የጉድ ላክ ጆናታን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደር ሐሳብ | አፍሪቃ | DW | 20.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የጉድ ላክ ጆናታን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደር ሐሳብ

የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ጉድ ላክ ጆናታን ሦስት ያገሪቱ ግዛቶችን ከቦኮ ሃራም ለመጠበቅ ያቀረቡት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደር ሃሳብ እክል ገጥሞታል። በቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ጥቃት በደረሰባቸው የሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ግዛቶች እ.ኤ.አ. ግንቦት

2013 ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገውና አሁን ፕሬዝዳንቱ እስከ መጪው የካቲት በድጋሚ እንዲራዘም ያቀረቡት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደር ሃሳብ ስኬታማ አይደለም ሲሉ የሃገሪቱ ምክር ቤት አባላት ተችተዋል።

የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ጉድ ላክ ጆናታን እ... ግንቦት 2013 ጀምሮ በአዳማዋ፤ቦርኖ እና ዮቤ ግዛቶች ተግባራዊ ተደርጎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተዳደር ለተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲራዘም ለሃገሪቱ ምክርቤት በደብዳቤ የጠየቁት ባለፈው ማክሰኞ ነበር። ፕሬዝዳንቱ በሶስቱ የሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ግዛቶች ሰላማዊ ሰዎችንና የሃገሪቱን ጦር ዒላማ ያደረጉ የቦኮ ሃራም ጥቃቶችን ለመከላከል ባቀረቡት ሃሳብ ላይ በዝግ የመከረው ምክር ቤት ግን በቀላሉ ከውሳኔ አልደረሰም።

ውሳኔውን ለዛሬ በይደር ያቆየው የናይጄሪያ ምክር ቤት የሃገሪቱ ጦር «ኤታ ማዦር» ሹም፣ በውይይቱ እንዲሳተፉ ጋብዟል። የጉድ ላክ ጆናታን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተዳደር በቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ከፍተኛ ጥቃት ከደረሰባቸው ሶስቱ ግዛቶች ከመጡ የምክር ቤቱ አባላት ዘንድ የሰላ ትችት ቀርቦበታል። ከዮቤ ግዛት የተመረጡት የምክርቤቱ አባል አህመድ ላዋን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተዳደሩ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ያመጣው ውጤት ባለመኖሩ ሊራዘም አይገባም ሲሉ ተደምጠዋል።

«ካሁን ቀደም የቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተዳደር ጥያቄ ተቀብለን ብናሳልፍም እና ሁለት ጊዜ እንዲራዘም ብንፈቅድም ለእኛ ያመጣው ለውጥ የለም። አሁንም በተመሳሳይ መንገድ፤በተመሳሳይ ሂደትና አሰራር ውስጥ በድጋሚ ማለፍ ምንም ጥቅም የለውም ብለን እናምናለን። ካሁን ቀደም በኒጀር ዴልታ ግዛት የሰርጎ ገቦችን ጥቃት ለመከላከል የሃገሪቱ ጦር ሲሰማራ እና ስኬታማ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነበር? አሁንም በሰሜን ምስራቅ አካባቢ ካለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተልዕኮዎችን መፈጸም እንችላለን። ነገር ግን ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች በትክክል ማወቅ አለብን። ታክቲክና ስልታችንም ትክክል መሆን ይኖርበታል። ባለፉት አስራ ስምንት ወራት ስኬታማ አልነበርንም። አሁንም ያለ ምንም ጥርጣሬ ለውጥ ማምጣት እንደማንችል አምናለሁ።»

ላለፉት አስራ ስምንት ወራት በአዳማዋ፤ቦርኖ እና ዮቤ ግዛቶች ተግባራዊ ሆኖ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተዳደር ቀጣይ እጣ ፈንታ ዛሬ የሚወሰን ይሆናል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ በሆነባቸው ግዛቶች የቦኮ ሃራምን አፈና፤ግድያ እና እንግልት መታደግ አልቻለም። በቀጣዩ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድጋሚ ለመመረጥ ጉድ ጉድ የሚሉት ጉድ ላክ ጆናታንም ሆኑ መንግስታቸው የቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድንን ጥቃቶች መከላከል አልቻሉም።

አለም አቀፍ ታዛቢዎች የአፍሪቃን ኢኮኖሚ በቀዳሚነት የምትመራውና በከፍተኛ የነዳጅ ሃብት የበለጸገችው ሃገር ከገባችበት ማጥ ለመውጣት መንግስታዊ መዋቅሩ ከሙስና መጽዳት እንዳለበት ይናገራሉ።

ላለፉት አምስት ዓመታት ከ10,000 በላይ ናይጄሪያውያን በቦኮ ሃራም ጥቃት ህይወታቸውን ሲያጡ ቡድኑ ከ20 በላይ ከተሞችን በሙሉና በከፊል በቁጥጥሩ ስር አውሏል።

እሸቴ በቀለ

ኡባሌ ሙሳ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic