የገዢዉ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር ዕጣ | ኢትዮጵያ | DW | 17.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የገዢዉ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር ዕጣ

በኢትዮጵያ የገዢዉና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር ከተጀመረ ሁለት ወራት አስቆጠረ። እስካሁን በተካሄዱት የቅድመ ድርድር፤አምስት መድረኮች የአደራዳሪና የታዛቢዎች፤ የመገናኛ ብዙሃንና የሥነስርዓት ጉዳይ ተነስተዉ ሲያነጋግሩ ቆይተዋል። ከገዢዉ ፓርቲ ጋር የሚካሄደዉ ድርድር በወኪሎች ይሁን አይሁን የሚለዉ ደግሞ ሌላዉ አነጋጋሪ ጉዳይ መሆኑ ተሰምቷል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:41

በመንግሥትና ተቃዋሚዎች የተጀመረዉ ድርድር

ከሀገር ዉስጥ የተገኘ ዘገባ እንደሚያመለክተዉ ከገዢዉ ፓርቲ ጋር መደራደር የጀመሩት 21 የተቃዉሞ ፒለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል ወይንስ በጋራ በድርድሩ እንቀጥል በሚለዉ ላይ ለመወሰን መጋቢት 4 ቀን ቀጠሮ ነበራቸዉ። በቀጠሮም 12ቱ ብቻ እንደነበሩ ዘገባዉ ይገልጻል። በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል ከተባሉት ፓርቲዎች አንዱ ሰማያዊ ፓርቲ ነዉ። ሊቀመንበሩ አቶ የሺዋስ አሰፋ ግን ስብሰባዉ በማን እና ለምን እንደተጠራ ግልጽ እንዳልሆነ በመግለጽ፤ በተጠቀሰዉ ጉዳይ ላይ የፓርቲያቸዉን አቋም እንዲህ ይናገራሉ።

«አሁን እሱ እርስበርሳችን እንድንጨቃጨቅ ለማድረግ ተነጋገሩና ተወካከሉ ምናም ይላል፤ ሲጀመር የተለየያየ ፕሮግራም፤ የተለያየ ደንብ ምናምን ያለዉ እኮ አንድ መሆን ስላልቻለ ነዉ። አይደለም? እና እና ያቀረብነዉ ሃሳብ አጀንዳዉ አንድ ሊያደርገዉ ይችላል። ለምሳሌ እስረኞችን ለማስፈታት ሰማያዊ መኢአድ፤ መድረክ እና ሌሎችም የታሠሩባቸዉ አብረዉ ይቆማሉ። ስለዚህ አጀንዳ ነዉሊለየን የሚገባዉ እንጂ እኔ ይኼ ኢህአዴግ ድርድሩን እየሸሸ ነዉ ባይ ነኝ። አንዱ ፓርቲ እኮ ከሌላዉ ፓርቲ የሚጠብቀዉ ምንም ነገር የለም።»

አቶ የሺዋስ የተጀመረዉ ድርድር ወደፊት እንዳይጓዝ ችግር የሆነዉ ገዢዉ ፓርቲ የመድረኩ መሪ በመሆኑ ነዉ የሚልም እምነት አላቸዉ። ድርድሩ ከመነሻዉ የተነሱ ይህና መሰል ነጥቦች አሁን እያነጋገሩ መሆኑን፤ ይህንንም ገዢዉ ፓርቲ ጊዜ ለመግዛት እየተጠቀመበት እንደሆነም ያስረዳሉ። ለድርድሩ ስኬት ዋናዉ የአደራዳሪ ጉዳይ ነዉ ይላሉ።

«እሱ ከተፈታ እኮ ሰብሳቢዉ ከኢህአዴግ እጅ ይወጣል። ከዚያ በኋላ በዓለም አቀፍ ሕግ እንዴት ነዉ ድርድር የሚደረገዉ፤ እንዴት ነዉ ፓርቲዎች ሲበዙ የሚጠበዉ ምናምን የሚለዉ እኮ የራሱ ይኖረዋል። ስለዚህ ዋናዉ ነጥብ ኢህአዴግ እየሸሸዉ ያለዉ ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ መሰየም እንፈልጋለን፤ እኛ የሰዎችን ስም ዘርዝረን በሙያቸዉ፣ በስነ ምግባራቸዉ፤ በሀገር ወዳድነታቸዉ የታወቁ ሰዎችን አስገብተናል እዛዉ።»

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ትናንት ለምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረዉ ድርድር ሊደናቀፍ ይችላል የሚል ስጋታቸዉን ገልጸዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ እንደዉም ቆሟል ነዉ የሚሉት።

«ድርድሩ እኮ ቆሟል። ሊደናቀፍ ይችላል ሳይሆን ተደናቅፏል። (በምን ምክንያት?) አንደኛ የሀገር ሽማግሌዎች ከሀገር ዉስጥ እና ከዉጭ የመጡ ነበሩ ድርድሩን የጀመሩት፤ ኢህአዴግ አጀንዳዉን ነጥቆ ራሱ ጠሪ ሆነ እና አበላሸዉ።  ከዚያ በኅላ በሁለት ቀን ሊያልቅ የሚችለዉን፤ አራት ነጥብ እኮ ናቸዉ፤ አደራዳሪ፣ ታዛቢ፣ ሚዲያ እና ሥነስርዓት፤ እሱን አስራ ሁለት ቦታ በትኖ አመጣዉ፤ ከዚያ በዚህ ስንጨቃጨቅ ሁለት ወር አለፈ። ስለዚህ ለእኔ ድርድሩ ቆሟል ባለበት።»

ነገ እንደሚካሄድ በሚጠበቀዉ ድርድርም ገዢዉ ፓርቲ እስካሁን የቀረቡለትን ጥያቄዎች አስተዉሎ የአደራዳሪነት መድረኩን ሌሎች እንዲይዙት በማድረግ ትክክለኛ መፍትሄ ለማምጣት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በበኩላቸዉ 21 ሆኖ ከገዢዉ ፓርቲ ጋር ከመደራደር በወኪል መደራደር ይሻላል ብሎ ፓርቲያቸዉ እንደሚያምን ገልጸዋል። ለዚህም ድርድሩ በመድረክ እና በገዢዉ ፓርቲ መካከል ቢደረግ የሚል ሃሳብ ፓርቲያቸዉ ማቅረቡን ገልጸዋል።

«አንደኛ ኢህአዴግ ገዢ ፓርቲ ነዉ። መድረክ ደግሞ ዋና ተቃዋሚ ነዉ። ባለፉት ምርጫዎች ባቀረባቸዉ እጩዎች ብዛት፤ ኢህአዴግ እንግዲህ የፈለገዉን ያህል ቆጥሮ ለራሱ ወስዶ የተረፈዉን ለፖለቲካ ድርጅቶች ይህንን አገኙ በሚለዉም ብንሄድ መድረክ ከቀሩት ሁሉ የበላይ ነዉ። የድርድር ነጥቦቹን በጋራ ስብሰባ ተነጋግረን ከተስማማን በኋላ መድረክ እና ኢህአዴግ ተቀምጠዉ ይደራደሩ፤ የዚያንም ድርድር ዉጤት ለዚህ ለጋራ ጉባኤዉ መድረክ እያመጣ ሪፖርት ያደርጋል፤ ሃሳብም ይቀበላል፤ የሚል አይነት አካሄድ ነዉ እኛ ያቀረብነዉ።»

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረዉ ድርድር ሊደናቀፍ ይችላል የሚል ስጋታቸዉን ቢገልጹም፤ የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ግን ሊቀጥል ይችላል የሚል ተስፋቸዉ አልተሟጠጠም። በህዝብ ተዓማኒነትን አግኝቶ ድርድሩ እንዲቀጥል የሚያደርገዉ መፍትሄ በመንግሥት እጅ ዉስጥ መሆኑንም ያሳስባሉ።

Professor Beyene Petros derzeitiger Vorsitzender des Oppositionsbündnisses Medrek

የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ

 

«በድርድሩ ዉስጥ እና መቆየት የምንችለዉ፤ የሕዝብ ድጋፍ አብሮን ሲኖር ነዉ። ሕዝባችን ከኢህአዴግ ጋራ የምናደርገዉን ግንኙነት ትክክልም ነዉ ተገቢም ነዉ በዚህ ዉጤት ይገኛል ብሎ ሲያምን ድጋፍም ሲሰጠን ነዉ። እናም ለዚህ ለመብቃት ኢህአዴግ የተረጋጋ መንፈስ እና ስሜት የሚፈጥር ሁኔታን የመፍጠሪያ ርምጃን መዉሰድ አለበት ብለናል። ይኸም ለምሳሌ የታሰሩትን የፖለቲካ መሪዎቻችንን ይፍታ፤ በዋስም ቢሆን ይልቀቅና ሕዝባችን እኛም ላይ እምነት እንዲኖረዉ ይርዳን። ይህንን የጊዜያዊ አዋጁን ደግሞ ያንሳዉ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንደኛ ፀረ ሕገ መንግሥት ነዉ፤ እና እነዚህ እነዚህ ጉዳዮች በኢህአዴግ በኩል ርምጃ ወስዶ እስካልታየ ድረስ እኛ በድርድሩ ለመቆየትም ትልቅ ጫና ነዉ የሚፈጥርብን፤ ዉጤቱንም ለመተንበይ ያስቸግረናል።»

የድርድሩ መቀጠልም ሆነ አዎንታዊ ዉጤት ማምጣት በገዢዉ ፓርቲ ፈቃደኝነት ላይ እንደሚወሰንም አክለዉ አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic