የጀርመን ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት | ኢትዮጵያ | DW | 18.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የጀርመን ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት

የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚቴና በጀርመንኛው «ፔን ሴንትሩም ዶይችላንድ» ተቋም የጀርመኑ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ስለሠብዓዊ መብትና ስለመናገር ነፃነት መገደብ በይፋ እንዲናገሩ በደብዳቤ ጠየቁ። በጀርመን ምክር ቤት የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴና በምክር ቤት የኢኮኖሚ ትብብር ኮሚቴ ም/ሊቀመንበርም ተመሳሳይ ነጥብ አንስተዋል።

እጅግ የተከበሩ የጀርመን ፕሬዚዳንት፤ ስለነፃነት መጠየቁ ተሸላሚው ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ሀገርን በከፍተኛ ሁኔታ መክዳትና ሽብርተኝነት በሚል ለ18 ዓመታት እስር ዳርጎታል ይላል ይፋዊው ደብዳቤ ሲንደረደር። ደብዳቤውን ለጀርመኑ ፕሬዚዳንት ጽፈው ይፋ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚቴና በጀርመንኛው «ፔን ሴንትሩም ዶይችላንድ» የተሰኘው ተቋም በአንድነት ነው። የተቋሙ ምክትል ፕሬዚዳንትና በእስር ቤት ለሚገኙ ፀሀፊዎች የሚሟገተው ተቋም ሃላፊ ዛሻ ፎይሸርት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ዮኣሒም ጋውክ በኢትዮጵያ ጉዟቸው ወቅት ግልፅና ይፋ በሆነ መልኩ ሊያስተላልፉት የሚገባ መልዕክት አለ ይላሉ።

«የጀርመን ፕሬዚዳንት ጋውክ ግልፅ በሆነ መልኩ ስለ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬና ርዕዮት ዓለሙ ጉዳይ በግልፅ አንስተው እንዲናገሩ፣ ስለሚፈቱበት ሁኔታም ጥረት እንዲያደርጉ እንፈልጋለን። በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ጋውክ በግልፅና በይፋ እዚያ በጋዜጠኞች፣ በፀሐፊዎችና በተቃዋሚዎች ላይ የሚታየው ሁናቴ ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ግልፅ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን።»በጀርመን ምክር ቤት የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴና በምክር ቤት የኢኮኖሚ ትብብር ኮሚቴ ም/ሊቀመንበር ቲሎ ሆፐም የጀርመኑ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉዞን አስመልክተው መግለጫ አውጥተዋል። ቲሎ ሆፐ በመግለጫቸው ፕሬዚዳንቱ በአንድ ዓመት የስራ ዘመናቸው የፖለቲካ ነፃነት አጥብቆ ወደ ተገደበባት ሀገር መሄዳቸው አንዳች ወሳኝ ምልከታ ነው በሚል ፅፈዋል። የጀርመኑ እንደራሴ ቲሎ ሆፐ በኢትዮጵያ ያለውን ሁናቴ ሲያስረግጡ እንዲህ ብለዋል።

«የሰው ልጅ ነፃነት መብት፣ የዜግነት መብት፣ የመሰብሰብ ነፃነት፣ የመፃፍና ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት በአሁኑ ወቅት ከበድ ባለ ሁናቴ ተገድቧል።»

ዛሻ ፎይሸርት በበኩላቸው የጀርመን ፕሬዚዳንት ዮኣሂም ጋውክ ከምንም በላይ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ነው እስር ቤት የሚገኙት ስለተባሉት ሶስቱ ጋዜጠኞች ሊያነሱ ይገባል ብለዋል።«ፕሬዚዳንቱ የፀሀፊዎቹ መታሰር ተቀባይነት እንደሌለው፣ የጀርመን መንግስት ነፃ መለቀቃቸውን እንደሚሻና በኢትዮጵያ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ ሁናቴው የጀርመን መንግስትን እንደሚያሳስበው በዲፕሎማሲያዊው መንገድ ከጀርባ ሳይሆን በግልፅ ይፋ በሆነ በማያሻማ መልኩ መጠየቅ አለባቸው ነው የምንለው።»

እንደራሴ ቲሎ ሆፐ ገዳቢው የሽብርተኝነት ሕግ ነፃ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁናቴ ቅድመ-ምርመራ እንዲደረግባቸው አድርጓል ብለዋል። አያይዘውም የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ
«ሂውማን ራይትስ ዎች» ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የተባበሩት መንግስታት ፀረ ቁም ስቅል (ስቅየት) ኮሚቴ ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ተቺዎች ላይ ስልታዊ ክትትል፣ እንግልትና ስቅየት እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ ሲሉ ጠቅሰዋል። ቲሎ ሆፐ አያይዘውም ።

« እኔም በአዲሱ የመንግስት መሪ በኩል የአሰራር ዘይቤው የሚለሰልስበትና ነፃ የመሆኑ ነገር የሚቀየርበት ሁናቴ ይፈጠራል፣ የተሻለ የሰብዓዊ መብት ሁናቴም ይታያል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ግን የሚያሳዝን ሆኖ የእነዚህ አይነት ነገሮች ምልክቶች አይታዩም።»

እንደራሴው በተጨማሪም የጀርመን መንግስት ከኢትዮጵያ ጋ ለሚያደርገው የልማት ትብብር ትልቅ ግምት እንደሚሰጡ ጠቅሰው፤ይህ ትብብር ያለሠብዓዊ መብት መከበር እውን እንደማይሆን የጀርመን መንግስት ከአሁን ቀደሙ በበለጠ መልኩ ግልፅ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።የፔን ሴንትሩም ተቋም ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት መገደብ እንደሚያሳስባቸው ጠቅሰዋል። አያይዘውም ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችና ፀሐፊዎች በፅሁፋቸው ብቻ ጫና ይደረግባቸዋል፣ ይታሰራሉ፣ በርካቶቹም ሀገሪቱን ለመልቀቅ ይገደዳሉ ሲሉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከዓለማችን በርካታ ጋዜጠኞች ጣጥለዋት የሚሸሿት ሀገር ሆናለች፣ ጋዜጠኞችን በግልፅ ሊጋፋ የሚችለው፣ ደስ የማይሉ እውነቶችን ጋዜጠኞች ላይ ለመጠቀም የሚያስችለው ሽብርተኝነትን የሚመለከተው ህግ በኢትዮጵያ አለ፣ ያ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን ብለዋል። ከኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚቴጋ ባወጡት መግለጫቸውም ጋዜጠኞችንና የመንግስት ተቃዋሚዎችን ለተለያያ የቁም-ስቅል (የስቅየት) ድርጊት የሚዳርገው የማሰቃየት ተግባር በአስቸኳይ ቆሞ ፀረ ስቅየት የዓለም አቀፍ ድንጋጌ እንዲከበር ጠይቀዋል። በማጠቃላያቸውም የጀርመኑ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉዞ ለ21 ዓመታት የሠብዓዊ መብት ጭቆና ስለታየባት የምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር እንዲናገሩና በግልፅ እንዲተቹ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic