የጀርመን ፓርላማ ውሳኔና የቱርክ ቁጣ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 07.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ፓርላማ ውሳኔና የቱርክ ቁጣ

የጀርመን ፓርላማ የኦቶማን ቱርክ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት በአርመኖች ላይ ያካሄደው ግድያ የዘር ማጥፋት ነው ሲል ያሳለፈው ውሳኔ ቱርክን በእጅጉ አስቆጥቷል ። ውሳኔው በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ቱርክ እያስጠነቀቀች ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:39

የጀርመን ፓርላማ ውሳኔ እና የቱርክ ቁጣ

የጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ የኦቶማን ቱርክ ከአንድ መቶ አመት በፊት በአርመኖች ላይ የፈፀመው ግድያ «ዘር ማጥፋት» ነው ሲል ውሳኔ ያሳለፈው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነበር ። ይኽው አንድ ተቃውሞ እና አንድ ድምፀ ተአቅቦ ብቻ የገጠመው ውሳኔ በቱርክና በጀርመን መካካል ውዝግብ አስነስቷል ። የጀርመን ፓርላማ እዚህ ውሳኔ ላይ እንዳይደርስ አስቀድማ ስታስጠነቅቅና ስትወተውት የቆየችው ቱርክ ውሳኔው ፍጹም ተቀባይነት የለውም ስትል ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰማች ነው ። በተቃውሞ ብቻ ሳትወሰነም አምባደሯን ከበርሊን የጠራች ሲሆን ከፕሬዝዳንቱ አንስቶ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጀርመን መንግሥትና የቱርክ ዝርያ ባላቸው የምክርቤት አባላት ላይ ይዝቱ ይዘዋል ። የቱርክ ፕሬዝዳንት ታይፕ ሬቼፕ ኤርዶሃን ውሳኔው ፣ጀርመን ጠቃሚ ወዳጅዋን ቱርክን እንድታጣ ያደርጋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል ። የቱርክ ዝርያ ያላቸው 11 የጀርመን ፓርላማ አባላትንም የአሸባሪ ቅጥያ ሲሉ ክፉኛ ዘልፈዋቸል ።
«ደማችሁ ያልጠራ ነው ። የማን ቃል አቀባይ እንደሆኑ ይታወቃል ። ጀርመን የሚገኙ የአሸባሪዎች ቅርንጫፍ ናቸው »
ከነዚህ የምክር ቤት አባላት አብዛኛዎቹ የግድያ ዛቻ እየተሰነዘረባቸውም ነው ።የጀርመን ምክር ቤት የኦቶማን ቱርክ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአርመናውያን ላይ የፈፀመው ግድያ ዘር ማጥፋት መሆኑ አለመሆኑ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ የያዘው

የግድያው መቶኛ ዓመት በተዘከረበት ባለፈው ዓመት ነበር ። ይሁንና ውሳኔው የአንካራና የበርሊንን ግንኑነት ሊጎዳ ይችላል በሚል ስጋት ነበር እስካሁን የቆየው ።ሆኖም ጊዜው በመግፋቱ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት እና የመንግሥቱ ተጣማሪ ሶሻል ዴሞክራቶች እንዲሁም ተቃዋሚዎቹ አረንጓዴዎች «በአርመናውያንና በሌሎች አናሳ ክርስቲያኖች ላይ በጎርጎሮሳዊው 1915 እና 1916 የተፈፀመው የዘር ማጥፋት መታሰቢያ »በሚል ያዘጋጁት የውሳኔ ሃሳብ ለፓርላማው ቀርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተደርጓል ። ቱርክና አርመን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በተካሄደ የጅምላ ግድያ ከረዥም ጊዜ አንስቶ ሆድ እና ጀርባ ናቸው ። አርመኖች በዚህ ጦርነት የኦቶማን ቱርክ ከ1915 እስከ 1917 ስልታዊ በሆነ መንገድ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ አርመኖችን ፈጅቷል ይላሉ። የኦቶማን ቱርክ መንግስት ከተፈረካከሰ በኋላ የተተካችው ዘመናዊቷ ቱርክ ግን ይህን እንደማትቀበል ለዘመናት ስታሳውቅ ቆይታለች ። አንካራ በዚህ ወቅት በኦቶማን ቱርክ ላይ ያመጹ ከ300 እስከ 500 ሺህ የሚደርሱ አርመናውያን ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ቱርኮችም ተገድለዋል ስትል ነው የምትከራከረው ። ቱርክ ይህ በጦርነት ወቅት የተፈፀመ ግን በተደራጀ ዘመቻ የተካሄደ ግድያ ወይም ዘር ማጥፋት አይደለም ስትልም ታስረዳለች ። ይሁንና ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት የተካሄደው የጅምላ ግድያ «የዘር ማጥፋት»ነው ሲሉ ከ20 በላይ ሃገራት እውቅና ሰጥተዋል ። የጀርመን ፓርላማ ያኔ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ብሎ መወሰኑ የሚያስተላለፈው መልዕክት ምንድነው ተብለው የተጠየቁት የጀርመን ፓርላማ ፕሬዝዳንት ኖርቤርት ላሜርት በመጀመሪያ የፓርላማው ውሳኔ በሙሉ ድምፅ ሊባል በሚችል ደረጃ ማለፉን አስረድተው ዓላማው የቱርክና አርመን ግንኑነት የሚሻሻልበትን መሠረት መጣል መሆኑን ገልፀዋል ።
«በመጀመሪያ ይህ የጀርመን ፓርላማ የጋራ አቋም መሆኑ ሊያጠራጥር አይችልም ። እስካሁን በማንኛውም የተለመደ የፖለቲካ ክርክር ላይ ልዩነት ይኖራል ። ሆኖም በዚህ ውሳኔ ላይ ግን የምክር መቀመጫ በያዙ ፓርቲዎች መካከል መሠረታዊ የሚባል

ልዩነት አልነበረም ።በሁለተኛ ደረጃ ሁለቱ ሃገራት በዚህ የጋራ ታሪካቸው ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችላቸው ሂደት መጀመር እንዳለባቸው ለማሳመን የምናደርገው ተከታታይ ሙከራ ነው ። እኛም ያለፍንበትን ተሞክሮ በማስታወስ ይህ ለወደፊቱ የጋራ መግባባት እርቅና ትብብር ቅድመ ሁኔታም ነው ።»
ሆኖም በቱርክና በአርመኖች መካከል ከዚህ ቀደም የተጀመሩ አንዳንድ የእርቀ ሰላም ሂደቶች ነበሩ ። እነዚህ ጥረቶች እያሉ ውሳኔውን ማሳለፉ ይህን የመሳሰለውን ጅምር ይጎዳል የሚል ትችት ቀርቧል ። ላሜርት በዚህ ጉዳይ በሰጡት አስተያየት በዚህ ረገድ የተጀመሩ ሂደቶች የነበሩ ቢሆንም አለመዝለቃቸውን ነው ያስረዱት ። ቀደም ሲል ችግሩን የመፍታት ጥረት ያለ ይመስል እንደነበረ ያሳወቁት ላሜርት በአሁን ደረጃ ላይ ግን ሁለቱ ሃገራት እንደዚህ ዓይነት የጋራ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ የሚገልፅ ማስረጃ እንደሌለ ነው የተናገሩት ። በዚህ መነሻም ውሳኔው
«ውሳኔውን ያሳለፍነው ተቃራኒው እየተደረገ መሆኑን ስለተገነዘብን ነው በበኩላችን እስካሁን በየትኛውም መንገድ ቢሆን በአንድ በተጀመረ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለንም ።ይህ የሁለት ወገኖች ጉዳይ አይደለም ። በየትኛውም ዓለም ቢሆን በሁለት ጎረቤት አገራት መካከል በሚፈጠር ችግር ላይ አስተያየት አንሰጥም ። ስለዚህ ልዩ ጉዳይ የምንናነገረው የጀርመን ሥረ ወመንግሥት በአንድ የተወሰነ ታሪካዊ አጋጣሚ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ስለመሳተፉ ነው ።እስካሁንም ቢሆን እኛ ራሳችን ስላለብን ሃላፊነታችን መነጋገራችን አልቀረም ።»
የሃላፊነት ጉዳይ ከተነሳ ጀርመን የራስዋን የዘር ማጥፋት ወንጀል አስቀምጣ የዛሬ አንድ መቶ ዓመቱ የአርመኖች የጅምላ ግድያ የዘር ማጥፋት ነው የማለት መብት የላትም ትላለች ቱርክ ። የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬቼፕ ታይብ ኤርዶሃን ጀርመን በሁለተኛ የዓለም ጦርነትና በናሚብያ ከፈፀመችው ከራስዋ ታሪክ በመነሳት የዘር ማጥፋት የተባለውን ውሳኔ መቼም ቢሆን አንቀበለውም ነው ያሉት ።ጀርመን ቅኝ በገዛቻት በናምቢያ ከጎርጎሮሳዊው ከ1904 እስከ 1908 ባመፁ የሄሬሮና የናማ ጎሶ አባላት ላይ

የግፍ ጭፍጨፋ በመፈጸም ተወንጅላለች ። በያኔው አዛዥ በሌተና ጀነራል ሎታር ፎን ቶርታል ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ የተፈጁት ናሚብያውያን ቁጥር ከ80 ሺህ በላይ ይገመታል ።ለዚህ የጅምላ ግድያ የተለያዩ የጀርመን መንግሥታት ለብዙ አስርት ዓመታት እውቅና ሳይሰጡ ቆይተዋል ። ይሁንና ባለፈው ዓመት የጀርመን ፓርላማ ፕሬዝዳንት ኖርበርት ላመርት ያኔ የተፈፀመውን ግፍና በደል የዘር ማጥፋት ብለውታል ።ይሁንና እስካሁን የጀርመን መንግሥት ለዚህ ወንጀል በይፋ ይቅርታ አልጠየቀም ። የጀርመን ፓርላማ የአርመኖች ግድያ የዘር ማጥፋት ነው ሲል ከወሰነ በኃላ ጀርመን በናሚብያ ባካሄደችው ጭፍጨፋ ላይ ምን ዓይነት አቋም እንደሚይዝ የተጠየቁት ላምቤርት አቋሙ ከርሳቸው የተለየ እንደማይሆን ነበር የመለሱት ።
«እኔ በግሌ ለሁለቱም ተመሳሳይ ክስተቶች ላይ ባለፈው ዓመት በጣም ተመሳሳይ መግለጫ ሰጥቻለሁ ። እናም የጀርመን ፓርላማም ተመሳሳይ አቋም እንደሚይዝ አንዳችም ጥርጥር የለኝም ።»
በናሚብያዎቹ በሄሬሮና በናማ ጎሶ አባላት ላይ የተፈጸመው በደል የዘር ማጥፋት መሆኑ እውቅና እንዲሰጠው በመንግሥት ደረጃም ይቅርታ እንዲጠየቅ በአሁኑ ጊዜ ናሚብያ እና ጀርመን እየተደራደሩ ነው ።በጉዳዩ ላይ የሚካሄደው ድርድር በያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ 2016 ዓም ማብቂያ ላይ ፍጻሜ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል ።የጀርመንና የናሚብያ ፓርላማዎች ስምምነት ላይ ከደረሱ ጀርመን ያኔ ለተፈፀሙት ወንጀሎች እውቅና ይቅርታ ትጠይቃለች ።ከዚህ ሌላ ጀርመን እና ናሚብያ በሁለቱ ሃገራት ስለ ዘር ማጥፋቱ ወንጀል የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድም ይስማማሉ ተብሎ ይጠበቃል ።የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሚለው የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው

የናሚብያ መንግሥት ውይይት ገንቢ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ነው ።ይሁንና በሁለቱ መንግሥታት ላይ እምነት የለንም የሚሉት የሄሬሮ እና የናማ የመብት ተሟጋቻቾች ከጀርመን መንግስት ጋር በቀጥታ እንደራደር የሚል ጥያቄ አቅርበዋል ።የተጨፈጨፉት ህዝቦች ዝርያ ያለን ህዝቦች ነን ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተን የሚሉት እነዚህ የመብት ተሟጋቾች እነርሱን የማይጨምር ይቅርታ እንደማይቀበሉ ተናግረዋል ። የነዚህ ወገኖች አንዱ ጥያቄ ካሳ ሲሆን የጀርመን መንግሥት ግን ለሄሬሮና ለናዋች የካሳ ክፍያ እንደማይሰጥ ከዚያ ይልቅ ካሳው በተዘዋዋሪ መንገድ እንደሚሰጥ ነው የተገለፀው ።ያም ማለት ጀርመን ካሳውን በልማት እርዳታ መልክ ነው እስጣለሁ የምትለው ። ይሁንና ፓርላማው የናሚብያውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እውቅና አዘግይቶ ለአርመኖቹ ግድያ ቅድሚያ የሰጠበት ምክንያት አሁንም ማነጋገሩ ቀጥሏል ።ቱርክን ያስቆጣው የጀርመን መንግስት ውሳኔ አርመኖችን አስደስቷል ።
የጀርመን ምክር ቤት የዛሬ መቶ አመቱን የቱርክ ኦቶማን የአርመኖች ጭፈጨፋ ዘር ማጥፋት ሲል ባሳለፈው ውሳኔ ፋይዳ ፣በቱርክ ማስጠንቀቂያ እና ጀርመን ተመሳሳይ ውንጀላ የቀረበባት የናሚብያው የጅምላ ግድያ ጉዳይ ላይ ያተኮረው የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ ያበቃል አድማጮች ጀርመን ተጠያቂ በሆነችበት በናምቢያ ጭፍጨፋ ላይ መውሰድ ያለባትን እርምጃ አዘግይታ የኦቶማን ቱርክ በአርመኖች ላይ የፈፀመውን ግድያ አሁን የዘር ማጥፋት ማለቷን እንዴት ታዩታላችሁ ። አስተያየታችሁን በSMS በፌስቡክ እንዲሁም በዋትስ አፕ አድራሻዎቻችን ላኩልን ።እናስተናግዳለን ።
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic