የጀርመን ፌደራል ባንክና የ 50 ዓመታት የዕድገት ሚናው | ኤኮኖሚ | DW | 01.08.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመን ፌደራል ባንክና የ 50 ዓመታት የዕድገት ሚናው

የጀርመን ፌደራል ባንክ ከተመሠረተ ሰሞኑን 50 ዓመት ሆነው። ባንኩ ለአራት አሠርተ-ዓመታት ያህል ለጀርመን ብሄራዊ ምንዛሪ ለ ዴ-,ማርክ ጥንካሬና መረጋጋት ዋስትና ከመሆን ባሻገር በተከታዩ ጊዜም ለአውሮፓ የምንዛሪ ፖሊሲ አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ኖሯል።

የጀርመን ፌደራል ባንክ

የጀርመን ፌደራል ባንክ

ፌደራላዊው የገንዘብ ተቋም ዛሬም በኤውሮ ምንዛሪ ዕድገት ላይ ጠቃሚ ሚና አለው። የዴ-ማርክ ምንዛሪ የበላይ ጠባቂ ዘብ ቡንደስ-ባንክ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተንኮታኩታ ከወደቀች በኋላ በምዕራቡ ክፍል ላሣየችው ተዓምራዊ የኤኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። በዓለም ላይ በዕርጋታው እንደታወቀው የቀድሞ የአገሪቱ ምንዛሪ ዴ-ማርክ፣ የብልጽግና መለያ እንደሆነችው ዝናኛ ፎልክስ-ዋገን አውቶሞቢልና ገናና Made in Germany የጀርመን ምርቶች በሕዝብ ዘንድ ዕውቅናን-ከበሬታን አትርፎ ቆይቷል።

ከሃምሣ ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ዕለት ሥራውን የጀመረው ፍራንክፉርት ከተማን ማዕከሉ ያደረገው የጀርመን ፌደራል የገንዘብ ተቋም ቡንደስ-ባንክ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ነው። ከባንኩ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የምንዛሪ ሕትመት፣ የወለድ መርህ አወጣጥ፣ እንዲሁም የጀርመንን የወርቅና የገንዘብ ተቀማጭ (ሪዘርቭ) ማስተዳደር ሆኖ ቆይቷል። ማዕከላዊው ባንክ ከፖለቲካ ነጻ ሲሆን ፌደሬሺኑ እንደ ባለቤት ለሕትመቱ ተቋም የዓመት ገቢውን ያስተላልፏል። ይሄው ገንዘብ ባለፈው 2006 ዓ.ም. 4,2 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ይጠጋ ነበር። ፌደራሉ ተቋም የአገሪቱን የወርቅና የምንዛሪ ተቀማጭ በማስተዳደር፤ በተጨማሪም ለሌሎች የገንዘብ ተቋማት በተወሰኑ ቅድመ-ግዴታዎች ገንዘብ በማበደር ገቢውን ያዳብራል።

የባንኩ የበላይ አካል ፕሬዚደንቱን፣ ምክትሉንና ሌሎች ተጨማሪ አምሥት ዓባላትን የሚጠቀልለው መንበር ነው። ፕሬዚደንቱ ለምሳሌ በወለድ ለውጥ ላይ ውሣኔ የመስጠት ሥልጣን ያለው በዚያው በፍራንክፉርት ተቀማጭ የሆነ 15 ዓባላትን ያቀፈ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ዓባልም ነው። ፌደራሉ ባንክ እስካለፈው ዓመት ድረስ 11 ሺህ ገደማ የሚጠጉ ሠራተኞች ነበሩት። ዘጠኝ ዋና አስተዳደሮችና 59 ቅርንጫፎችን ያቀፈው ባንክ አሁን ይዞታውን ለማጥበብ በያዘው ዕቅድ ተቀጣሪዎቹን እስከ 2012 ድረስ ወደ ዘጠኝ ሺህ ለመቀነስ ያቅዳል። ግማሽ ምዕተ-ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው ፌደራል ባንክ ምዕራባዊት ጀርመን ከጦርነቱ በኋላ ባሣየችው የኤኮኖሚ ዕርምጃና በዴ-ማርክ ጥንካሬ ረገድ ብርቱ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ቅድመ-ኤውሮው የጀርመን ምንዛሪ ዶቼ-ማርክ ወይም ዴ-ማርክ አገሪቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከወደቀችበት አዘቅት በመነሣት ያሣየችው ተሃድሶ መለያ, አርአያ ነው። የያኔው የጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገት ተዓምር ዓለም በአድናቆት የተመለከተው ነበር። የጊዜው የፌደራል ሬፑብሊክ ጀርመን የመጀመሪያ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር ሉድዊግ ኤርሃርድ ቆራጥ በሆኑ ውሣኔዎች ተዓምር ላሰኘው የኤኮኖሚ ዕድገት ጥርጊያ ያመቻቻሉ። ፌደራሉ ባንክም ለምንዛሪው ዕርጋታ፤ እንዲያም ሲል ቀጣይነት ላለው ዕድገት ድርሻውን ያበረክታል። እንግዲህ የኤኮኖሚው ዕድገት ተዓምር ሁለቱም፤ የፖለቲካው ሥርዓት ያሰፈነው መርህና ጠንካራው ምንዛሪ ነበሩ።

ይህንኑ ተከትሎ የጀርመን ምንዛሪ ዴ-ማርክ በዓለም ላይ ሁለተኛው ጠንካራ ተቀማጭ ገንዘብ ሊሆን ይበቃል። ፌደራሉ ባንክ ወለድ ከፍ ዝቅ ባደረገ ቁጥር፤ ከተሰሚነቱ ብዛት የተነሣ ሌሎቹም አውሮፓውያን ማዕከላዊ ባንኮች በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነበር በተመሳሳይ ዕርምጃ የሚከተሉት። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ቁርጠኛ በሆነ ማረጋጊያ ፖሊሲው በዜጎች የተከበረውን ያህል በፖለቲከኞች ዘንድ ግን ሁልጊዜ ተወዳጅ አልነበረም። ከ 15 ዓመታት በፊት የጊዜው የአውሮፓ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ዣክ ዴሎር ከፍተኛው የገንዘብ ተቋም በአገሩ ሕዝብ፤ በጀርመናውያን ዘንድ ስላለው ከበሬታ በአድናቆት ሲናገሩ፤ መላው ጀርመናውያን እግዚአብሄርን አማኞች አይደሉም፤ ነገር ግን ሁሉም በፌደራሉ ባንክ ያምናል ነበር ያሉት።

ወደ ፌደራሉ-ባንክ ቅድመ ታሪክ መለስ እንበልና፤ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ 1945 ዓ.ም. ባበቃ ማግሥት የገንዘብ እንቅስቃሴው የሚካሄደው በጀርመን ክፍለ-ሐገራት ባንኮች አማካይነት ነበር። ፌደራል ሬፑብሊክ ጀርመን የተመሠረተችው አራት ዓመታት ቆየት ብላ በ 1949 ነበር። ጀርመንን በጊዜው ይቆጣጠሩ የነበሩት የጦርነቱ አሸናፊ አበር መንግሥታት አዲሷ ጀርመን በባንኩ ዘርፍም በፌደራላዊ መልክ መዋቅሯን ይመርጣሉ። ለዚህም ምክንያት ነበራችው። ከዘውዱ አገዛዝ ዘመን አንስቶ ቀደምቱ ራይሽስ-ባንክ ትቶት ያለፈው ቅርስ ከትውስት የወጣ ገና የሩቅ ታሪክ አልነበረም። Marsch

ራይሽስ-ባንክ ከተመሠረተ ከ 1876 ዓ.ም. አንስቶ የገንዘብ አወጣቱና ጥበቃውም ብቸና ሃላፊ ነበር። ሆኖም ከቫይማሩ ሬፑፕሊክ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በስተቀር የራይሹ አስተዳደር ትዕዛዝና የፖለቲካ መርህ ጥገኛ መሆኑ አልቀረም። የራይሽ-ባንክ በሂደቱ አጠያያቂ ለሆኑ የፖለቲካ ዕርምጃዎች፤ ለምሳሌ አከራካሪ የጦርነት ብድር በመስጠት መሣሪያና ተገዢ ይሆናል። በመጨረሻም ይሄው ጥገኝነቱ በናዚው ዘመን ለደረሰው ፍጅትና ወረራ አብሮ ተጠያቂ ሊያደርገው በቅቷል። የኋላ ኋላ ግን ከዚህ ሁሉ ትምሕርት መቀሰሙ አልቀረም። ለዚህም የራይሽስ-ባንክ ተከታይ የሆነው የጀርመን ክፍለ-ሐገራት ባንክ ከፖለቲካ መርህ ራሱን ነጻ አድርጎ መቋቋሙ ነው።

ይህ ደግሞ የባንኩ የመጀመሪያ ፕሬዚደንት ካርል በርናርድም አጥብቀው የቆሙለት ጉዳይ ነበር። “የሕትመቱን ባንክ ነጻነት የምንጠይቀው ከተጋነነ ስሜትና ከሆነ የትልቅነት አስተሳሰብ የተነሣ አይደለም። ይልቁንም የምንዛሪው ፖሊሲ ከፖለቲካ ነጻ በሆነ፤ ከፓርቲዎች ንኪኪ በሌለውና ገለልተኛ ሃላፊነት ጥላ ሥር መዋል እንዳለበት አጥብቀን በማመናችን ነው”

ጽናትም ይኖረዋል። ፌደራል ሬፑብሊክ ጀርመን በሃምሣኛዎቹ ዓመታት አጋማሽ መልሳ ሉዓላዊነቷን ካገኘች በኋላ በመከታተል አዳዲስ ተቋማት ሕያው ይሆናሉ። ከነዚሁም አንዱ ፌደራሉ ባንክ ነበር። በመጀመሪያ የክፍለ-ሐገራቱ ማዕከላዊ ባንኮች በአንድ ተዋሕደው የጀርመን ክፍለ-ሐገራት ባንክ ይሆናሉ። ይሄው የምንዛሪ ተቋም ደግሞ በመጨረሻ ወደ ጀርመን ፌደራል ባንክነት ይለወጣል። ይህ የሆነው የጀርመን ፌደራል ም/ቤት ቡንደስታግ በ 1956 ዓ.ም. ባስተላለፈው የፌደራል ባንክ ሕግ መሠረት ነበር።

እርግጥ የጊዜው ፖለቲከኞች የባንኩን ነጻነት በመሠረቱ ቢቀበሉትም በሌላ በኩል በገንዘቡ ተቋም ሃላፊዎች ላይ ማስጠንቀቂያ መንጋጋቱ አልቀረም። በተለይ የመጀመሪያው የአገሪቱ ቻንስለር ኮንራድ አደንአወር በምንዛሪው ዘቦች ተግባር ላይ የበለጠ ተጽዕኖ እንዲኖራቸው ፈልገው እንደነበር ነው የሚነገረው። ከጅምሩ ከባንኩ ጋር ውዝግብ እንደሚገጥማቸው ቀድመው ሳይገነዘቡት የቀሩ አይመስልም። አደናዋር ሲናገሩ፤ “የማዕከላዊው ባንክ ሸንጎ፤ ክቡራትና ክቡራን ፤ በፌደራሉ መንግሥት ፊት ነጻ የሆነ አካል ነው። ለዚህ አካል ፓርላማም ሆነ መንግሥት ማንም ሃላፊ አይደለም። በመሆኑም ክቡራትና ክቡራን በኔ አስተሳሰብ የዚህ መሰሉ አካል ዓባል በግሉ የሚሸከመው ሃላፊነት ይበልጥ የተለቀ ነው”

በተለይ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በፖለቲከኞችና በባንኩ መካከል በተወሰኑ ጥያቄዎች ላይ የሃሣብ ልዩነት መንጸባረቁ አልቀረም። ማዕከላዊው ባንክ የምንዛሪ ዕርጋታን ለመጠበቅ በተሰጠው ሃላፊነት መሠረት የምንዛሪ ውድቀት እንዳይደርስና ሕዝብን መልሶ የኤኮኖሚ ችግር ላይ የሚጥል ሁኔታ እንዳይፈጠር አዘውትሮ ወለድ ማሳደጉ ለመንግሥት ከሚሻው በላይ ሆኖ የተገኘበት ጊዜ አልታጣም። መንግሥት በባንኩ ዕርምጃዎች የአገሪቱ የኤኮኖሚ ዕድገት እንዳይጓተት ደጋግሞ ነበር የሚያስጠነቅቀው። የአገሪቱን ገንዘብ ዴ-ማርክ በሌሎች ምንዛሪዎች አንጻር ከፍ በማድረጉ የወቅት አመራረጥ፣ የባንኩን የወርቅ ተቀማጭ የመንግሥትን የበጀት ቀዳዳ ለመሙላት በመጠቀሙ ረገድም ጥል መፈጠሩ አልቀረም። ግን የአንዴው የባንኩ ፕሬዚደንት ካርል ክላዘን በመንግሥትና በገነዘቡ ተቋም መካከል ውዝግብ መፈጠሩ ተወደደም ተጠላ የሚጥበቅ ያለና የሚኖር ነገር ነው ባይ ናቸው።

“የአንድን ምንዛሪ እርጋታ መጠበቅ በየጊዜው ከአጭር ጊዜ አንጻር ጠንካራ የሚመስሉ፤ በተለይ መልሰው ለመመረጥ ለሚፈልጉ ፖለቲከኞች የማይመቹ ዕርምጃዎችን መውሰድን ይጠይቃል። እዚህ ላይ የፖለቲከኞቹ ፍላጎት ስኬትም በምንዛሪው ተረጋግቶ መቀጠል ላይ ጥገኛ መሆኑን ደግሞ-ደጋግሞ ለማሳመን መጣሩ ግድ ነው የሚሆነው። እና ተመሳሳይ ችግሮች ወደፊትም እንደሚከሰቱ ዕምነቴ ነው”

ይሁንና በወቅቱም ሆነ ወደፊት ፌደራሉ ባንክ በወለድ መጠንም ሆነ በምንዛሪው ውጣ-ውረድ ላይ አይወስንም። ምክንያቱም የጀርመኑ ብሄራዊ ምንዛሪ ዴ-ማርክ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ያለፈ ታሪክ ነው። በጋራው ምንዛሪ በኤውሮ ተተክቷል። በኤውሮ መስፈን ደግሞ ብዙው የመወሰን ሥልጣን ወደ አውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ መሸጋገሩ አልቀረም። የተረጋጋ ምንዛሪ ለለመዱት ጀርመናውያን፤ ቢቀር ለአብዛኞቹ ከሚወዱት ዴ-ማርክ ስንብት አድርጎ ኤውሮን መቀበሉ በጊዜው የተዋጠላቸው ቀላል ዕርምጃ አልነበረም። በመሆኑም የጀርመን መንግሥት አዲሱን ምንዛሪ ለመቀበል አንዳንድ ነገሮች መሟላታቸውን ቅድመ-ግዴታ ነበር ያደረገው። በተለይ ዋነኛው ደግሞ የአውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ እንደ ጀርመኑ ፌደራል ባንክ ሁሉ ከፖለቲካ ነጸ መሆን ነበር።

በአጠቃላይ የጀርመን ፌደራል ባንክ ከአርባ ዓመታት በላይ ለተረጋጋ ምንዛሪ ዋስትና ሆኖ ኖሯል። ዛሬም ቢሆን፤ በ 1999 ዓ.ም. የምንዛሪው ማረጋጋት ሃላፊነት ለአውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ ከተሸጋጋረ ወዲህ ፌደራሉ ባንክ የሚያደርገው አስተዋጽኦ እጅግ ጠቃሚ ነው። በአውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ መዋቅር ውስጥ የጀርመኑ ፌደራል የምንዛሪ ተቋም ፕሬዚደንት አክስል ቬበር ታላቋን የአውሮፓ ኤኮኖሚ የሚወክሉት ናቸው። ጀርመን በኤውሮው ምንዛሪ ተጠቃሚ አገሮች ክልል ውስጥ፤ ማለት በኤውሮ-ዞን ከጠቅላላው ምርት 30 በመቶውን ድርሻ የምትይዘው አገር ናት። ይህ ደግሞ በአውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ ስለ ኤኮኖሚ ዕድገት፣ ስለ ገንዘብ ብዛት፣ ወይም የወለድ ፖሊሲ በሚወራበት ጊዜ የድምጿን ተሰሚነት ከፍተኛ ያደርገዋል።

ትልቁ ነገር ደግሞ የአውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ በፍራንክፉርት ተቀማጭ መሆኑ ብቻ ሣይሆን በጀርመኑ ፌደራል ባንክ አርአያ የተቋቋመ መሆኑ ነው። ማለት ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ሆኖና የምንዛሪ ዕርጋታ ጥበቃን ዓቢይ ተልዕኮው አድርጎ! ዛሬ የአውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ ፕሬዚደንት ፈረንሣዊው ዣን-ክላውድ-ትሪሼ የጋራው ምንዛሬ ኤውሮ እንደ አንዴው የጀርመን ማርክ ጠንካራ መሆኑን በኩራት ሊናገሩ ይችላሉ። ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በፊት የተቋቋመው የጀርመን ፌደራል ባንክ፤ ለአገሪቱ ተዓምራዊ የኤኮኖሚ ዕድገት ወሣኝ የነበረውን የዴ-ማርክን ዕርጋታ በማረጋገጥ ያደረገው አስተዋጽኦ ታሪካዊ ክብደት የሚሰጠው ነው። ታላቅ ትምሕርታዊነትም አለው።


ተዛማጅ ዘገባዎች