የጃዊ ተፈናቃዮች “በቂ እርዳታ አይደርስንም” አሉ | ኢትዮጵያ | DW | 10.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የጃዊ ተፈናቃዮች “በቂ እርዳታ አይደርስንም” አሉ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በአዋሳኝ አካባቢዎች ከሰሞኑ በተፈጠሩ ግጭቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በቂ እርዳታ እንደማይደርሳቸው ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ተፈናቃዮቹ ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ እንደማይፈልጉም ገልጸዋል። አንድ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለስልጣን በበኩላቸው ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ያለው ሰላም መሻሻሉን አስታውቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:14

በቤንሻንጉል ያሉ ተፈናቃዮች “በቂ እርዳታ አይደርስንም” አሉ

ከሁለት ሳምንት በፊት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተቀሰቀሰ ብሔር ተኮር ግጭት ዳፋው ለሺህዎች ተርፏል። በክልሉ በዳንጉር ወረዳ በሁለት ግለሰቦች ጠብ እንደተጫረ የተነገረለት ግጭት ወሰን አቋርጦ የአማራ ክልል አጎራባች አካባቢዎችን ያዳረሰ ሲሆን በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት እና ለሺህዎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። በሰሞኑ ግጭት እና “የብቀላ ጥቃት” ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች አራት ሺህ እንደሚጠጉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታውቋል። 

ከተፈናቃዮቹ አንዱ የሆኑት አቶ ውዱ ተክሌ በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ የሚገኘውን ቀያቸውን ለቅቀው ወደ ግልገል በለስ ከተማ ከሸሹ ዛሬ 10ኛ ቀናቸውን ይዘዋል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት፣ ፖሊሶች እና የአካባቢው ነዋሪ ታጣቂዎች ፈጽመውታል ባሉት ጥቃት ሶስት የቤተሰብ አባላት እንደተገደሉባቸው ይናገራሉ። አምስት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ከሞት ቢያመልጡም እርሳቸው እና ሌላ የቤተሰባቸው አባል በጥይት መቆሰላቸውን ያስረዳሉ። 

አቶ ውዱ አሁን እንደእርሳቸው ሁሉ ጥቃቱን ሸሽተው ቀያቸውን ከለቀቁ የአካባቢያቸው እና የዳንጉር ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በግልገል በለስ ከተማ ባለ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለዋል። ተፈናቃዮቹ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የተወሰነ የምግብ እርዳታ ቢያገኙም በቂ እንዳልሆነ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። 

በግልገል በለስ የተፈናቃዮች አስተባባሪ የሆኑት አቶ መልኬ ጊሳ እነ አቶ ውዱ የሚያሰሙትን ቅሬታ ይቀበላሉ። እርዳታው በበቂ ሁኔታ ሊዳረስ ያልቻለው በየጊዜው የተፈናቃዮች ቁጥር በመጨመሩ ነው ይላሉ። በግልገል በለስ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 1,406 ሰዎች ተጠልለው እንደሚገኙ አስተባባሪው ይናገራሉ።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባየታ ከግልገል በለስ በተጨማሪ በሁለት ሌሎች መጠለያዎች ያሉ ተፈናቃዮች አራት ሺህ እንደሚጠጉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተወላጆች በተጨማሪ የአማራ፣ የአገው እ የሌሎች ብሔር አባላትም በመጠለያዎቹ እንደሚገኙ ገልጸዋል።  በግልገል በለስ ከተማ የተጠለሉት አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ከአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን ጃዊ ወረዳ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው የማህብረሰብ ክፍሎች መሆናቸውን አቶ አበራ ገልጸዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገዢ ፓርቲ ቤጉህዴፓ ትላንት ባወጣው መግለጫ ከሳምንት በፊት በአካባቢው በሚኖሩ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ላይ ተሰነዘረ ያለውን “ብሔር ተኮር የብቀላ ጥቃት” “ጅምላ ግድያ” ሲል ጠርቶታል። የክልሉ የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እስካሁን ድረስ በጥቃቱ መሞታቸው የተረጋገጠ ሰዎች 219 ናቸው ይላሉ።  

ግጭት ወደ ነበረባቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አጎራባች ቦታዎች የመከላከያ ሰራዊት በመሰማራቱ በስፍራዎቹ ያለው ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን አቶ አበራ ይናገራሉ። ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መልሶ በእርሻ ስራቸው ላይ እንዲሰማሩ ግጭቱ ከነበረባቸው ቦታዎች ነዋሪዎች ጋር ውይይት በመደረግ ላይ እንዳለ ኃላፊው ገልጸዋል።

እርሳቸው ይህን ቢሉም አቶ ውዱ እና ሌሎች ተፈናቃዮች ግን ወደ ቀድሞ ቀያቸው የመመለሱን ሀሳብ በግልጽ ተቃውመውታል። የደህንነታቸው ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው የሚናገሩት ተፈናቃዮች በትውልድ ክልላቸው ቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚሰፍሩበት ቦታ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል። 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች