የጅግጅጋ ተፈናቆይች እና ጅቡቲ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሮሮ | ኢትዮጵያ | DW | 08.08.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የጅግጅጋ ተፈናቆይች እና ጅቡቲ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሮሮ

ሰዉ ወደ መኖሪያ አካባቢው መመለስ አልቻለም። መንገዱ በመዘጋቱ ቤት ንብረታቸው በመውደሙ እና በፀጥታ ስጋት ከተጠለሉበት ቦታ መውጣት ያልቻሉ ብዙ ናቸው ። በሌላ በኩል የሶማሌ ክልል እና የድሬዳዋው ግጭት ጅቡቲም ተሻግሮ እዚያ በሚገኙ ዜጎች ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን ጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:00

የጅግጅጋ ተፈናቆይች ሮሮ

የሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ በንጽጽር  ሲታይ ዛሬ ፀጥታዋ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነዋሪዎችዋ ተናገሩ። ይሁን እና በሰሞኑ ግጭት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ቤተክርስቲያን ዉስጥ የተጠለሉ ነዋሪዎች የሚባላም ሆነ የሚጠጣ ማግኘት እንደተቸገሩ ገልጸዋል። የከተማዋ ሱቆች በመዘረፋቸው እና በመዘጋታቸው ገንዘብ እያላቸው እንኳን ምግብ መግዛት እንዳልቻሉ አስረድተዋል። ከከተማዋ የሚያስወጡ እና ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ መንገዶች መዘጋታቸው የምግብ ችግሩን እንዳባባሰው በቤታቸው ሰዎችን ያስጠለሉ ነዋሬ ገልጸዋል። በሌላ በኩል የሶማሌ ክልል እና የድሬዳዋው ግጭት ወደ ጎረቤት ጅቡቲም ተሻግሮ እዚያ በሚገኙ ዜጎች ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን ጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለዶቼቬለ ተናግረዋል። 
ባለፈው ቅዳሜ ጅግጅጋ ውስጥ በተፈፀመው ጥቃት ከተፈናቀሉት መካከል የባጃጅ ታክሲ አገልግሎት የሚሰጥ እና በዚሁ ስራ የሚተዳደረው የ35 ወጣት አንዱ ነው። ተወልዶ ባደገባት እና በሚኖርባት ከተማ «አይቼው የማላውቀው ነገር»ነው የደረሰው ይላል። ቅዳሜ እለት አይኑ እያየ ባጃጁ ተወሰዶበት ሌሎች ንብረቶቹም ተዘርፈውበት ቀበሌ 06 በሚገኘው ሚካኤል ቤተ

ክርስቲያን ተጠልሎ ይገኛል። ዛሬ አምስተኛ ቀኑ። በርሱ አባባል በቤተ ክርስቲያኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኛሉ። ምግብም ሆነ ውሐ ማግኘት ተቸግረዋል።  
 45 ሰዎች አስጠግተው በመርዳት ላይ የሚገኙት አንድ  የጅግጅጋ ነዋሪም የምግብ ችግር እንዳለ ይናገራሉ። ላስጠጓቸው ሰዎች ምግብ የሚሰጡት ከዚህ ቀደም ካስቀመጡት መሆኑን የገለጹት እኚሁ ነዋሪ ሱቆች እና መደብሮች አለመከፈታቸው ከበድ ያሉ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። 
ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የተጠለለው ወጣት እንደሚለው መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ወደ ክልሉ ከገቡ በኋላ በንጽጽር ሲታይ ጂግጅጋ የተሻለ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። መከላከያ ከገባ በኋላም አንዳንድ ለውጦች አሉ። 
ሆኖም ሰዉ ወደ መኖሪያ አካባቢው መመለስ አልቻለም። መንገዱ በመዘጋቱ ቤት ንብረታቸው በመውደሙ እና በፀጥታ ስጋት ከተጠለሉበት ቦታ መውጣት ያልቻሉ ብዙ ናቸው ።
በሌላ በኩል የሶማሌ ክልል እና የድሬዳዋው ግጭት ጅቡቲም ተሻግሮ እዚያ በሚገኙ ዜጎች ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን ጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
የጂግጅጋ ነዋሪዎችም ሆኑ ጅቡቲ የሚገኙ ዜጎች መንግሥት ከሚገኙበት ችግር እንዲያወጣቸው ተማጽነዋል። 

ኂሩት መለሰ 
አርያም ተክሌ
 

Audios and videos on the topic