የጅቡቲ ምርጫ እና የሞዛምቢክ ጥቃት | አፍሪቃ | DW | 10.04.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የጅቡቲ ምርጫ እና የሞዛምቢክ ጥቃት

ጅቡቲ ሚያዝያ 1 ቀን 2013 ዓ,ም ፕሬዝደንታዊ ምርጫዋን አካሂዳለች። የጅቡቲ አገር ውስጥ ጉዳይ ምኒስትር ሙሚን አሕመድ ሼይክ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ኢስማኤል ኦማር ጉሌሕ በምርጫው ከተሰጡ ድምጾች 98 በመቶውን በማግኘት አሸንፈዋል። በሞዛምቢክ የተደጋገመ ጥቃት የደቡብ አፍሪቃ ሃገራትን ስጋት ውስጥ ከትቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:17

ትኩረት በአፍሪቃ ሚያዝያ 2 ቀን 2013 ዓ,ም

የ73 ዓመቱ ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ ድሬደዋ ውስጥ በጎርጎሪዮሳዊው 1947 ዓ,ም ኅዳር 27 ቀን ነው የተወለዱት። አማርኛን ከማቀላቸፋቸውም ሌላ ሶማሊኛ፣ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛና እንግሊዝኛም ይናገራሉ። ጅቡቲ በጎርጎሪዮሳዊው 1977 ዓ,ም ከቅኝ ተገዢነት ነጻ ስትወጣ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሆነው ለ22 ዓመታት በሥልጣናቸው የቆዩት ሀሰን ጉሌድ አፕቲዶን የአባታቸው ወንድም ናቸው። ገና በለጋ የወጣትነት ዕድሜያቸው አንድነትና ዴሞክራሲን የሚያሰፍን ግንባር የተሰኘው አባታቸውና አጎታቸው አባል የሆኑትበት ነጻነትን በሚያቀነቅነው ፓርቲ መሳተፍ ጀመሩ። የቀድሞው የጅቡቲ መሪ ኦብፕቲዶን ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው በጎርጎሪዮሳዊው 1999 ሲለቅቁም የወንድማቸው ልጅ የሆኑት ጉሌህ ፓርቲያቸውን ወክለው ለምርጫ ቀረቡ፤ አንዳንዶች በአጎታቸው ተመረጡም ይላሉ። ያም ሆነ ይኽ በወቅቱ ተፎካካሪያቸው ሆነው በግል ተወዳዳሪነት የቀረቡትን ሙሳ አህመድ ኢድሪስን አሸንፈው በዚሁ ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የጅቡቲ ፕሬዝደንት ሆኑ። በቀጣይም በጎርጎሪዮሳዊው 2005 ሚያዝያ ወር በተካሄደው ምርጫ ያለምንም ተቀናቃኝ 100 በመቶ ድምጽ አግኝተው ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን አረጋገጡ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጉሌህ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጠቅላላ ጉባኤ በማሳመን ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ካደረጉ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ በ2011 ለምርጫ ፉክክር ቀረቡ። በዚህ ወቅት በመላው አረብ ሃገራት ተንቀሳቅሶ የነበረው አብዮት ወደ ጅቡቲም ደርሶ ስለነበር ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ የታየውን የለውጥ ፈላጊዎች ንቅናቄ የጉሌህ መንግሥት በጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ብዙም ሳይገፋ አከሰመው። በሀገር ውስጥ የታየው የለውጥ ፍላጎት ተዳፍኖ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በ2011 በተካሄደው ምርጫ አንሳተፍም ሲሉ ጉሌህ አሁንም 80 በመቶ ድምጽ አግኝተው የሥልጣን መንበራቸውን አጸኑ። በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭም የመብት ተሟጋቾች ትችት የጠናባቸው ፕሬዝደንት ጉሌህ በቀጣይ ለምርጫ እንደማይቀርቡ ቢናገሩም እንደገና በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓ,ም 87 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸው ታውጆ በቤተ መንግሥቱ ኑሯቸውን ቀጠሉ። ዘንድሮም ለአምስተኛ ጊዜ ትናንት በፖለቲካው መንደር ብዙም ታዋቂነት ከሌላቸው ዛካሪያ ኢስማኤል ፋራህ ጋር ለውድድር ቀርበዋል። የጅቡቲ ዋነኛ የሚባሉ የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ምርጫ አልተሳተፉም። ብቸኛ ተፎካካሪያቸው ሆነው የቀረቡት የ56 ዓመቱ ፋራህ የጽዳት ምርቶችን ከውጭ የሚያስገቡ የንግድ ሰው ናቸው።

Infografik Karte Dschibuti Militärbasen Bab el-Mandeb Meerenge EN

ስልታዊ አቀማመጥ ያላት ጅቡቲ

በዘንድሮ የጅቡቲ ምርጫ 215 ሺህ ዜጎች ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል። አንድ ሚሊየን ዜጎች ያሏት በምሥራቅ አፍሪቃ ቀንድ ዳርቻ የምትገኘው ሀገር በአህጉሩ ካሉ እጅግ ትናንሽ ሃገራት አንዷ ናት። ጅቡቲ ትንሽ ሀገር ብትሆንም ባላት መልእክአ ምድራዊ አቀማመጥ ስልታዊ ተፈላጊነቷና ጠቀሜታዋ ግን ጉልህ ቦታ ሰጥቷታል። በቀይ ባሕር እና በአደን ባሕረ ሰላጤ መላከል በባብ ኤል ማንዳብ መገናኛ አፍ ላይ የምትገኘው ጅቡቲ የአፍሪቃ እና የአረብ ባሕረ ሰላጤ መዋሰኛም ወደብ ናት። ያልተረጋጋ በሚባለው በዚህ አካባቢ የሰከነችው በረሃማዋ ጅቡቲ የውጭ ኃይሎችን ትኩረት በመሳቧ በርካታ ሃገራት የጦር ሰፈር መስርተውባታል። ፈረንሳይ በአፍሪቃ ውስጥ ያላት ትልቁ የጦር ሰፈር የሚገኘው በጅቡቲ ወደብ ላይ ነው፤ 1500 ወታደሮች አሏት። ቻይና፤ ጃፓን፤ እንዲሁም ጣሊያንም የየራሳቸውን ወታደሮች ያካተቱ የጦር ሰፈሮች ካቋቋሙ ከርመዋል። ዩናይትድ ስቴትስም በአፍሪቃ ቋሚ የጦር ሰፈሯ የሚገኘው ጅቡቲ ላይ ነው። በሶማሊያም ሆነ በመላው አፍሪቃ ለፀረ ሽብር ዘመቻ የሚንቀሳቀስ 4000 የአሜሪካ ወታደር በዚያ ሰፍሯል። ሕንድ እና ሳውድ አረቢያም በስልታዊቱ ጅቡቲ የባሕር ዳርቻዎች ላይ ዓይናቸውን በመጣላቸው  በቅርቡም የየራሳቸውን የጦር ሰፈር ሊያደራጁ እንደሚችሊ ይጠበቃል።

ጅቡቲን የሁሉም ዓይን ማረፊያ ያደረጋት ሌላው ጉዳይ የዓለም የንግድ መተላለፊያ ዋነኛ መንገዶች ከሆኑት አካባቢዎች በአንዱ ዳርቻ መገኘቷ ነው። ከእስያ በመርከብ ተነስቶ በሱዝ ካናል አልፎ ወደ አውሮጳ ለመጓዝም ሆነ ከአውሮጳ ወደ እስያ ማለፊያው የጅቡቲ ደጅ ነው። የጅቡቲ የባሕር ወደብ ከዓለም ንግድ ከ10 በመቶ የሚበልጠውን ያስተናግዳል። በአጓራባቿ ካሉት ሃገራት በተሻለ መረጋጋት የምትታየው ጅቡቲ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የብዙዎችን ትኩረት መሳቧ በተጠና መንገድ የተሠራበት እንደሆነ ይናገራሉ የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ ጀርመናዊቱ አኔተ ቬበር።

«በዚህ ረገድ ጅቡቲ ራሷ ስልታዊ አጋር መሆኗን በተግባር አሳይታለች። በእርግጥ በአካባቢው ያለችው ብቸኛ ተዋናይ ናት ማለት አልችልም። ነገር ግን ይኽ የሆነው እንዲሁ ሳይሆን ጅቡቲ ራሷ በአግባቡ አቅዳ ለዚህ መሥራቷን ግን መናገር ይቻላል።»

Dschibuti Hafen Symbolbild

የጅቡቲ ወደብ

ምንም እንኳን የሌሎች ሃገራት ወታደሮች በአቅራቢያ መገኘት የራሱ ስጋት ቢኖረውም በሌላ ጎኑ ደግሞ በዚህች ሀገር ላይ ሌሎች ጥቃት የመሰንዘር ድፍረት እንዳይኖራቸው ያደርጋል ባይ ናቸው ቬበር። ለሀገሪቱ ኤኮኖሚ አዎንታዊ ድርሻ እንዳለውም መዘንጋት እንደሌለበትም አጽንኦት ይሰጣሉ።

በአንጻሩ ጅቡቲ የዓለም አቀፍ የጦር ሰፈሮች መከማቻ እንድትሆን ያበቁት ኢስማኡል ኦማር ጉሌህ ለሀገሪቱ ይኽ ነው የሚባል ብልጽግና አላመጡም በሚል የሚተቹም አሉ። ናይሮቢ ኬንያ የሚገኘው ሆርን የተሰኘው ተቋም ዳይሬክተር ሀሰን ካኔንጄ ዛሬም ከአንድ ሚሊየን የማይበልጠው የጅቡቲ ሕዝብ እጅግ በድህነት ሕይወቱን እንደሚገፋ ነው የሚናገሩት።

 «በመሬት ላይ ያለውን ኤኮኖሚ ስንመለከት የባሰ ዕዳ ከመጨመር ውጭ ይኽ ሁሉ ለእድገቱ በቂ አስተዋጽኦ ማድረጉን የሚያሳይ ማስረጃ የለም። በአሁኑ ጊዜ እንኳን 70 በመቶ ደርሷል፤ ይኽ ደግሞ ለአፍሪቃዊት ሀገር እጅግ ከፍተኛው ነው። ጅቡቲ ውስጥ ወረድ ብሎ መሥራት ይጠይቃል። ሕዝቡ አሁንም በከፋ ድህነት ውስጥ ነው። ከአህጉሩ ድሀ ሃገራት አንዷ ናት። እናም ምንም እንኳን ዋና ዋናዎቹን ኃያላን ብታስተናግድም አብዛኛውን ሕዝብ በሚጠቅም መልኩ ወደ ኤኮኖሚ ጥቅሞች አልተለወጠም።»

ብዙዎች ፕሬዝደንት ጉሌህ የጅቡቲን ስልታዊ ጠቀሜታ አጉልተው ማውጣት እንደተሳካላቸው ይናገራሉ። የሀገሪቱ የባሕር ወደቦች ለጅቡቲ መንግሥት ቋሚ ገቢ ከማስገኘታቸውም በላይ ወታደራዊ ሰፈሮቹ ደግሞ ከ100 ሚሊየን ዩሮ በላይ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገቡ መረጃዎች ያሳያሉ። አብዛኛውን የውጭ ምንዛሪ መንግሥት መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ይጠቀምበታል። ዋነኛ የባሕር በሩ ተጠቃሚ የሆነችው ኢትዮጵያና ጅቡቲን የሚያገናኘው የባቡር መስመርም ከዚህ ይደመራል። ሠሪዋም ቻይና ናት። የቻይና ተፅዕኖ ጅቡቲ ላይ ያለውን ሚና የሚያጠኑት በሆንግኮንግ ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ፕሮፌሰር ዣን ፒየር ካቤስታን ጅቡቲ በዚህ በኩል ለውስጥ እድገቷ የሚሆን ነገር አላተረፈችም ባይ ናቸው።

«ትልቁ ጥያቄ በእርግጥ ይኽ አዲሱ የነጻ ገበያ ቀጣና ለጅቡቲ የተወሰነ የኢንዱስትሪ መሠረት ይጥልላታል ወይ የሚለው ነው። ይኽን ይጠራጠራለሁ። ዝም ብሎ መሸጋገሪያ፣ የመሸጋገሪያ ማዕከል፣ የመገናኛ መስመር ብቻ በመሆኑ የኢንዱስትሪ መንደር ለመሆን አዳጋች ይሆናል። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ አስተኛ የሕዝብ ቁጥር፤ ከምንም በላይ ደግሞ የኢንዱስትሪ ባህል ፈጽሞ በጅቡት አለመኖሩም ዋናው ነው።»

እሳቸው እንደሚሉትም ጅቡቲ ውስጥ ኢንዱስትሪን መገንባትና ማስፋፋትን መመኘቱ ብቻውን ውጤት ሊያመጣም አይችልም። ኅብረተሰቡን የተዋጣለት የኢንዱስትሪ ሠራተኛ አድርጎ ለማሰልጠንም በራሱ ረዥም ጊዜ ይፈጃል። የናይሮቢ ሆርን ተቋም ዳይሬክተሩ ሀሰን ካኔንጄ በሀገሪቱ የሰፈሩ የውጭ ኃይሎችን ለጅቡቲ መንግሥት ከለላ የሚሰጡ አድርገውም ይመለከቷቸዋል። ይኽም በሀገሪቱ ለሚታሰበው ዴሞክራሲ እንቅፋት መሆኑንም ያመለክታሉ። ፕሬዝደንት ጌሌህ በዚህ ምርጫ ዳግም መመረጣቸው ከተረጋገጠ ጅቡቲ ነጻነቷን ካገኘች ወዲህ ለረዥም ዓመት በፕሬዝደንትነት መንበር የተቀመጡj የሀገሪቱ መሪ ይሆናሉ። ጉሌህ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አለማጠናቀቃቸውን ከሚያመለክት መረጃ የዘለለ የትምህርት ደረጃቸውን የሚያሳይ ነገር በይፋ የወጣ የለም።

በሞዛምቢክ የተደጋገመው ጥቃትና የደቡብ አፍሪቃ ሃገራት

የደቡብ አፍሪቃ አምስት ሃገራት ፕሬዝደንቶች በዚህ ሳምንት በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቱ ተሰብስበው በሀገሪቱ የአማጽያንን እንቅስቃሴና ጥቃት እንዴት መግታት እንደሚችሉ ተወያይተዋል። የመሪዎቹ ስብሰባ የተካሄደው ራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለው ጽንፈኛ ቡድን ባካሄደው ጥቃት ሞዛምቢኳ ፓልማ ግዛት ውስጥ የ12 ሰዎችን አንገት መቅላቱ ከተሰማ በኋላ ነው። በስብሰባው የተሳተፉት የቦትስዋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ የታንዛንያ እና የዚምባብዌ መሪዎች ናቸው። መሪዎቹ በሰሜን ሞዛምቢክ የተባባሰው የታጣቂዎች እንቅስቃሴና ጥቃት፣ የአካባቢው መረጋጋት ላይ ያስከተለውን አደጋ አስመልክተው ተወያይተዋል። ባለፉት ወራት የሀገሪቱን ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት አደጋ ላይ የጣለ ጥቃት የደረሰ ሲሆን በጥቃቱ በሺህዎች የሚገመቱ ሲገደሉ በተመሳሳይ በርካቶች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል። በተለይም በካቦ ዴልጋዶ ክፍለ ሀገር ከፅንፈኛው ቡድን ጋር ትስስር እንዳለው የሚገመተው የታጣቂዎች ጥቃት ለሞዛምቢክ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሃገራት ደህንነትት ጭምር አስጊ መሆኑ ነው የተገለጸው። ጥቃቱን ያወገዙት የደቡብ አፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ከአካባቢው ሃገራት ወታደራዊ እና የጸጥታ ጉዳይ ባለሥልጣናት እንዲሁም የደቡብ አፍሪቃ የልማት ማኅበረሰብ በምህጻሩ ሳዴክ ዋና መሪዎች ጋር በመሆን ለሁለት ቀናት ካካሄዱት ውይይት በኋላም ሐሙስ ዕለት ባሳለፉት ውሳኔ በአፋጣኝ አንድ የቴክኒክ ቡድን ወደ ሞዛምቢክ ለመላክ ወስነዋል።  ሆኖም የሞዛምቢክ ፕሬዝደንት ፊሊፕ ናዩሲ ሀገራቸው የውጭ ኃይል ድጋፍ ያስፈልጋት እንደሁ አስቀድሞ ሊጠና ይገባል ብለዋል። ምላሻቸው ባዶ ኩራት አይደለም ያሉት ናዩሲ የሉአላዊነት ጉዳይ መታየት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

Mosambik Palma | nach Angriff von Rebellen

ጥቃት የደረሰባት የፓልማ ግዛት

ከሌላው የአፍሪቃ ክፍል አኳያ ሲታይ ደቡቡ የአህጉሪቱ ክፍል አንጻራዊ መረጋጋት ነበረው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተለይ በሞዛምቢኳ ካቦ ዴልጋዶ ክፍለ ሀገር ሸማቂዎች ጥቃት እያደረሱ ነው። በተቀናጀ ጥቃትም ሸማቂዎቹ በብዙ ቢሊየን ዶላር የሚገመተው እና ለሞዛምቢክ ኤኮኖሚ ወሳኝ የሆነው የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ያለባት ፓልማ ወደብን ያዙ። በስፍራው የሚገኘውን የነዳጅ ፕሮጀክት የያዘው የፈረንሳዩ የነዳጅ አቅራቢ ቶታል ኩባንያ ሠራተኞቹን ከአካባቢው አስወጥቷል። በአካባቢው አሸባብ እየተባለ የሚጠራው ሆኖም ግን ሶማሊያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው ተመሳሳይ መጠሪያ ካለው ቡድን ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው የተገለጸው የካቦ ዴልጋዶ ጅሀዳዊ ቡድን እስላማዊ የኻሊፋ አስተዳደር ለመመስረት በአካባቢው በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች ላይ ከ800 ጊዜ በላይ ጥቃት አድርሷል ነው የተባለው። በዚህም ከ2,600 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ወደ 670 ሺህ የሚገመቱት ደግሞ ከአካባቢው ተፈናቅለዋል። የተመድ የአሁኑ ሰዓት ወደ1,3 ሚሊየን የሚገመት ሕዝብ አፋጣኝ ሰብዓዊ ርዳታ እንደሚያስፈልገው አስታውቋል። በካቦ ዴልጋዶ የቀጠለው የሸማቂዎቹ ጥቃት እንዳሳሰበው የገለጸው የደቡብ አፍሪቃ የልማት ማኅበረሰብ ከአካባቢው ሃገራት የተውጣጣ ኃይል ወደ ስፍራው አዝምቶ ጥቃት አድራሾችን እንደሚበቀል እየዛተ ነው። እስካሁን ግን የሞዛምቢክን ይሁንታ ያገኘ አይመስልም።

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic