የጀርመን ጦር ከኩንዱዝ መውጣትና ስጋቱ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ጦር ከኩንዱዝ መውጣትና ስጋቱ

የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር የጀርመን የአፍጋኒስታን ኩንዱዝ ተልዕኮ ማብቃቱን ባለፈው ቅዳሜ አስታውቋል። የጀርመን ጦር ኩንዱዝን ሙሉ ለሙሉ ለቆ መውጣት የአካባቢውን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለጦሩ የተለያየ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ አፍጋናውያንን አስግቷል ።

የጀርመን ወታደሮች ላለፉት 10 ዓመታት ለሰላም ተልዕኮ የዘመቱባትን ሰሜናዊ አፍጋኒስታን የሚትገኘዋን ኩንዱዝን ባለፈው ቅዳሜ ሙሉ በሙሉ ለቀው ወጥተዋል ። ጀርመን የኩንዱዝን እዝ በይፋ ለአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይሎች ያስረከበችው ከ 2 ሳምንት በፊት የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቶማስ ደ ሜዝየር እና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለ በተገኙበት ስነ ሰርዓት ላይ ነበር ። መከላከያ ሚኒስትር ደ ሜዝየር ሃላፊነቱን የተረከቡት የአፍጋን ኃይሎች የኩንዱዝን ፀጥታ ያስጠብቃሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው በወቅቱ አስታውቀው ነበር ። የጀርመን ጦር ኩንዱዝን ለቆ ወጣ ማለት ደግሞ ደሜዝየር እንዳሉት እስከነአካቴው ይረሳታል ማለት ግን አይደለም ።

« የጀርመን ጦር ዛሬ ከኩንዱዝ ቢወጣም ኩንዱዝን መቼም አንረሳትም ። የጀርመን ወታደሮች እንደ ኩንዱዝ የጎላ ተሳትፎ ያደረጉበት ቦታ የለም ። በኩንዱዝ ገንብተናል ፣ ተዋግተናል አልቅሰናል ተፅናንተናል ሞተናል ወድቀናል »

ኩንዱዝ ውስጥ ብቻ በተካሄዱ ውጊያዎችና በደረሱ ግጭቶች 20 የጀርመን ወታደሮች ተገድለዋል ። በአጠቃላይ አፍጋኒስታን ውስጥ በግዳጅ ላይ ሳሉ የሞቱ የጀርመን ወታደሮች ቁጥር 35 ይደርሳል ። ከ2ተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ጀርመን ይህን ያህል ወታደር ተገድሎባት አያውቅም ። 19 ደግሞ በተለያዩ አደጋዎችና የራሳቸውን ህይወት በማጥፋት እዚያው አፍጋኒስታን ሞተዋል ። የጀርመን ወታደሮች ኩንዱዝ 10 ዓመት እንደመቆየታቸው ነዋሪዎቿ ለምደዋቸዋል ።

Omid Nouripour Bündnis 90/Die Grünen MdB

ኦሚድ ኑሪፑር

ምንም እንኳን ወታደሮቹ የከተማይቱን ጥበቃ ለአፍጋኒስታን ኃይሎች አስረክበው የሚሄዱ ቢሆንም ኩንዱዝን ለቀው መውጣታቸው ለነዋሪዎቿ ከተማይቱን መንግሥትንና አፍጋኒስታን የሰፈሩ ዓለም ዓቀፍ ኃይሎችን ለሚወጉት ለታሊባን አጋልጦ እንደመስጠት ነው የተቆጠረው ። በዚህ ስጋት ምክንያት አንዳንድ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን መዝጋት የጀመሩ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ወደ ጀርመን ለመሰደድ እየሞከሩ ነው ። ፊኡላህ ሳህል ሰሜን አፍጋኒስታን የምትገኘው የኩንዱዝ ነዋሪ ነው ። ሁሌም ከፍርሃት ጋር የሚኖረው ሳፊኡላህ «አሁን ቢያገኙኝ ደጃፌ ላይ ሊገድሉኝ ይችላሉ » ይላል ። ሳፊኡላህ ሊገድሉኝ ይችላሉ የሚለው የጀርመን ጦር ኩንዱዝን ለቆ ሲወጣ እንደገና ያንሰራራሉ ተብለው የሚፈሩትን ሰርጎ ገቦችና ታሊባኖችን ነው ። ሳፊኡላህ ሳህል አፍጋኒስታን ለዘመተው የጀርመን ጦር እየተከፈላቸው ከሚሰሩ አፍጋናውያን አንዱ ነው ። ታሊባኖች እንደ ፊኡላህ አፍጋኒስታን ውስጥ ለጀርመኖች የሚያገለግል ማንኛውንም ሰው እንደ አገር ከሃዲ ነው የሚቆጥሩት ። እጎአ ከ 2006 ዓም አንስቶ ለጀርመኖች የሚሰራው ሳፊኡላህ እንደሚለው ታሊባኖችና ሌሎችም ሰርጎ ገቦች ለጀርመን ጦር የሚሰሩ አፍጋናውያን ይሰልላሉ ጥቃትም ያደርሱባቸዋል ። በዚህ የተነሳም በበኩሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ነው የሚያደርገው ።

«ኩንዱዝ ውስጥ ያን ያህል ብዙም ጥቃት በማይደርስበት በከተማዋ ማዕከል ብቻ ነው የምንቀሳቀሰው ። ከከተማ ለመውጣት ግን አልተማመንም ። ከከተማይቱ ወጣ ያሉ ቀበሌዎችም አደገኛ ናቸው ። አማፅያኑ ኩንዱዝ ውስጥ ለጀርመኖች የሚሰሩ አፍጋናውያንን ይሰልላሉ አደጋም ይጥሉባቸዋል ። እኔን ቢያገኙኝ ምናልባትም ደጃፌ ላይ ይገድሉኝ ነበር ። ሆኖም ሁሌም በመጠንቀቅ ለቤተሰቦቼ እንኳን የት እንደምሄድ ነግሬያቸው አላውቅም ። ያም ሆኖ ከፍርሃት ጋር ነው የምኖረው »

እንደ ሳህል ሁሉ አፍጋኒስታን ለዘመተው የጀርመን ጦር የሚሰሩ አፋጋናውያን ቁጥር ወደ 1500 ይደርሳል ። እነዚህ አፋጋውያንም በዋነኛነት ለጀርመን ጦር በአስተርጓሚነት በሾፌርነት በምግብ አብሳይነት እና በፀጥታ አስከባሪነት ነበር የሚሰሩት ። የጀርመን መንግሥት ከመካከላቸው አፍጋኒስታን ቢቆዩ ለአደጋ ይጋለጣሉ ተብሎ የሚታሰቡትን ሰራተኞች ለመርዳት ቃል ገብቷል ። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሃንስ ፔተር ዲትርሽ ቃል እንደገቡት መንግሥታቸው ማንንም ለአደጋ አጋልጦ አይሰጥም ። አፍጋናዊያኑ ሰራተኞች የጀርመንን ጦር በመርዳታቸው ምክንያት ለችግር የሚዳረጉ ከሆነ ወደ ጀርመን እንዲመጡ እንደሚደረግ ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት ። ይሁንና የጀርመን የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ የፀጥታ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ኦሚድ ኑሪፑር መንግሥት ጉዳዩን የያዘበትን መንገድ ይተቻሉ ።

« ብዙ ነገሮች በተሳሳተ መንገድ እየተከናወኑ ነው ። በመጀመሪያ ደረጃ ከለላ ሲሊሰጣቸው የሚገባ ሰዎችን የመቀበል ብዙ ምልክት አይታይም ። ሁሉም ከለለላ አያስፈልጋቸውም ሆኖም የሚያስፈልጋቸውን መውሰድ ይገባል ። በነገራችን ላይ ቤተሰቦቻቸውንም እንዲሁ ። የምንነጋገረው በቁጥር ጥቂት ስለሆኑ ሰዎች ነው ። በአፍ መሸንገል ብቻ ውጤት አያመጣም ። ሰዎች አደጋ ላይ የሚገኙትን ሰዎች መቀበል እንዳለብን በግልፅ ሊታወቅ ይገባል ። »

የጀርመን ፌደራል መንግሥት የእያንዳንዱን ጉዳይ በየተራ ይመረምራል ። ወደ ጀርመን መምጣት የሚፈልጉ መጀመሪያ ማመልከቻ ማስገባትና ራሳቸውም ሆነ ቤተሰባቸው ለአደጋ መጋለጣቸውን እዚያ ለሚገኑ አለቆቻቸው ማሳመን ይኖርባቸዋል ። ኑሪፐር እንደሚሉት ይህን መሰሉ ጥርጣሬ የተሞላበት አሠራሩ ጊዜ የሚወስድና የተንዛዛም ነው ። ብርጋድየር ጀነራል ሚሸል ፌተር ወደ ጀርመን መሄድ የሚገባቸውንና እዚያ መቅረት የሚችሉትን የሚወስነው ኮሚቴ ሃላፊ ናቸው ። በተለይ ጦሩ ኩንዱዝን ለቆ ሲሄድ ሥራ ላጡት በሌላ አካባቢ በሚገኙ ክፍት የሥራ ቦታዎች የማሰማራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይናገራል

«በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የውጭ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ና የመከላከያ ሚኒስቴር ተወካዮችም ይገኛሉ ። በአጠቃላይ እነዚህን በሃገር ውስጥ ይሰሩልን የነበሩ ሰዎችን ማቆየት መቻል አለመቻላችንን የመገምገም ግብ አለን ። በኩንዱዝም ይህን አድርገናል ። በኩንዱዝ ስራቸውን ያጡ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች በሌሎች አካባቢዎች ለምሳሌ በማሳር ኢሻሪፍ ክፍት የሥራ ቦታዎች እንዲፈለግላቸው ይደረጋል »

አፍጋኒስታን ውስጥ ለጀርመን ጦር ሲሰሩ የቆዩ ጦር ጋር ይሰሩ ከነበሩት መካከል አፍጋኒስታን ውስጥ አሁን የጀርመን ጦር አካባቢውን ለቆ ሲወጣ የደፈጣ ተዋጊዎችና የታሊባን ኃይሎች ሰለባ መሆናችን አይቀርም የሚለው ስጋታቸው ጨምሯል ። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም እንዲሁ ፍርሃት ነግሶባቸዋል ። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው አብዱላህ ራሶሊ ያለ ጀርመን መከላከያ ሠራዊት ሥራችንን ማስፋፋት አንችልም ነው ያሉት ። በርሳቸው አስተያየት ከኩንዱዝ ወጣ ብለው በሚገኙ ቀበሌዎች ታሊባኖች የበላይነቱን እንደያዙ ነው ። በነዚህ አካባቢዎች የታጠቁ የወንጀለኞች ቡድኖች ይንቀሳቀሳሉ ። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚናገረው እስካሁን 289 አፍጋናውያን ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ማመልከቻ አስገብተዋል ። ከመካከላቸው የ275 ቱ ጉዳይ ታይቷል ከነዚህም 173 ቱ በእጅጉ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸው ታውቋል ። ከነዚህም 23 ቱና ቤተሰቦቻቸውን ጀርመን እንደምትቀበል ቃል ተገብቶላቸዋል ። የተቀሩት 150ው ደግሞ በቅርቡ ወደ የጀርመን መንግሥት እንደሚቀበላቸው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል ። ሰዎቹ ባለቤቶቻቸውንና ልጆቻቸውንም ይዘው ወደ ጀርመን መምጣት ይችላሉ ። ምንም እንኳን የጀርመን ወታደሮች ኩንዱዝን ለቀው መውጣት ብዙዎችን ቢያሰጋም ፀጥታው ሊሻሻል ይችላል ብለው ተስፋ የሚያደርጉ አልጠፉም ። ከነዚህ አንዱ ኩንዱዝ የሚገኝ የባህልና ስነ ፅሁፍ ተቋም ሃላፊ ናቸው ። በርሳቸው አስተያየት የጀርመን ወታደሮች ሲወጡ ለውጭ ጦር ጥላቻ ያላቸው ኃይሎች ውጊያ ሊቆሙ ይችላሉ ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic