የገቢ ግብር ማጭበርበር በጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የገቢ ግብር ማጭበርበር በጀርመን

የታዋቂው የጀርመን የእግርኳስ ክለብ ባየር ሚውኒክ ፕሬዝዳንት ኡሊኽነስ የገቢ ግብር በማጭበርበር ወንጀልከ 12ቀናት በፊት 3 ዓመት ተኩል የእስር ቅጣት ተበይኖባቸዋል ። ባለፀጋ ኽነስ ብይኑን ይግባኝ ሳይሉ ወህኒ እንደሚወርዱ አስታውቀዋል። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በኽነስ ላይ የተላለፈው ብይንና አስተምህሮቱ ላይ ያተኩራል ።

በሃገራቸው የገቢ ግብር ላለመክፈል ገንዘባቸውን አነስተኛ ቀረጥ ወደ ሚከፈልባቸው ወይም ምንም ቀረጥ በማይከፈልባቸው ሌሎች አገራት ባንኮች የሚያሸሹ የዓለማችን ባለሃብቶች ቁጥር ከ130 ሺህ እንደሚበልጥ ይገመታል ። ከነዚህም ውስጥ በርካታ ጀርመናውያን እንደሚገኙበት ከአንድ ዓመት በፊት በዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች የተመረመረ መረጃ አጋልጧል ። አነስተኛ ቀረጥ በሚከፍልባቸው የግለሰቦችን የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች በምስጢር በሚይዙት በነዚህ ባንኮች የተቀመጠው ገንዘብ መጠን ከ16 እስከ 25 ትሪሊዮን ዩሮ ማለትም ከ21 እስከ 33 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል የሚል ግምት አለ ። ከአንድ ዓመት ግድም በፊት ቢልድ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ እንደዘገበው ጀርመናውያን ከሃገራቸው ውጭ በሚገኙ ባንኮች የሸሸጉት ለመንግሥት ቀረጥ ያልከፈሉበት ገንዘብ መጠን ወደ 400 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 516 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ። በጀርመን ህግ የገቢ ግብር አለመክፈል በእስር የሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል መሆኑን የህግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋ ያስረዳሉ ።

በዚሁ መሰረት በውጭ ያስቀመጡትን ገንዘብ ባለማሳወቅና ግብር ባለመክፈል በአቃቤ ህግ ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተጣርቶ የተቀጡ ጀርመናውያን ባለሃብቶች ጥቂት አይደሉም ። ከመካከላቸው በመልካም ስነ ምግባራቸውና በበጎ አድራጎታቸው የሚመሰገኑ በልዩ ልዩ መስክ ለአገራቸው ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡም ይገኙበታል ። በዚሁ ቅሌት ምክንያት የቀድሞ የባየር ሙኒክ የእግር ኳስ ክለብ የፕሬዝዳንትን ሥልጣን የለቀቁት ኡሊ ኽነስ ከነዚህ አንዱ ናቸው ። የ62ዓመቱ ኽነስ የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዋንጫ በወሰደበት እጎአ የ1974ቱ የዓለም ዋንጫ የተካፈሉ ተዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች ነበሩ ። ከ1970ዎቹ መጨረሻ አንስቶ እስካሁን የመሩትን የባየር ሙኒክን የእግር ኳስ ክለብ በማሳደግ የዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ክለብ እንዲሆን በማድረግ በጀርመናውያን ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጣቸውም ሰው ናቸው ። በእግር ኳሱ ባፈሩት ገንዘብ አንድ ግዙፍ የቋሊማ ማምረቻን ጨምሮ በሃብት ላይ ሃብት በመጨመር የልዩ ልዩ ንብረቶች ባለቤት ለመሆኑ የበቁት ኽነስ ገንዘባቸውን ግን ብቻቸውን አልበሉም ። ለልዩ ልዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ገንዘብ በመስጠት ዝናቸው የናኘ ለጋሽም ነበሩ ። በብዙ አቅጣጫ አርአያ የነበሩት እኚህ የናጠጡ ባለፀጋ ገንዘባቸውን በሚስጢር በስዊስ ባንክ ማስቀመጣቸው ባለፈው ዓመት እንደተደረሰበት መንግሥት ገንዘባቸውን በውጭ ባንኮች ሸሽገው የገቢ ቀረጥ ላልከፈሉ ግለሰቦች ያሻሻለውን ህግ ተጠቅመው ራሳቸውን አጋልጠው ነበር ሆኖም ይህ ከጥፋተንኝት ነፃ አላደረጋቸውም።

ኽነስ እጎአ ከ2003 እስከ 2006 መቀረጥ የነበረበትን 27.2 ሚሊዮን ዩሮ ባለመክፈላቸው የ3 ዓመት ከ6 ወራት እሥራት ተፈርዶባቸዋል ። በኡሊ ኽነስ ላይ የተላለፈው ብይን ተገቢ ነው ሲሉ የደገፉ የመኖራቸውን ያህል አነሰ ሲሉም የተከራከሩ አልጠፉም ።ስለ ብይኑ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ለረዥም ዓመታት ጀርመን የኖሩ ኢትዮጵያውያንን አነጋግረን ነበር ።ል አቶ በላይነህ ተሾመ ፍርዱ ትክክለኛና አአስተማሪም ነው ብለዋል ። በላይነህ ለሌላው አስተያየት ሰጭ ለአቶ ኤልያስ ይመርም በጀርመን የህግ የበላይነትን በማስከበር ሂደት የነፃ ፕሬስ አስተዋጽኦ ትልቁን ቦታ ይይዛል ይላሉ ።አንዳንድ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች በቅርብ ዓመታት ገንዘባቸውን ስዊዝ ስለደበቁ ሰዎች መረጃ የያዙ ሲዲዎችን ከገዙ በኋላ ቀረጥ አልከፈልንም ሲሉ ራሳቸውን ያጋለጡ ጀርመናውያን ቁጥር ጨመሯል ። መንግሥት ያሻሻለውን ህግ ተጠቅመው በውጭ ያሸሹትን ገንዘብ መጠን አሳውቀው የሚፈለግባቸውን ቀረጥ በመክፈል ከቅጣትና ማንነታቸው ይፋ ሳይወጣ ከሰው አፍ ያመለጡብዙዎች ናቸው ። የጀርመን የታክስ ከፋዮች ፌደሬሽን እንዳስታወቀው ባለፉት 4 ዓመታት ውጭ የደበቁትን ገንዘብ መጠን በፈቃዳቸው ለመንግሥት ያሳወቁ ባለሃብቶች ቁጥር 55 ሺህ ይደርሳል ።

አብዛኛዎቹ በተለይ ከ16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶችም ከደቡብ ጀርመኑ የባድን ቩርተንበርግ የምዕራቡ የኖርድ ራይን ቬስትፋልን እና የደቡቡ የባየርን ግዛቶች ነዋሪዎች ናቸው ። እጎአ ከ2010 በኋላ ከታክስ አጭበርባሪዎች የተገኘው ቀረጥ 3.5 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 4.78 ቢሊዮን ዶላር ነው። የገቢ ቀረጥ አለመክፈል የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑ እየታወቀ ብዙዎች ገንዘብ ለማሸሽ የመድፈራቸው ምክንያት ጀርመን ከሃያ ዓመት በላይ የኖሩት ዶክተር ጸጋዮ ደግነህ እንደሚሉት የሃገሪቱ የቀረጥ አሰራር ሊሆን ይችላል ። ገንዘባቸውን ወደ ውጭ ያሸሹ ሰዎች ራሳቸውን አጋልጠው ቀረጥ መክፈላቸው የሃገሪቱን ገቢ ከፍ እንዲል ማድረጉ በጎ ጎን ቢሆንም የአሰራሩ ፍትሃዊነት ግን አጠያያቂ መሆኑ አልቀረም ። በገቢ ቀረጥ ማጭበርበር ሶስት ዓመት ተኩል እሥራት የተበየነባቸው ኽነስ በሚቀጥሉት 2 ወራት የእስር ቅጣታቸውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic