የጆሴፍ ኮኒ ዕጣ ፈንታ | አፍሪቃ | DW | 23.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጆሴፍ ኮኒ ዕጣ ፈንታ

በአፍሪቃ በእስራት የሚፈለጉት እና በወቅቱ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ተሸሽገው የሚገኙት የዩጋንዳ ዓማፅያን ቡድን፣ በምህፃሩ የሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣ « ኤል አር ኤ » መሪ ጆሴፍ ኮኒ እጃቸውን ለመስጠት በማሰላሰል ላይ መሆናቸው ተሰማ።

ኮኒ እአአ ከ 1987 ዓም አንስቶ በዩጋንዳ፤ ደቡብ ሱዳን፣ በምሥራቅ ኮንጎ እና በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዉስጥ ዓመፅና ግጭት በመቀስቀሳቸው፣ በጦር እና በስብዕና አንፃር በፈፀሙት ወንጀል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ተላልፎባቸዋል። ግን፣ እስካሁን በርካታ ዓለም አቀፍ ጥረት ቢደረግም በቁጥጥር ስር ማዋል አልተቻለም። ኮኒ እጃቸውን የሚሰጡት ለደህንነታቸው ዋስትና ሲያገኙ ብቻ እንደሚሆን የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መንግሥት አስታውቋል። የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ሚሼል ጆቶጂያ እንደሚሉት፣ በወቅቱ ከኮኒ ጋ በመደራደር ላይ ሲሆኑ፣ ኮኒ እጃቸውን እንዲሰጡ ለማግባባት በመሞከር ላይ ይግኛሉ፣ ይሁንና፣ ዩኤስ አሜሪካ ኮኒ በወቅቱ እጃፀውን ለመስጠት በመደራደር ላይ ባሉት ያማፅያን ቡድኖች ውስጥ ተጠቃለዋል ብላ አታምንም።

ጆሴፍ ኮኒ በሰሜናዊ ዩጋንዳ ያቋቋሙት የሎርድ ሬዚስተንስ አሚ፣ « ኤል አር ኤ » ሲጀመር በዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ መንግሥት አንፃር ነበር የሚዋጋው። ግን፣ በዩጋንዳ ሽንፈት የደረሰበት የዚሁ ብድን ርዝራዦች ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እንቅስቃሴአቸውን በጎረቤት ሀገራት ውስጥ ነው ያደረጉት። ያማፂው ቡድን አባላት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናትን በግዳጅ ለውጊያ ተግባር መልምለዋል፣ እንዲሁም፣ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ለወሲብ ባርነት ተጠቅመውባቸዋል በሚል ይወቀሳሉ። ከቡድኑ ሰለባዎች አንዷ የሆነችው እና አሁን በጋዜጠኝነት ሙያ የተሰማራችው ባርባራ አሞኒ ያማፅያኑን የኃይል ተግባር እንዲህ ታስታውሳለች።
« እአአ ጥቅምት ዘጠኝ ፣ 1996 ዓም ሌሊት ነበር ሎርድ ሬዚስተንስ አሚ ዓማፅያን ቅድስት ማርያም ኤዣ ቦኬ የተባለውን ትምህርት ቤታችንን አጥቅተው ተማሪዎችን ያገቱት። እንደሚመስለኝ 195 ተማሪዎች ነበሩ የታገቱት። እኔም ከታገቱት መካከል አንዷ ነበርኩ። ጥቂት እንደቆየን 130ዎቻችንን ለቀቁን፣ የተሳካላቸው ጥቂቶችም አመለጡ ፣ ግን 30 የሚሆኑትን መርጠው በማስቀረት ወደ ቡድኑ መሪ ወደ ጆሴፍ ኮኒ ወሰዱዋቸው። »

የሎርድ ሬዚስተንስ አሚ ዋና አዛዦች ሚስቶች መሆን እንደተገደዱ ነው አሞኒ የገለጸችው።
ኮኒ ለደህንነታቸው ዋስትና ካገኙ እጃቸውን ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል መባሉ የቡድኑ የጭካኔ ተግባር ሰለባዎች በሚኖሩበት በሰሜናዊ ዩጋንዳ ጥርጣሬ አስከትሎዋል። አሞኒ እና ሌሎች ያካባቢው ነዋሪዎች ኮኒ እጃቸውን ለመስጠት ያሰቡበት ዋነኛው ምክንያት ምን ይሆን ስትል አጠያይቀዋል።
« ኮኒን ለማመን በመጀመሪያ ያነሳሳቸውን ምክንያት ማወቅ የግድ ይሆናል። ግን ትልቁ ጥያቄ እጃቸውን ከሰጡስ በኋላ ምን ይከተላል የሚለው ነው። ዋስትና ካገኙ በኋላ ምሕረት እንዲደረግላቸው ይጠብቁ ይሆን? ወይስ ሰሜን ዩጋንዳ ያለው ሕዝብ ያደረጉትን ሁሉ እንዲረሳላቸው ይፈልጉ ይሆን? ትልቅ ጉዳይ ነው።»
« ኤል አር ኤ » እጁን ለመስጠት መፈለጉ አስገራሚ ርምጃ ነው። ምክንያቱም ካሁን ቀደም በዩጋንዳ መንግሥት ወይም በሀይማኖት ቡድኖች በኩል የተደረገው ብዙ ሙከራ አልተሳካም ነበር። »


የጆሴፍ ኮኒ እንቅስቃሴን ለማብቃት ከሞከሩት ፖለቲከኞች እና ድርጅቶች መካከል አንዱ የሰሜን ዩጋንዳን ውዝግብ መፍትሔ ለማፈላለግ እና ዕርቅ ሰላም እና ውይይት ለማስገኘት እአአ በ1997 ዓም የተቋቋመው አቾሊ ሀይማኖት መሪዎች የሰላም ንቅናቄ ሲሆን፣ የቡድኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን አባ ማቲው ኦዳን የኮሴፍ ኮኒ እጅ የመስጠትን ዕቅድ ጦርነቱ እንዲያበቃ ስለሚያደርግ እና ይህንንም ሕዝቡ ከብዙ ጊዜ ወዲህ የጠበቀው በመሆኑ መልካም ነው ይላሉ። እጃቸውን ከሰጡ በኋላ የእስር ማዘዣ ያስተላለፈባቸው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት፣ « አይ ሲ ሲ » ምን ዓይነት ርምጃ እንደሚወስድ ግን እንደማይታወቅ አባ ማቲው ኦዳን አስታውቀዋል።
« « አይ ሲ ሲ » ኮኒን ለሰሩት ወንጀል በኃላፊነት ለመጠየቅ በያዘው ዕቅዱ ፀንቶ ይቆያል አይቆይም በወቅቱ ምንም አላውቅም። እኛ በጎረቤት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በውዝግቡ በመሰቃየት ላይ ያለውን ሕዝብ ችግር በሚገባ የምንረዳው በሰሜን ዩጋንዳ ያለን ዜጎች በግልጽ የምናውቀው ጉዳይ ቢኖር ኮኒ የሚያካሂዱት ጦርነትቱ እንዲያበቃ መፈለጋችንን ነው። ኮኒ የሚፈፅሙትን የጭካኔ ተግባር እና ዓመፅ አሁኑኑ ያብቁ። »
ዩጋንዳ ጆሴፍ ኮኒን እጃቸውን ከሰጡ በኋላ የመያዝ ዕቅድ እንዳላት የዩጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ፓዲ አንኩንዳ ከዶይቸ ቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ኮኒ እና ወታደሮቻቸው በአንድ ቦታ እስከተሰበሰቡ ድረስ ጥቃት እንደማይሰነዘርባቸው አስታውቀዋል።
እአአ በ2007 ዓም በደቡብ ሱዳን ከ« ኤል አር ኤ » ጋ የተካሄደው የሰላም ድርድር ኮኒ ከድርድሩ በኋላ የተዘጋጀውን የስላም ውል፣ ከውሉ ፍለማ በኋላ የመታሰር ዕጣ ሊገጥማቸው እንደሚችል የሰጉት ኮኒ አልፈርምም ባሉበት ምክንያት መክሸፉ ይታወሳል። ኮኒ እጃቸውን ከሰጡ የዩጋንዳ መንግሥት « አይ ሲ ሲ » በኮኒ ላይ የያዘውን ጉዳይ እንዲተው ለማድረግ ሌሎች ያካባቢ ሀገራት መሪዎችን ለማግባባት እንደሚሞክሩ ፓዲ አንኩንዳ አስታውቀዋል። በዚያም ሆነ በዚህ ግን ወደፊት ምን ሊደረግ ይችላል ወደሚለው ጉዳይ ከመታለፉ በፊት ፣ ኮኒ ለማን ነው እጃቸውን ለመስጠት የፈለጉት የሚለው እና እስካሁን መልስ ያላገኘው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርበታል።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic