የጅቡቲ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ | ኢትዮጵያ | DW | 08.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የጅቡቲ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ

ዛሬ ጅቡቲያውያን መሪያቸውን ለመምረጥ ድምጽ ሲሰጡ ውለዋል። በስልጣን ላይ ያሉት ኢስማኤል ኦማር ጌሊ እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል። ዋንኞቹ ተቃዋሚዎች ከምርጫው ራሳቸውን አግለዋል።

default

ኢስማኤል ኦማር ጌሌ

በአፍሪካ ብቸኛው የአሜሪካ የጦር ይዞታና ትልቁ የፈረንሳይ ጦር ሰራዊት ካምፕ የሚገኝባት በዓለም ከፍተኛ የውደብ እንቅስቃሴ የሚታይባት ናት ጅቡቲ ።  የዛሬው ፕሬዛዳንታዊ ምርጫ በእርግጥ በስልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሊን ለተጨማሪ አምስት አመት ለማቆየት እንጂ አዲስ ፊት አዲስ መሪ የሚሳይ እንዳልሆነ በሰፊው ይነገራል። ከ860 ሺህ ህዝቧ 150ሺው በመራጭነት ተመዝገቦ ድምጽ እየሰጠ ነው። ተቃዋሚዎች ከመነሻው ራሳቸውን ያገለሉበትና ፕሬዝዳንት ኦማር ጌሌ አንድ ተፎካካሪ ብቻ ያገኙበት ምርጫ በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት የምርጫን መስፈርት ያላሟላ ተብሎ የተነቀፈ ቢሆንም ጂቡቲያውያን ዛሬ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሄደው ለሚመርጡት ድምጻቸውን ሰጥተዋል። በጂቡቲ የዶቸ ቬሌ ተባባሪ ዘጋቢ ሚካሂል ባሬ እንደሚለው ምርጫው በሰላም ሲካሄድ ውሏል።

በዛሬው ምርጫ የ63 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ኦማር ጌሌ እና ብቸኛው ገለልተኛ ዕጩ ሞሀመድ ዋርሳሜ ተፎካክረዋል። ተቃዋሚዎች ምርጫ ላይ እንደማይሳተፉና ህዝባዊ አመጽ እንደሚጠሩ ካሳወቁ ካለፈው የካቲት ጀምሮ ኦማር ጌሌ ብርቱ ነቀፌታ ሲቀርብባቸው ከርሟል። ህገመንግስቱ እንዲ ሻሻል በማድረግ በምርጫው እየተወዳደሩ ያሉት ጌሌ ይህ የመጨረሻዬ ነው። ከዚህ በኋላ አልወዳደርም ሲሉ ባለፈው ማክሰኞ አስታውቀዋል። ጂቡቲ ምርጫ ስታደርግ ይዛሬ የመጀመሪያ አይደለም። ተቃዋሚ የሌለበት ምርጫ እንደዛሬው ሁሉ ከዚህ ቀደምም ተካሂዶ ኦማር ጌሌን ስልጣን ላይ አክርሟቸዋል። ከ1999 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉት ኦማር ጌሌ ባለፈው መጋቢት ወር በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ድጋፍ የሚንቀሳቀስን አንድ የምርጫ ተቀጣጣሪ ድርጅት ካባረሩ በኋላ በዚያች ሀገር የሚካሄድ ምርጫ ነጻና ዲሞክራሲያዊ ሊሆን እንደማይሆን በሰፊው ሲነገር ሰንብቷል። ህዝቡ አማራጭ ያላገኘበት ምርጫ ይሆናልም ተብሏል። ተባባሪ ዘጋቢ  ሚካሂል ባሬ ስለምርጫው ሂደት ሰላማዊነት ሲገልጽ ቢያንስ ታዛቢዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ነው።

በዛሬው ምርጫ ተቃዋሚዎች አለመሳተፋቸው በእርግጥ የመጪውን የጅቡቲ ምክር ቤት ውክልና አጠያያቂ ያደርጋል የሚል ትችትም ከወዲሁ እየቀረበበት ነው። የዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ እየተካሄደ ያለውን ምርጫ ተቃዋሚዎች ያልተሳተፉበት መሆኑ በራሱ ትክክለኛ ፍትሀዊ ሊያደርገው አይችልም ሲል ገልጿል። የአፍሪካ የፖለቲካ ባለሙያ ፕሮፌሰር ማርሻል ሮናልድ ቀጣዩ የጅቡቲ ምክር ቤት ብዙው ህዝብ የማይወከልበት ይሆናል ሲሉ ይገልጹታል።

መሳይ መኮንን

ሂሩት መለሰ