የጊኒ ጥሬ ሃብት | ጤና እና አካባቢ | DW | 12.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የጊኒ ጥሬ ሃብት

ምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ጊኒ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ሀገር ናት። በአለም ዙርያ ከርሰምድር ዉስጥ ከሚገኘዉ ቦክሳይት ማለት የአልሙንዩም ንጥረ ነገርን የያዘ ድንጋይ ሁለት ሶስተኛዉ በጊኒ ከርሰ-ምድር ይገኛል።

የአልሙንየምን በዉስጡ የያዘዉ ቦክሳይት የተሰኘዉ ንጥረ ነገር በዓለማችን ገበያ ላይ በተለይም በመኪና ምርት ኢንዱስትሪ እጅግ ተፈላጊ ነዉ። ግን የጊኒ 14 ሚሊዮን ህዝቧ ሀገሪቱ ከቦክሳይት ማዕድን የዉጭ ገበያ ገቢ የሚያገኙት ጥቅም እጅግ ጥቂት ነዉ። ጊኒ አሁንም እጅግ ደሃ ከተሰኙት 20 የዓለም ሀገራት አንዷ ናት። የሀገሪቱ ፕሪዚደንት አልፋ ኮንዴ በአዲሱ የጥሪ ሃብት ፖሊቲካ የአገራቸዉን ገፅታ ለመቀየር መነሳታቸዉ ተገልጾአል።

ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ስልጣን ላይ ያሉት ፕሪዚደንት አልፋ ኮንዴ በዲሞክራሲ መንገድ የተመረጡ የመጀመርያዉ የጊኒ ፕሪዝዳንት ናቸዉ። የዶቼ ቬለዉ ቦብ ቤሪ ከጊኒ መዲና ኮናክሪ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘዉ ዴቤሊን የማዕድን ማዉጫ ተጉዞ ቦክሳይት ማዕድንን ለማዉጣት የሚደረገዉን ትግል እና ከንጥረ ነገሩ ማን ተጠቃሚ መሆኑን ያስቃኘናል። ዴቤሊን የማዕድን ማዉጫ በምዕራባዊ ጊኒ ኪንዲአ ክፈለ-ግዛት በሚገኝ አነስተኛ ቦታ ላይ ይገኛል። የማዕድን ማዉጫዉ አካባቢ የማንጎ ዛፍ እንዲሁም ሌሎች ትላልቅ የፍራፍሪ ዛፎች ይገኛሉ። የመሪቱ አፈር ቀይ እና የተቃጠለ ዓይነት ሽታም አለዉ። በዝያ አፈር ዉስጥ ነዉ አልሙንዩም ንጥረ ነገርን የያዘዉ ቦክሳይት የተሰኘዉ የጊኒ እጅግ ግዙፉ የተፈጥሮ ሃብት ተደብቆ የሚገኘዉ።

ከሃያ አመታት በላይ የሩስያ ኩባንያዎች በሀገሪቱ ንጥረ ነገሩን ከከርሰ ምድር በማዉጣት ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት ሩሳል የተሰኘዉ የሞስኮዉ ኩባንያ ቦታዉ ላይ ይገኛል። መሃመድ ሲላ በዚህ ማዕድን ማዉጫ ዉስጥ መስራት ከጀመረ አምስት ዓመታትን አስቆጥሮአል።

«የምርት ክፍል ሃላፊ ነኝ። የማዕድን ማዉጫዉን ማሽን በታቀደዉ ርቀት እና ዕቅድ መስራቱን እቆጣጠራለሁ። » ሲላ ብርሃን የሚያንፀባርቅ ቢጫ የመከላከያ ሰደርያ እና በአደጋ ግዜ የራስ ቅል መከላከያ ብርቱካናማ ቆብ አጥልቆአል። የሀገሪቱ ሃብት አልሙንዩም ንጥረ ነገርን የያዘዉ ቦክሳይት ማዕድንን ከሚገኝበት አካባቢ የመጣ በመሆኑም የማዕድኑ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆንን ይፈልጋል። «የምናገኘዉ ደምወዙ በቂ አይደለም። በቤተሰብ ዉስጥ እጅግ ችግር አለብን። በወሩ መጨረሻ የተከፈለን ሁሉ ስለሚያልቅ፤ ለኑሮ በቂ አይደለም»

በዚሁ የማዕድን ማዉጫ የፈረቃ ሃላፊ የሚሰራዉ ወጣት ጀምስ ካማራ ሁኔታ ደግሞ ከዚህ ለየት ያለ ነዉ። ጀምስ የከፍተኛ ትምህርቱን በሞስኮ ሲያጠናቅቅ፤ አንድ የጊኒ ፍራንክ እንኳ አልከፈለም። ይኸዉ የሩስያ ኩባንያ ነዉ የነፃ ትምህርት ዕድልን ሰቶት ትምህርቱን አጠናቆ ወደ አገሩ ለመመለስ የበቃዉ። ጀምስ ካማራ ዛሪ በ 32 ዓመቱ የመጀመርያ ስራዉን በሩስል የማዕድን ማዉጫ ይዞ፤ በቀን ዉስጥ ያለዉን የስራ ሂደት ይቆጣጠራል። ካማራ አባቱ በዚሁ ማዕድን ማዉጫ ይሰሩ እንደነበር እንዲህ ያስታዉሳል። «ሩሳል ለሰራተኞቹ በፃፈዉ ደብዳቤ፤ ለሰራተኞቹ ልጆች አንድ ዉድድር እንደሚያደርግ አስታወቀ። በዚህ ዉድድር የሂሳብ፤ የፊዚክስ እና የኩሚስትሪ ፈተናን ማለፍ ነበረብን። ከዝያም የነፃ ትምህርት ዕድልን ያገኙ አምስት ልጆች ተመረጥን» ከዛሪ አንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ወጣቱ የፈረቃ ተቆጣጣሪ ሲሆን፤ ከከርሰ ምድር የሚወጣዉን ቦክሳይት ማዕድን እንዲት እንደሚወጣ እና እንዴት በተሽከርካሪ ተጭኖ እንደሚመላለስ ይቆጣጠራል።

እንደ ሩሳል የማዕድን ማዉጫ ኩባንያ ገለፃ ቦክሳይት ማዕድን በዓለም ገበያ ላይ በመርከሱ ምክንያት፤ ማዕድኑን የማዉጣቱን ስራ ወጭ መቀነስ እንደሚፈልግ ይገልጻል። ስለዚህም ኩባንያዉ ከጀርመን ተንቀሳቃሽ የመቆፈርያ እና የመዛቅያ ገልባጭ መኪና ማሽንን ገዝቶአል። የፈረቃ ተቆጣጣሪዉ ካማራ በኩራት ፈገግታ አንዱን ገልባጭ በማሳየት ማሽኑ መሪት በመቆፈር በመቦርቦር እና በመዛቅ ስራዉን እንዴት እንደሚያቀላጥፍ ይገልጻል። ይህ ገልባጭ መኪና ማዕድኑን ከመሪት ዝቆ በማዉጣት በመሰባበርና መኪና ላይ በመጫን በአንድ ግዜ ሶስት ስራን በፍጥነት ያከናዉናል። «ይህ ማሽን በአንድ ሰዓት ዉስጥ 750 ቶን ማዕድን የያዘ አፈር ቆፍሮ ማዉጣት ይችላል-በዚህ ሂደት እስከ 7 የጭነት መኪና ሙሉ የያዘ አፈር ማጋጋዝ እንችላለን።»

በዚህ ዘዴ ሩስል የማዕድን ማዉጫዉን ሰዓት እስከ ሰባ በመቶ መቀነስ እንደሚቻል ካማራ ይናገራል። በዚህ ዉጤትም ወደ 300 ያህል የማዕድን ማዉጫ ኩባንያዉ ሰራተኞች የስራ ቦታቸዉን ማጣታቸዉን የአገሪቱ ሰራተኛ ማህበራት ይገልጻሉ። በዚህም ሰራተኛዉ አዲሱንና ፈጣኑን የመቆፈርያ ገልባጭ መኪና እጅግ ሲጠላ፤ የሩሳል አስተዳዳሪዎች ግን ይወዱታል። አልፎ አልፎ ብቻ ነዉ ይህ የመቆፈርያ መሳርያ ብልሽት የሚያጋጥመዉ ወይም ስራን የሚ ያቆመዉ ሲል ጀምስ ካማራ ይገልጻል፤ «አሁን በዝናባማ ወራት ቦክሳይት ማዕድኑ ከአፈር ጋር ተደባልቆ ስለሚጨቀይ የመቆፈርያ ማሽን ለመጠቀም ባጣም አዳጋች ሁኔታን ፈጥሮብናል። ስለዚህም ማሽኑ ቆፍሮ ድንጋዩን እያወጣ፤ በትንሽ በትንሹ ሲባብሮ ፤መኪና ላይ ሲጭን፤ ማሽን ዉስጥ የጨቀየዉ ድንጋይ እንዳይወተፍ፤ በማሽኑ ላይ ያላማቋረጥ ወሃ እናፈሳለን።»

ትንሽ ሜትር ራቅ ብሎ በጥሞና ለሰራተኞች ትዕዛዝ በመስጠት ላይ ያለዉ ማማዱ ቤሪን እናገኛለን። ማማዱም እንዲሁ በጊኒ መንግስት በኩል በተሰጠዉ የነፃ ትምህርት ዕድል፤ በሩስያ ሳንት ፒተርበር ዩንቨርስቲ በማዕድን ፍልጋ ሞያ ትምህርቱን ጨርሶ በጊኒ የማዕድን ማዉጫ ዉስጥ ከሚገኙት ወጣት ስራ አስኪያጆች መካከል ተሰልፎአል። ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላም በሩሳል የማዕድን ማዉጫ አንድ ሩስያዊ የስራ አስኪያጅን ተክቶ ምርት ክፍሉን በማስተዳደር ላይ ይገኛል።

«እዚህ ስራ እንተቀጠርኩ በቂ ደምወዝ አላገኝም ነበር። አሁን ግን በቂ የስራ ልምድ ስላለኝ ደምወዜ ጨምሮአል፤ በአሁኑ ሰዓት ደስተኛ ነኝ። በቂ ገንዘብ ስለማገኝ ትዳር መስርቼ አሁን አንዲት ሴት ልጅ አለችኝ።

Conakry: Hôtel de l’Indépendance – das größte Hotel Guineas Foto DW/Bob Barry. Die Bilder aus Conakry, der Hauptstadt des westafrikanischen Guinea hat DW-Mitarbeiter (Volo) Bob Barry im Februar 2010 gemacht

አሁን በዘመናዊዉ የማዕድን ማሽን ሳይሆን በባህላዊ መንገድ ድንጋይ ወደ ሚፈለጥበት የማዕድ ማዉጫ ስፍራ ደግሞ እናመራለን። ቦታዉ በመኪና የጥቂት ደቂቃዎች መንገድ ርቀት ላይ ይገኛል። በማዕድን ማዉጫዉ ስፋራ የለዉ አየር የተቃጠለ የመሪት ሽታ ያዘለ ነዉ። በጥቂት ደቂቃዎች ዉስጥ ጥቁር የለበሰዉ ኢንጂኔር፤ ጎኒካ ቶሪ በድማሚት ማዕድኑን ስለሚያነጉድ ከአካባቢዉ መራቅ እንዳለብን ተነገረን፤ ከፍንዳታዉ በኋላ ጥቁር እና ፍም የመሰለ ጭስ ድንጋዩን አለበሰዉ። ኢንጂኔሩም በኩራት የስራዉን ዉጤት ሄዶ ተመለከተ። «ከስምንት አመት ጀምሮ ድማሚት የሚቀበርበትን ጉድጓዶች በተመለከተ ሃላፊነቱን ወስጄ እሰራለሁ። ይህ ስራ በርግጥ ለህይወት እጅግ አደገኛ ነዉ። ዓለት ድንጋዪ በአንድ በኩል ብቻ ከፈነዳ፤ ጭንቅላትህን ሊያገኝህ ይችላል። ፍንዳታዉ ከተከናወነና ዓለቱ ከተሰባበረ በኋላ መኪኖች መጥተዉ የተሰባበረዉን ድንጋይ ሰብስበዉ ለፋብሪካ ያቀርባሉ» ቶሪ የጠቀሱት ፋብሪካ እዝያዉ ዓለቱ በተሰባበርት አካባቢ የሚገኝ ፋብሪካን ነዉ። በፋብሪካዉ ትልልቁ ዓለት በትንሽ ትንሽ እስኪሰባበር ብዜ ግዜን ይወስዳል። ለዝያም ነዉ ሩሳል የማዕድን ማዉጫ ዘመናዊዉን የድንጋይ መሰባበርያ ገልባጭ መኪናን መጠቀም የጀመረዉ። ማዕድኑ የያዘዉ ድንጋይ ከሚሰባበርበት ቦታ ወጣ ብሎ ግቢዉ ደጃፍ በሚገኘዉ የመግብያ መቆጣጠርያ አካባቢ ሰራተኞች ሲጋራ፤ ዉሃ አልያም ፤የሚበላ ዳቦ መግዛት ይችላሉ። አንድ ወጣት አንድ የማንጎ ዛፍ ስር ካለ አነስ ያለ ግንብ ላይ ተቀምጦአል። አሴኒ ካማራ ይባላል፤ በእቃ መጫኛ ባቡር ሊጫን የተዘጋጀዉን የቦክሳይት ማዕድንን የያዘዉን የተሰባበረ ድንጋይ አተኩሮ ይመለከታል። ካማራ በአካባቢዉ ከሚገኘዉ እጅግ ብዙ ስራ አጥ ቡድኖች መካከልም አንዱ ነዉ። እንደሱ አባባል ጥሪ ሃብት በታደለዉ የትልዉድ ሀገሩ ሥራ ማግኘት አለመቻሉ፤ ሊገባዉ የማይችል ጉዳይ ነዉ።

«በደብሌን የሚገኙ በርካታ ወጣቶች አሁንም ስራ ማግኘት አልቻሉም፤ ሁላችንም በሞያ ሰልጥነናል፤ ሩሳል ስራ ለማግኘት እንዲረዳን እንጠይቃለን» በትዉልድ ቀየ አካባቢ ስራን ማግኘት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አልሴኔ ይገላጻል። እንደ በርካታ የጊኒ ተወላጆች የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ሀገርን ጥሎ ላለመሄድ ወደ አዉሮጳ ላለመሰደድና በግዴታ ስራን ማግኘት አስፈላጊ ነዉ። ሌላዉ የጊኒ ዜጋስ ኑሮዉ እንዴት ነዉ? በተፈጥሮ ሃብት ከታደለችዉ ሀገራቸዉ ድርሻቸዉ ምንድን ነዉ?

ጥሪ ማዕድኑ ከሚወጣበት የአንድ ሰዓት የመኪና ጉዞ አድርገን 200, 000 ህዝብ በሚኖርባት የአዉራጃ ዋና ከተማ ኪንዲያን ጎበኘን። ከተማዋ በአረንጓዴ ሰንሰለት ተራራ ተከባ ከሩቅ ትታያለች። ኪንዲያ በጊኒ በፍራፍሪ እና በቅጠላቅጠል ምርቱ ታዋቂ ነዉ። በተፈጥሮ የበቀለ የማንጎ ዛፍ ለማግኘት እና በጆንያ ሙሉ ፍራፍሪ ለመሰብሰብ ደን ዉስጥ ዘልቆ መግባት አያስፈልግም። ግን ኪንዲያ ፍራፍሪ የሞላባት ገነት ብቻ ሳትሆን በዓለም ከሚገኙት የቦክሳይት ማዕድን ምንጭ አንዷም ነች።

ከተማዉ መግብያ ላይ በሚገኘዉ በአንድ ያረጀ ህንጻ ዉስጥ ገባን። ወደ ቢሮዎቹ ዘልቆ ሲገባ ኮሪደሩ በጨለማ ተዉጦአል፤ ኤሌትሪክ በመጥፋቱ ነዉ። በቢሮ ዉስጥ በእድሜ ጠና ያሉ ባለስልጣኖች ተቀምጠዋል፤ በቢሮ ዉስጥ የሚገኘዉ የመጸሃፍ መደርደርያ ላይ የተቀመጡት መዝገቦችም አቧራ ለብሶ ይታያል።

ሩሳል በጊኒ መንግስት እና በማዕድን ማዉጫዉ መካከል ስምምነት እንደሚደረግ እና ሩሳል ከሚያገኘዉ የቦክሳይት ምርት 0,01 በመቶዉን ይሰጣል። ይህ ማለት ከአንድ መቶ ቶን የቦክሳት ምርት አንድ አንድ ዩኤስ ዶላር ነዉ የሚያገኙት ማለት ነዉ። ይህ እንደሩሳል በዓለም ላይ ታዋቂ ለሆነ ኩባንያ ደግሞ ብዙ አይደለም። ይህ ገንዘብ ወደ ዋናዉ ተጠሪ ቢሮ መግባት ነበረበት ግን ለረጅም ግዜ ተፈፃሚ አልሆነም ነበር ይላሉ ዋና ተጠሪ ድራማኒ ኮንዴ «ይህ የሩሳል ስህተት አይደለም። እጎአ 2008 ዓ,ም ወታደሮች ወደ ስልጠና መጡ። ከዝያ ነዉ ገንዘቡ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ገቢ አልፈቀዱም። ሁኔታዉ በተረጋጋ መልኩ ዲሞክራስያዊ መንገድን ተከትሎ ገቢ እንዲሆን ነዉ የፈለጉት። ልክ አሁን እንደሚሆነዉ » አልፋ ኮንዴ ከጎአ 2010 ዓ,ም ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉ ለመጀመርያ ግዜ በዲሞክራስያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሪዚደንት ናቸዉ። ሩሳል የተሰኘዉ ድርጅት በአሁኑ ወቅት በማዕድን ማዉጫዉ አካባቢ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል ገንዘቡንም መክፈል ጀምሮአል። ድርጅቱ በ 2012 ዓ,ም ላይ ይህ ኩባንያ ሁለት የገጠር አካባቢዎች ኤሌትሪክ እንዲዘረጉ እንዲያስችላቸዉ 350,000 ይሮ ወጭ አድርጎአል። ከነዚህ የገጠር አካባቢዎች መካከል አንዱ ማንቢያ ነዉ። ማንቢያ መንደር ወደ መዲና ኮናክሪ በሚወስደዉ መንገድ አቅጣጫ የምትገኝ በጭቃ የተሰሩ ቤቶችን የያዘች አነስተኛ ማህበረሰብ የሚገኝባት ገጠር ናት። የቦክሳይት ማዕድን ማዉጫዉ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በአብዛኛዉ የሚተዳደሩት በእርሻ ሲሆን እርሻቸዉ አረንጓዴ ለብሶ ይታያል። ካንዴ ኦማር ካማራ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ተጠሪ ነዉ።

«ሩሳል ድርጅት ትምህርት ቤቶችን ገንብቶአል፤ አንድ የህክምና ማዕከልን አቋቁሞአል፤ ለመንደሩ የመብራት ሃይል ዘርግቶአል። ይህ ለብዙ ጥቃቅን ድርጅቶች የተሻለ እንዲቀሳቀሱ ጠቀሜታን ሰጥቶአል።» ለብዙ ፕለቲከኞች ግን ይህ በቂ አይደለም። አካባቢዉ ላይ የሚመረተዉ አብዛኛዉ የቦክሳይት ማዕድን ምርት ገቢ ሀገሪትዋ ዉስጥ እንዲቀር ይጠይቃሉ። በዚህም ምክንያት በጊኒ እንደ ጎ,አ 2011 ዓ,ም ከመስከረም ወር ጀምሮ በመዓድን ሃብት ዙርያ አዲስ ህግ ጸድቆአል። ይህም የማዕድን አዊጭ ኩባንያዎች ለመንግስት እስከ 30 በመቶዉን ገቢ እንዲሰጡ ይወስናል። በጊኒ በስትራቴጂ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት ኦስማኔ ካባ ሩሳል የማዕድን አዉጭ ድርጅት ይበልጥ መክፈል ይገባዋል ባይ ናቸዉ።

Conakry: Palais des Nations im Zentrum Kaloum. Foto DW/Bob Barry. Die Bilder aus Conakry, der Hauptstadt des westafrikanischen Guinea hat DW-Mitarbeiter (Volo) Bob Barry im Februar 2010 gemacht

«እንደሚታወቀዉ ማዕድኑ የጊኒ ሃብት ነዉ። ለዚህም ነዉ ከሩሳል ጋር የተለያየ የሃሳብ አቋም ይዘን የምንገኘዉ። ጥናቶች እንዳረጋገጡት ጊኒ ከማዕድን ሃብትዋ ምንም ጥቅም ያላገኘችበት ሩሳል የማዕድን ድርጅት ባለፉት ዓመታት ካወጣዉ እና ጥቅም ላይ ካዋለዉ የማዕድን ሃብት ገቢ ለጊኒ ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር ማካካሻ ገንዘብ መክፈል ይኖርበታል። ፓቬል ቫዚሊፍ የሩስያዉ የማዕድን አዉጭ ድርጅት ሩሳል የአፍሪቃዉ ክፍል ተጠሪ በዚህ ጉዳይ አይስማሙም። «አዲሱ የማዕድን ጉዳይ ህግ የማዕድን አዉጭ ድርጅቶች ን የሚቸቁን ነዉ። በዓለም ዙርያ በዓልሙንየም ንግድ በደረሰ ቀዉስ ምክንያት የአልሙንየም ማዕለ ንዋይ አፍሳሾች በጊኒ በወጣዉ ንግድ ምክንያት አገሪቲን ለመልቀቅ ተገደዋል። » አሁንም ቢሆን የአልሙንየም ማዕድን የያዘዉን ቀይ ድንጋይ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ቀን በቀን ኪንዳ ከተማን እየለቀቁ በመዉጣት በኮናክሪ ወደብ መርከብ ላይ በመጫን ወደ ዩክሪይን አቅጣጫ ይላካሉ። በዩክሪይን ቦክሳይት ከተሰኘዉ ማዕንድ አልሙንየም ተመርቶ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይሰራጫል። ጊኒ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት ከ53 ዓመት በኋላ ዛሪም ክብር ያለዉን ቀይ መልክ የያዘዉን የጥሪ ሃብቷን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ኢንዱስትሪ የላትም።

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic