የጃፓኑ ቀውስና የዓለም ኤኮኖሚ | ኤኮኖሚ | DW | 16.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጃፓኑ ቀውስና የዓለም ኤኮኖሚ

ባለፈው አርብ በጃፓን ከባድ ጥፋት ያደረሰው የመሬት ነውጽና ሃያል ማዕበል መላውን ዓለም እንዳስደነገጥ ነው።

default

በተፈጥሮው ቁጣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ የፎኩሺማ የአቶም ሃይል ጣቢያ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ መሆን ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል። በሌላ በኩል ሰብዓዊው ጥፋት ያስከተለው ሃዘን መለኪያ የማይገኝለት ቢሆንም ጠበብት በቀውሱ ሳቢያ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ሊከተል የሚችለውን ሁኔታ ማጤን መጀመራቸው አልቀረም። ለመሆኑ የጃፓኑ ሁኔታ የዓለምን ኤኮኖሚ መልሶ ቀውስ ላይ ሊጥል የሚችል ነውይ?

ወቅቱ ዓለም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከባድ ከሆነው የቅርቡ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ማገገም የያዘበት እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም የጃፓኑ የተፈጥሮ ቁጣ ያስከተለው ሁኔታ ማስደንገጡና ለአዲስ ስጋት መንስዔ መሆኑ አልቀረም። የምንዛሪ ገበዮች ለጊዜውም ቢሆን በዓለም ዙሪያ እየተንገዳገዱ ነው። ሆኖም ግን የኤኮኖሚ ጠበብት በ 2008 ዓ.ም. በአሜሪካ የሌህማን ብራዘርስ ባንክ ክስረት ተከስቶ የነበረው የዓለም የፊናንስና ኤኮኖሚ ቀውስ የመደገሙ አደጋ የመነመነ ነው ባይ ናቸው።

እርግጥ ለጃፓኝ ሁኔታውን ይበልጥ የሚያከብደው በተፈጥሮው ቁጣ ላይ የአቶም ቀውስ አደጋ በመደረቡ ነው። የመሬቱ ነውጽና የማዕበሉ ጥፋት ብቻውን በዓለም ገበዮች ላይ ከአጭር ጊዜ ያለፈ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም።

“የኑክያሩን ቀውስ በተመለከተ ችግሩንና ይሄው ምን መልክ እየያዘ እንደሚቀጥል አሁንም ገና በትክክል አናውቅም። እናም መጪውን መገመቱ ከባድና ምናልባትም ጨርሶ የማይቻል ነገር ነው”

ይህን የሚሉት የአውሮፓ የኤኮኖሚ ምርምር ማዕከል ፕሬዚደንትና በጀርመን መንግሥት የተሰየመ የኤኮኖሚ ጠበብት ቡድን መሪ ቮልፍጋንግ ፍራንስ ናቸው። ነውጹ ባደረሰው ጥፋት የጃፓንን ኤኮኖሚ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ,መጣሉ ግልጽ ነው። እርግጥ ማዕበሉ የመታው አካባቢ ከጃፓን የኤኮኖሚ ውጤት ሰባት በመቶውን ድርሻ ብቻ ነው የሚይዘው። ሆኖም የጃፓን ኤኮኖሚ ከወዲሁ በመዳከሙ ለአዲስ ቀውስ መጋለጡ አልቀረለትም። የሆነው ሆኖ የዴካ ባንክ ዋና የኤኮኖሚ ባለሙያ ኡልሪሽ ካተር እንደሚሉት ጃፓን ቀውሱን በአጭር ጊዜ ለመቋቋም የምትችል ናት።

“ካለፈው ጊዜ ያገኘነው ልምድ አለ። እንዳሁኑ የተፈጥሮ ቁጣ በሚደርስባቸው ጊዜያት ሁኔታው በኤኮኖሚው፤ በኢንዱስትሪና በኤነርጂ ምርት ወዘተ... ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ በተለይም መንግሥት በሚወስዳቸው የመልሶ ግንባታ ዕርምጃዎች በፍጥነት ይለወጣል። እናም በመልሶ ግንባታው ተግባር በሚከተሉት ወራት የማበብ ሂደትን እንደምናይ እርግጠኛ ነኝ”

በሌላ በኩል ጃፓን በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ያላት ድርሻ ባለፉት ዓመታት እየቀነሰ ነው የመጣው። በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በአይ.ኤም.ኤፍ. መረጃ መሠረት የአገሪቱ የዓለም ኤኮኖሚ ድርሻ ወደ 8,7 ከመቶ ዝቅ ብሏል። ይሄው እ.ጎ.አ. በ 1990 ዓ.ም. 14,3 ከመቶ ይጠጋ ነበር። አገሪቱ ባለፈው ዓመት ደግሞ በኤኮኖሚ ጥንካሬ በዓለም ላይ ከአሜሪካ ቀጥሎ የነበራትን ሁለተኛ ቦታ ለቻይና በማስረከብ ወደ ሶሥተኛው ስፍራ ማቆልቆሉ ግድ ነው የሆነባት።

በዚህ በጀርመንም ቢሆን የጃፓን ኤኮኖሚ ተጽዕኖ በጣም ዝቅተኛ እየሆነ መሄዱን ነው የአገሪቱ ጠበብት የሚያመለክቱት። ጀርመን ወደ ውጭ ከምትልከው ምርት ወደ ጃፓን የሚሄደው አንድ በመቶው ብቻ ነው። የምታስገባው ደግሞ ከሶሥት ከመቶ አይበልጥም። እንግዲህ ለጀርመንም ቢሆን ለጊዜው የጃፓን ቀውስ ጠንካራ ተጽዕኖ አይኖረውም ማለት ነው። ቮልፍጋንግ ፍራንስ እንደሚሉት ይሁንና የሶሥተኛ አገሮች ሁኔታ ችግር ሊፈጥርም ይችላል።

“ወደ ጃፓን ምርቶችን በሰፊው በመሸጥ የውጭ ንግድ የሚያካሂዱ አገሮች ክስረት የሚደርስባቸው ከሆነ ይሄው እኛ ወደነዚህ አገሮች በምናደርገው የውጭ ንግድ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ይህም የዓለምን ኤኮኖሚ ውስብስብ ትስስር ማጤን ያስፈልጋል ማለት ነው”

በጃፓን ሁኔታው በተጨባጭ ምን ይመስላል? የቶኪዮ ወኪላችንን ወሰንሰገድ መርሻን በስልክ አነጋግረናል፤ ያድምጡ!

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ