የጊኒ ቢሳው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ | ኢትዮጵያ | DW | 27.06.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የጊኒ ቢሳው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ

የመምረጥ መብት ያላቸው ስድስት መቶ ሺህ የጊኔ ቢሳው ዜጎች በነገው ዕለት በሀገሩ በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ በተወዳዳሪነት ከቀረቡት አስራ አንድ ዕጩዎች መካከል አንዱን ይመርጣሉ።

default

የኩምባ ያላ የምር ጫ ጣቢያ

ቀጣዩ ተመራጩ ፕሬዚደንት በሀገሪቱ ተሀድሶ ለውጥ ማንቀሳቀስና በሀገሪቱ በተስፋፋው ህገ ወጡ የዕጸ ሱስ ንግድ አንጻር ርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል።

--------

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፡ የቀድሞው ፕሬዚደንት ዦአኦ ቪየራ በጦር ኃይሉ ከተገደሉ ከአራት ወራት በኋላ ፡ እንዲሁም፡ የመፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል አንድ ዋነኛ ፕሬዚደንታዊ ዕጩ እና አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በምርጫው ዘመቻ ወቅት ከተገደሉ በኋላ የወታደራዊው መንግስት መሪዎች ምርጫው በነገው ዕለት እንዲደረግ መፍቀዳቸው ራሱ እንደ ትልቅ እመርታ ተቆጥሮዋል፣ ምክንያቱም በዚሁ ድርጊታቸው ቢያንስ የሀገሪቱን ህገ መንግስት አክብረዋል። ምርጫው፡ ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ስርዓተ ዴሞክራሲን መትከል እና በህገ ወጥ ሱስ አስያዥ ዕጽ ንግድና በተቀናቃኝ የጦር ኃይሉ ቡድኖች መካከል በቀጠለው ውዝግብ ሰበብ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ማብቃት መቻልዋ የሚፈተንበት ይሆናል። ይሁን እንጂ ፡ ምርጫው በሀገሪቱ የፖለቲካ ተሀድሶ ለውጥ ያስገኛል ተብሎ አይጠበቅም። ምክንያቱም፡ የጊኒ ቢሳው አመራር ስልጣን አሁንም ያለው በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ባሳረፈውና ስምንት ሺህ ወታደሮች ባሉት የጦር ኃይል እጅ ነውና።
በፕሬዚደንታዊው ምርጫ በተወዳዳሪነት ከቀረቡት አስራ አንድ ዕጩዎች መካከል ደህና የማሸነፍ ዕድል አላቸው የሚባሉት ሶስት ዕጩዎች ሲሆኑ፡ የመጀመሪያው ሀገሪቱን ከመፈንቅለ መንግስት በኋላ እአአ ከ 1999-2000ዓም በጊዚያዊ ፕሬዚደንትነት ያገለገሉት በምህጻሩ ፔኤአይጂ ሲ የሚባለው የትልቁ የነጻነት ፓርቲ ዕጩ ማላም ባካይ ሳኛ ናቸው። ሳኛ በጊኒ ቢሳው ዘላቂነት የሚኖረው መረጋጋት እንዲወርድ ከተፈለገ የጦር ኃይሉ ትልቅ ርምጃ ማበርከት እንዳለበት ነው የሚናገሩት።
« ሰላም ከፈለግን በኃይሉ ተግባር መጠቀም አንችልም። የጦር ኃይሉም የበኩሉን ድርሻ ማበርከት አለበት። ይህ ገሀድ ይሆን ዘንድ ውይይት የሚካሄድበትን መንገድ ማመቻቸው ይኖርብናል። »
ከነገው ምርጫ በኋላም ገዢው የነጻነት ፓርቲ ፒ ኤ አይ ጂ ሲ በሀገሪቱ ጠንካራው ፓርቲ ሆኖ እንደሚቆይ የፓርቲው ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚንስትሩ ካርሎሽ ጎሜሽ ገልጸዋል።
« ፒ ኤ አይ ጂ ሲ ካለሁለተኛ ዙር ምርጫ እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ነኝ። እስካሁን እንደታየው በምርጫ ወቅት አሸንፋለሁ ብየ ከተናገርኩ ሁሌ አሸንፋለሁ። »
ሌላው ፕሬዚደንታዊ ዕጩ የትልቁ ጎሳ ባላንተ ጎሳ ድጋፍ ያላቸውና ካሁን ቀደም ሳኛን በምርጫ አሸንፈው እአአ በ 2003 ዓም እስከተወገዱበት ጊዜ ድረስ በስልጣን የቆዩት የቀድሞ የፍልስፍና ፕሮፌሰር ኩምባ ያላ ናቸው። ኩምባ ያላም ልክ እንደ ተፎካካሪያቸው ማላም ባካይ ሳኛ በጊኒ ቢሳው ሰላም ለሚወርድበት አሰራር ትኩረት ሰጥተዋል።
« የኛ ፓርቲ ለልማት፡ ለሰላም፡ ለመቻቻል፡ ለዴሞክራሲና ለውይይት መዳበር የሚሰራ ፓርቲ ነው። »
ኩምባ ያላ ከሰላሳ አምስት ዓመት የፒ ኤ አይ ጂ ሲ አገዛዝ በኋላ በሀገሪቱ የተሀድሶ ለውጥ ለማካሄድ ዕቅድ እንዳላቸው ነው የምርጫ ዘመቻው እስካበቃበት እስከትናንቱ ዕለት ድረስ ሲያስተጋቡ የቆዩት። ሌላው የሀገር መሪነቱን ስልጣን የመያዝ ዕድል ሊኖራቸው ይችላሉ የሚባሉት ሶስተኛው ዕጩ ደግሞ የድሆቹን የጊኔ ቢሳው ዜጎች የኑሮ ሁኔታን እንደሚያሻሽሉ ቃል የገቡትና እስከ 2005 ድረስ በምክትል ፕሬዚደንትነት የሰሩት ኦንሪኬ ፔሬራ ሮዛ ናቸው።
በጊኔ ቢሳው አንድ ፕሬዚደንታዊው ዕጩ የብዙ መራጭ ድምጽ አግኝቶ ቢያሸንፍም ከአንዱ ወይም ከሌላው የጦር ኃይሉ ቡድን ድጋፍ ከሌለው በስተቀር ስልጣኑን በርግጥ በስልጣኑ መስራት መቻሉ አዳጋች እንደሚሆን ወደ ፖርቱጋል የሸሹ አንድ የቀድሞ የሀገሪቱ ባለስልጣን አስረድተዋል። የተከፋፈለው የጊኒ ቢሳው የጦር ኃይሉ ብዙ ጊዜ የጊኒ ቢሳውን አለመረጋጋት እና በሚገባ ቁጥጥር የማይደረግባቸውን የሀገሪቱን ደሴቶችንም ዕጸ ሱስን ኮኬይን ወደ አውሮፓ ለማሸጋጋሪያ ከሚጠቀሙባቸው ከኮሎምቢያ የኮኬይን ህግ ወጥ ንግድ አራማጆች ከፍተኛ ድጋፍ ያገኛል። በዚህም የተነሳ ቀጣዩ የጊኒ ቢሳው ፕሬዚደንት አንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን ህዝብ የሚኖርባትን ሀገር ከክሽፈት መጠበቅ በጦር ኃይሉ ውስጥ ተሀድሶ ለውጥ የማድረግና ተጽዕኖዋቸውን በሀገሪቱ ባሳረፉት በህገወጦቹ የላቲን አሜሪካ የኮኬይን ንግድ አራማጅ ድርጅቶች ሁነኛ ርምጃ የመውሰድ ትልቅ ተግባር ይጠብቀዋል። እርግጥ የህገ ወጡ ዕጸ ሱስ ኮኬይን ንግድ በሀገሪቱ ላንዳንዶች ብልጽግናን ቢያስገኝም፡ አሳና የካሹ ፍሬን በዋነኛ በንግድ ወደ ውጭ የምትልከው ሀገር ጊኒ ቢሳው አሁንም በዓለም እጅግ ድሀ ከሚባሉት ሀገሮች መካከል እንደ አንድዋ ትቆጠራለች።
በሞሪታንያና በጊኒ መፈንቅለ መንግስት ከተካሄደና በኒዠርም የፖለቲካው ውዝግብም እየተባባሰ የመጣበት ሁኔታ ሲታሰብ፡ በነገው ዕለት በጊኒ ቢሳው የስልጣኑ ለውጥ በሰላማዊ ምርጨ የሚደረግበት ሂደት ምዕራብ አፍሪቃውያቱ ሀገሮች ከመፈንቅለ መንግስትና ከምስቅልቅል ሁኔታ የሚላቀቁበት መልካም ዕድል መኖሩን እንደሚያመላክት የፖለቲካ ተንታኞች ይገመታሉ።

AA/MM/RTR/DW

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች