሰቦቿ ወደ ጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተመልሳ የጀመረችውን ትምህርት እንድታጠናቅቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ትናገራለች።

«እህቶቼ ተመልሼ እንድመጣ ፈቃደኛ አልነበሩም ወንድሜ ተቃውሞኛል። ሌላ የምትሄጂበት የሻለ ቦታ አጣሽ ወይ ብሎ ተከራክሮኛል። እኔ ግን በየትኛውም ቦታ ቢሆን ደህንነታችን ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ ነው ብዬ አላምንም። በየትኛውም ቦታ ቢሆን ለደህንነቴ ዋስትና የሚሆነው ፈጣሪ ብቻ ነው።»
የኬንያ መንግስት የተማሪዎቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ከጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ደጃፍ ቋሚ የፖሊስ ጣቢያ አቋቁሟል። አሸባብም ከማዕከላዊ ናይሮቢ እስከ ሶማሊያ ቦታ እና ስልት እየቀያየረ በኬንያውያን ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ቀጥሏል።
እሸቴ በቀለ
ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች