የጊኒ የምርጫ ዉዝግብ | አፍሪቃ | DW | 14.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጊኒ የምርጫ ዉዝግብ

የአዉሮጳ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በጊኒ የተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተዓማኒ መሆኑ አስታወቀ። የሀገሪቱ የተቃዉሞ ፖለቲካ ፓርቲ እጩዎች በበኩላቸዉ ምርጫዉ ተጭበርብሯል ተቀባይነት የለዉም እያሉ ነዉ። በመገናኛ ብዙሃን ይፍ የሆነዉ የመጀመሪያ የምርጫ ዉጤት ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ እየመሩ መሆናቸዉን ያመለክታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:06
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:06 ደቂቃ

የጊኒ ምርጫ

የኅብረቱ ታዛቢ ቡድን ምርጫዉ ተዓማኒ ነዉ ቢልም በሂደቱ ላይ የታዩ ጉድለቶችንም ጠቁሟል። ያም ቢሆን ግን የእሁዱን ምርጫ አጠቃላይ ዉጤት ጥያቄ ላይ የሚጥል እንደማይሆን አመልክቷል። የአፍሪቃ ኅብረት ታዛቢ ቡድንም ተመሳሳይ መግለጫ ነዉ የሰጠዉ።

ጊኒ አመፅ በተቀላቀለዉ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የምትታወቅ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሃገር ናት። በፈረንሳይ ቅኝ በመገዛትዋም ቀደም ባሉት ጊዜያት የፈረንሳይ ጊኒ ስትባል ኖራለች። ከጊኒ ቢሳዎ እና ከኢኳቶሪያል ጊኒ እንድትለይ ደግሞ ጊኒ ኮናክሪ በመባል ትታወቃለች። ከፈረንሳይ የቅኝ ተገዢነት በጎርጎሪሳዊዉ 1958ዓ,ም ነፃ ከወጣች ወዲህ ጊኒ ኮናክሪ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስታካሂደ ሁለተኛዋ መሆኑ ነዉ።ፈረንሳይኛን ለብሔራዊ ቋንቋነት የምትጠቀመዉ ይህች ሀገር የራሷ የሆኑ 24 ቋንቋዎችም ይነገሩባታል።

Wahlkampf Guinea 2015

በምርጫ ቅስቀሳዉ ወቅት

እሁድ ዕለት በሀገሪቱ የተካሄደዉን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የተከታተለዉ የአዉሮጳ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች እጥረት እና የምርጫ ጣቢያዎች ዘግይተዉ መከፋቸዉን እንደእንከን ይጠቅሳል። የኅብረቱ ታዛቢ ቡድን መሪ ፍራንክ ኤንግልስ ሁለት ሶስተኛዉ የምርጫ ጣቢያ በአስፈላጊ ቁሳቁሶች እጥረት ዘግይቶ መከፈቱን፤ አንዳንዱም ጋየድምጽመክተቻሳጥንእንዳልነበርአመልክተዋል። ያ ማለት ግን የተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል ዉጤቱን ጥያቄ ላይ የሚጥል አይደለም እንደኤንግልስ።ምክንያቱ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በአብዛኛዉ የምርጫ ጣቢያ ተገኝተዋል፤ ድምፅ ቆጠራዉም በአመዛኙ ግልፅ ነበር ሲሉ እማኝነታቸዉን ሰጥተዋል።የአፍሪቃ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድንም የአዉሮጳ ኅብረት ታዛቢ ቡድን የሰጠዉን አስተያየትና ትዝብት እንደሚጋራ አስታዉቋል።የሀገሪቱ የተቃዉሞ ፖለቲካ አባላትና ደጋፊዎች ግን ምርጫዉ ተጭበርብሯል ተቀባይነት የለዉም እያሉ ነዉ።የቻተም ሃዉሱ የፖለቲካ ተንታኝ ፖል ሜሊ ተቃዋሚዎቹ አጠቃላይ የምርጫዉ ዉጤት ከመነገሩ አስቀድመዉ ተጭበርብሯል በሚል ያወገዙበት ምክንያት ታሪካዊ ይዘት አለዉ ይላሉ።

«አንደኛዉ የጊኒ ታሪክ ነዉ። ይህ በታሪኳ ሁለተኛዉ ዴሞክራሲ መሰል ምርጫ ነዉ። እስከ 2009 እና 2010 ድረስ ጊኒ አምባገነት መንግሥት ነበረች፤ ከአምስት አሰርት ዓመታት በላይም ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የነበራት፣ምርጫ ቢካሄድም ሙሉ በሙሉ የሚጭበረበር፤ ያን ያህል የፖለቲካ ምርጫ እንዲኖር የማይፈቅድ ነፃነት የሌለባት ነበረች።ስለዚህ በተቋማቱ ላይ እምነት ለማሳደር ሂደቱ በጣም አዝጋሚ ነዉ።»

Präsidentenwahl Guinea Alpha Condé

ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ

በዚህም ላይ ይላሉ ሜሊ ፕሬዝደንት ኮንዴ ራሳቸዉ ነገሮችን አቻችሎ ለመስማማት ከመቅረብ ይልቅ ጫና የሚያደርጉም ይመስላል። የዛሬ አምስት ዓመት ከተመረጡ በኋላም መድበለ ፓርቲን የሚፈቅዱ ዓይነትም አልሆኑም። የምርጫ ኮሚሽኑ አወቃቀርም ፖለቲከኞቹን ሲያጨቃጭቅ የቆየ ጉዳይ ነዉ። ምንም እንኳን የምርጫዉ ታዛቢዎች ሂደቱን ተከታትለዉ አስተያየታቸዉን ቢሰጡም፣ እንደፖል ሜሊ አባባል፣ ምርጫ ላይ የሚፈፀመዉ ጫና አስቀድሞ የሚከናወን ነዉ።

«ታዛቢዎች በእርግጥ በምርጫዉ ወቅት የሚከናወኑ ተግባራትን እና የምርጫዉንም ቴክኒካዊ አካሄድ መከታተል ቢችሉም ምርጫ ላይ የሚፈፀም አብዛኛዉ ተፅዕኖ የሚከናወነዉ እጅግ አስቀድሞ ነዉ። የፖለቲካ ተሳታፊና እጩዎች ማግኘት የሚገባቸዉ መገናኛ ብዙሃንን መጠቀምን በተመለከተም ስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ በጣም ሰፊና ጠንካራ ሽፋን ተሰጥቷቸዋል።»

በሀገሪቱ ራዲዮ ጣቢያዎች ሰኞ ዕለት ይፋ የሆነዉ የምርጫዉ የመጀመሪያ ዉጤት ስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ ተፎካካሪዎቻቸዉን በሰፊ ልዩነት እንደሚመሩ አመልክቷል። የምርጫ ታዛቢዎችም ተቃዋሚዎች ምርጫዉ ተጭበርብሯል ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ ወደጎን በማድረግ ተዓማኒ እንደሆነ ገልጸዋል።

Guinea Conakry Wahlen Cellou Dalein Diallo

የተቃዉሞ ፖለቲከኛዉ ሴሉ ዳሊን ዲያዮ

በሌላ በኩል ግን ምናልባት የመለያ ምርጫ ሊካሄድ ይችል ልሆናል የሚል ግምት አለ። አጠቃላይ ዉጤቱ ይፋ ከመሆኑ በፊት የቀረበዉ የታዛቢዎቹ አስተያየት ተፅዕኖ ማስከተሉ እንደማይቀር ሜሊ ይናገራሉ።

«አንደኛ ተቃዋሚዎች በተሳትፏቸዉ እንዲቀጥሉ ያደርጋል። ድጋሚ ምርጫ ማካሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ ዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች አንሳተፍም ለማለት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። አልፋ ኮንዴን ድጋሚ ለመፎካከር አንሳተፍም ካሉ የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ እንደሌላቸዉ ያዉቃሉ።»

የዛሬ አምስት ዓመት በተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የዋናዉ የተቃዉሞ ፖለቲካ ፓርቲ የጊኒ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት እጩ ሴሉ ዳላን ዲያሎ እና ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ በድጋሚ ተፎካክረዋል። በአሁኑ ምርጫ ግን እስካሁን ግልፅ የወጣ ነገር የለም። ሰባት የተቃዋሚ ፓርቲ እጪዎች ናቸዉ የተወዳደሩት። 10,5 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት የሚነርላት ጊኒ ከአንድ ዓመት በላይ በምዕራብ አፍሪቃ በኤቦላ ተሐዋሲ ክፉኛ ከተጎዱ ሃገራት አንዷ ናት።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic