1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጉጂው ውዝግብና የተወካዮችና የባለስልጣናት ውይይት

ሐሙስ፣ የካቲት 30 2015

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምስራቅ ቦረና በሚል የመሰረተው የክልሉ 21ኛ ዞን ኢፍትሃዊ ነው በማለት የጉጂ ህዝብ መቃወሙን ተከትሎ የዞኑ ተወካዮች ቅሬታቸውን ለፌዴራልና ለክልሉ መንግስታት አቀረቡ፡፡የጉጂ የሀገር ሽማግሌዎች ከመንግስት የተመሰረተው ዞን እንደማይቀለበስ፤ ይሁንና ሦስቱ ጎሳዎች ተመካክረው መቀየር እንደሚችሉ ተነግሮናል፡፡

https://p.dw.com/p/4OSsD
Addis Ababa Guji
ምስል Seyoum Getu/DW

የተመሰረተው ዞን እንደማይቀለበስ፤ ነገር ግን ስያሜውን ሦስቱ ጎሳዎች ተመካክረው መቀየር ይችላሉ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል በማለት ምስራቅ ቦረና በሚል የመሰረተው የክልሉ 21ኛ ዞን ኢፍትሃዊ ነው በማለት የጉጂ ህዝብ መቃወሙን ተከትሎ የዞኑ ተወካዮች ቅሬታቸውን ለፌዴራልና ለክልሉ መንግስታት አቀረቡ፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ በዚሁ ቅሬታ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የጉጂ የሀገር ሽማግሌዎች ከመንግስት የተመሰረተው ዞን እንደማይቀለበስ፤ ነገር ግን ስያሜውን ሶስቱ ጎሳዎች ተመካክረው መቀየር እንደሚችሉ ተነግሮናል ብለዋል፡፡

ጥያቄያችን ምስራቅ ቦረና በሚል የተሰየመውን ዞን ስሙን ከመቀየርም በላይ ነው ያሉት የጉጂ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎቹ በመንግስት ምላሽ አለመርካታቸውን ገልጸው፤ ውሳኔው የህዝብ በመሆኑ ህዝብ ግን እናወያይበታለን ብለዋል፡፡

Addis Ababa Guji
የጉጂ ዞን ተወካዮች ቅሬታቸውን ለፌዴራልና ለክልሉ መንግስታት አቀረቡምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. አደረኩ ባለው 6ኛ የስራ ዘምን 2ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ምስራቅ ቦረና የተባለውን 21ኛ ዞን ከቦረና ሞያሌ፣ ጉቺ እና ዋችሌ ወረዳዎችን፤ ከጉጂ ጉሚ የልደሎ እና ሊበን ወረዳዎች እንዲሁም ነጌሌ ቦረና ከተማን፤ እንዲሁም ከባሌ ዞን መደወላቡ፣ ኦቦርሶ እና ሀረና ቡሉቅ ወረዳዎችን በማካተት መሰረትኩ ብሏል፡፡ በውሳኔው መሰረት ከዚህ በፊት የጉጂ ዞን ዋና ከተማ ሆና ስታገለግል የነበረችው ነገሌ፤ ነጌሌ ቦረና በሚል መጠሪያ የምስራቅ ቦረና ዞን መቀመጫ ትሆናለች፡፡ አዶላ ሬዴ ደግሞ የጉጂ ዞን ዋና ከተማ እንድትሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ይህንኑን ተከትሎም ተቃውሞና አለመረጋጋት በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ባለፉት ሁለት ሳምንታት መስተዋሉም አይዘነጋም፡፡

 

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ