1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ሙሉ በሙሉ ከትጥቅ ትግል መውጣቱን ዐስታወቀ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 18 2015

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ካሁን በኋላ በስሙ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል አለመኖሩን ገለጸ፡፡ በጋምቤላ ክልል እና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ የነበረው ታጣቂ ቡድኑ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከመንግስት ጋር ከስምምነት ከደረሰ ወዲህ 205 አባላቱ ወደ ተሀድሶ ስልጠና መግባታቸውን የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ጋትሎዋክ ቡም ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4Qa6z
Karte Äthiopien Südsudan Gambella Englisch

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር በስሙ የሚንቀሳቀስ የታጠቀ ኃይል እንደሌለ አስታወቀ

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ካሁን በኋላ በስሙ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል አለመኖሩን ገለጸ፡፡ በጋምቤላ ክልል እና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ የነበረው የጋምቤላ ነጻነት ግንባር  ታጣቂ ቡድን  በሰላማዊ መንገድ ለመታገል  ከመንግስት ጋር ከስምምነት  ከደረሰ ወዲህ 205 አባላቱ ወደ ተሀድሶ ስልጠና መግባታቸውን የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ጋትሎዋክ ቡም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት በበኩሉ በሰላማዊ መንገድ ልዩነቶችን በመፍታት ታጣቂዎቹ ወደ ተሀድሶ ስልጠና መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር እና የክልሉ መንግስት ከየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ  በደቡብ ሱዳን ጁባ እና በአዲስ አበባ ውይይቶችን ካደረጉ በኃላ ከስምምት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡  የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ጋትሉዋክ ቡም በክልሉ ሰላማዊ ትግል መታገል ባለመቻሉ   ወደ ትጥቅ ትግል  መቀላቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ከመንግስት ጋር በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች በሰላማዊ መንገድ ለመቀንቀሳቀስ ወደ ጋምቤላ መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሚያዚያ 12/2015 ዓ.ም 195 የሚደርሱት ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ መፍታታቸውን አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አመራሮችን ጨምሮ ወደ 205 የሚሆኑት የታጣቂው ቡድኑ አባላት በስልጠና ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር በክልሉ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የውክልና እና እኩልነት ጥያቄ እንዳለው የተጠቀሱት አቶ ጋትሉዋክ ቡም  ከመንግስት ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም በጋምቤላ ታስረው የሚገኙ የድርጀቱ አባላት ከእስር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ ከጋ.ነ.ግ ጋር የተደረገው ስምምነት በክልሉ ሰላም ለማሰፍን ከተደረጉ ጥረቶች መካከል ከፍተኛ ስራ የሚሰጠው ነው ብሏል፡፡ ታጣቂዎች ይንቀሳቀሱበት የነበረው ስፍራ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችም ከጸጥታ ችግር ስጋት ተላቆ  ወደ ልማት የሚመለሱበት ወቅት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ስልጣን የሚገኘው በህዝብ ድምጽ ብቻ መሆኑን፤ ልዩነቶችን ደግሞ  በውይይት ለመፍታት ከቡደኑ ጋር መስማማታቸውን ጠቁሟል፡፡ ታጣቂዎቹም  ለስጠልና ወደ ቦንጋ የተላኩ መሆናቸውን እና  በተመረጡ ዘርፎች እንደሚሰማሩ ተናግረዋል፡፡

ሰኔ 7/2014 ዓ.ም የጋምቤላ ነጻነት ግንባር እና የክልሉ ጸጥታ ሀይሎች መካከል በጋምቤላ ከተማ በተፈጠረው ግጭት በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በወቅቱ 50 የሚደርሱ ሰዎች ህይወት በክልሉ ጸጥታ ሀይሎች  መጥፋቱን ይፋ አድረጓል፡፡ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ካሁን በኃላ በስሙ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ሀይል እንደማይኖርም ገልጸዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሀመድ